Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በደብረ ብርሃን ከተማ በዋሻ ውስጥ በጥንቁልና ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

0 654

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የካቲት 2/2010 በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ በተፈጥሮ ዋሻ ውስጥ ተሸሽገው በጥንቁልና ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

በከተማው በተለያዩ ጊዜያት አራት ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለው ዘርፈዋል በሚል የተከሰሱ ሁለት ወንጀለኞችም በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተቀጥተዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል መርማሪ ኦፊሰር ረዳት ሳጅን ፋኖስ አንዳርጌ ለኢዜአ እንደገለጹት በጥንቁልና ተግባር ተሰማርተው የተያዙት ሁለት ግለሰቦች ናቸው።

በእነዚሁ ግለሰቦች የሕመም ፈውስና ሃብት እናገኛለን በሚል ከተለያዩ አካባቢዎች ተታለው የመጡ 12 ግለሰቦችም ተይዘው ጉዳያቸው እስኪጣራ በዋስ መለቀቃቸውን ተናግረዋል።

እንደ ረዳት ሳጅን ገለጻ፣ ግለሰቦቹ በከተማው “አንሳስ ማሪያም” እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የተፈጥሮ ዋሻ ውስጥ በድብቅ የጥንቆላ ተግባር ሲፈጽሙ ጥር 20 ቀን 2010 ዓ.ም እጅ ከፈንጅ ተይዘዋል።

ግለሰቦቹ የመጋረጃ መግቢያ በማለት ከአንድ ግለሰብ 101 ብር በመቀበል ሲያጭበረብሩ መቆየታቸውን ጠቁመው፣ በተያዙበት ወቅትም 6 ሺህ 800 ብር ጥሬ ገንዘብ መገኘቱን ተናግረዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ ለባህላዊ መድኃኒት መቀመሚያ በሚል ከግለሰቦች የሰበሰቡት 2 ኪሎ ግራም ማርና 1 ሊትር የአበሻ አረቄ በእግዚቢትነት መያዙንም አብራርተዋል።

የተገኘው ማር ከባዕድ ነገር ጋር ያለውን ውህደትና በሰው ልጅ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን የጤና ችግር ካለ ለመለየት ለምርመራ አዲስ አበባ መላኩንም አስታውቀዋል።

ውጤቱ እንደደረሰ መዝገቡን ለአቃቤ ህግ እንደሚሰጥ የጠቆሙት ረዳት ሳጅን ፋኖስ፣ ግለሰቦቹ ሕብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ መሰረት በቁጥጥር ሥራ መዋላቸውን አመልክተዋል።

“ሕብረተሰቡ በየአካባቢው የሚስተዋሉ ህገወጥ  ድርጊቶችን ሲመለከት ወዲያው በመጠቆም ወንጀልን በጋራ የመከላከል ባህል ሊያዳብር ይገባል” ሲሉም ረዳት ሳጅን ፋኖስ አሳስበዋል።

በሌላ ዜና በደብረብርሃን ከተማ በተለያዩ ጊዜያት አራት ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለው ዘርፈዋል በሚል የተከሰሱ ሁለት ወንጀለኞች በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት መቀጣታቸውን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል።

የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የወንጀል ዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ትዕዛዙ ጌታቸው ለኢዜአ እንዳስታወቁት ውሳኔው የተሰጠው ወንጀለኞቹ በዋና ወንጀል ፈፃሚነት ተሳታፊ መሆናቸው በመረጋገጡ ነው።

ከሰኔ ወር 2009 እስከ ጥቅምት 20 ቀን 2010 ባለው ጊዜ ውስጥ ጨለማን ተገን በማድረግ በጩቤ  ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ያጠፉት  አበራ ደጀንና ገብሬ ተስፋየ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው።

ወንጀለኞቹ ወንድወሰን ሽታዬን፣ ሰለሞን ዘዉዴን፣ ናርዶስ የሺጥላንና በድሉ አባይነህ የተባሉ ግለሰቦችን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል ሞባይል በመንጠቅ ዝርፊያ መፈፀማቸው በቀረበ ማስረጃና ወንጀለኞቹ በሰጡት የእምነት ቃል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ነው።

በመሆኑም በፈፀሙት ከባድ የውንብድና ወንጀል ጥር 30 ቀን 2010 በዋለው ችሎት እያንዳንዳቸው በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት የተፈረደባቸው መሆኑንም አቶ ትዕዛዙ አስታውቀዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy