Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተጨማሪ አቅም፣ ተጨማሪ ተስፋ

0 316

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተጨማሪ አቅም፣ ተጨማሪ ተስፋ

                                                     ታዬ ከበደ

ኢትዮጵያ ነዳጅ ከሌላቸው የሰሃራ በታች ከሚገኙ አገራት ውስጥ ፈጣን እድገት የምታስመዘግብ ቀዳሚዋ አገር መሆን የቻለች አገር ናት። አገራችን ይህን እድገት ማስመዝገብ የቻለችው ለእድገት የሚሆን ነዳጅ ወይም ሌላ የተፈጥሮ ሃብት ሳይኖራት መሆኑ ግልፅ ነው።

በዚህም በአማካይ ላለፉት 10 ዓመታት ከ10 በመቶ በላይ እድገት እያስመዘገበች መጥታለች። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የተለያዩ የተፈጥሮ ሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እየተገኙ ነው። ነዳጅንና ወርቅን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። እነዚህና ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች ወጥተው ጥቅም ላይ ሲውሉ የኢኮኖሚ እድገቱ በአያሌው መፋጠኑ አሌ አይባልም።

ይህም አገራችን ወደ መጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ለመሸጋገር የወጠነችውን እቅድ ሊያሳካ የሚችል ነው። ይህ ሁኔታም በነበረን ተስፋ ላይ ተጨማሪ አቅምንና ተስፋን የሚያስገኝልን ነው። የኢትዮጵያ ህዳሴ በእርግጥ እውን እንደሚሆንም የሚያረጋግጥ ነው። ታዲያ እዚህ ላይ የነበረንን አቅምና ተስፋን ማውጋት ተጨማሪውን አቅምና ተስፋን እንድናውቅ ያደርገናል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ ላለፉት አስር ዓመታት በአማካይ ከ10 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች። ይህም ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ያላት ሀገር እንድትሆን አስችሏታል። “የአፍሪካ መነሳሳት” ተጠቃሽ ምሳሌ እንድትሆንም አድርታል።

ይህም በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት የተከተለው ትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ ውጤት መሆኑ አይካድም። እንደሚታወቀው ሁሉ የአርሶ አደሩን ህይወት ለማሻሻልና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዘው ዕቅድ ያለፉት አስር ዓመታት አፈጻጸም ሲቃኝ አበረታች እንደነበር በተለያዩ መድረኮች ተገልፀዋል። ያለፉት ዓመታት የግብርናው ዘርፍ ዕድገት እንደቀደሙት ዓመታት ሁሉ አበረታች ነበር።

በግብርናው ዘርፍ በተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች የታዩትን መልካም ተሞክሮዎች በማስፋት አርሶ አደሩን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ ተሰርቷል። ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲቻል የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ አርሶ አደሩን ለማገዝ ጥረት ተደርጓል።

እንደ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር የመሳሰሉ ግብዓቶች በማቅረብ ረገድም ቀላል የማይባል ሥራ ተከናውኗል። ከዚህ አንጻር የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ ያስቻለ እንቅስቃሴ መደረጉን መረጃዎች ያሳያሉ።

ምርጥ ዘርን የማራባትና ለአርሶ አደሩ የማከፋፈል ተግባር አንዱ እየተሰራበት ያለ ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ በማዕከል ደረጃ ካለው የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት በተጨማሪ ክልሎች እንደየአስፈላጊነቱ የምርጥ ዘር ማዕከላትን በማቋቋም አርሶ አደሩን በቅርብ እያገዙ ይገኛሉ። ይህም በያዝነው የምርት ዘመን የስንዴ፣ የገብስ፣ የጤፍ፣ የበቆሎ፣ የጥራጥሬና የቅባት ዘሮችን ተባዝተው ቀርበዋል።

አርሶ አደሩን  በሥልጠና፣ በሙያ እና በግብዓት የተለያየ ድጋፍ እየተደረገለት የዕለት ጉርሱንና የዓመት ልብሱን ሸፍኖ ገበያ ተኮር ምርት በማምረት በሚሊዮን የሚቆጠር ሃብት ማፍራት ጀምሯል፡፡ በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ገበሬዎች ሚሊዬነር መሆን የቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ ካለው ሥራ አንዱ የመስኖ ልማት ነው። አገራችን የብዙ ወንዞች ባለቤት ብትሆንም ለመስኖ ሥራ የዋለው የውኃ መጠን አነስተኛ ነው፡፡ ዛሬ ይህ ተለውጦ የተፋሰስና የመስኖ ስራዎች በመላ ሀገሪቱ እየተካሄደ ነው። ባለፉት ዓመታት ለልማቱ አጋዥ የሆኑት እንደ መንገድ፡ ቴሌኮምና መብራት የመሳሰሉት ዋና ዋና  የመሠረተ ልማት አውታሮች በከተሞች ብቻ የተወሰኑ ነበሩ። ባለፉት 26 ዓመታት ግን መሠረተ ልማትን በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋት ተችሏል።

በቀደሙት ሥርዓታት ለትምህርት ተቋማት መስፋፋትና ለፍትሃዊ የትምህርት ተደራሽነት የተሰጠ ትኩረት አልነበረም፡፡ ከታች እስከ ላይ ድረስ የነበሩት የትምህርት ተቋማት ውስን ከመሆናቸውም በላይ የተቋቋሙት በከተሞች ብቻ ነበር፤ በአገሪቱ አንድም የግል ዩኒቨርስቲ ሆነ ኮሌጅ አልነበረም። ዛሬ ግን ወደ 43 ከፍ እንዲሉ እየተሳ ነው።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአሁኑ ወቅት ትምህርት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ዘልቆ ገብቷል፡፡ በከተሞችም እንዲሁ ተስፋፍቷል፡፡ እድሜው ለትምህርት  የደረሰ ህጻን ሁሉ የማዕዱ ተቋዳሽ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

በአገሪቱ ያለው የትምህርት ሽፋንም ሰፍቷል፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት በሙሉ የሚታደሙበት ማዕድ ሆኗል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በገጠር ቀበሌዎች ሳይቀር ተስፋፍተዋል፡፡

ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ የትምህርትን አስፈላጊነት ከማስተማር ጎን ለጎን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር  በትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ህጻናት የምገባ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ምገባው  ህጻናት በምግብ አቅርቦት ማነስ ምክንያት ከትምህርታቸው እንዳይሰናከሉ ማገዝ ችሏል፡፡

ቀደም ሲል የነበረውን የትምህርት ቤቶች ሥርጭት ኢ ፍትሃዊነትን ለማስወገድ በአገሪቱ እያደገ የመጣው የትምህርት ቤቶች ቁጥር ሥርጭት ፍትሃዊነቱን እንዲጠብቅ ተደርጓል፡፡  ከዚህ አንጻር ቀደም የአገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩል ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡

በትምህርት ሥርጭት ላይ የነበረው ኢፍትሃዊነት በክልሎች መካከል ልዩነት ፈጥሮ ነበር፡፡ ይህ ኢፍትሃዊ ሥርጭት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በተመጣጣነ ሁኔታ ማደግ አለመቻላቸውንና  የልማት ተጠቃሚነታቸውም ላይ ልዩነት መፍጠሩ አልቀረም፡፡

ወጣቶች ሥራ ፈጣሪና ባለሙያ ሆነው የሚሰለጥኑበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ በአገሪቱ ሥራ ፈጣሪና በራሱ የሚተማመን ወጣት ማፍራት የሚችሉ ከአምስት መቶ በላይ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተቋቁመው የሥልጠና አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

በአንድ በኩል አገሪቱ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ጥናቶችንና ምርምሮችን ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ባለፉት 10 ዓመታት በአገሪቱ የነበሩት ሁለት ዩኒቨርስቲዎች እንዲስፋፉና ለትምህርት አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች እንዲሟሉላቸው በመደረጉ የቅበላ አቅማቸው አድጓል፡፡ የሚሰጡት የሥልጠና ዓይነትና ደረጃም በዚያው ልክ ሰፍቷል፡፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የኅብረተሰቡን ችግር መፍታት  የሚያስችሉ የምርምርና የጥናት ተግባራት ላይ ማተኮር መጀመራቸው ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ ቅድመ ኢህአዴግ ጥናትና ምርምር ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ አልነበረም፡፡

በዩኒቨርስቲዎች የሚደረጉ ጥናቶችም የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘቡና  የህዝቡን ተጨባጭ ችግሮች ለመፍታት ያለሙ አልነበሩም፡፡ የነበረው ሥርዓትም ይህንን የሚያበረታታ አልነበረም፡፡

ባለፉት 10 ዓመታት ዩኒቨርስቲዎች የአርሶና አርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል የሚያግዙ በርካታ ጥናቶችና ምርምሮች አካሂደዋል፡፡ በጓሮ አትክልት፣ በእንስሳት እርባታ፣ በመስኖ ሥራ፣ በአፈር ለምነት እና በምርጥ ዘር አቅርቦት የተለያዩ የምርምር ተግባራት ተከናውነው ወደ ተግባር ተለውጠዋል።

በአገራችን ለተመዘገበው ሁለንተናዊ ለውጥ ሌላው መገለጫ በጤናው ዘርፍ የተገኘው ስኬት ነው፡፡ ጤናማ ትውልድ መገንባት ዋነኛው የልማት አካል ነው፡፡ ጤናማ አምራች ዜጋ ዘላቂ ልማት አይታሰብም፡፡ ከዚህ አኳያ አገራችን የነበረችበት ሁኔታ የከፋ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት ግን በመንገስት ጥረት ሁሉም ነገር ተስተካክሏል፡፡ የጤና ሽፋን በሁም አካባቢዎች ተስፋፍቷል። የህፃናትንና የእናቶች ሞትን መቀነስ ተችሏል።

መንግስት ባደረገው ጥረት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በመመደብ ገጠርና ከተማን ሳይለይ ሁሉም ህብረተሰብ የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በከተሞች ብቻ የነበረው የጤና አገልግሎትም ወደ ገጠር ዘልቆ ገብቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የጤና ጣቢያ አለያም የጤና ኬላ የሌለበት የገጠር ቀበሌ የለም፡፡

የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና የጤና ተቋማት መስፋፋት፤ የጤና አገልግሎት ከከተማው አልፎ የገጠር ቀበሌዎችን ማዳረስ፤ ወባንና ኤች አይ ቪ ኤድስን በመከላከልና ሥርጭቱን በመግታት፤ በጤናው ዘርፍ የግል ባለሃብቶች በሰፊው እንዲሳተፉ በማድረግ ረገድ ባለፉት ሁለት ዓመታት አገራችን ባስመዘገበችው ፈጣን እድገት የተከናወኑ ናቸው። የከተማ ሥራዎችን በተመለከተ በዋነኝነት የከተማውን ነዋሪ የገቢ አቅም ለማሳደግ የተካሄደው የሥራ ዕድል ፈጠራና የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ልማት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ከተቀመጠው ግብ አንፃር አበረታች ርቀት ተሂዶበታል። ይህ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እምነት ተይዞ እየተሰራ ነው፡፡

በአገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል የኮንደምኒየም ቤቶች ግንባታ እየተፋጠነ ይገኛል፡፡ እስካሁን በአዲስ አበባ ብቻ ከአሥር ሺህዎች ቤቶች በላይ ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል፡፡ ሌሎች  ከአሥር ሺህዎች በላይ የሚሆኑ ቤቶች ደግሞ በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡

በመልካም አስተዳደር በኩል ያሉትን ሁኔታዎች በመፈተሽ በተለይ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ተጀምሮ የነበረው በሁሉም ክልሎች ከነዋሪው ጋር በችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ህዝቡን ያሳተፈ የማጥራትና የመልካም አስተዳደር ማስፈን እንቅስቃሴ ተካሂዷል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ገዥው ፓርቲና መንግስት ለህዝቡ በገቡት ቃል መሰረት በመከናወን ላይ ይገኛል። ህዝብን ሊያረካ የሚችል መፍትሄ ይኖራል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

እነዚህ ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ አቅሞችና ተስፋዎች በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ይበልጥ እንዲጎለብቱ እየተሰራ ነው፡፡ ስራው አገራችን በአርሶ አደሩ አነስተኛ ማሳ ላይ በምታደርገው የግብርና ልማት የተገኘ ነው፡፡ የፈጣንና ተከታታይ እድገቱ ምንጭም እስካሁን የኸው የግብርና ስራ ነበር፡፡

አሁን ደግሞ ይህን እድገት ሊያፋጥኑ የሚችሉ ተጨማሪ አቅምና ተስፋ የሚሆኑ እንደ ነዳጅና ከፍተኛ የወርቅ ክምችት ዓይነት ሃብቶችን አግኝተናል፡፡  በነበረን አቅምና ተስፋ ላይ እነዚህ ተደማሪ አቅሞች እያሳለጥነው ላለነው ልማት ተጨማሪ አቅምና ተስፋ እንደሚሆኑን አያጠያይቅም፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy