Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አረንጓዴው አብዮት

0 323

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አረንጓዴው አብዮት

ስሜነህ

 

ዓለምን እያነጋገሩ ካሉት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛው ነው። ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በሰዎች ህይወትና አኗኗር ላይ እየተከሰተ ያለው ለውጥና ጉዳት ከባድና አሰቃቂ መሆኑንም ጥናቶች እያረጋገጡ ነው። የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው ችግር አካባቢ ባይመርጥም  በአዳጊ አገሮችና ህዝቦች ላይ ግን ጉዳቱ የበረታ እንደሚሆን አያከራክርም። እነዚህ አገሮችና ህዝቦች ምንም እንኳን በዓለማችን እያንዣበበ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ባይሆኑም ለውጡ በሚያስከትለው ጉዳት ቅድሚያ ተጠቂዎች መሆናቸው እርግጥ ነው።

ለአየር ንብረት ለውጥ መከሰት ዋነኛ ምክንያት የበለጸጉት ሃገራት የበለጸጉበት መንገድ እንደሆነም ነው ጥናቶቹ ያጠየቁት። የኢኮኖሚ እድገታቸው በኢንዱስትሪ ላይ የተመሠረተ ሲሆን ከኢንዱስትሪያቸው የሚወጣው በካይ ጋዝ ለሰውም ሆነ ለእንስሳት አልፎም ለአካባቢ መጎዳት ምክንያት እየሆነ ነው። ተመራማሪዎችና ጥናት አድራጊዎች የሚመሰክሩት ለአየር ንብረት ለውጥ የአካባቢ ብክለት ትልቁን አስተዋጽኦ አድርጓል። እየደረሰ ያለውን አደጋ ለመከላከልና ብሎም ለማስወገድ የግብርናም ሆነ የኢንዱስትሪ አመራረት ዘይቤን ማስተካከልና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ በማተኮር አሁን ያለውን የካርበን ልቀት መጠን ዝቅ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ነው የምሁራኑ ድምዳሜ።

በዓለማችን በየጊዜው በሚከሰተው የአየር ንብረት ለውጥና ለውጡ በሚፈጥረው አደጋ የማይጎዳ አገርና ህዝብ አይኖርም። ወቅቶችና ሁኔታዎች ይለያዩ እንጂ ጉዳቱ አይነካኝም ብሎ የሚተማመን አካባቢና ህዝብ የለም። በአየር ንብረት ሚዛን መዛባት ምክንያት የበረዶ ግግር እየቀለጠ፣ አካባቢን ለውሃ መጥለቅለቅ አደጋ እያጋለጠ፣ በአውሎ ንፋስና በእሳት አደጋ የሰው ህይወትና ንብረት እየተበላ መሬት እየተደረመሰና ህንፃዎች እየፈራረሱ፣ የፀሐይ ንዳዱም ህይወት ያለውን ፍጡር እስትንፋስ እያሳጠረ ስለመሆኑ ዓለማችን ያስተናገደቻቸው ክስተቶች ይመሰከራሉ።

ኢትዮጵያ በአለማችን ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ከሆኑ 10 ሀገራት መካካል አንዷ መሆኗን የመንግስታቱ ድርጅት የአከባቢ ጥበቃ ድርጅት (UNEP) ጥናት ያመለክታል፡፡ በአማካይ ሙቀት መጠን መጨመርና የዝናብ ስርጭት መዛባት የመሰሉ ቀጥተኛ የሆኑ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች ተጠቂ ናት፡፡ የአገሪቱ 80 በመቶ ዜጎች መተዳደሪያ እንዲሁም 40 በመቶ ሀገራዊ ምርት የተመሰረተበት የግብርናው ዘርፍ፤ የአየር ንብረት ለውጡ ቀጥተኛ ተጠቂ መሆናቸው ተጋለጭነቱን ያባባሰው መሆኑም በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

በ2017 ዓ.ም (እ.ኤ.አ በ2025) መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ራዕይ ሰንቃ በመንቀሳቀስ ላይ የምትገኘውን ኢትዮጵያ፣ በተለይ አረንጓዴ ልማት ለሕዝቧ የህልውናና የኑሮ መሠረት በመሆኑ፣ እየተሠራ ያለው ሥራ ዓለም ጭምር በሞዴልነት እየወሰደና እየሠራበት እንደሚገኝም ነው ጥናቶች እያረጋገጡ ያሉት።  

በፍጥነት ለማደግ የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ፣ የሥርዓተ ምህዳር አገልግሎቶች ሳይዛነፉ የተሻለ ጥቅም እንዲሰጡ አድርጎ፣ ቀጣይነት ያለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና አጠቃቀምን ዕውን ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ደግሞ እንደኛ በማደግ ላይ ለሚገኙ ሃገራት ትልቅ ፈተና ነው፡፡የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ የሥርዓተ ምህዳር አገልግሎቶች እንዳይዛነፉ ለማድረግና የተሻሉ ጥቅሞችን እንዲሰጡ፣ አመጣጥኖና ጠብቆ ለመሄድ ቴክኖሎጂ ወሳኝ ነው፡፡

ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ ከውጭ በማስገባት፣ በማለማመድና ጥቅም ላይ በማዋል፣ የአገር ውስጥ አቅምን ገንብቶ ቴክኖሎጂን በአገር ደረጃ የማፍለቅ አቅም ግንባታ ሥራ ለመሥራት፣ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ቢሆንም፤ በምርምር የተገኙ ቴክኖሎጂዎች በጥቅም ላይ ሳይውሉ ወይም ለተጠቃሚው ሳይደርስ በመደርደሪያ ላይ እንደሚቀሩ ነው ጥናቶቹ በማረጋገጥ የፈተናውን ክብደት የሚያወሱት፡፡

ስለሆነም ተመራማሪዎች በየጊዜው ቴክኖሎጂዎች ሠርተው ሲያቀርቡ፣ ደረጃቸውን በጠበቁና ከወረቀት ላይ ከማስቀመጥ ባሻገር፣ አጠር ባለና በቀላሉ አገላለጽ የተቀመጠ ምክረ ሐሳብ ለተጠቃሚዎች በሚመጥንና እነሱን ማዕከል ባደረገ አግባብ ሊያቀርቡ ይገባል።ተመራማሪው በየምርምር ተቋማቱ የተሠሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወስዶና አደራጅቶ፣ የቀረውን በመለየት የመመራመር ሥራ መሥራት አለበት፡፡  

የአገር ውስጥ ተመራማሪዎች በሠሯቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች የተመረቱ ምርቶች እያሉ፣ ከውጭ አገር ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ፣ ተመራማሪው ለተሻለ ምርምር እንዳይነሳ እንቅፋት እንደሆኑበት ከተመራማሪዎች በኩል የሚቀርብ ቅሬታ ነው።  የአካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ሚንስቴር ለዚህ ቅሬታ እንደሰጠው ምላሽ ከሆነ ግን ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት የሚቻል ከሆነና የሕዝቡን ፍላጎት ሊመልስ የሚችል ምርት በአገሪቱ ካለ በትክክል ተረጋግጦ ማስተካከል እንደሚቻል ነው፡፡ በአገር ውስጥ ምርት ራስን መቻል የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረቱም በተጨማሪ ለዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ከመደገፍና የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ከማድረግ አንፃር፣ ከሚመለከታቸው አካላት በመነጋገር በቀጣይ የሚፈታ መሆኑንም አመልክቷል።  

የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት በበኩሉ በምርምር የተገኙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለባለድርሻ አካላት ተደራሽ መሆናቸውንና ለኅብረተሰቡም በሚገባ መተዋወቃቸውን መፈተሽና ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻል፡፡በተለይ የእንጨት ኢንዱስትሪ ከውጭ በማስገባት በተደረገው ምርምር ብዙ ውጤት መገኘቱን  የሚገልጸው ኢንስቲቲዩት ከ60 በላይ አገር በቀል የዛፍ ዝርያዎችን አጥንቶ ወደ እንጨት ኢንዱስትሪው እንዲገባ ማድረጉንም በአብነት ይጠቅሳል፡፡

ኢትዮጵያ ከአየር ብክለት የጸዳ ኢኮኖሚ ለመገንባት የካርበን ልቀት ቅነሳ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የልማቱ አንድ አካል ሆኖ ተቀምጧል።እንደ አየር ንብረት ለውጥ የመሰሉ አለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ማድረግ በተለይም ለኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ትልቅ እድል ይከፍታል። ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂዋን ውጤታማ ለማድረግ በታዳሽ ኃይል ዘርፉ የጀመረችው ሥራ አገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ  የወሰደችው አቋም ሁነኛ ማሳያ መሆኑንም አለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች እያረጋገጡ ያሉት በዚህ አግባብ ስለተሰራና ውጤት ስለተገኘበት ነው። ኢትዮጵያ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በካርበን ልቀት ቅነሳ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ባስቀመጠችው ግብ ልክ አብዮቱን በማቀጣጠሏም ድሉን ተጎናጽፋለች።

አሁን ለአየር ንብረት ለውጥ መባባስ ምክንያት የሆኑም፣ ያልሆኑም አገሮች ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን መገንባት ወሳኝ መሆኑን የተግባቡበት ጉዳይ ሆኗል። ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ለአየር ንብረት ለውጥ መባባስ ድርሻዋ ዝቅተኛ ቢሆንም ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ጉልህ ድርሻ በማበርከት ላይ ትገኛለች። ይህም ጥረቷ ዓለም አቀፍ ኃላፊነት የሚሰማት መሆኗን እንደሚያመለክት በቅርቡ የአካባቢና ደን ሚኒስትር ከአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪሽያ ሃስላክ ጋር የድጋፍ ስምምነት ፊርማ ባካሄዱበት ወቅት መናገራቸው ይታወሳል።

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ቀርፃ በመንቀሳቀስ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ የበርካታ አገሮችን ቀልብ ስባለች። በተለይ ከበለፀጉ አገሮች መካከል ኖርዌይ፣ እንግሊዝ፣ ዴንማርክ፣ ስዊድን፣ ፈረንሳይና አሜሪካ የመሳሰሉ አገሮች ድጋፋቸውን እየሰጡ ይገኛሉ። አገሪቱ የነደፈችውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ተከትላ በአገር ውስጥ የምታከናውናቸው ሥራዎች የራሷን ልማትና ዕድገት የሚያፋጥኑ፣ ለዓለም ስጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከልና አደጋዎቹን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታምኖበታል። ለአየር ንብረት ለውጥ መባባስ ትልቅ ሚና የነበራቸው አገሮች ሳይቀሩ ለምታከናውነው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ድጋፋቸውን ለመስጠት የወሰኑት ችግሩ ያስተሳሰራቸውና የጋራ ጥቅም ወደሚያስገኝ መፍትሔ የሚወስዳቸው ሆኖ በማግኘታቸው መሆኑን መገመት አይከብድም።

ኢትዮጵያ የያዘችው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምና ዝቅተኛ የካርበን ልቀት መጠን እንዲኖር የሚያደርግ አብዮት  ነው። ስትራቴጂው በአንድ ጎን ልማትና ዕድገቷን የሚያፋጥንና ዘላቂነቱን አስተማማኝ የሚያደርግ አካባቢ ይፈጥራል። ተፈጥሮን ከመንከባከብና ተጠቃሚ ከመሆን በተጨማሪ ለብክለትና ለውድመት ከሚዳርጉ አደጋዎች ጠብቆ ለማቆየት ሁነኛ መፍትሔ ያዘለ ሆኗል።

አሁን ኢትዮጵያ ለዘላቂ የልማት ግብ ታትራ በመሥራት ላይ ትገኛለች። ወደ ኢንዱስትሪ ልማት በመሸጋገርም ሂደት ላይ ናት። የኢንዱስትሪ ልማቷም ለአየር ንብረት ለውጥ መባባስ ምክንያት መሆን እንደሌለበት በቅድሚያ አስባበታለች። በመሆኑም ነው የአየር ንብረት ለውጡን መቋቋምና መግታት ለዘላቂ ልማት ግብ ዳር መድረስ ወሳኝ መሆኑን አምና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂዋን በመተግበር ላይ ያለችው። እንደ ምኞቷና እንደተግባራዊ እንቅስቃሴዋ በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ከአካባቢ ከብክለት የፀዳ የኢንዱስትሪ ማዕከል ሆኖ ለመገኘት እየሠራች ነው። የኢንዱስትሪውን ዕድገት ከታዳሽ ኃይል አማራጭ ጋር አስተሳስራ እያካሄደች መሆኗም ይህንኑ ነው የሚያረጋግጠው።

ለአካባቢ ጥበቃና ለደን ልማት ኢትዮጵያ የሰጠችው ትኩረት የግብርና ልማቷን የሚደግፍ ነው። በተለይም ሰፊው አርሶ አደር የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን የመሸፈኑን ውጤት በቅርብ እየተረዳ በመምጣቱ በስፋት የሚያከናውነው ተግባሩ አድርጎ ይዞታል። የተራቆቱ ተራሮችን ደን በማልበስ፣ ተዳፋቶችን በማቃናት ለአፈር መሸርሸር የተጋለጡትን በመከተርና ደን በማልበሱ የአካባቢው አፈር ለምነቱ ጨምሯል። ውሃ የማመንጨት አቅምም አድጓል። የደረቁ ወንዞች ባለማቋረጥ ይፈሳሉ። ለበረሃማነት በመጋለጣቸው ሙቀታማ የሆኑ አካባቢዎች ነፋሻማና ለሰዎችም ሆነ ለእንስሳት ተስማሚ እየሆኑ ናቸው። በተለይ አርሶ አደሩ በተከታታይ ዓመታት ባከናወናቸው የተፋሰስ ልማትና የደን ተከላና ክብካቤ ሥራዎቹ ውጤታማ እየሆነ ነው። ይሁንና ከቦታ ቦታ ወጣ ገባ አሰራር እየታተበት ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ አጠናክሮ በሁሉም አካባቢ መተግበር ወሳኝና ወቅቱ የሚጠይቀው አብዮት ነው፡፡

አብዮቱ ለኑሮ ተስማሚ ምድር፣ መራብና መጠማት፣ ስደትና መፈናቀል፣ ድህነትና ኋላ ቀርነት የተወገዱባት፣ ዕድገትና ብልጽግና የሰፈነባት አገር ለመገንባት የሚያስችል ነው።  የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን ተግባራዊ እያደረገች ያለችው ኢትዮጵያ ለደን ልማት አመቺ አደረጃጀት በመፍጠርና ሀብት በመመደብ፣ መላው ህዝብ እንዲሳተፍና በባለቤትነት እንዲያከናውነው በማድረጓ ዓለም የተጨነቀበትን የአየር ንብረት ለውጥና ያስከተለውን አደጋ ለማስቀረት ከኢንዱስትሪዎች የሚወጣውንና ወደ አየር የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ ለመምጠጥ የሚያስችል የተሳካ አብዮት እያካሄደች ነው።

ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ መንግስት የአየር ንብረት መዛባት በዓለማችን ላይ እያስከተለ ያለውን አደጋ ለማስቀረት ቁርጠኛ ስለመሆናቸው ከላይ የተመለከቱት  ተግባራት ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው። ከተግባሩም ሆነ ከውጤቱ አድናቆት አትርፈውበታል፣ ይህም ይበልጥ እንድንተጋ አድርጎናልና የበለጠ ለመስራት ጥረታችን እንደቀጠለ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy