Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አንድ አይና …

0 634

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አንድ አይና …

ወንድይራድ ኃብተየስ

 

ዘመን የማይሽረው ታላቁ አርቲስት እንዲህ ሲል አቀንቅኖ ነበር።  “ሣቅ ፈገግታ ደስታ …  በአገር  ነው”  አዎ ሁሉም ነገር የሚኖረው አገር ስትኖር ነው።  ለሁላችንም ያለችን አንድ አገር ናት። “አንድ አይን ያለው በአፈር አይጫወትም”። ይባላል። አሁን…አሁን የምናየው ነገር አገራችንን ወደ ገደል እየገፋናት ይመስለኛል። 1983 ዓ.ም ሁኔታ ከቶ ተዘንግቷል ባይ ነኝ። “A vow made in the storm is forgotten in the calm”  ይላሉ ፈረንጆቹ። እንደኔ እንደኔ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በአንዳንድ ኃይሎች የሚፈፀሙ ድርጊቶች ለአብሮነታችን የሚበጁ አይመስሉኝም። ከሁሉም ነገር ያሳሰበኝ ደግሞ ይህን ድርጊት  ሁሉም አካል ሲያወግዙት አለማስተዋሌ ነው።  

 

ሌላ ጉዳይ ላንሳ። ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓትን መከተል ከጀመረት 27 ዓመታትን ልታስቆጥር ጥቂት ወራት ቢቀሩት ነው። በእነዚህ ዓመታት ኢትዮጵያ የቀንዱ አካባቢ ሠላም ደሴት መሆኗን በተግባር አሳይታለች። አገራችን የተረጋጋች ሠላም የሰፈነባት ለመሆን የበቃችው የህዝቧቿ መሠረተዊ ጥያቄዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ሥርዓት መከተል በመቻሏ ብቻ ነው።

 

በርካታ ልዩነቶችና ፍላጎቶች ለአብነት የብሄር፣ የኃይማኖት፣ የማንነት፣ የአስተሳብ የሚስተዋሉባት እንዲሁም በዓለም በነውጥ ቀጠናነቱ በሚታወቀው ባልተረጋጋው እና ተለዋዋጭ የፖለቲካ ሁኔታ በሚታይበት የምሥራቅ አፍሪካ  ቀጠና የምትገኘው አገራችን  ስኬታማ ለመሆን የበቃችው በፌዴራላዊ የአስተዳደር ሥርዓቷ ነው። ባለፉት ሥርዓቶች የነበረሩት አሃዳዊ ሥርዓቶች አገሪቱን ለምን ዳርገዋት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።   

 

ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ካለችው ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ምጣኔ ሀብታዊ እድገት የአገራችን ህዝቦች ብቻ ሳይሆኑ ጎረቤት አገሮች ጭምር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አገራችን ለሁሉም ጎረቤት አገራት ዜጎች እንደሁለተኛ አገር የምትቆጠር ለመሆን በመብቃቷ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ሙገሳ ሳይቀር ተችሯታል።  ዛሬ ላይ አገራችን ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ የጎረቤት አገራት ስደተኞችን አስጠልላለች። ይህ አኃዝ ምናልባት የአንዳንድ  የአፍሪካ አገራት የህዝብ ቁጥር እንደሆነ ማየት ይቻላል። መንግሥት ከራሱ ዜጎች አልፎ የአካባቢው አገሮች ህዝቦችን በሚችለው ነገር ሁሉ ተጠቃሚ ለማድረግ  የሚያከናውነው ጥረት ሊደነቅ ይገባዋል። ይህም ለሌሎች መንግሥታት ተምሣሌት ሊሆን የሚገባው ተግባር ነው።  የውስጡ ሠላም የሌለው መንግሥት ለውጪ ዓለም ሠላማዊ ሊሆን ከቶ አይቻለውም።

 

ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በፈጣን ሁኔታ ማደግ በመቻሉ ከጎረቤት አገራት ጋር በንግድ፣ በባህል፣ በሠላም ማስከበር ወዘተ…ትስስሩ እየጠነከረ መምጣት ጀምሯል። ኢትዮጵያና ጅቡቲ እጅግ የጠነከረ ግንኙነት በመፍጠር ዛሬ ላይ አንዷ አገር ለሌላኛዋ የህልወና ምንጭ እስከመሆን መድረሳቸውን መመልከት ይቻላል።  

 

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ማለትም ከደቡብ ሱደን፣ ሱዳን፣ ኬንያ እንዲሁም ሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጎልበት የሚያስችሉ የተለያዩ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ለአብነት ዘመናዊ የመንገድ ግንባታ፣ የባቡር ማስመር ዝርጋታ፣ በአየር በረራ መስመሮች ማስፋፋት፣ የኃይል አቅርቦት ወዘተ… በማካሄድ ላይ ነች።

 

ኤርትራ ህዝብም ቢሆን ኢትዮጵያ ካስመዘገበችው የምጣኔ ሀብት እድገት በቀጥታ ባይሆንም በተዘዋዋሪ ሁኔታ ተጠቃሚ መሆን የቻለበት ሁኔታዎች እንዳለ ማየት ይቻላል። አምባገነኑ የኤርትራ መንግሥት በሕዝቡ ላይ በሚያደርሰው ከፍተኛ በደል ሣቢያ በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ኤርትራዊያን ኢትዮጵያ መጠጊያ መሸሺያ ሆናለች።

 

በምሥራቅ አፍሪካ ያለው የሕዝብ ለህሕብ ግንኙነት እንዲጠናከር የኢፌዴሪ መንግሥት  ከሚያደርገው የመሠረተ ልማት ማስፋፋትና ስደተኞችን አቅም በፈቀደ ሁሉ  ከመንከባከብ   ባሻገር የቀጠናውን ሠላም ለማረጋገጥ አገሪቱ የአንበሣውን ድርሻ በመወጣት ላይ ነች።

 

እንግዲህ እነዚህ ሁሉ መልካም ቁም ነገሮች የመነጩት ከህገ መንግሥታችን መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። የፌዴራል ሥርዓቱ  የህዝቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ  መብቶች ከማረጋገጥ ባሻገር አገሪቱን በፈጣን የምጣኔ ሀብት ለውጥ ምህዋር ውስጥ አስገብቷታል።

 

ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ መድረክ የነበራት ገጽታም ሆነ  ተሰሚነት ባለፉት 27 ዓመታት እጅጉን ተለውጧል፤ በአገሪቱ አስተማማኝና ዘላቂ ሠላም በመስፈኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ  የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ምጥታለች። በአገሪቱ ከባድ ድርቅ ለተከታታይ ዓመታት ቢከሰትም በራስ አቅም መቋቋም ተችሏል።

 

ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ  በአፍሪካ ሆነ  በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ ጨምሯል። በአገሮች መካከል ግጭት ወይም ያለመግባባት ሲከሰት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአደራዳሪነት ወይም ሸምጋይነት ግንባር ቀደም ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ያላት ተሰሚነት፣ በአፍሪካ ህብረት ያላት የመሪነት ሚና እንዲሁም በኢጋድና በሌሎች ትላልቅ መድረኮች ያላት ቦታ ከሰማይ የወረደ መና አይደለም።  መንግሥት ባከናወነው አኩሪ ተግባሮች እንጂ።

 

በመጨረሻም አንድ መታወቅ ያለበት ቁምነገር አለ። ይኸውም ኢትዮጵያ ከላይ የተገለጹትን ስኬቶች ማስመዝገብ የቻለችው ሕዝቦቿ በመከባበርና በመቻቻል አብሮ በመኖራቸው ነው። አብሮ መኖር ያስቻለን ደግሞ ልዩነቶቻችንን ማስተናገድ ያስቻለን  የፌዴራል ሥርዓቱ ነው።

 

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy