Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስራ ፈጣሪዎች እንዲበረታቱ…

0 370

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስራ ፈጣሪዎች እንዲበረታቱ…

ዳዊት ምትኩ

ወጣቶች ስራ ፈጠራ ናቸው። መንግስት ባመቻቸው ሁኔታ ተጠቅመው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም አገራቸውን ለመጥቀም ጥረት እያደረጉ ነው። ይህ ጥረታቸው መንግስት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቀረፀው ፕሮግራም መሰረት እየተከናወነ የሚገኝ ነው። ወጣቶች በሁሉም የልማት መስኮች የጀመሩት ስራ ፈጠራ ሊጠናከርና ተገቢውም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።  

ወጣቶች በተመቻቹላቸው በእነዚህ ዕድሎች ላይ በጥረታቸው ከተሳተፉ ከጠባቂነት መንፈስ ተላቅቀው ራሳቸውንና ህዝባቸውን መጥቀም መቻላቸውን እያሳዩን ነው። ይህን እውን ለማድረግ የእነርሱ ጥረት ወሳኝ ነው።

ታዲያ ጥረታቸው እውን መሆን ያለበት ከሁለት ጉዳዩች አኳያ ይመስለኛል። አንደኛው የየትኛውንም ፅንፈኛ ሃይል አሉባልታ ባለመስማት ፊታቸውን ወደ ተመቻቸላቸው የልማት መስክ በማዞር ነው። ሁለተኛው ደግሞ ተስፋቸው ይህን አገር በመምራት ላይ የሚገኘው መንግስት እንጂ ከማንም አለመሆኑን በሚገባ በመረዳት ነው።

ወጣቱ ሚዛናዊና ፍትሃዊ አስተሳሰብ ያለው በመሆኑ፤ በሁከት ፈጣሪ ሃይሎች አማካኝነት የሚቀርቡ “ጎስም ነጋሪት፣ ክተት ሰራዊት” ዓይነት የጥፋት እንዲሁም ፀረ-ልማት ጥሪዎችን አይቶ እንዳላየ፤ ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ ማለፍ ይገባዋል፡፡ እርግጥ እዚህ ላይ “ለምን?” የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡

እንደሚታወቀው ሁሉ ወጣቱ ባለፉት 15 የፈጣን ዕድገት ዓመታት ውስጥ የመንግሥት ልማታዊ አቅጣጫን በሚገባ ይገነዘባል ብዬ አስባለሁ፡፡ እናም ማንኛውንም ጊዜያዊ ችግር መንግሥት እንደሚፈታው ማመን ያለበት ይመስለኛል። እናም ችግሩን በመቋቋም ወደ ዘላቂው መፍትሔ መግባት ያለበት ይመስለኛል—የሁከት ኃይሎች መጠቀሚያ ከመሆን የሚገኝ ነገር የለምና።

ምንም እንኳን ወጣቱ በአሁኑ ወቅት ስልጣንን ለግል ጥቅማቸውና ለኑሮ ማደላደያነት ለማዋል በሚሹ ኃይሎች አማካኝነት የተፈጠረ ችግር ቢኖርበትም፤ ችግሩ በሀገሪቱ በመመዝገብ ላይ የሚገኘው ልማታዊ ድል ጊዜያዊ እንቅፋት መሆኑን መረዳት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ባሻገርም፤ የመንግሥትን የለውጥ ኃይልነት ስለሚያውቅ፤ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ እንደማይወጣና እንደሚለወጥም ማመን ይኖርበታል፡፡

እርግጥ አንድ መንግሥት ወይም የፖለቲካ ድርጅት በባህሪው ህዝባዊ ከሆነ፤ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያማከሉ መሆናቸው አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በባህሪው ህዝባዊና ልማታዊ በመሆኑ፤ ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ህዝቡን በአብዛኛዎቹ መስኮች በየደረጃው ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ወጣቱም የዚህ እድገት ተጠቃሚ መሆን ችሏል፡፡ የጀመረው የስራ ፈጠራ ክሂሉ ሊበረታታ ይገባዋል።

እርግጥ ወጣቱ ከመንግስት የሚሻው ነገር ተጠቃሚነትን ነው። ይህን ለመከወንም መንግስት ለወጣቱ ስራ ፈጠራ ሊውል የሚችል ቢሊዮኖችን መድቧል። ወጣቱም ወደ ስራ ገብቷል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት እያስመዘገበም ነው። የአገሩ ተስፋ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ደማቅ የተጠቃሚነት መንገዶችን እየተጓዘ ነው።

እርግጥ የወጣቱ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በልማቱ ልክ በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ ሆኗል ማለት አይቻልም። ያም ሆኖ ግን ዛሬም ከትናንቱ በተሻለ ሁኔታ የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሩህ ተስፋዎች ተወጥነዋል። እንዳልኩት ወጣቶች የዛሬ አፍላ የልማትና የዴሞክራሲ ኃይሎችና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች እንደመሆናቸው በትምህርት የታነፀና የተገነባ አቅም እንዲኖራቸው ከፍተኛ ትኩረት ለመስራት ታቅዷል።

የወጣቶችን ሁለንተናዊ ብቃት በማሳደግ በአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም ልማታዊ አስተዳደር ግንባታ እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በተደራጀና በተቀናጀ አኳኋን የነቃና ግንባር ቀደም ተሳትፎ እንዲያደርጉና ከውጤቱም በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት ቁርጠኛ አቋም ይዟል።

የሀገራችን ወጣቶች አካበባቢ ከሥራ ስምሪት ጋር ተያይዞ የሚታየውን የተሳታፊነትና ፍትሐዊ ተጠቀቃሚነት ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ መረጃዎች ያስረዳሉ። በዚህም በተለያዩ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ዘርፎች የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከግምት ውስጥ ያስገቡ እንዲሆኑ፣ ወጣቶች በህብረት ሥራ ማህበራት በመደራጀት የብድርና ቁጣባ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ታስቧል።

በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከቴክኒክ ሥልጠና ማዕከላት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት የወደፊት የሀገራችን ተስፋ በሆኑ አምራች ዘርፎች ማለትም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ በኢንዱስትሪዎችና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ተሰማርተው የወደፊት የሀገራችን ልማታዊ ባለሃብቶች መፍለቂያ እንዲሆኑ ሁለንተናዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት በመንግስት የስልጣን መዋቅር ውስጥ በተፈጠረው የመልካም አስተዳደር ችግር ወጣቱን ከተጠቃሚነት ጎራ ያፈናቀለውና በተገቢው መንገድም ከልማቱ ተጠቃሚ እንዳላደረገው ይታወቃል።

በአሁኑ ወቅት አገራችን ውስጥ ለወጣቱ አዲስ መድረክ ተፈጥሯል። የወጣቱ ስራ ፈላጊ ድምፅ ይበልጥ ሰሚ፣ ይበልጥ ተደማጭ ሆኖ ገንዘብም ተመድቦለት ወደ ስራ ገብቷል። እንዲያውም እንደ ኦሮሚያ ያሉ ክልሎች ባለሃብቶች ወስደው ያላለሟቸውን አካባቢዎች ለወጣቱ በመስጠት ወጣቱ ራሱን በስራ እንዲችል እያደረጉ ነው። የወጣቱ ስራ ፈጠራም በገሃድ እየታየ ነው። የሚያሰራው አካል ካገኘ ወጣቱ ስራ ፈጣሪ መሆኑን እያስመሰከረ ነው።

ወጣቶች የዚህች ሀገር ገንቢዎች ናቸው። ሀገራችንን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው ትግል ፋና ወጊዎች ሆነው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል። በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ሀገርን ማበልፀግ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል። በእኔ እምነት እንደ ኢትዮጵያ ያለ በርካታ ቁጥር ወጣት ያለው ሀገር በወጣቱ ላይ ኢንቨስት አድርጎ ከወጣቱ አፍላ ጉልበት የሚያገኘውን ልማታዊ ፋይዳ ማረጋገጥ ይኖበታል።

በዚህ መሰረት መንግስት ተገቢውን ትኩረት ለወጣቱ እየሰጠ ነው። ይህ ትኩረት መጠናከር አለበት። ሰሞኑን እየቀረበ ባለው “በኢትዮጵያ የተሰራ “Made In Ethiopia” ኤክስፖ ላይ የወጣቱ ፈጠራ እስከየት ድረስ የሚጓዝ እንደሆነ እየተመለከትን ነው።

ይህ የስራ ፈጣሪነት መንፈስ እጅግ የላቀ እውቅና ሊቸረው ይገባል። ምክንያቱም የወጣቶችን የስራ ፈጠራ ማጠናከር እንደ አገር ልንደርስበት የምንችለውን ግብ ከወዲሁ እየተመለከትነው ስለሆነ ነው። በመሆኑም የወጣቱ ስራ ፈጠራ በመንገስት ብቻ ሳይሆን በህብረተሰቡም ጭምር በጎ ምልከታ ሊኖረውና ሊጠናከር ይገባል።

       

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy