Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አዋጁ ለምን ታወጀ?

0 469

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አዋጁ ለምን ታወጀ?

                                                      ቶሎሳ ኡርጌሳ

ከመሰንበቻው በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዙሪያ የተለያዩ መላ ምቶች እየተሰነዘሩ ነው። አንዳንዶቹ መላ ምቶቹ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተገነዘቡ የሚመስሉ አይደሉም። ያም ሆኖ ሰሞኑን የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያትና ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ህገ መንግስታዊውን ስርዓት በሃይል ለማፍረስ የሚደረግ አካሄድ መታየቱ፣ በበርካታ አካባቢዎች ስርዓት አልበኝነት በመንገሱ እና የህግ የበላይነትን መሸርሸር መጀመሩን ሚኒስትሩ ገልፀዋል። እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች የልማት አውታሮች ለውድመት እየተጋለጡ መሆናቸው፣ የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት መገደቡ፣ የዜጎችን  በሰላም ወጥቶ የመግባት መብት መጣሱ፣ ዜጎች በፍርሃትና በጭንቀት ውስጥ መውደቃቸውና ሌሎች ጉዳዩች ለአዋጁ መታወጅ ምክንያት ሆነዋል።

እንደሚታወቀው ህገ-መንግስቱ አንቀፅ 93 ላይ እንደደነገገው ሀገሪቱ ላጋጠማት ችግር ፈጣንና ወቅታዊ መፍትሔ ለመስጠት እንዲቻል በማሰብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ታውጇል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ኮማንድ ፖስት የአዋጁን አፈፃፀም ይመራል። እርግጥ በአንድ ሀገር ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት በርካታ ጉዳዩች ከግምት ውስጥ ይገባሉ። ሁሉም መብቶች ሊከለከሉ አይችሉም። ሁሉም መብቶችም አይፈቀዱም። አስፈላጊ ናቸው የሚባሉ አንዳንድ መብቶች ላይ ገደብ ሊጣል ይችላል። ሁከትና ብጥብጥ ያባብሳሉ ወይም የሀገሪቱን ህገ-መንግስታዊ አንድነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ በሚባሉ መብቶች ላይ ገደብ ሊጣል ይችላል።  

ምንም እንኳን የአዋጁን ሙሉ ይዘት በዚህ አጭር ፅሑፍ ለማብራራት ባይቻልም፤ ሰሞኑን የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ከሰጡት የአዋጁ ሙሉ ክፍል መግለጫ በመነሳት ገደብ የተደረገባቸውን ዋና ዋና ጉዳዩችን ለአንባቢዎቼ ማንሳት ያስፈልጋል። ማንኛውም አዋጅ የሚወጣው ተፈፃሚ እንዲሆን ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ በአዋጁ ላይ የተገለፁት ጉዳዩችን በጥብቅ እንዲከበሩ ማድረግና ማስከበር ይገባል። ታዲያ ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ሰሞኑን በኮማንድ ፖስቱ የተገለፀውን የአዋጁን መመሪያ አንኳር ጉዳዩችን መቃኘት ይገባል። በቅድሚያ የምንመለከተው በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ውስጥ የተከለከሉ ተግባራትን ነው። ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የሚጥስ ተግባር መፈፀም፣ የህዝቦችን መቻቻልና አንድነትን የሚጎዳ ተግባር መከወን፣ በአሸባሪነት ከተፈረጁ ድርጅቶች አመራሮች፣ አካላትና ፀረ-ሰላም ቡድኖች ጋር ማናቸውንም ግንኙነቶች ማድረግ፣ የአሸባሪ ድርጅቶችን ዓላማ ማስፈፀም፣ ፅሑፎችን መያዝና ማስተዋወቅ፣ የትራንስፖርትን እንቅስቃሴን ማወክ፣ የህዝብን አገልግሎት ማስተዋወቅና ማቋረጥ እንዲሁም በመሰረተ ልማቶች፣ በህዝብ፣ በመንግስትና በግል ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ፣ የህግ አስከባሪዎችን ስራ ማወክና በእነርሱም ላይ ጥቃት መፈፀም በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ውስጥ የተከለከሉ ተግባሮች ናቸው።

ክልከላው ያልተፈቀዱ ሰልፎችና የአደባባይ ስብሰባዎች እንዲሁም ከኮማንድ ፖስቱ ፈቃድ ውጭ ማናቸውንም ሰልፍና የአደባባይ ስብሰባ ማድረግ፣ በትምህርት ተቋማትና በስፖርት ማዘውተሪያዎች አድማ ማድረግ እንዲሁም ሁከቶችንና ብጥብጦችን መፍጠር እንደማይቻል ያስረዳል። ከዚህ በተጨማሪ ሁከትና ብጥብጥ የሚያነሳሳ ቅስቀሳና ግንኙነት ማድረግ፣ አድማና ህገ ወጥ ተግባር መፈጸም ወይም እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ይፋዊም ሆነ ድብቅ ቅስቀሳ በማናቸውም በኩል ማድረግ ፅሁፍ ማዘጋጀት፣ ማተምና ማሰራጨት፣ ትዕይንት ማሳየት፣ በምልክት መግለፅ ወይም መልዕክት በማናቸውም ሌላ መንገድ መግለፅ፣ ማንኛውንም ህትመት ወደ አገር ወሰጥ ማስገባት ወይም ወደ ውጭ አገር መላክ፣ በሞባይል፣ በፅሁፍ፣ በቴሌቪዥን፣ በራድዮ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ወይም ሌሎች የግንኙነት ዘዴዎች መለዋወጥ ክልክል ነው።

መሰረታዊ ሸቀጦችን ከቦታ ቦታ ማዘዋወርና ስርጭቱን ማወክ እንዲሁም ባህላዊ፣ ህዝባዊና ዓይማኖታዊ በዓላትን ማወክ፣ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት በሁሉም የሀጋችን ከፍሎች ውስጥ የተከለከሉ ተግባራት ናቸው። ትጥቅን በሶስተኛ ሰው እጅ እንዲገባ ማድረግና የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማደፍረስ ድጋፍ መስጠት እንዲሁም ከኮማንድ ፖስቱ ፍቃድ ውጭ በፀጥታ ጉዳይ መግለጫ መስጠት የተከለከለ ነው። በአዋጁና አዋጁን ለማስፈፀም የወጡ መመሪያዎችን ማደናቀፍም አይፈቀድም።

ከላይ የጠቀስኳቸውና በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ተፈፃሚ የሚሆኑት ክልከላዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ በተወሰኑ የሀገራችን አካባቢዎች ኮማንድ ፖስቱ በሚወስነው አካባቢዎች የተከለከሉ ተግባራትም ይፋ ሆነዋል። ከእነዚህም ውስጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ፣ የሰዓት እላፊ እገዳ፣ በተለይም በኢንቨስትመንትና መሰል ተቋማት ኮማንድ ፖስቱ በሚወስነው ጊዜ ከተፈቀደ ሰዓት በስተቀር መንቀሳቀስ ክልክል መሆኑ እንዲሁም ሁከትና ብጥብጥን ብሎም አደጋን ለመከላከል የሚደረግ እንቅስቃሰሴን ማወክ የተከለከለ ነው።

አዋጁን በመተግበር በኩልም የዜጎች ግዴታ ተቀምጧል። በዚህ መሰረት የተከራይን መረጃ መያዝና ማሳወቅ፣ በየደረጃው የሚገኙ የህግ አስፈፃሚ አካላት መረጃ ሲጠይቁ የመስጠትና የመተባበር ግዴታዎች ተቀምጠዋል። የህግ አስፈጻሚ አካላት የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ የተዋረዱ የእዝ ሰንሰለቱን ተከትሎ እንደሚዋቀር፣ እርምጃዎች ሲወሰዱ የመተባበር ግዴታም እንዲሁ የአዋጁ አካል ነው።

የሚወሰዱ ርምጃዎችን አስመልክቶም ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውን ክልከላዎች የተላለፈ ማንኛውም ሰው፤ የህግ አስከባሪዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር የማዋል፣ አዋጁ አስከሚያበቃ ድረስ ኮማንድ ፖስቱ በሚወስነው ቦታ አንዲቆይ የማድረግ፣ ተገቢውን የተሃድሶ ትምህርት በመስጠት የሚለቀቀው እንዲለቀቅ፣ ወደ ፍርድ ቤት የሚቀርበው በህጉ መሰረት እንዲቀርብ የማድረግ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል። እንዲሁም የአካባቢውን ፖሊስ በማሳተፍ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማናቸውም ጊዜ ብርበራ የማድረግ፣ ማንኛውንም ወንጀል የተፈጸመበትን ወይም ሊፈጸምበት የሚችለውን ንብረት የመያዝ፣ ባለበት እንዲጠበቅ የማድረግ፣ የተዘረፉ ንብረቶችን በማጣራት ለባለቤቶቹ እንዲመለሱ የማድረግ እና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ርምጃዎችን መውሰድ እንደሚችሉ ተዘርዝሯል።

ተጠርጣሪዎች በሚመለከታቸው የህግ አስከባሪ አካላት በመስፈርቱ መሰረት ተጠርጣሪዎች በመለየት ተጠያቂ እንዲሆኑም ያደርጋሉ። በአዋጁ ወቅት የህግ አስፈፃሚ አካላት ብርበራ ሲያካሂዱ፤ መታወቂያ የማሳየት፣ የፍተሻውን ዓላማማ የሚካሄድበትን ምክንያት የመግለፅ፣ የቤቱ ባለቤት (ነዋሪ) ፍተሻውን እንዲከታተል የመፍቀድ፣ የአካባቢው ፖሊስና ህብረተሰብ እንዲገኙ የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸውም ተመልክቷል። የሃይል አጠቃቀምን አስመልክቶም ህግ አስከባሪ አካላት የአዋጁን መመሪያ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ የራሳቸውን እንዲሁም የሰዎችን ህይወትና ንብረት በመጠበቅ አስፈላጊና ተመጣጣኝ ሃይል ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ተገልጿል። እንዲሁም መመሪያውን ለማስፈፀም ህግ አስከባሪ አካላት በትምህርት ቤቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲሁም በግልና የመንግስት ተቋማት ውስጥ አድማ የሚያደርጉ ሰዎችን ለመያዝና ለማስቆም በመግባትና በመቆየት አስፈላጊውን ርምጃ መውሰድ ይችላሉ።

እነዚህን የአዋጁን መመሪያዎች አንኳር ነጥቦች ያነሳኋቸው ያለ ምክንያት አይደለም—ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሀገራችንን ሰላም ወደ ነበረበት ሁኔታ ለመመለስ በሚደረው ጥረት ተሳታፊ እንዲሆን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው። በመሆኑም የታወጀበትን ምክንያት በውል በመገንዘብ ሰላማችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል።

ከዚህ አዋጅ በዋነኛነት የሚጠቀመው ህብረተሰቡ ነው። ሌላ ማንም አይደለም። እንደሚታወቀው በተለያዩ አካባቢዎች ህብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ መግባት መቸገሩን በግልፅ ሲናገር ነበር። ይህን ሁኔታ መቀልበስ የሚቻለው በዚህ መንገድ የህዝቡን ጥቅምና ሰላማዊ እንቅስቃሴን ሊያረጋግጥ በሚችል አዋጅ ነው። አዋጁ በአንዳንድ አካባቢዎች ተገድቦ የነበረውን የዜጎችን የመንቀሳቀስ መብት የሚያስጠብቅና ለእኩይ ዓላማ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ፍላጎት የሚገድብ ነው። በዚህ አዋጅ ዜጎች ከተከለከሉ የተወሰኑ ቦታዎች በስተቀር ህጋዊነታቸውን ጠብቀው ሊንቀሳቀሱና በልማት ስራው ላይ ተሳታፊ ሊሆኑ ይችላሉ።

በዚህ መነሻነትም ሁሉም ዜጋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማክበር አለበት። ለጥቆም ለአዋጁ ተፈፃሚነት ትብብር ማድረግ ይጠበቅበታል። አዋጁን የማያከበርና ለተፈፃሚነቱም ከኮማንድ ፖስቱ አባላት ለሚቀርብለት የድጋፍ ጥያቄ የማይተባበር ማንኛውም ግለሰብ በአዋጁ መሰረት ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም። ያም ሆኖ ግን ጉዳዩ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን የጥፋት ተልዕኮ የመታደግ ብሎም ዕድገታችን ያስኮረፋቸውን አንዳንድ የውጭ ሀገራትን የእጅ አዙር ሴራ መከላከል በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል።

ርግጥ የትኛውም ሀገር ወዳድ ዜጋ በእነዚህ ኃይሎች ሰላሙ እንዲደፈርስ፣ ማናቸውም ህገ-መንግስታዊ መብቶቹ ተነጥቀው የስርዓት አልበኞች መፈንጫ ሆኖ ህይወቱን፣ ሃብቱንና ንብረቱን እንዲያጣ ብሎም ሀገር አልባ ሆኖ በትርምስ ውስጥ እንዲኖር አሊያም በጎረቤት ሀገር ውስጥ የጥገኝነት ህይወትን እንዲገፋ ይፈልጋል ተብሎ አይታሰብም። ይህ እንዳይሆን ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማክበርና ለተፈፃሚነቱ መተባበር የግድ ይላል። አዋጁ የሚቆየው ለስድስድ ወር ሲሆን፤ እንደ ሁኔታው እየታየ ሊጨምር ይችላል።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የሚታዩትን መጥፎ ክስተቶች በስድስት ወራት ውስጥ ገትቶ በተለመደው ሰላማዊ የህይወት መስመር ውስጥ መግባት ያስፈልጋል። ይህን ዕውን ለማድረግም አዋጁን አክብሮና በነቃ ሁኔታ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመተባበር የህግ የበላይነት ለማስከበር ሁሉም ዜጋ የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy