Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ኣግዓዚ ጦር” ማነው?

0 773

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ኣግዓዚ ጦር” ማነው?

                                                ፈለቀ ማሩ

(ክፍል አንድ)

አንድ ወዳጄ ያለ ወትሮው ከአዘቦት ቀናቶች ውስጥ በአንዱ ደወለልኝ። ቀደም ባሉት ጊዜያት ወዳጅነታችን ጠንካራና ቅርበት ያለው ስለነበር ‘ለምን ደወለልኝ?’ የሚል ጥያቄ የአዕምሮዬን ጓዳ ታክኮት አላለፈም። ምክንያቱም ጊዜው ዘለግ ቢልም ያሳለፍነው እነዚያ ጥብቅ የወንድማማችነት ቅርበት ትዝ ባለኝ ቁጥር ወደ አልፎ…አልፎ በእጅ ስልኬ ቁጥሩን ስለምመታ ነው። ከነበረን አቅርቦት አኳያ ይህ ባልንጀራዬ መደወሉ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።

ታዲያላችሁ ወዳጄ የደወለልኝ እንዲያው ለዋዛ ለፈዛዛ ጉዳይ አልነበረም። ነገሩ ራሴን እንድፈትሽ፣ የመረጃዎችን ጓዳ እንድዳስስና አንድ ዓይነት ድምዳሜ ላይ እንድደርስ ያደረገኝ ነው። ይህ ባልንጀሬ ለካስ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገፆች የሚመለከታቸው አስገራሚ ትንተናዎች፣ የዚህ ሀገር ሰላምና መረጋጋት እንደ አባ ጨጓሬ የሚኮሰኩሳቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በተለያዩ መገናኛ ብዙሃናቸው እየደጋገሙ የሚያነሷቸው አስልጥ አሉባልታዎች እንዲሁም እነርሱን ተከትሎ ደጋግመው የሚያነሱት አንድ ስም ከንክኖት ኖሯል። “ኣግዓዚ” የተሰኘ።

ይኸው ባልንጀራዬ “በባህሪያዊ ማንነቱ የሚታወቀውን፣ በሚያከናውናቸው ተግባሮቹ ድፍን አፍሪካና ዓለም የሚያመሰግነውን፣ እንኳንስ ለገዛ ህዝቡ ቀርቶ ለጎረቤቶቹም ሰላም ሟች የሆነውን፣ ምናልባት እርሱ ባይኖር ኖሮ የሀገራችን ታሪካዊ ጠላቶችና የውስጥ አጋፋሪዎቻቸው ተቀናጅተው ኢትዮጵያን እንደ ያኔዋ ሶማሊያ፣ እንደ ዛሬዎቹ የመንና ሊቢያ እንዲሁም እንደ ዲሞክራቲክ ኮንጎ የርስ በርስ ብጥብጥ ውስጥ እንዳይከቷት እየሞተ ያኖረንን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት፤ ኣግዓዚ እያሉ የሚጠሩት ለምንድነው?” የሚል ጥያቄ አቀረበልኝ። “ለመሆኑ ኣግዓዚ ጦር ማነው?” ሲልም አከለ።

በእውነቱ ከባድ ጥያቄ ነበር። ቁንፅል እውቀትን ሳይሆን ጠቅላላ ግንዛቤን የሚጠይቅ ጥያቄ። ስሜታዊነትን ሳይሆን ሚዛናዊነትንና ሀገራዊ ጥቅምን የተመረኮዘ ምላሽ የሚሻ ጥያቄ። ሰራዊትን እንደ አንድ ሀገር ደህንነት ዋስና ጠበቃ እንዲሁም ግለሰብን እንደ ጥሩ ተምሳሌት መመልከት የሚያሻ ጥያቄ። ግላዊ ጥቅምንና ብሔራዊ ጥቅምን (National Interest) ነጣጥሎ በመመልከት ወደ እውነታው ማምራትን የሚፈልግ ጥያቄ።…ወዘተርፈ። ጥያቄው ጭንቅላቴ ውስጥ ያላጫረብኝ የሃሰበ ደርዝ የለም።

እውነት “ኣግዓዚ ጦር ማነው?”—በገሃዱ ዓለም ላይ ያለ ወይስ ምናባዊ ድርሰት?፣ በስሜት የሚነዳ አካል የፈጠራ ትርክት ወይስ ከሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሀዝቦች አብራክ የተገኘን ሰራዊት ጥላሸት የመቀባት ዘመቻ?…ምንም እንኳን የሀገራቸውን ሰላም ለማወክ በባዕዳን ተገዝተውና ባህር ማዶ ሆነው የእሳት ማቀጣጠያ ሚዲያዎቻቸውን ጡሩንባ ወደ ሀገራችን ቀስረው የሚለፍፉ ፅንፈኞች፤ በህዝባዊ ማንነቱ የሚታወቀውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትን ለምን “የኣግዓዚ ጦር” እያሉ እንደሚጠሩት ባውቅም ቅሉ፤ የወዳጄን ጥያቄ በአጥጋቢ ሁኔታ ለመመለስ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ለማግኘት እግርቼን ከወዲያ ወዲህ ማላወስ ግድ ሆኖብኛል። የኮምፒውተሬን ቁልፎች መነካካትም አስፈልጎኛል። ከስሜት በፀዳ ተጨባጭ እውነታዎች ላይ መመርኮዝም ነበረብኝ። እናም ሳምንቱን ሙሉ “እውን ኣግአዚ ጦር ማነው?” ስል ባክኛለሁ። በገባኝ መጠንም የራሴ ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ።

ድምዳሜዬንም በውስጤ አምቄ አልያዝኩትም። በስተመጨረሻም ይህች አጭር ፅሑፍ ለሁለት ወገኖች ምላሽ ትሆን ዘንድ ብዕሬን ከወረቀት ጋር ላዋድድ ፈቀድሁ። አንድም፤ የጥያቄው ባለቤት ለሆነው ባልንጀራዬ መልስ ለመስጠት፣ ሁለትም፤ ፖለቲከኞቻችን በተገቢው መንገድ የቤት ስራቸውን ባለመስራታቸው ሳቢያ፤ በህገ መንግስቱ መሰረት የህዝቡን ሰላምና መረጋጋት ለማስጠበቅ ከሁለት ዓመት በላይ እዚህም…እዚያም ሲባክን ለነበረውና ላለው እንዲሁም በቅርቡ የኢፊዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመሩትና በህገ መንግስቱ አግባብ በ1994 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 257/1994 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው “የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት” (National Security Council) (የሁሉም ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት ተቋማት በአባልነት የሚገኙበት መሆኑን ልብ ይሏል!) አማካኝነት ታዝዞ ከህዝቡ ጋር በመሆን ሀገሩን ከውድቀት የታደገውን ህዝባዊው መከላከያ ሰራዊታችን ሆን ብለው ምግባሩን ለማጠልሸት ሲሉ በአላዋቂ ሳሚነት “የኣግዓዚ ጦር” እያሉ የሚጠሩት ፅንፈኞች “ተሳስታችኋል” ለማለት የሚያስችል ነው። በዚህም በስሜት የሚነዳውና በሀገራችን ላይ የራሳቸውን ዓላማና ጥቅም ለማራመድ የሚቋምጡ የውጭ ሃይሎች ፌስ ቡክን በመሳሰሉ የትስስር መረቦችና እንደ “ኢሳት” በመሰሉ ገበርዲን ቀዳጅ ሚዲያዎች አማካኝነት በተላላኪነት የሚሰራው ፅንፈኛ ኃይል ለሰራዊታችን ያልተገባ ምስል ለመስጠት ለሚያደርገው አሉባልታዊ ጥረት የደረስኩበትን ድምዳሜ ለማስረዳት እሞክራለሁ።

ስለ “ኣግዓዚ ጦር” ማንነት ከማውሳቴ በፊት ግን፤ በቅድሚያ “ኣግዓዚ ራሱ ማነው?” ብሎ መጠየቅ የተሟላ ምስል ለመስጠት ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ። ፅንፈኛው ኃይል የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትን “የኣግዓዚ ጦር” ብሎ ስለጠራው ማንነቱን ያኮሰሰበት መስሎት የታየው ይመስለኛል። ዳሩ ግን ይህ አስተሳሰብ ፈፅሞ ትክክል ያልሆነና ሃቅን ካለመገንዘብ የተሰነዘረ መሆኑን ከዚህ በታች ከማቀርባቸው ሃሳቦች መረዳት የሚቻል ይቻላል።

ያገኘኋቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ኣግዓዚ ከትግራይ ህዝብ አብራክ የተገኘ፣ ‘የህዝቦችና ስቃይና ሰቆቃ ማየት በቃኝ’ በማለት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርቱን አቋርጦ ዱር ቤቴ ያለ ጀግና ወጣት ነበር—በንጉሱ ዘመን። ወጣቱ አግዓዚ በኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ታሪክ ውስጥም ጉልህ ስፍራ ነበረው። በ1964 ዓ.ም “የብሔረ ትግራይ ተወላጆች የዩኒቨርስቲ ማህበር” (ማህበር ተጋሩ ዩኒቨርስቲ) የተባለው እንቅስቃሴ ሲጀመር ዋነኛ ተዋናይም ነበር። በ1966 ዓ.ም “የብሔረ ትግራይ ተራማጆች ማህበር” (ማህበር ገስገስቲ ትግራይ) በሰባት ሰዎች ሲመሰረትም ኣግዓዚ አንዱ መስራች ነው። በወቅቱም ለትጥቅ ትግል አመቺ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ጉልህ ሲጫወት እንደነበር የህይወቱ ድርሳን ያስረዳል።

ወቅቱ የተለያዩ የሀገራችን ህዝቦች ከአምባገነኑ የደርግ ስርዓት ጋር ሆድና ጀርባ የሆኑበት ነበር። ከዛሬዎቹ ፅንፈኞች በስተቀር በዚያን ወቅት የደርግ የአፈና አገዛዝ ያላንገሸገሸው ኢትዮጵያዊ የለም ማለት ይቻላል። በተለይ የደርግ መቋጫ የሌለው ግፍ እንደ እሬት የመረረውና የስቃይ ቀንበሩ ከአቅሙ በላይ የሆነው የትግራይ ህዝብ እንደ ሌሎቹ የሀገራችን ህዝቦች ሁሉ፤ ብረት አንስቶ መዋጋትን እንደ መፍትሔ ወሰደ። ገና በጨቅላ ዕድሜው ለጭቁን ህዘቦች ቤዛ ለመሆን የቆረጠው አግዓዚም የትግሉ ጀማሪ ሆኖ ተሰለፈ።

በዚህም በደርግ ውስጥ ለትግሉ እርሾ የሚሆኑ ታጋዩችን የመመልመልና የማንቀሳቀስ ስራዎችን ያከናውን ነበር። በደደቢት በረሃ ላይ ትግሉ መጀመሩን የሚያበስረውን ችቦ ከለኮሱት 10 ታጋዩች ውስጥ ኣግዓዚ አንዱ ነው። በትግሉ ጅማሬ ወቅት አመራር ሆኖ ሲቀጥል፤ ትግሉ የሚጠናከርበትን መንገድ የመሻት፣ አባሎችን የመመልመል፣ ፖለቲካዊ ሃሳቦችን የማስረፅና ትግሉን በሀገር ውስጥ የማስተዋወቅ ስራን ያከናውን የነበረ ታጋይ ነው። ግና ይህ ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ለጭቁን ህዝቦች ሲታገል የነበረ ወጣት ትግሉ በይፋ ተጀምሮ ብዙም ሳይቆይ ከአክሱም ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘውና “ውቅሮ ማራይ” በምትባለው ከተማ በደርግ ተሰዋ። ለጭቁኖች እየታገለ በደርግ ጨካኝ ቢላዋ የተቀጠፈ የህዝብ ልጅ ነው። ዛሬ ለተገኘው አስተማመኝ ሰላም፣ ሁለንተናዊ ዕድገትና ስር በመስደድ ላይ ለሚገኝ ዴሞክራሲ ፋና ወጊ ሆኖም ያለፈ ነው—አግዓዚ።

ታዲያ እዚህ ላይ ከኣግዓዚ ጋር በግንባር ቀደም መስራችነት ተሰልፈው የተሰውት እነ ሙሴ፣ ዋልታ፣ ቀለበት፣ ስሑል፣ ማርታ…ወዘተ አሁን ለምንገኝበት ስርዓት በር የከፈቱ መሆናቸውን ማንም ሊክደው አይችልም። ምናልባት ያኔ ትግሉ ባይጠነሰስ ኖሮ፤ የዛሬዎቹ ፅንፈኞች እነ ‘አያ እንቶኔ’ የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደ ብረት ቀጥቅጠውና እንደ ሰም አቅልጠው ደብዛቸውን ሳያጠፏቸው የሚቀሩ አይመስለኝም።

ግና ምስጋና ለትግሉ መስራቾች ለእነ ኣግዓዚ እንዲሁም ከደርግ ጋር ጥሻ ለጥሻ ተሯሩጠው፣ ጋራና ሸንተረር ወጥተውና ወርደው፣ ደማቸውን አፍስሰው፣ አካላቸውን አጉድለውና አጥንታቸውን ለሌሎች ሲሉ ማግደው እነሆ ዛሬ መላው የሀገራችን ህዝቦች አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱና ከስርዓቱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገዋል። ዛሬ ራሱን ችሎ የማይንቀሳቀስ፣ በራሱ ቋንቋ የማይማርና የማይዳኝ እንዲሁም ባህላዊ ትውፊቶቹን ያላሳደገ ብሔርና ብሔረሰብ የለም። ዛሬ እንደ ትናንቱ “ቋንቋህ ብረት ሰባሪ ነው፤ ፊቴ ቆመህ እንዳትናገር!” እየተባለ የሚንቋሸሽና የሚሸማቀቅ ብሔርም ይሁን ብሔረሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈልጎ አይገኝም። ሌላ ሌላም።….እነዚህ ጉዳዩች ያለንበት ዘመን ጥቁርና ነጭ እውነቶች ነው። እንዲያው በስሜት መነዳት ካልፈለግን በስተቀር፤ የስርዓቱን ጓዳ መፈታተሽ የፈለገ ሰው የሃቆቹን ዘበዞች ሳይመዛቸው ራሳቸው እጁ ላይ ዱብ ማለታቸው አይቀርም።

ርግጥ ኣግዓዚ በህዝባዊ ተግባሩ የተገዘፈ ስም ያለው ታጋይ ነው። ፅንፈኛው ኃይል ምንም ይበል ምን፣ መከላከያ ሰራዊታችን አሊያም ክፍሎቹ በዚህ ሰው ስም ተጠርተው ከሆነ፤ ምንም ዓይነት ነውር የሚኖረው አይመስለኝም። እነዚህን የተሰው የህዝብ ዋስና ጠበቃዎች ስማቸውን ከመቃብር በላይ ማንሳት ክፋቱ ምን እንደሆነ ለማንም ግልፅ ሊሆን አይችልም። ሆኖም ባገኘሁት መረጃ መሰረት ቀደም ባሉት ጊዜያት የሰራዊቱ አንድ ክፍል የተሰዋውን ታጋይ የዓላማ ፅናት፣ ጀግነትና ህዝባዊነት አዲሱ ትውልድ እንዲወርስ በማሰብ “አግዓዚ ኮማንዶ” የተሰኘ ክፍለ ጦር እንደነበር ተረድቻለሁ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በበላይ ዘለቀ፣ በዓባይ፣ በአብዲሳ አጋ…ወዘተ. የሚጠሩ ክፍሎችም እንደነበሩና እንዳሉም እንዲሁ። በአሁኑ ወቅት ግን በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ለብቻው ተለይቶ የሚታወቅና የተነጠለ “ኣግዓዚ ጦር” የሚባል ስያሜ የለም። ስያሜው ፅንፈኞቹ የልቦለድ ተረክ ነው። ያም ሆኖ አሁንም በሰራዊቱ ውስጥ የሚገኝ አንድ ክፍል መጠሪያውን ወጣትነቱን ለጭቁኖች መብት በሰዋ ታጋይ ስም ቢያደርግ ምንም ችግር የለውም። በበርካታ ኢትዮያዊያን አርበኞችና ጀግኖች የሚጠሩ ክፍሎች አሉና። ሀገራችን ውስጥ ያለው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት እንጂ “አግዓዚ” የሚባል ጦር አይደለም።

‘እናስ ፅንፈኞቹ ከየት አምጥተው ነው—ሰራዊቱን አግዓዚ ጦር እያሉ የሚጠሩት?’ ብለን ስንጠይቅ፤ ከበስተጀርባው ያለውን የተንኮል ሴራ ለመገንዘብ ብዙም የሚከብድ አይደለም። ይኸውም ፅንፈኛው ኃይል የኤርትራ መንግስትንና አንዳንድ የሀገራችንን መዳከምና መውደቅ የሚሹ ጠላቶች አጀንዳ ተሸካሚና አስተላላፊ በመሆኑ፤ የእነርሱን ተልዕኮ ተቀብሎ የሚሰራ መሆኑ ነው። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ጠላቶች አጀንዳ፤ ሀገራችንን ለመበታተን የዘየዱት የለየለት ውሸትን በሚያካሂዱበት ‘የጥቁር የፕሮፓጋንዳ’ (Black Propaganda) ዘዴ በቅድሚያ የስርዓቱ የመጨረሻ ምሽግ የሆነውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትን በአሉባልታ ስሙን በማጠልሸት ተዓማኒነት እንዳይኖረው ማድረግ ነው።

የኢትዮጵያ ጠላቶች ይህን ሰራዊት በህዝብ ዘንድ ያለውን አመኔታ ካሳጣን ሀገሪቱን ማፍረስ እንችላለን የሚል የማይሰካ አጀንዳን ቀርፀው እየተንቀሳቀሱ ናቸው። በእነዚህ የሀገራችን ጠላቶች ሳንባ የሚተነፍሱትና ጠላቶቻችን ሲያስነጥሳቸው ተሽቀዳድመው መሃረብ የሚያቀብሉት ፅንፈኞች ደግሞ በመልዕክት አድራሽነት የተሰደሩ ናቸው። ለዚህም ነው— በየማህበራዊ ድረ ገፁና በኢትዮጵያ ጠላቶች “ፈንድ” በሚንቀሳቀሱ ሚዲያዎቻቸው አማካኝነት በህዝባዊ ባህሪው የሚታወቀውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትን በሌለ ስያሜው “የኣግዓዚ ጦር” እያሉ በመጥራት ሌላ ትርጉም ሊያሰጡት እየሞከሩ ያሉት።   

ርግጥ የሀገራችን ጠላቶች አጀንዳ ተሸካሚና አስተላላፊ የሆነው ፅንፈኛ ኃይል ማለት የፈለገው ግልፅ ነው። እርሱም መከላከያ ሰራዊቱን ከአንድ ብሔር ብቻ የተገነባ አድርጎ በመሳል የተዛባ ትርጉም ለማሰጠት የመሞከር የለየለት ውሸት ነው።

እውነታው ግን እነርሱ እንደሚሉት አይደለም። የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በህገ መንገስቱ አንቀፅ 87 መሰረት፤ በአዋጅ በ1988 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 27/88 በአዲስ መልክ ህብረ ብሔራዊ ሆኖ እንዲደራጅ ተደርጓል። በዚህ መሰረትም ዛሬ መከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ገብቶ የሰራዊቱን ስብጥር ለመመልከት የሚሻ ማንኛውም ሰው፤ የሀገራችንን ዥንጉርጉርነት መመልከቱ የሚቀር አይመስለኝም። ህብረ-ብሔራዊነት ምን ማለት እንደሆነም በተጨባጭ ይገነዘባል። ስብጥሩ ደማቅ ህብርን የሚፈጥርና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ነፀብራቅ መሆኑን ያለ አስረጅ መግለፁ አይቀሬ ነው። ሰራዊቱ ከአንድ ብሔር የተገነባ አለመሆኑን እጁን አውጥቶ መመስከሩም እንዲሁ።

ውድ አንባቢያን በቀጣዩ ክፍል ሁለት ፅሑፌ ፅንፈኛው ኃይል ህዝባዊውን መከላከያ ሰራዊት ለምን “አግዓዚ ጦር” እያለ እንደሚጠራው መረጃዎችንና ማስረጃዎችን አስደግፌ አቀርባለሁ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy