Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በስሜት ጅረት መዳረሻው…

0 285

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በስሜት ጅረት መዳረሻው…

አባ መላኩ

የአማራና የትግራይ ህዝቦች መለየት በማይቻልበት ሁኔታ የተቀላቀሉ አንዱ ሌላውን መስሎ ሳይሆን  ሌላውን ሆኖ የሚኖሩ፤ የዘመናት የአብሮነት ታሪክን የሚጋሩ ህዝቦች ናቸው።  የእነዚህ ህዝቦች ቁርኝት በበርካታ ነገሮች እጅግ የጠበቀ፣ ጠንካራ አንድነት የሚንጸባረቅበት፣ የሃይማኖት፣ የባህል፣ የቋንቋ ትስስር የሚስተዋልበት በመሆኑ ማንም ዕለቱን ተነስቶ ሊያፈርሰው  እንደማይችል ሊታወቅ ይገባል።  እነዚህ ህዝቦች ለዘመናት ክፉውንም ደጉንም አብረው አሳልፈዋል፤ አንተ ትብስ እኔ ልብስ ተባብለው  ለዘመናት ኖረዋል፣ እየኖሩም ነው፤ ኢህአዴግ ኖረም አልኖረም ነገም ይህ አብሮነታቸው ይቀጥላል።  ምክንያቱም  አንዱ ካላንዱ ጎዶሎና ባዶ ነውና።  የአማራና  የትግራይ  ህዝቦች አንዱ ለሌላው ቆስሏል፣ ሞቷል፤ ተርቧል፣ ታርዟል፤ በመሆኑም በደምና አጥንት የተሳሰረው ግንኙነታቸው ጊዜ አይፈታውም፤  ዘመንም አይሽረውም። ጽንፈኞች ያስቀመጡላቸውን ቅርቅፍቶችንም  ይሻገሯቸዋል፤  እነዚህ  መንገራገጮች ሁሉ ያልፋሉ። የሁለቱ ህዝቦች አብሮነት ግን  ህያው እንደሆነ ዘመናትን ይሻገራል።

አዎ እነዚህ  ህዝቦች በርካታ መልካምና መጥፎ ታሪክን ተጋርተዋል። ከላይ እንዳነሳሁት መለየት በማይቻልበት ሁኔታ አንዱ ሌላውን መስሎ ሳይሆን ሆኖ የሚኗኗሩ ህዝቦች ናቸው። ባለፈው ዓመት በአንዳንድ የአማራ አካባቢዎች የተከሰቱ ሁከቶች የእነዚህን ህዝቦች አብሮነት ተፈታትኖታ እያልን ስንጮህ አሁን ደግሞ በወልዲያና አካባቢው  እንዲህ ያለ ነገር ዳግም ተነስቷል። በአምናው ግጭት ወቅትም ሆነ  በዘንድሮው ሁከት ዋንኛ  አቀንቃኞች  ተማርኩ የሚለው  እንዳንድ  ወጣት ሃይል ነው።  ይህ ሃይል በጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ሴራ  በቀላሉ ተጠልፎ የህዝቦች መቻቻልና አብሮነት የማይታየው አካል ለመሆን በቅቷል።

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ በባለፉት 25 ዓመታት የፈራናቸው ሁሉም ባይባሉም ቀላል የማይባሉ ወጣቶች ለአብሮነትና መቻቻል የሚሰጡት ቦታ እምብዛም መሆኑን የታዘብኩት በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ሁከቶችን  ስመለከት  ነው። በአብዛኛው አካባቢዎች የተመለከትኳቸው ሁከቶች የሚመሩት  በታዳጊ ወጣቶች ነበር።  ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ይህ ሃይል ለጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች መሰሪ አካሄድ እንደተጋለጠ ነው። መንግስት እና ኢህአዴግ  ይህን ሃይል  በአግባብ  መያዝ  ባለመቻላቸው  የዳያስፖራ ፖለቲከኞች  የዚህን  ወጣት ሃይል  ስሜት  በቀላሉ መኩርኮር  እንዲችሉ  በር ከፍቶላቸዋል። በርካታ ወጣቶችንም ለጥፋት አጋልጦ ሰጥቷቸዋል።  

በአስቸጋሪ ወቅት እንኳን  ህብረተሰባችን ለአብሮነት ያለውን አመለካከት  ተመልክተን ኮርተናል። ማገናዘብ  የቻለው  የህብረተሰብ ክፍላችን የጥፋት ሃይሎችን  ሲገስጽ፣ ሁከተኞችን ሲቆጣ ተመልክተናል፣ ጉረቤቶቻቸውን ከጥቃት ለመከላከል ሲሯሯጡ ተመልክተናል፣ ንብረታቸውንም  ከውድመት ለመከላከል ጥረት አድርገዋል፤  ከአቅም በላይ ሲሆኑባቸው ደግሞ አብረው  ሲላቀሱ፣ ሲያዝኑና ሲያስተዛዝኑ  ተመልክተናል።  ህብረተሰባችን በአብሮነቱ  የመጡበትን  ማንኛውንም አካል  ልጁ ቢሆን እንኳን  ለህግ  አሳልፎ ሲሰጥ ተመልክተናል።  እኛ የምናውቀው  ኢትዮጵያዊነት  ይህ ነው።  አዲሱ ትውልድ ሆይ ረጋ በል፤ ቆም ብለህ አስብ፤ ነገሮችን  አመዛዝን፤ ከስሜት ጅረት ውጣ፣ የስሜት ጅረት መዳረሻው መጠፋፋትና እልቂት  ነው።  በሁከትና  ነውጥ የሚመጣ  መፍትሄ  ለሁሉም አይበጅም፤ በሁከትና ነውጥ ለውጥ የሻቱ አገራትን መጨረሻቸውን  ተመልክተናል። ውድቀት!

የአማራና የትግራይ ህዝቦች ድንበር ሳይለያቸው ቋንቋ ሳይገድባቸው  ተጋብተው ተዋልደው ያለውን ተሰጣጥተው፣ አንዱ ለሌላው  ዋስ ጠበቃ ሆነው  የኖሩ ወደፊትም  የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው፤ ተወደደም ተጠላም  ይህን አብሮነታቸውን ሊነጣጥል ማንም  አይቻለውም።  በጥላቻ ፖለቲካ  የተጠመዳችሁ  ሁሉ  እባካችሁ ለማይረባ የፖለቲካ ትርፍ ብላችሁ  የአብሮነት እሴቶቻችን  አትሸርሽሩ።  ጽንፈኛና መርዘኛ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች እባካችሁ  የዘረኝነት  ፖለቲካ አጥፊ ነውና  ለስልጣን እርካብነት አትጠቀሙበት።  የአገሬ ወጣት ሆይ በስሜት ባህር ውስጥ እንድትገባ አድርገውህ ወደ አዙሪት ፖለቲካቸው   ሊከቱን  ከሚሯሯጡ  የዳያስፖራ ሴረኞች  ራሳችሁን ጠብቁ። ጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች  ሆይ አውሮፓና አሜሪካ  የቅንጦት ኑሯችሁን እየገፋችሁ  በደሃ ልጆች  ደም  የስልጣን  መንገዳችሁን  አትዋጁ።

በአማራና ትግራይ ህዝቦች መካከል አሜኬላ ለመዝራት  መሯርጡ  ቢበዛም  እነዚህ ህዝቦች ትላንትን በፍቅር እንደኖሩ ሁሉ  በእርግጠኘነት ነገም ግንኙነታቸው  ይቀጥላሉ።  ምክንያቱም አንዱ ካላንዱ ባዶና ጎዶሎ  ነውና። እንደተመለከትነው በእነዚህ ህዝቦች መካከል ሁከትና ብጥብጥ  እንዲነግስ   የሚሯሯጡት   ተማርኩና ዘመናዊ ሆንኩ የሚለው አንዳንድ የወጣቱ  ክፍል  ነው። ይህን አካል ማስተካከል የሁላችንም ተግባር መሆን መቻል አለበት። እያንዳንዳችን በተግባር ልናስመሰክረው ይገባናል። ወጣቶቻችንን እንምከራቸው። ይህ አልሆን  ግን የህግ የበላይነት ከድርድር የሚቀርብ መሆን መቻል የለበትም።

የሁለቱን ህዝቦች  አብሮነት  ለመሸርሸር  በማህበራዊ  ሚዲያዎች  የሚሰራጩ  መረጃዎች እውነትነት የራቃቸው  በመሆናቸው  ልናወግዛቸው  ይገባል። በዚህ ድርጊት ላይ የተጠመዱ አካላትንም   በቃችሁ  ልንላቸው  ይገባል።  ሁሉም አካል  ሰከን ይበል፤ ሰክኖ ማሰብ ውጤቱ መልካም ነው። ወጣቶች ሆይ  በስሜታዊነት እየተነሳችሁ  የአብሮነት እሴቶቻችንን አሽቀንጥራችሁ አትጣሉብን። የጥበትና ትምክህት ሃይሎች እንኳን ህዝብን ቤተሰብን የሚነጣጥል መሰሪ አካሄድን የሚከተሉ በመሆናቸው ተገቢው ጥንቃቄ ካላደረግን እንዲሁም አካሄዳቸውን ካልነቃንባቸው አገራችንን ወደቀውስ ሊያመሯት ይችላሉ። የጽንፈኛው አካል የበሬ ወለደ ፖለቲካው ማንንም ስሜታዊ ያደርጋል።  ማንንም ያሳስታል። በተለይ ወጣቶች ላይ ይበረታል። በመሆኑም ወጣቶች የእነዚህን መሰሪ ሃይሎች  አካሄድ ሊነቁባቸው ይገባል።      

የአማራና የትግራይ  ህዝቦች ኮንፍረንስ ላይ አንድ  አባት እንዲህ ሲሉ ተናግረው ነበር። በእርግጥ እኚህ አባት እራሳቸው  የሌላን ሰው አገላለጽ ጠቅሰው  ነበር።  አባባሉ እንዲህ ነው። “የአማራና የትግራይ ህዝብ ከወንድማማችና እህትማማች በላይ መንትያ ህዝብ ነው” መንትያ ወንድማማች ወይም እህትማማች አይደለም ማለቴ አይደለም፣ ነገር ግን መንትያ አብሮ የተፈጠረ፣ በጋራ አንድ መሃጸን የተኛ፣ በጋራ አንድ ጡት የጠባ ማለት ነው።  እነዚህ ህዝቦች ለዘመናት ተጋብተው ተዋልደው በደምና በስጋ  ተሳስረው፣ ተከባብረውና እርስ በርስ ተሳስበው  የኖሩ ህዝቦች ናቸው።  አምና በዚህን ወቅት በሰሜን ጎንደር  በደምና በሥጋ የተሳሰረውን  የሕዝቦች አንድነት በፀረ ሰላም ኃይሎች ሴራ እንዲያ ሲሆን ስንመለከት ሁላችንም   አዝነን፣ ተቆጭተን ጥፋተኞችን ተቆጥተን መክረን አስመክረን  ዳግም እንዲህ ያለ ነገር እንዳይከሰት  ብለን  ስናበቃ  ደግሞ  አሁን በሰሜን ወሎ እንዲህ ያለ ነገር መከሰቱ የሁላችንንም ልብ የሚሰብር ድርጊት ነው። በዚህ ድርጊት ውስጥ ሚና የነበራችሁ ሁሉ እባካችሁ እጃችሁን ሰብስቡ።

እንዲህ ያሉ ቅጥ ያጡ አካሄዶች ዳግም እንዳይከሰቱ  ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። መንግስት ለቅሬታዎች በወቅቱ ምላሽ ይሰጥ።  ለሁሉም የህዝብ ጥያቄዎች  አዎንታዊ  ምላሽ መስጠት እንደማይቻል  መንግስት ተረድቶ በወቅቱ   “አይሆንም” ወይም  “አይቻልም” የሚል  ምላሽ  መስጠት ይልመድ።  እንዲሁም  የአገልግሎት አሰጣጡን ያቀላጥፍ፤ ሁሉም  እኩል የሚስተናገድበት ሁኔታን ይፍጠር።  ህብረተሰቡም  የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያድርግ፤ ሁሉንም ልማት ማረጋገጥ  አቅምና ጊዜ ይጠይቃል። የተጠየቀ ነገር ሁሉ እለቱን ይስተካከላል  ብሎ ማሰብ  ተገቢነት የለውም። የምስራቅ አፍሪካ  አካባቢንም  ጂኦ  ፖለቲክስ  መመልከቱ ተገቢ ነው።  በዙሪያችን ያሉ አገራት የሚተኙልን አይነት አይደሉም።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy