Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰላም የነሱንን ስንለያቸው

0 258

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰላም የነሱንን ስንለያቸው

 

ስሜነህ

በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለተከሰቱት ችግሮች ዋነኛው ተጠያቂ እኔ ነኝ ብሎ መንግስት ሃላፊነቱን መውሰዱ ይታወሳል። ሃላፊነት መውሰድ ብቻ አይደለም ህዝቡን ይቅርታ ጠይቆ ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችሉትን አቅጣጫዎች አስቀምጧል። በዚሁ አቅጣጫ መሰረት  ወደ ተግባር እየገባ ባለበት በዚህ ወቅት ደም አፋሳሽ የሆኑ ግጭቶችን አሁንም እየተመለከትን ነው። ዜጎች በገዛ አገራቸው ‹‹መጤ›› እየተባሉ ጥቃት ሲፈጸምባቸው፣ ሲፈናቀሉና ሲገደሉ በተደጋጋሚ እየተመለከትን ነው፡፡ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት በሕገ መንግሥት አማካይነት ቃል ኪዳን በተገባበት አገር ውስጥ፣ ዜጎች የግፍ ፅዋን እየተጎነጩ ነው፡፡ በተደራጁ ኃይሎች አማካይነት ተቀስቅሰው በተነሱ አፍለኞች ሳይቀር ለዘመናት አብሮ በሰላም ከኖረ ሕዝብ ፍላጎት ውጪ በርካቶች ተገድለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ከቀዬአቸው ተሰደዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቱን ሥጋት ላይ የጣሉ ግጭቶች ፍንትው አድርገው የሚያሳዩት ነገር ቢኖር አገርን ቀውስ ውስጥ የሚከቱ ኃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶችን ነው፡፡

በሌላ በኩል ከላይ በተመለከተው አግባብ አቅጣጫዎች ያስቀመጠው መንግስት እና መሪ ድርጅቱ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት ሲያቅታቸው እያየ አሁንም መተኛቱ የችግሩ አንዱና ዋነኛው ምክንያቱ እንደሚሆን የሚያጠይቁ ብዙ ማሳያዎችን እየተመለከትን ነው። ችግር አባባሽ የሆኑ ባለስልጣናትን እኮ አሁንም በቴሌቭዥን መስኮት እያየን ነው። የኮሚዩኒኬሽን ሃላፊ ሚኒስትሩ ግጭት አባባሽ የሆኑ ሚዲያዎችን ሲያስጠነቅቁ “የግል አስተያየታቸው ነው” ሲሉ በማግስቱ ቁጣቸውን የገለጹት የብሮድካስት ባለስልጣን ዳይሬክተሩ የደፈሩት የሚኒስትሮች ምክር ቤትን መሆኑ እየታወቀ ዝም ሲባሉ እየተመለከትን እንዴት መንግስት የገባውን ቃል ይፈጽማል ብለን እንመነው? የሚሉ ወገኖች እየተበራከቱ ነው። ምሁራን ሳይቀሩ ከዚህች አስተያየት በኋላ ተስፋ መቁረጣቸውን ሲናገሩ ተደምጠዋል። እኚሁ ባለስልጣን ቀጠሉናም ደግሞ እነዚህን የሚዲያ ተቋማት ገስጻለሁ ሲሉ ሰሞኑን በጠሩት መድረክ ላይ መስሪያ ቤታቸው በእንጀራ ልጅነት የሚመለከታቸው የሚዲያ ተቋማት ስለመኖራቸው በአደባባይ ተመለከትን። የቡኖ በደሌን ግጭት ከውጭ በመጣ ምስል አጅቦ ያቀረበ ሚዲያን በዚህ መድረክ መጥራታቸው አይደለም የሚያሳዝነው፤ ይቅርታ ጠይቋል ሲሉ ሊከራከሩለት መሞከራቸው ነው። በአናቱ ደግሞ የየክልሎቹን ሚዲያዎች በዚህ መድረክ ሳይጠሩ “ከበትሩ ካሮቱ” ሲሉ በዚህ ጨዋ ህዝብ ላይ ማላገጣቸው ነው። “ማንን ተማምነው እንደሆነ አላውቅም ማስጠንቀቂያችንን አይሰሙም” ያሏቸውም የሚዲያ ተቋማት “የሚተማመኑት እርሳቸውን እንደሆነ” ከአንድ ከፍተኛ የክልል ባለስልጣን ሲነገራቸው በይፋ እየተመለከትን ዛሬም እኚህ ሰው ዳይሬክተር መሆናቸው በእርግጥም መንግስት እጀ ሰባራ ነው ብለን ብንጠራጠረው ተገቢ ምክንያት ስላለን ነው የሚሉ ወገኖችን ምክንያታዊነት የሚያረጋግጥልን አንደኛው ደርዝ ነው። ለእኚህ ማሳያ ለሆኑን ግለሰብ መቼም የረዥምም ሆነ የመካከለኛ ጊዜ እቅድ አያስፈልጋቸውም። ጉባዔ መጥራትም የሚጠበቅ አይደለም። በአንድ ደብዳቤ መሸኘት እየተቻለ ማባበሉ አሁንም መንግስት የገባውን ቃል መፈጸም አይችልም፤ እያሞኘን ነው የሚሉ ወገኖችን ምክንያታዊነት የሚያጠይቅ ነው።  

ብሮድ ካስት ባለስልጣን በጥቅሉ ግጭት አባባሽ በሆነበት አግባብ ስለሰላም የሚሰብክን መንግስት ለመመልከት የፈቀደ ሁሉ እውነትም ጨዋ ነው። ጎንደሬው፣ ሶማሌው፣ ኦሮሞው፣ አማራው፣ ሃጫሉ፣ ቴዲ አፍሮ፣ ባንዲራ ህገመንግስት ወዘተ እያሉ የማይገናኙ ነገሮችን ለማያያዝ እና እንደገና የግጭቱ አባት ሊሆኑም ሲዳዳቸው በተመለከትንበት አግባብ እኚህን ሰው የመንግስት ሃላፊ አድርጎ አሁንም ማስቀጠል በህዝቡ ላይ የሚቀልድ መንግስት እንጂ የሚታረም መንግስት አለን ብሎ ለመናገር ያስቸግራል። ሚዲያውን ትተው ኮንሰርት ጋር ጎራ ማለታቸው የመድረኩ አላማ ዛሬም የሚያስፈራሩ ሃይሎች እንዳሉና እንዳልሞቱ ለማሳየት የታለመ ያስመስላል።

ብሔርን መነሻ ያደረጉ ጥቃቶች የሚፈጸሙት እንሂን የመሰሉ ከኋላ የሚቆሰቁሱ ኃይሉች ስላሉ ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች አንድም ሥርዓቱን በዚህ መንገድ ለመጣል የሚፈልጉ ሲሆኑ፣ በሌላ በኩል በገዥው ፓርቲ ውስጥ ሆነው ለፖለቲካዊና ለኢኮኖሚያዊ የበላይነት ትንቅንቅ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በዚህም ሳቢያ የሕግ የበላይነት እንዲጠፋ ተደርጎ ገለልተኛ ሆነው ኃላፊነታቸውን መወጣት ያለባቸው የፀጥታ ኃይሎች ጭምር የግጭቱ አሟሟቂ  እንዲሆኑ እየተደረገ ነው፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች፤ ወልዲያ – ቆቦ ወዘተ መካከል የተነሳው ግጭት ከዚህ ምልከታ ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡ በኦሮሚያም ሆነ በወልዲያ ቆቦ ጥቃት የተፈጸመባቸው የሌሎች ብሔሮች ተወላጆችም የእዚህ ዓይነቱ ሴራ ሰለባ ናቸው፡፡  

 

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል መካከል የተነሳውን ግጭት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ በሰጡት ምላሽ  እየታየ ያለው ችግር በገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶች መካከል ሳይሆን፣ በአመራሩ የተፈጠረ መሆኑን ገልጸው የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡ እሳቸው በፓርቲ አመራሮች ዘንድ ሁሉንም ሕዝብ እንደ ራስ ሕዝብ ያለማሰብ አቋም መኖሩን፣ ይህም ችግር የሁሉም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና የአጋር ድርጅቶች መሆኑን በግልጽ አስረድተው የነበረ መሆኑም በተመሳሳይ፡፡ የፀጥታ አካላትም ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት አክብረው ማስከበር ሲገባቸው፣ በደምና በጎሳ በመለየት ሕዝብን የማየት አዝማሚያ እንደስተዋለባቸው ጠቁመዋል፤ በግጭት ውስጥ የተሳተፉ መኖራቸውን ጭምር፡፡

ታዲያ ይህንን በግልጽ የዘገቡ ሚዲያዎችንም ጭምር ብሮድካስት ባለስልጣን ግጭት  ቀስቃሽ ብሎ በአደባባይ ሲወቅሳቸው ስንሰማ እውነት ብናዝን ይፈረድብናል?። ሁሉንም ሚዲያ እንደራስ ሚዲያ የማይመለከት ሃላፊ ከላይ በተመለከተው አግባብ ሁሉንም ህዝብ እንደራስ ህዝብ ከማይመለከቱት አመራሮች ጎራ የተሰለፈ ስላለመሆኑስ ምን ማስረጃ አለ?? በኮሚዩኒኬሽን ሃላፊ ሚኒስትሩ አፋቸውን ያሟሹት ዳይሬክተር ጭራሽ ብለው በርካቶች ያረጋገጡትን እና በአደባባይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር ከላይ የተባለለትን ጉዳይ አንደኛውን ሚዲያ ግጭት ለመቀስቀስ ብለህ ዘግበሃል አይነት ወቀሳ ሊያደርሱበት ሲሞክሩም በይፋ ተመለከትን። በእርግጥ መጠቅለያው የችግሩ ምንጭ እራሱ ባለስልጣኑ እንደሆነ በዚያው በመድረኩ የተነገረው ቢሆንም፤ ግን ደግሞ መድረኩን የተመለከተ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ማዘኑን መንግስት አጽንኦት ሰጥቶ ሊያጤነው ይገባል። ህዝቡ በሃገሩ ተስፋ እንዳይቆርጥ ካስፈለገ እኝህን እና መሰል የሆኑ ሃላፊዎችን “አካፋ” ማለቱ ተገቢ ነው።

እንዲህ አይነት ግምገማና የመድረክ ላይ ድንፋታ በመሠረቱ የሕግ የበላይነትን የሚፃረርና አብሮ መኖርን ችግር ውስጥ የሚከት የአገር ሕመም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብን ፍላጎት የሚቃረንና የዘመናት መስተጋብሩን የሚደረምስ ማስፈራሪያ ነው፡፡ መንግሥት ባለበት አገር ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ አሳፋሪ ተግባር ሲፈጸም ዝም ብሎ ማየት ካላስጠየቀ ምን ሊያስጠይቅ ነው? ሕገ መንግሥቱ ሥልጣንና ኃላፊነታቸው በግልጽ የደነገገላቸው አካላት ከዚያ በላይ ሊሄዱ ሲሞክሩ ዛሬም መመልከት ነበረብን ወይ? ይህንን በሕግ የተገደበ ሥልጣናቸውን ለሌላ ዓላማ ሲያውሉት ዝም ማለትስ ምን ማለት ይሆን? ይህ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በግልጽ ሊነገረው ይገባል፡፡

በሌላ በኩል እራሱን ለማረም መንግስት ያስቀመጠው አቅጣጫ ወራት እያስቆጠረ ነው። በአባላት፣ በጠቅላላ ጉባኤ ወዘተ የሚታዩ የፓርቲ ስራዎች እንዳሉ እና ጊዜ ሊወስዱ የሚችሉ እንደሆነ ቢገመትም፤ መንግሥት ግን በሕገ መንግሥቱ መሠረት አሠራሩን ለሕዝብ ግልጽ ማድረግ አለበት። አገር በግጭቶች እየታመሰች፣ ክቡር የሆነ የሰው ሕይወት እየተቀጠፈ፣ በሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች እየተፈናቀሉና የአገር አንጡራ ሀብት እየወደመ ሕዝብ ስለአገሩ መረጃ የለውም፡፡ ያልተሟሉና ከላይ በተመለከተው መልኩ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ መረጃዎች በመንግሥት አካላት እየተለቀቁ ግራ እየተጋባን ነው፡፡ መንግሥት ኃላፊነት የሌለበት ይመስል መረጃ ነፍጎ ሕዝብ ለአሉባልታና ለሐሰተኛ ወሬ ጭምር እየተዳረገ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ መንግሥት በሕጉ መሠረት ሥራውን ማከናወን ሲያቅተው ውዥንብር ይነግሣል፡፡ ውዥንብር በተራው ለግጭት በር ይከፍታል፡፡

አንደኛው አንድ ሲል ኢቢሲ 10 ይላል። ይህ ቆርጦ ቀጥል የሆነ መስሪያ ቤትም ሃይ ሊባል የሚገባው እንደሆነ ሃገራችን ስለገጠማት ችግር የሚያወጉ ሁሉ እየተናገሩ ነው። በወልዲያ ግጭት መነሳቱን ያልነገረን ኢቢሲ አንጻራዊ ሰላም የመስፈኑን ዜና ሊያበስረን መሞከሩ ንቀት ብቻ ሳይሆን ህዝብና መንግስትን ከማራራቅ ተነጥሎ የማይታይ ነው። የግጭት መንስኤ ከሆኑት ምክንያቶች መካከል ሀገር ውሸት ውስጥ መዘፈቋ መሆኑ አንደኛው ነው። የኢህአዴግ አራት ብሄራዊ ድርጅቶች የሰጡት መግለጫ እዚያው በኢቢሲ በብሄራዊ ሬዲዮውና  በቴሌቪዥኑ የተላለፈው ለየቅል ነው።ይህ ደግሞ አሳፋሪ እና ህዝብ የተደበቀው ነገር እንዳለ የሚያመላክት ነው። የሚያናድድ አሽቃባጭነትም ነው። አንድ ሃገር የሆነውን ጉዱን ከላይ በተመለከተው አግባብ የተመለከትንለትን ብሮድካስት ባለስልጣን በተመለከተ ኢቢሲ የሰራው “ሚዲያዎች ግጭት አባባሽ የነበሩ እንደሆነ ተመለከተ” አይነት ዜና ቆሽት የሚያበግን የሚያስማማ ሳይሆን የበለጠ የሚያጋጭ ውሸት ነው። ስለሆነም ስለሃገር ሰላም መንግስት ይህንንም ቤት ይመልከተው እንላለን።

የዜጎች ደኅንነት ማንንም ሊያሳስብ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው የባይተዋርነት ስሜት የሚሰማቸው ብሔርተኝነት እየተለጠጠ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ሲፈታተነው ነው፡፡ ዜጎች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደራቸው፣ በራሳቸው መዳኘታቸው፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸው፣ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ማሳደጋቸው፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማጎልበታቸውና በማንነታቸው መኩራታቸው መከበር አለበት፡፡ ለምን ዘፈንክ ብሎ ነገር፤ ለምን የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቀምክ፤ ለምንስ የኮንሰርቱ አዳማቂ ሆንክ? ብሎ ቁጣ ከላይ የተመለከተ የዜጎችን መብት አለመቀበል ነው። ይህ አይነቱ አመለካከት እና አመራር የትም ሊያደርሰን አይችልም።

በተለይ ወጣቶች ራሳቸው ላይ አጥር ሠርተው ሌሎች ወገኖቻቸውን አትድረስብኝ፤ አልደርስብህም የሚል ችግር ውስጥ እንዲገቡ የሚደረጉት፣ ይህን በመሰሉ ገፊ ምክንያቶች መሆኑንም ማመን ተገቢ ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ለዘመናት አብሮ የኖረው ይህ ታላቅ ሕዝብ ጠባብነትና የጋራ እሴቱን የሚንዱ ድርጊቶችን እንደማይቀበል በታሪኩ በተደጋጋሚ አሳይቷል፡፡ ይህ ኩሩና አስተዋይ ሕዝብ የሚፈልገው በክፉና በደግ ጊዜያት አብሮ ተደጋግፎ እንደኖረው በዚሁ መሠረት መቀጠል ነው፡፡ ይህንን አስደሳችና የሚያኮራ የጋራ እሴት ለአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ግንባታ መሠረት ማድረግ ሲገባ፣ ለግለሰቦችና ለቡድኖች ጥቅም ብቻ ሲባል ግጭት እየፈጠሩ አገር ማመሰቃቀል ሊቆም ይገባል፡፡ ከአገርና ከሕዝብ በላይ ማንም የለም፤ በመሆኑም፣ ተወደደም ተጠላም በተለያዩ በመንግሥት ሥልጣንና የኃላፊነት ደረጃ ላይ ያሉ ሳይቀሩ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ሰላማችን ወደነበረበት የሚመለሰውም በዚህ መንገድ ብቻ ነው።

ከዚያ ውጭ ግን በስሜታዊነት የሚካሄድ አንዳች ተግባር የትኛውንም ወገን ተጠቃሚ አያደርግም። መብትን በአመጽና በብጥብጥ ማስከበር እንደማይቻል፣ በአንጻሩ በሰከነ አዕምሮ፣ በሰለጠነ አካሄድ፣ በመነጋገር እና በመወያየት ማንኛውንም ችግር መፍታት ይቻላል። የዴሞክራሲ ባህልን እየተዉ በመሄድ አገርን መገንባት አይቻልም። ችግሮችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ በአመጽና በግርግር ለውጥን ለማምጣት የሚደረግ ጥረት በርካታ አገራትን መንግሥት አልባ አድርጎ ወደ ውድመት እንዳመራ በአረብ አገራት በቅርቡ የተከሰቱትን ችግሮች ወጣቱ ሊያስታውስ ይገባል፡፡ ከታሪክ እንደምንረዳው፣ ግጭት ማንንም ተጠቃሚ አያደርግም። የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ዕድገት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የምንችለው በቅድሚያ ሰላምና መረጋጋትን ስናሰፍን ነው። ሰላም ለአገራችን የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው። ግጭት የድህነታችንን ዕድሜ የሚያራዝም፣ በድህነት ላይ ከከፈትነው ጦርነት የሚያዘናጋን ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy