Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተግባራዊነቱን ናፍቀናል

0 243

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተግባራዊነቱን ናፍቀናል

ኢብሳ ነመራ

በህዝብ የስልጣን ውክልና የተሰጠው መንግስት ህዝብ እንዲተዳደርበት በወሰነው ህገመንግስት መሰረት የማሰተዳደር አደራና ግዴታ አለበት። በውክልና ስልጣን የተረከበ የመንግስት አስፈጻሚ አካል፣ ስልጣን በህገመንግስቱ የተገደበ ነው። ህገመንግስቱን መሰረት በማደረግ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቁ ህጎችን፣ ለምርጫ አቅርቦ ይሁንታ ያገኘባቸውን አማራጭ  ፖሊሲዎች ያስፈጽማል። የህዝብ ቅሬታዎችን፣ ተቃውሞዎችንና በተለያየ መንገድ የሚቀርቡ አቤቱታዎችንም የማዳመጥ ግዴታ አለበት።

የኢፌዴሪ መንግስትና ክልላዊ መንግስታት በ2007 ዓ/ም የተካሄደውን 5ኛ ዙር ሃገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ አሸንፈው በህዝብ ውክልና ስልጣን ተረክበው ስራ በጀመሩ ማግስት በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የተቃውሞ ድምጾች ተሰምተዋል፤ ግጭቶች ተቀስቅሰዋል። በዚህ ምክንያት የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ የህዝብና የግለሰቦች ሃብት ወድሟል፣ ሰዎች ከኑሯቸው ተፈናቅለዋል። የተቃውሞዎቹና የግጭቶቹ መንስኤ መንግስት ጋር የነበረ የኪራይ ሰብሳቢነት መስፋፋትና የመልካም አስተዳደር መጓደል በህዝብ ላይ ያሳደረው የመረረ ተቃውሞ ነበር።

ባለፉት ዓመታት የኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት በአዋጅ የተፈቀደ እስኪመስል ደረስ የተለመደ ለመሆን የበቃበት ሁኔታ ታይቷል። የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትም የበላይነት ያገኘበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በኪራይ ሰብሳቢነት ምክንያት የመልካም አስተዳደር ችግር ሊሆን የሚችለውን ያህል የከፋበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የመንግስት መስሪያ ቤቶች ዜጎችን የሚያገለግሉ ሳይሆኑ፣ በእጅ መንሻ ካልሄዱባቸው ዜጎችን ከኮሪደር አለፈው ወደፈአሰፈጻሚ ቢሮ የማያስገቡ አማራሪ ተቋማት ለመሆን የበቁበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ፍርድ ቤቶች ህግ ላይ በመመስረት ፍትህ የሚገኝባቸው ሳይሆኑ፣ ውሳኔ የሚሸጥባቸው ሱቆች ሆነዋል። አርሶ አደሮች በልማት ስም መሬታቸውን ተነጥቀው ከነቤተሰባቸው ለከፋ የኑሮ ችግር ተዳርገው የሚያሰሙት ለቅሶ በመላ ሃገሪቱ ለማስተጋባት በቅቷል።

በሌላ በኩል፤ ይህ ነው የሚባል ህጋዊ  የንግድ ወይም የማምረት ስራ ሳይኖራቸው፣ ሎተሪ ሳይደርሳቸው፣ ወርስ ሳያገኙ በድንገት የበለጸጉ ሃገር በቀል “ባለሃብቶች” እንደ አሸን ፈልተዋል። ብዙሃን በግፍ የተገፈፉትን ሃብት ጥቂቶች እየተጎናጸፉት በሃገሪቱ የፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ሚዛን ተዛብቷል። ስራ አጥነት፣ የመኖሪያ ቤት እጦትና ውድነት የከተማዎች መገለጫዎች ሆኗል። ሃገሪቱ ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ብታስመዘግብም፣ ኪራይ ሰብሳቢነት የፈጠረው ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ስርአት መዛባት ብዙሃኑን ተጠቃሚ ማድረግ አልቻለም። እናም በተለይ በከተሞች የድህነት ሁኔታው መሻሻል ማሳየት ሳይችል ቀርቷል።

በዚህ ላይ ህገመንግስታዊ መፍትሄ ሊበጅላቸው ይገባ የነበሩ ከማንነትና ከወሰን ይገባኛል ጥያቄ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች የቀሰቀሷቸው ግጭቶች ታክለውበት ሁከትና ግጭት የዘውትር ጉዳይ ሆኗል። ባለፉት ሁለት ተኩል ዓመታት ሃገሪቱ በሁከትና ግጭት ስጋቶች ውስጥ ነበር የቆየችው። እያንዳንዱ ማህበራዊ ሁነት የሁከትና የግጭት አጋጣሚ እንዳይሆን በሚል ስጋት በጭንቀት ውስጥ የታለፈበት ሁኔታ ነበር። በአጠቃላይ ሃገሪቱ በሁከትና ግጭት ተወጥራ ስትቃትት ነበር የከረመችው።

እርግጥ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የ5ኛውን ዙር የመንግስት ስልጣን ሲረከብ ህዝብ የመረጠን ሌላ የተሻለ አማራጭ ስላጣ ይታረማሉ በሚል እምነት ነው፤ ብዙ ችግሮች አሉብን ብሎ በይፋ ተናግሮ ነበር። ነሃሴ ወር ላይ በተካሄደው 10ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውም ላይ የኪራይ ሰብሳቢነት መስፋፋትና የመልካም አስተዳደር መጓደል በመሰረታዊ ችግርነት ተነስቶ የመፍትሄ አቅጣጫ ተቀምጦለታል። መንግስት ስራ ሲጀምር ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር ችግሮቹን ለማቃለል ወስኖ እንደነበርም ይታወሳል። ይሁን እንጂ የህዝቡ ብሶት አይሎ ኖሮ፣ ህዝባዊ ንቅናቄው ከመጀመሩ በፊት የህዝቡ ቁጣ ቀደመ። ከዚህም በኋላ ቢሆን ኢህአዴግና መንግስት ራሳቸውን በጥልቀት በማደስ ችገሮቹን በማቃለል የህዝብ እርካታ ለመፍጠር ወስነው ተንቀሳቅሰዋል።

በቅርቡ ደግሞ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴውን አካሄድ እንዲሁም ሌሎች የአፈጻጸም ማነቆ የሆኑ ውስጣዊ ችግሮችን ገምግሞ ውሳኔ አሳልፏል። የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ውሳኔዎቸ ተግባራዊ መሆን ጀምረዋል። በውሳኔዎቹ ተግባራዊነት በተለይ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን ረገድ ተጨባጭ ወጤት ይታያል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔወች ያሳለፈበትን ስብሰባ ተከትሎ የህወሃትና ኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ስብሰባዎችን አካሂደው መግለጫዎችን አውጥተዋል። በተለይ የበረታ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲካሄድበት የቆየውን የኦሮሚያ ክልል የሚያሰተዳድረው የኦህዴድ መግለጫ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል። በመሆኑም በዚህ ጽሁፍ ከመግለጫው ላይ ጥቂት አንኳር ጉዳዮችን በመጥቀስ አንደምታቸውን ለመመልከት ወድጃለሁ።

የኦህዴድ መግለጫ፤ . . . ግንባራችን ኢህአዴግ በጥልቅ ለመታደስ የጀመረውን ንቅናቄ ዳር ለማድረስ በቅርቡ ራሱን ገምግሞ አቅጣጫ ማስቀመጡ የሚታወስ ሲሆን፣ ከግምገማው በመነሳትም አገራችን ኢትዮጵያና ክልላችን  በፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች ያለችበትን ሁኔታ በዝርዝር በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል በማለት ይጀምራል።  መግለጫው አያይዞም፤ የፌዴራላዊ ስርዓታችንን አደጋ ላይ የጣሉ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን፣ ሕዝቡ በመሪ ድርጅቱ ላይ እንዲያምጽ ያስቻሉ የመልካም አስተዳደር እጦቶችን፤ ስልጣን ህዝብን ማገልገያ መሳሪያ መሆኑን በመዘንጋት በርስትነት ይዞ ለግል ምቾትና ጥቅም ቅድሚያ መስጠትን፣ በነጻነት ተዘዋውሮ የመስራት መብትን ነፍጎ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሕዝቦችን እስከማፈናቀል የደረሰ ድርጊትን፤ በኢንቨስትመንት ስም የመንግስትና የህዝብ መሬት መመዝበሩን፤ እንዲሁም የሕዝቦች ሰላምና ጸጥታ መደፍረሱን እና የመሳሰሉትን እየተፈጸሙ ያሉ አደገኛ ድርጊቶችን ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ አምርሮ በመታገል የአገራችንን ሕልውና መታደግ ልዩ ትኩረት የሚሹ አበይት ጉዳዮች መሆናቸው በዝርዝር ተመክሮባቸዋል ይላል። መግለጫው ከሌሎች ክልሎች ጋር ሊኖር ስለሚገባ ግንኙነትና ሃገራዊ አንድነት፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች መሃከል ስላለው ችግር፣ በኢህአዴግ እህት ድርጅቶች መሃከል ሊኖር ስለሚገባው ግነኙነትና ሌሎችም ጉዳዮች አንስቷል።

እነዚህ በመግለጫው ላይ የሰፈሩ ሃሳቦች የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ  የተላለፉ ውሳኔዎች ላይ የተኮረ መሆኑን ያመለክታል። ከዚሀ በተጨማሪ ባለፉት ዓመታት በሃገሪቱ፣ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ለተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች ምክንያት የሆኑ የመልካም አስተዳደር መጓደልና የኪራይ ሰብሳቢነት የበላይነት የማገኘት ችግሮችን የመታገል ጉዳይ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ያመለከታል። የሃገሪቱ እንድነትንና በህዝቦች መሃከል ሊኖር ስለሚገባበው ወንድማማችነትን፣ የሰላም ማስፈን ጉዳይ ወዘተ የትኩረት ማረፊያው መሆናቸውንም ያመለክታል።

ኦህዴድ እነዚህን ትኩረት ያደረገባቸውን ጉዳዮች ተፈጻሚ ለማድረግ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንደሚያስፈልገው አመልክቶ መልዕክትና ጥሪ አስተላልፏል። መልዕክትና ጥሪ ካስተላለፈላቸው በርካታ አካላት መሃከል በተለይ ለኦሮሞ ወጣቶች፣ በውጭ ሃገራት ለሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆችና በኦሮሞ ህዝብ ላይ አተኩረው ለሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያስተላለፈውን ጥሪ እንመለከት።

መግለጫው ለኦሮሞ ወጣቶች ባስተላለፈው መልዕክት፣ . . . ወጣቶቻችን በሁሉም መስክ የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴና መልካም ጅምሮች ወደ ላቀ ድል እንዲሸጋገሩ በባለቤትነት መሳተፍና ኃላፊነትን መወጣት፣ ይህንንም በተደራጀ መልኩ መተግበር ይገባቸዋል። ወጣቱ በሁሉም መስክ የሚያደርገውን ትግል ምክንያታዊና ሳይንሳዊ በሆኑ ሃሳቦች እየተመራ፤ ዴሞክራሲያዊነትን በጠበቀና ተደማሪ ለውጦችን በተንከባከበ መልኩ የሁሉም መብት ተከብሮ፣ የሀገራችንም ህልውናና የክልላችን ሰላም እንደተጠበቀ የሚቀጥልበት አካሄድ እንዲረጋገጥ ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ድርጅታችን ኦህዴድ ጥሪውን ያቀርባል ብሏል።

እንደሚታወቀው አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በወጣትነት እድሜ ክልል ያለ ነው። ባለፉት ሁለት ተኩል ዓመታት በኦሮሚያ ውስጥ የተካሄደውን ተቃውሞ የመራውና ያካሄደውም ወጣቱ ነው። ወጣቱ የሃገሪቱን እጣ ፈንታ የሚወስን የስራና የልማት ሃይል ሆኖ ሳለ በኪራይ ሰብሳቢነትና በመልካም አስተዳደር መጓደል ከልማት ተሳትፎ ርቆ በሚፈለገው ልክ የልማቱ ተጠቃሚ ሳይሆን ቀርቷል። ወጣቱን ለተቃውሞ ያስነሳውም ይህ ሁኔታ ነው። እናም ወጣቱ ከስሜታዊነት ተቆጥቦ በሳይንሳዊ መርህ እየተመራ የልማትና የሰላም ሃይል እንዲሆን የቀረበው ጥሪ ተገቢ ነው። ጥሪው ብቻ የሚፈለገውን ውጤት እንደማያመጣ ግን መታወቅ አለበት። ወጣቱን የልማትና የሰላም ሃይል ማድረግ የሚያስችሉ መድረኮች መፈጠር አለባቸው።

በውጭ ሃገር ለሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች የተላለፈው ጥሪ፤  . . . በውጭ አገር የምትኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች በሕዝባችን ጥቅም ላይ ያለምንም ድንበርና ልዩነት በጋራ እንድንሰራ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል ይላል።

የኦሮሞ ተወላጆች እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሃገሪቱ በነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ሳቢያ ባለፉት አርባ ዓመታት በብዛት ወደውጭ ሃገራት ተሰድደዋል። ባለፉት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታትም በኦሮሞዎች ዘንደ ቀደምት እውቅና ካለው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች ተሰድደዋል። በተቀሩት የሃገሪቱ አካባቢዎችም እንዳለው በኢኮኖሚያዊ ምክንያት ከሃገር የወጡትም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። እነዚህ የኦሮሞ ተወላጅ ዳያስፖራ አባላት በቦታ ቢርቁም በስሜት ከሃገራቸው ጉዳይ እንዳልራቁ የሚያመለከቱ እውነታዎች አሉ። ይሁን እንጂ በቦታ ከሃገራቸው መራቃቸው፣ ወደውጭ ሃገር እንዲሰደዱ ካደረጋቸው ሁኔታና ወቅት ጋር ተዳምሮ በኦሮሚያም ሆነ በአጠቃላይ በሃገሪቱ ሁኔታ ላይ ያላቸው ምልከታ የተዛባ እንዲሆን ማድረጉን የሚያመለከቱ ሁኔታዎች አሉ። እውነታውን ማወቅ የሚያስችላቸው የመረጃ ክፍተትም አለባቸው።

እናም፣ በስሜት ከሃገራቸው ሊነጠሉ ላልቻሉት በውጭ ሃገር ለሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች የሃገራችሁ ጉዳይ ይመለከታችኋል በሚል ትኩረት መሰጠቱ በራሱ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው። ከዚህ በተጨማሪ ካለምንም ገደብ በሃገራቸው ጉዳይ ላይ እንዲሳተፉ መጋበዙ፣ ማየት ማመን ነውና ርቀትና የመረጃ ክፍተት የፈጠረውን የተዛባ ግንዛቤም ሊደፍን ስለሚችል መልካም ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ በውጭ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ወደሃገር ቤት መጥተው ለመሳተፍ የሚያደፋፍራቸውን ሁኔታ የሚፈጥሩላቸው መደረኮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ማዘጋጀት የሚገባ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። የዳያስፖራ አባላቱም ከጭፍን ጥላቻ ተላቀው ከኦህዴድም ሆነ ከሌሎች ቡድኖች ጋር በአንድ የኦሮሞ ህዝብና ኦሮሚያ ጉዳይ ላይ ለመምከር መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። በኦህዴድ በኩል ብቻ የታየው መነሳሳት የትም አያደርስምና።

በመጨረሻ የምመለከተው በኦሮሞ ህዝብ ላይ አተኩረው ለሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረበውን ጥሪ ነው። . . . በዚህ ወሳኝ ወቅት የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት የሚፈተንበት ጊዜ መሆኑ ግለፅ ነው። በመቀራርብና በመነጋገር የፖለቲካ ባህላችንን እንድናሻሽል ብሎም የሀገራችንን መፃኢ ዕድል በጋራ ማበጀት እንችል ዘንድ ተቀራርበን እንድንሰራ ድርጅታችን ይፈልጋል። በዚሁ መሰረት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያላችሁ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ በሀገራችንና በሕዝባችን የጋራ ጥቅም ላይ ከድርጅታችን ኦህዴድ ጋር አብራችሁን እንድትሰሩ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል ይላል፣ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ።

የኦሮሞ ህዝብ በብሄራዊ ማንነቱ አንድ ቢሆንም እንደማንኛውም ህዝብ በፖለቲካ አመለካከት መለያየቱ አይቀሬ ነው። በኦሮሞ ህዝብ ላይ አተኩረው የሚሰሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የዚሁ ነጸብራቅ በመሆናቸው የርዕዮተ ዓለምና የፖሊሲ ልዩነት ይኖራቸዋል። ሁሉም ግን በኦሮሞ ህዝብ ጥቅምና መብት ላይ አይደራደሩም። በኦሮሞ ህዝብ ጥቅም፣ መብትና ነጻነት ላይ የማይደራደሩ በመሆናቸው መሰረታዊ ጉዳይ ላይ ይስማማሉ። ይህን መሰረታዊ መተማመን ችላ በለው፣ አንዱ ሌላውን ተለጣፊ፣ ስውር ዓላማ ያለው ምንትስ ቅብጥርስ እየተባባሉ የሚፈራረጁ ከሆነ ይህ መፈራረጅ በደጋፊዎቻቸው መሃከልም  መፈጠሩ አይቀሬ ነው። ይህ ደግሞ ዴሞክራሲ የሚጠይቀውን መቻቻል በማደብዘዝ በጠላትነት ለመተያያት፣ እንዲያም ሲል ለግጭት ይጋብዛል። ይህ  ቆመንለታል የሚሉትን ህዝብ በእጅጉ ይጎዳል።

እናም፣ በኦሮሞ ህዝብ ላይ አተኩረው የሚሰሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታቸውና ወደስልጣን የሚያወጣቸው ህዝቡ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማካሄድ የሚያስችል መተማመን በመሃከላቸው መፈጠር ይጠበቅባቸዋል። ይህ ደግሞ ተቀራርቦ መስራትን ይጠይቃል። እናም ኦህዴድ አሁን የክልሉ ገዢ ፓርቲ በመሆኑ፣ ተቀራረቦ ለመስራት ያቀረበው ጥሪ ድንቅ ነው። ተግባራዊነቱ ግን መፍጠን አለበት።

በአጠቃላይ፣ ኦህዴድ ኪራይ ሰብሳቢነትንና ኮንትሮባንድ ንግድን የመሳሰሉ ተያያዥ ችግሮችን፣ የመልካም አስተዳደር መጓደልን ለማቃለል ያሳየው ቁርጠኝነት አበጀህ የሚያሰኝ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከአያቶቹ በወረሰው የጋዳ ስርአት መሰረት ከሌሎች ብሄሮችና ብሄረሰቦች ተወላጆች ጋር በሰላም ለመኖር፣ ከሌሎች ክልሎች ህዝቦች ጋር ወንድማማችነትን በማጎልበት ሃገራዊ አንድነትን ለማጠናከርና አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት የወሰደው ተነሳሽነት ከክልሉም አልፎ ለሃገሪቱ መጻኢ እድል ለመስራት ያለውን ፍላጎት ያሳያል። ይህ በኦሮሞ ድርጅቶች ዘንድ ያልተለመደ ነው። እናም የሚደነቅ አቋም ነው። ከላይ ለተገለጹት አቋሞቹ ተግባራዊነት ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ያስተላለፈው መልእክትና ጥሪ ይዘትም ድንቅ ነው። በመሆኑም ተግባራዊነቱ ተናፍቋል። በአጠቃላይ የኦህዴድ መግለጫ የሰላም፣ የዴሞክራሲ፣ የአንድነትና የልማት ጥሪ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy