Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቀዳሚ ተጎጂ ማነው?

0 270

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቀዳሚ ተጎጂ ማነው?

ዳዊት ምትኩ

ሰሞኑን በአንዳንድ አካባቢዎች የታየው ክስተት ፅንፈኛው ሃይል ህብረተሰቡ የዕለት ጉርሱን የሚያገኝበትን የንግድ ተቋማት የመዝጋት እንዲሁም የትራንስፖርት ፍሰት እንዲስተጓጎል መንገድ የመዝጋት ተግባሮችን ሲያከናውን ተስተውሏል። ህብረተሰቡም የንግድ ተቋሞቹን በፍርሃት ለመዝጋት ተገድዷል። መንገድ ሲዘጋም ዝምታን ይመርጣል። ይህ መሆን እንደሌለበት ጉዳይ ነው። ምክንያቱም በግብይት ተቋማትም መዘጋትም ይሁን በትራንስፖርት ፍሰት መቆም ቀዳሚው ተጎጂ ራሱ ህብረተሰቡ ስለሆነ ነው። ፅንፈኛው ይህን የሚያደርገው የሀገራችንን ኢኮኖሚ ለማዳከም ካለው ፍላጎት በመነሳት መሆኑን ህብረተሰቡ ግንዛቤ ሊይዝ ይገባል።

እርግጥ ፅንፈኛው ኃይል የራሱን ጥቅም እነጂ የህብረተሰቡን ተጎጂነት አይገነዘብም። ይህ ህብረተሰብ ኑሮው ገና የደረጀ አይደለም። የህዝቡ የነፍስ ወከፍ ገቢ እየጨመረ ቢሆንም፤ ብዙ መስራትን ይጠይቃል። አብዛኛው ወጣት ተጠቃሚ መሆን የጀመረው በቅርቡ ነው። እንኳንስ መንገድ ተዘግቶና የንግድ ተቋማት እንዳይከፈቱ ተደርጎ ቀርቶ በአሁኑ ወቅት እየተደረገ ያለው ጥረት ገና ጅምር ላይ ያለ በመሆኑ ሊያስመካ የሚችል አይመስለኝም። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፤ ይህ የፅንፈኛው ፍላጎት ኑሮውን ለመግፋት ደፋ ቀና የሚለው አብዛኛው ወጣት ያለ ስራ እንዲቀመጥና ተጎጂ እንዲሆን ከማሰብ የመነጨ ነው።

እርግጥ መንግስትም ቢሆን ፅንፈኞችን ቀድሞ መገኘት ያለበት ይመስለኛል። አገራችንን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው ትግል ፋና ወጊዎች ሆነው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል። እርግጥ ነው አገራችንን የመሰለ በርካታ ቁጥር ወጣት ያለው አገር በወጣቱ ላይ ኢንቨስት አድርጎ ከወጣቱ አፍላ ጉልበት የሚያገኘውን ልማታዊ ፋይዳ ማረጋገጥ ካልቻለ ችግሮች መፈጠራቸው አይቀርም። ወጣቱ እንደ ሰሞኑ ዓይነት አላስፈላጊ የመንገድ ስራዎች ተግባር ሊሰማራ ይችላል። እናም መንግስት አቅም በፈቀደ መጠን ከግንዛቤ ማስጨበጫ ጀምሮ እስከ ተጠቃሚነት ድረስ ያሉትን ዕድሎች አሟጦ መጠቀም ይኖርበታል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ከድህነት ጋር ፍልሚያ ገጥሞ ተጠቃሚ እየሆነ ያለው ወጣት፤ በምንም ዓይነት ምክንያት ሁለንተናዊ የጥቅም ተጋሪነቱ የኋሊት ተጎትቶ እንዲሸረሸርበት አይፈልግም፡፡ ነገ ትልቅ የዕድገት ባለቤት ለመሆን ያለመው ወጣት ዜጋ፤ ትኩረቱን ማድረግ ያለበት የትናንት እሱነቱን በስራ ለመቀየር ደፋ ቀና በማለት እንጂ፤ ሁከትን በማዳመጥ አይደለም፡፡ በመሆኑም እነርሱ ባህር ማዶ ሆነው ልጆቻቸውን በሰላም እያስተማሩ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለውንና ህይወቱን ለመቀየር እየተጋ ያለውን ወጣት በእሳት ለመማገድ የሚሹ ፅንፈኛ ኃይሎችን ጥሪዎች ማምከን ይኖርበታል።

ወጣቱ ከሁከቱ ወዲህ ስለ እነዚህ ኃይሎች ባዶና የአሉባልታ አጀንዳ አራማጅነት እንዲሁም ስለ መንግሥት ትክክለኛነት የልማት አቅጣጫዎች መገንዘብ ይኖርበታል። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት መንግስት የወጣቱን ተጠቃሚነት በዳግም ተሃድሶው ይበልጥ ለማረጋገጥ እየሰራ ነው። እርግጥ ስራው እየተከናወነ ያለው በሂደት ነው። ሁሉንም ጥያቄዎች በአንድ ጊዜ ማሟላት አይቻልም። አቅም ይጠይቃል። በእርግጠኝነት ለመናገር ግን ሁሉም ጥያቄዎች ጊዜያቸውን ጠብቀው በፍጥነት የሚመለሱ ናቸው።

እርግጥ የኢትዮጵያ መንግስት አደርገዋለሁ ብሎ ገቢራዊ ያላደረገው ምንም ዓይነት ነገር የለም። በየጊዜው እያደገ ከመጣው የህዝብ ቁጥር ጋር ዕድገቱ ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ ካለማድረጉ በስተቀር። ያም ሆኖ አብዛኛውን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። መወጣቱም የማናቸውንም ጥያቄዎች መፍትሔ ከመንግስት ብቻ መሻት አለበት።  

መንግስት ቀደም ባሉት ጊዜያት በአገሪቱ ውስጥ ድህነትን አቅም በፈቀደ መጠን በመቀነስ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ እንደሚደርግ፤ ትምህርትን፣ ጤናን፣ የመሠረተ-ልማት አውታሮችን እንደሚያስፋፋ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ስር እንዲሰድ አደርጋለሁ በማለት የገባቸውን የተስፋ ቃላት ተፈፃሚ አድርጓቸዋል። አስተማማኝ ሰላም በማረጋገጥ ረገድም የገባውን ቃል አላጠፈም። እነዚህን እውነታዎች ወጣቱም ይሀነ መላው ህብረተሰብ ይገነዘባል።

በቅርቡ ሀገራችን ውስጥ የተፈጠረውን ጊዜያዊ ችግር መንግሥት መስመር እንደሚያሲዘው ማመን ያለበት ይመስለኛል። እርግጥ ባለፉት ጊዜያት ገዥው ፓርቲና መንግሥት የለውጥ አደራጅና ቀያሽ መሆናቸውን ወጣቱ በሚገባ ስለሚያውቅ፤ አሁን የተፈጠረው ችግር በመንግስት እንጂ በፅንፈኛ ሃይሎች የመንገድ መዝጋትና የሱቆች መቆለፍ መፍትሔ ኪሆን አይችለም። ምንም እንኳን ፅንፈኛ ኃይሎቹ በተቀናጀ ሁኔታ የህዝቡን ብሶቶችና የራሳቸውን አሉባልታዎች በማያያዝ አያ ለማራገብ ቢሞክሩም እንዲሁም ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑና የሚምታቱ ፀረ-ልማት ሃሳቦችን እያቀረቡ ወጣቱን ለማሳሳት ቢሞክሩም ወጣቱ ተጎጂው ራሱ መሆኑን በማወቅ ምላሽ ሊሰጣቸው አይገባም።

አሁንም እንደ ዜጋ ደግሜ ደጋግሜ መናገር የምሻው ወጣቱ የእነዚህን ጽንፈኛ ሃይሎች ዓላማና ግብ በሚገባ መረዳት ይኖርበታል። ፀረ-ሰላም ኃይሎቹ የትኛውንም የሀገራችንን ህዝብ የሚወክሉ አይደሉም። ሊወክሉም አይችሉም። ምክንያቱም ዓላማቸውና ግባቸው ከበስተኋላቸው የሚደጉማቸውን ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይል ፍላጎት ማስፈፀም ብቻ ስለሆነ ነው።

የኤርትራ መንግስት ለረጅም ጊዜ የሚያልመው በሁከት የተዳከመችና የተበታተነች ኢትዮጵያን ማየት ነው። ለዚህም ሲል የሀገራችንን አሸባሪዎችና ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በጉያው ውስጥ ወሽቆ ሰላማችንን ለማደፍረስና የጀመርነውን ፈጣን ዕድገት ለማስተጓጎል ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም።

በአሁኑ ሰዓትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲታወጅ እንዴት እንደተንጫጫና ዓላማው ምን እንደሆነ መገንዘብ ይኖርበታል። ግና የአገራችንን ሰላም ለማረጋገጥ አዋጁ ተኪ የሌለው ሚና እንደሚጫወት ህብረተሰቡ ሊያውቅ ይገባል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የተረጋጋ ሰላም እንዳይኖርና ኢኮኖሚያችን እንዳያንሰራራ የሚፈልጉ አንዳንድ የውጭ ሃይሎች መኖራቸው ይታወቃል። እነዚህ ሃይሎች ካደግን እንደምንለወጥና የተፈጥሮ ሃብታችንንም በዚያው ልክ እንደምንጠቀም ስለሚያውቁ አገራችን ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ተግተው የሚሰሩ ናቸው።

እነዚህ እንደ ፌስ ቡክ ዓይነት ማህበራዊ ድረ ገፆችን በመጠቀምና እንደ ጃዋር መሃመድ ዓይነት ግለሰቦችን በመቅጠር ወጣቱን በተሳሳተ መንገድ እየመሩት ነው። ይህ እውነታ በሁሉም የሀገራችን ህዝብ ሊታወቅ ይገባል።

ካደግንና ከተለወጥን የአፍሪካዊያን ምሳሌዎች እንዲሁም አፍሪካዊያን እኛ የምንከተለውን የልማት ሞዴል ተከትለው ሊበለፅጉ ይችላሉ የሚል ስጋት ያላቸው አንዳንድ የውጭ ሃይሎችም እድገታችን ላይመቻቸው ይችላል።

እናም ምናልባትም መንገድ በመዝጋቱና ከቤት እንዳትወጡ የሚል አድማ በመጥራቱ የበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይህ ልማትን የሚፃረር አካሄድ በቅድሚያ ተጎጂ የሚያደርገው ራሳችንን በመሆኑ ከተግባሩ መቆጠብ ይኖርብናል ብዬ አስባለሁ። ቸር ያሰንብተን።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy