Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ባተሌዎቹ

0 345

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ባተሌዎቹ…

ዳዊት ምትኩ

በአሁኑ ሰዓት በአመጽና በሁከት ላይ የሚገኙ ወጣቶች እጅግ ጥቂት መሆናቸው ይታወቃል። በርካታ ወጣቶች መንግስት ባመቻቸላቸው ሁኔታ በልማት ስራ ላይ ባተሌ ሆነው ደፋ ቀና እያሉ ነው። እነዚህ ባተሌ ወጣቶች የአገራችን መፃዒ ተስፋዎች ለሌላ አካል መጠቀሚያ መሆን አይገባቸውም። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የውጭ ሃይሎች መጠቀሚያ በመሆን የሚገኙት ጥቂት ወጣቶችም እንደ ባተሌዎቹ ፊታቸውን ተጠቃሚ ወደ ሚያደርጋቸው ስራ መመለስ አለባቸው። ባተሌዎቹም እንዲሁ።  

ታዲያ ወላጆችና ህብረተሰቡ እነዚህን ባተሌዎች በስራቸው ላይ እንዲተጉ በመምከርና በማበረታታት በአገራችን ልማት ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ባተሌዎቹም ራሳቸውን ሁከት በማራቅ በተጠቃሚነታቸው ላይ ማትኮር ተቀዳሚ ስራቸው መሆኑን መዘንጋት አይኖርባቸውም።

በአሁኑ ወቅት ወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንዱን አልወሰዱም እየተባለ በየሚዲያው እየተነገረ ነው። ይህም ሊያሰራ የሚችል ገንዘብ በመንግስት በኩል ተዘጋጅቶ ባተሌ ወጣቶችን እየጠበቀ ነው። እናም ጥቂት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የጥፋት መንገድን የሚከተሉ ወጣቶች ፊታቸውን ሊጠቅማቸው ወደሚችለው የልማት ሂደት መመለስ አለባቸው።

ወጣቶች በተመቻቹላቸው በእነዚህ ዕድሎች ላይ በጥረታቸው ከተሳተፉ ከጠባቂነት መንፈስ ተላቅቀው ራሳቸውንና ህዝባቸውን መጥቀም ይችላሉ። ይህን እውን ለማድረግ የእነርሱ ጥረት ወሳኝ ነው።

ታዲያ ጥረታቸው እውን መሆን ያለበት ከሁለት ጉዳዩች አኳያ ይመስለኛል። አንደኛው የየትኛውንም ፅንፈኛ ሃይል አሉባልታ ባለመስማት ፊታቸውን ወደ ተመቻቸላቸው የልማት መስክ በማዞር ነው። ሁለተኛው ደግሞ ተስፋቸው ይህን አገር በመምራት ላይ የሚገኘው መንግስት እንጂ ከማንም አለመሆኑን በሚገባ በመረዳት ነው።

ወጣቱ ሚዛናዊና ፍትሃዊ አስተሳሰብ ያለው በመሆኑ፤ በሁከት ፈጣሪ ሃይሎች አማካኝነት የሚቀርቡ “ጎስም ነጋሪት፣ ክተት ሰራዊት” ዓይነት የጥፋት እንዲሁም ፀረ-ልማት ጥሪዎችን አይቶ እንዳላየ፤ ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ ማለፍ ይገባዋል፡፡ እርግጥ እዚህ ላይ “ለምን?” የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡

እንደሚታወቀው ሁሉ ወጣቱ ባለፉት 15 የፈጣን ዕድገት ዓመታት ውስጥ የመንግሥት ልማታዊ አቅጣጫን በሚገባ ይገነዘባል ብዬ አስባለሁ፡፡ እናም ማንኛውንም ጊዜያዊ ችግር መንግሥት እንደሚፈታው ማመን ያለበት ይመስለኛል። እናም ችግሩን በመቋቋም ወደ ዘላቂው መፍትሔ መግባት ያለበት ይመስለኛል—የሁከት ኃይሎች መጠቀሚያ ከመሆን የሚገኝ ነገር የለምና።

ምንም እንኳን ወጣቱ በአሁኑ ወቅት ስልጣንን ለግል ጥቅማቸውና ለኑሮ ማደላደያነት ለማዋል በሚሹ ኃይሎች አማካኝነት የተፈጠረ ችግር ቢኖርበትም፤ ችግሩ በሀገሪቱ በመመዝገብ ላይ የሚገኘው ልማታዊ ድል ጊዜያዊ እንቅፋት መሆኑን መረዳት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ባሻገርም፤ የመንግሥትን የለውጥ ኃይልነት ስለሚያውቅ፤ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ እንደማይወጣና እንደሚለወጥም ማመን ይኖርበታል፡፡

እርግጥ አንድ መንግሥት ወይም የፖለቲካ ድርጅት በባህሪው ህዝባዊ ከሆነ፤ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያማከሉ መሆናቸው አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በባህሪው ህዝባዊና ልማታዊ በመሆኑ፤ ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ህዝቡን በአብዛኛዎቹ መስኮች በየደረጃው ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ወጣቱም የዚህ እድገት ተጠቃሚ መሆን ችሏል፡፡ ከሁከትና ከአመፅ ራሱን በማግለል ተጠቃሚነቱን ይበልጥ ማስፋት አለበት፡፡

ነገ ትልቅ የዕድገት ባለቤት ለመሆን ያለመው ወጣት ዜጋ፤ ትኩረቱን ማድረግ ያለበት የትናንት እሱነቱን በስራ ለመቀየር ደፋ ቀና በማለት እንጂ፤ ሁከትን በማዳመጥ አይደለም፡፡ እናም እነርሱ ባህር ማዶ ሆነው ልጆቻቸውን በሰላም እያስተማሩ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለውንና ህይወቱን ለመቀየር እየተጋ ያለውን ወጣት በእሳት ለመማገድ የሚሹ የሁከት ኃይሎችን ጥሪዎች ማምከን ይኖርበታል።

አብዛኛው ወጣት ከሁከቱ ወዲህ ስለ ጥፋት ኃይሎች ባዶና የአሉባልታ አጀንዳ አራማጅነት እንዲሁም ስለ መንግሥት ትክክለኛነት የልማት አቅጣጫዎች የተገነዘበ ይመስለኛል። መንግስት የወጣቱን ተጠቃሚነት በዳግም ተሃድሶው ይበልጥ ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ቃል ገብቷል። እናም በዚህ ቃል ተማምኖ ፊቱን ወደ ስራ ማዞር አለበት። ምክንያቱም የኢትዮጵያ መንግስት አደርገዋለሁ ያለውን የሚፈፅም መሆኑ ስለሚታወቅ ነው።

ይህን በመተማመንም ባተሌ ሆኗል። በባተሌነቱም ውጤት እያገኘ ነው። እናም በአቅራቢያው ለሚገኙ ወጣቶች ተጠቃሚነቱን በማውሳትና አሁንም መንግስት የመደበው በጀት ሰራተኛን እንደሚፈልግ በመግለፅ የእርሱን ፈለግ እንዲከተሉ ማድረግ አለበት።

እዚህ ላይ ባተሌ ለመሆን የስራን ክቡርነት መገንዘብ ያሻል። ወጣቱ ስራን ሳይንቅና ምናልባትም በስደት ቢሄድ ለባዕድ ሀገራት ሊያበረክተው የሚችለውን የጉልበት ስራ ዓይነት ጭምር ስራዎችን አክብሮ በመስራት የመንግስትን ትኩረት አሟጦ ሊጠቀምበት ይገባል። ስራ ክቡር ነው የሚለውን አርማ ከፍ አድርጎ ማውለብለብ አለበት። ያኔም ራሱን አሁን ካለው በላይ ይበጥ ሆኖ ያገኘዋል።

በአሁኑ ሰዓት አገራችን ውስጥ የተመቻቸ የስራ ምህዳር አለ። ዋናው ነገር ይህን ምቹ የስራ ድባብ በፈጠራ ክህሎት አጅቦ እንዴት ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ማወቁ ላይ ነው። የተመቻቸን ነገር በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ አደጋው የከፋ ይሆናል። ምክንያቱም ያልተመቻቸን ነገር ለመከተል እድል ስለሚከፍት ነው። በመሆኑም ባተሌ ለመሆን ያሉትንና በመንግስት በኩል የቀረቡትን ዕድሎች እስከ መጨረሻው መጠቀም አለበት።

ወጣቶች የዛሬ አፍላ የልማትና የዴሞክራሲ ኃይሎችና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች እንደመሆናቸው በትምህርት የታነፀና የተገነባ አቅም እንዲኖራቸው ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ለመስራት ታስቧል። ይህን ሁኔታ መንግስት ደጋግሞ እየገለፀው ነው። በዚያው ልክም ወጣቱ ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል።

ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ወጣቱ ሰላምን አጥብቆ መሻት አለበት። ፀረ ሰላም ኃይሎቹ የሚፈልጉት በአሁን ወቅት ያገኘውን ተጠቃሚነት እንዳያጣጥም መሆኑን ተገንዝቦ ወጣቱ ሴራቸውን በመገንዘብ ሁሌም ፊቱን ወደ ልማት ስራው ላይ ማዞር ይኖትበታል። እንደሚታወቀው ሁሉ ወጣቶች የዛሬ አፍላ የልማትና የዴሞክራሲ ኃይሎችና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች ናቸው። ይህን የሚገነዘበው መንግስት በትምህርት የታነፀና የተገነባ አቅም እንዲኖራቸው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል። የወጣቶችን ሁለንተናዊ ብቃት በማሳደግ በሀገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓትና መልካም ልማታዊ አስተዳደር ግንባታ እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በተደራጀና በተቀናጀ አኳኋን የነቃና ግንባር ቀደም ተሳትፎ እንዲያደርጉና ከውጤቱም በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው። ይህን በመጠቀም ባተሌዎቹ ይበልጥ ባተሌዎች መሆን ይጠበቅባቸዋል። ለዚህም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy