Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ኣግዓዚ ጦር” ማነው?

0 630

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ኣግዓዚ ጦር” ማነው?

                                                ፈለቀ ማሩ

(ክፍል ሁለት)

በክፍል አንድ ፅሑፌ በሀገርና በህዝብ የተሰጠውን ህገ መንግስታዊ ተልዕኮን በህዝባዊ ወገንተኝነት እየተወጣ ያለውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትን ፅንፈኛው ኃይል ለምን “ኣግዓዚ ጦር” እያለ እንደሚጠራው ለመግቢያነት ያህል የግል ዕይታዬን ጠቃቅሻለሁ። ቀጣዩ ትንታኔ እንዲህ የሚነበብ ነው።…

የሀገራችን ህብረ-ብሔራዊ ሰራዊት በአንድ ላይ የሚኖር፣ በእኩልነት መርህ የሚመራ፣ በፍትሐዊ ተጠቃሚነት በተቋሙ ውስጥ በሚገኙ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች አቅሙን በየጊዜው የሚያጎለብት እንዲሁም በጀትን አብቃቅቶ በመጠቀም የሀገሪቱ ዕድገት በሚፈቅደው መጠን በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ የሚገኝ ነው። ታዲያ ይህን እውነታ የሚገነዘብ ማንኛውም ሰው፤ የዚህ ለህዝብ የወገነ፣ ጀግና የሆነ፣ ከብረት የጠነከረ ህገ መንግስታዊ እምነት ያለውና በዲሲፕሊን የታነፀ እንዲሁም በወታደራዊ ሳይንስ እውቀቱን እያጎለበተ መሆኑን መረዳቱ የሚቀር አይመስለኝም።   

መከላከያ እንደ ተቋም ላለፉት 23 ህገ መንግስታዊ ዓመታት እየፈጠረ ያለው ሚዛናዊ ተዋፅኦን የመፍጠር አመርቂ ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በእኔ እምነት የውትድርና ሙያ በግለሰብ ደረጃ በልምድ የካበተ ክህሎትንና የጊዜ ቆይታን የሚጠይቅ በመሆኑ ባጠረ ጊዜ ውስጥ በሁሉም እርከኖች ሚዛናዊ ተዋፅኦን የመፍጠር ጉዳይ ያለ አንዳች እንከን ምሉዕ ማድረግ የሚቻል አይመስለኝም።

የውትድርና ሙያ ዳግም ሊገኝ የማይችለውን የሰውን ህይወት የማስተባበርና የመምራት ስራ በመሆኑ፤ የማዕረግ አሰጣጡ እንደ ሌሎች የስራ ዘርፎች በሹመት ሊከናወን ይገባል ሊባል የሚችል አይደለም። ይህም ምናልባት በሁሉም ደረጃዎች እኩል ተዋፅኦ እንዳይኖር ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም ላለፉት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች የማመጣጠን ስራ እየተከናወነ ነው። ይህን ፅሑፍ እያሰናዳሁ ባለበት ወቅት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በየማዕረግ እርከኑ የጊዜ ቆይታቸውን ለሸፈኑ፣ በግዳጅ አፈፃፀማቸው ህዝብና ሀገር የጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ለተወጡ ከብርጋዲየር ጄኔራል እስከ ሙሉ ጄኔራል ድረስ ላሉት 61 የሰራዊቱ ጄኔራል መኮንኖች የሰጡት የማዕረግ እድገት የዚህ ተዋፅኦን የመጠበቅ አሰራር ሁነኛ አስረጅ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ይመስለኛል።

እናም እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ከሰራዊቱ ምስረታ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የተለያዩ ውጣ ውረዶችን ተቋቁመው የሰራዊቱን አባላትና አመራሮችን በሂደት በማብቃት ዛሬ ተቋሙ ለደረሰበትና ወደፊትም ተጠናክሮ ለሚቀጥለው የብሔር ተዋፅኦ ቁመና ያበቁት በየደረጃው የሚገኙ የሰራዊቱ አመራሮች ሊመሰገኑ የሚገባቸው ይመስለኛል።

ታዲያ እዚህ ላይ እንዲህ ዓይነቱ ውጤት ዝም ብሎ የተገኘ አለመሆኑን መገንዘብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ምክንያቱም ውጤቱ የትኛውንም ወገን ለማስደሰት አሊያም ለማስከፋት ተብሎ የተፈፀመ አለመሆኑ ነው። “ለምን?” ከተባለ፤ ውጤቱ ተቋሙ፣ በየደረጃው የሚገኙት አመራሮቹና አባላቱ በህገ መንግስቱ ላይ ያላቸው የፀና አቋምና ታዛዥነት ምክንያት የፈጠረ ስለሆነ ነው።

ይሁንና በእኔ እምነት ስራው ዘመናዊ የውትድርና ሳይንስን ዕውቀት የሚጠይቅ በመሆኑም አንድን ሲቪል ሰው ያለ አንዳች የውትድርና ክህሎትና ብቃት ሻለቃ ወይም ኮሎኔል አሊያም ብርጋዲየር ጄኔራል አድርጎ ሰራዊትን እንዲመራ መሾም አይቻልም። ምንም እንኳን ስለ ውትድርና ሙያ እውቀቱ ባይኖረኝም፤ እንዲያው ከራሴ እሳቤ ተነስቼ ሁኔታውን ስመለከተው ይህ ቢደረግ በሰራዊቱ የግዳጅ አፈፃፀም ላይ የራሱን ከፍተኛ አሉታዊ ጫና ማሳረፉ አይቀርም። ይህም በሀገር ሉዓላዊነት ላይ ሊፈጥር የሚችለው አደጋ አሌ የሚባል አይደለም። ፅንፈኞቹ ግን ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር የሚሹ የሀገራችንን ጠላቶች አጀንዳ የሚያራምዱ በመሆናቸው እየደጋገመሙ ይህን የውሸት ዘር በየማህበራዊ ሚዲያው ላይ ለመዘራት ይጥራሉ። “ላም ባልዋለበት…” እንደሚባለው፤ ሰራዊቱን ሆን ብሎ “የኣግዓዚ ጦር” እያሉ በመጥራት አጀንዳ ፈጠራ ውስጥ ገብተዋል።

የፅንፈኛው ኃይል ሰራዊቱን ጥላሸት በመቀባት ህዘባዊ አመኔታን እንዲያጣ የማድረግ ተግባሩ በዚህ ብቻ የተገደበ አይደለም። በሌለ ቁመናው “የኣግዓዚ ጦር” እያለ ከመጥራት ባሻገር በየማህበራዊ ሚዲያው ስሙን ሲያጠለሽ ከርሟል። የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተፈጠረ ሁከት ምክንያት ሰራዊቱ ህገ መንግስቱ በሚፈቅድለትና በታዘዘው መሰረት በአንዳንድ ህገ ወጥ ተግባር ላይ በተሰለፉ አጥፊ ወጣቶችን በህግ ጥላ ስር ለማዋል ሲንቀሳቀስ ሆን ብሎ “አፋቸው የማይሰማ የኣግዓዚ ጦር አባላት” እያለ ሰራዊቱን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት ተንቀሳቅሷል።

እንዲህ ዓይነቱ ጥላሸት የመቀባት ተግባር ከመሰንበቻውም ቃል በቃል ሲደገምም ኣዳምጫለሁ። በቆቦና በወልዲያ ሆን ተብለው በተቀነባበሩ ግጭቶች ሳቢያ “አፋቸው የማይሰማ” እየተባለ ሲነገር ነበር። ይህም ፅንፈኛው ኃይል የሚነዛው ፕሮፖጋንዳ ሆን ተብሎ የሚደጋገም የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ደሴት ነው። መከላከያ የፌዴራል ተቋም እንደመሆኑ መጠን፤ ቋንቋውም በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠው አማርኛ ነው። በሌላ ቋንቋ የሚሰራ አይደለም። እንግዲህ ፅንፈኛው ኃይል ሰራዊቱን “አፉ አይሰማም” እያለ ስሙን ለማጠልሸት የሚሞክረው ይህን ፀሐይ የሞቀውን የአደባባይ እውነታ በመካድ ነው።

እንደ ፌስ ቡክ ዓይነት የትስስር መረቦችን በመጠቀም በሌላ ሀገር ዜጋ ውስጥ በተለያዩ ጉዳዩች የሞቱና ከእኛ ጋር በመልክ የሚመሳሰሉ ግለሰቦችን ፎቶ ከኢንተርኔት ፈልጎ በመውሰድ “በኣግዓዚ ጦር የተገደሉ” የሚል ታፔላ በመለጠፍ ህዝቡን ለማደናገር ይሞክራል። እንዲሁም ከዚሁ ኢንተርኔት ላይ የተለያዩ ምስሎችን ፈልጎ ፊቱ የማይታይና በጥይት የተመታ ግለሰብን በማሳየት “የኣግዓዚ ጦር የገደለው” እያለ ህዝቡ በሰራዊቱ ላይ የተለየ ምስል እንዲይዝ እያደረገ ነው።

ምን ይህ ብቻ። በሰማይ ላይ የሚጓዝ፣ ቦታው የትና መቼ እንደሆነ እንኳን የማይለይ የሄሊኮፍተር ፎቶን አሁንም ከአንድ የኢንተርኔት ጋዜጣ ላይ በመሰድ “ኣግዓዚ ጦር የቆቦን ከተማ ህዝብ ሲደበድብ” የሚል እጅግ አስገራሚ ልቦለድን ሲያቀናብር ሰንብቷል። አሁንም የ“በሬ ወለደ” ድርሰቱን በተለያዩ መንገዶች እያከናወነ ነው። በእኔ እምነት የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ የሆነው የህበረተሰብ ክፍል እንዲህ ዓይነቶቹን ከነባራዊው እውነታ የራቁ የፈጠራ ዜናዎችን መለየት ያለበት ይመስለኛል።    

እንደ አውነቱ ከሆነ የእነ “ኣግዓዚ”ን ህዝባዊ ወገንተኝነት ፈለግ ተከትሎ በህብረ ብሔራዊነት የተዋቀረው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ከአፈጣጠሩ ጀምሮ በህዝባዊ አመለካከት የደረጀ፣ ከራሱ በላይ ለህዝብና ለሀገር ቅድሚያ የሚሰጥ፣ የተሟላ ወታደራዊ ስብዕና ያለውና በዲሲፕሊን የታነፀ ነው።   

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በሀገራችንና በቀጣናው ህዝቦች እየተደገፈ ዛሬ ለደረሰበት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት የበቃ እንጂ፤ መቼም ቢሆን ህዝብን እንደ ጠላት ፈርጆ የማያውቅ ኃይል ነው። ቀዳሚ እሴቱም “ከምንም በላይ ለህዝብና ለሀገር” ብሎ የተሰለፈ ነው። ይህ ከሀዝብ ጋር ሆኖ ግዳጁን የተወጣና በመወጣት ላይ የህዝብ ወገን መልሶ ወደ ህዝብ ላይ ይተኩሳል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል።

ርግጥ በማንኛውም ሙያዊ ስራ ላይ በግለሰብ ደረጃ ህፀፆች ሊኖሩ ይችላሉ። የሰራዊቱ አባላት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡና ምናልባትም ግለሰባዊ ባህሪ በተልዕኮ ላይ ሊንፀባረቅ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ምንም ሊባል በሚችል ደረጃ የሚገለፁ ብቻ ሳይሆኑ፤ በተቋማዊ አቅም ግንባታ ስራዎች እየተፈቱ የመጡ ናቸው። ይህም በአሁኑ ወቅት ሰራዊቱ ህይወቱንና አካሉን ለህዝቦች ሁለንተናዊ መብቶች ሲል መስዕዋት እንዲያደርግ አስችሎታል። እናም በእኔ እምነት በዚህ ልዩ የሆነ የሀገራችን ውትድርና ባህሪ የታነፀ ሰራዊት ሊሆን የሚችለው የህዝብ አለኝታ ብቻ ነው።    

የኢፌዴሪ ሰራዊት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለተለያዩ ሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ ተልዕኮዎች ሲሰማራ ሁሉንም ተልዕኮዎቹን የሚወጣው የህዝቦችን ተጠቃሚነት ማዕከል አድርጎ ነው። ሰራዊቱ በህዝባዊ ወገንተኝነት እሴቱ እየተመራ ህዝብንና ሀገርን የሚጠቅም ስራ የሚያከናውን እንጂ፤ ፅንፈኞች እንደሚያስወሩት በየአካባቢው ማህበረሰቦች የጋራ መስተጋብሮች ውስጥ በሚፈጠሩ ችግሮችን እየተከተለ ጣልቃ የሚገባ አይደለም።

የሰራዊቱ አመጣጥም ይሁን ላለፉት 23 ዓመታት የተገነባበት አግባብ ይህን የፅንፈኞችን የቅንፈት አጀንዳ የሚያሳይ አይደለም። የአገራችን መከላከያ ሰራዊት እንኳንስ በሀገር ውስጥ ቀርቶ በውጭ ሀገርም ቢሆን የህዝቦችን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ በፍፁም ህዝባዊ መንፈስ ተግባሩን የተወጣና በመወጣት ላይ የሚገኝ ከህዝብ አብራክ የተገኘ ኃይል ነው።

በራሱ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ “ሲቪሎችን አክብር፤ በህዝብ ለተመረጡ ባለስልጣናት ተገዥ ሁን” በሚል የህዝባዊነት መገለጫዎች ያሉት ኃይል፤ ፅንፈኞቹ የፈጠራ ወሬ ህዝብን ሊተናኮል አይችልም። ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ታዛዥና ተገዥ እንዲሁም የደህንነታቸው ጠባቂ ይሆናል እንጂ፤ ለተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል የሚታገል ኃይል አይደለም። ፈፅሞ ሊሆንም አይችልም። የሰራዊቱ አስተሳሰብ ከዚህ የዘለለና ሁሉንም ሀዝብ በእኩልነት የሚመለከት ነው። እንዲያውም ዛሬ የሰራዊታችን አጀንዳ መላውን የሀገራችንን ህዝቦች ከማገልገል ባለፈ፤ የቀጣናው የሰላም አምባሳደር ሆኖ መስራት ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ዛሬ ከአፍሪካ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ቀዳሚዋ ሀገር እንድትሆን አድርጓታል። ሰራዊቱ በየተሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በፍፁም ህዝባዊ አሰራሩ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያምነው ነው። ይህም ፅንፈኛው በሚቀምረው “የኣግዓዚ ጦር” የሚባል የልቦለድ ድርሰት ለባዕዳን በሚላላከው ኃይል የፈጠራ አዕምሮ ውስጥ እንጂ በሀገራችን የሌለ መሆኑን አንድ ማሳያ ይመስለኛል።

ርግጥ በሀገር ውስጥ ሰራዊቱ በፅኑ ህገ መንግሥታዊ እምነቱ፣ በዓላማ ፅናቱና በማይነጥፍ ጀግንነቱ በተደጋጋሚ ብቃቱን አሳይቷል። የሀገሩን ዳር ድንበር በደምና በአጥንቱ አስከብሯል። ፀረ ሰላምና ፀረ ልማት ኃይሎችን በመደምሰስ ለልማቱ አስተማማኝ ሰላም ያሰፈነ ኃይል ነው። ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከማናቸውም የውጭና የውስጥ ፀረ-ሰላም ኃይሎችና አሸባሪዎች በመከላከል ኢትዮጵያ ውስጥ ሊከሰቱና የተከሰቱ ተጨባጭ አደጋዎችን ማስቀረት ችሏል።

ይህ የሰራዊቱ ሁለንተናዊ የማድረግ አቅም (Doing Capacity) የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ጠላቶች የሆኑ ኃይሎች አጀንዳ አስተላላፊ ቱቦዎች በመሆን ለሚሰሩት ፅንፈኞች አልተመቻቸውም። ሊመቻቸውም አይችልም። እናም የዚህን ህዝባዊ ወገንተኛ ኃይል ስም ለማጥፋት በሌለ ግብሩ “የኣግዓዚ ጦር” ሲሉ ቢጠሩት ምንም የሚደንቅ አይደለም። የሰራዊቱ ተልዕኮ አጀንዳ አስተላላፊ ቱቦዋቸው እንዳይሰራ የሚያደርግ ጭምር ስለሆነ ይህን ህዝባዊ ኃይል ከህዝቡ ጋር ለማላተም ያልሆነ ስም እየሰጡ ቢንቀሳቀሱ ማንንም ሊደንቀው ይገባል ብዬ አላስም—ነገርዬው “የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” እንዲሉት ዓይነት ነውና።

ፅንፈኞቹ በፌስ ቡክ ዓለም ያሻቸውን ቢሉም፤ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ግን የአብራካቸው ክፋይ ከሆነው ህዝባዊ ሰራዊት ጋር አብረው እየሰሩ ነው። ሰራዊቱ የተፈጥሮ አደጋ ሲደርስባቸው ቀድሞ የሚደርስ፣ በየተሰማራባቸው አካባቢዎች ሁሉ አቅመ ደካማዎችን የሚደግፍ፣ ማሳቸው ላይ እህል የሚዘራ፣ የሚያርም፣ የሚያጭድና የሚወቃ እንዲሁም በአላስፈላጊ ዝናብ እንዳይጎዳ የሚሰበስብ ኃይል መሆኑ ከህዝቡ የሚሰወር አይደለም። ካለችው አነስተኛ ደመወዝ እየቀነሰ ወላጅ አልባ ህፃናትን እንደ አባት ሆኖ የሚያስተምር፣ ትምህርት ቤቶችን የሚሰራ፣ መዝናኛዎችን የሚገነባ… ህይወቱንና ገንዘቡን ለህዝብ የሚሰጥ እንደሆነ ከባህር ማዶው ፅንፈኛው በስተቀር እዚህ ሀገር ውስጥ ያለው ሰው በሚገባ ያውቃል። ርግጥም እነዚህ መለስተና ማሳያ ክንዋኔዎች መከላከያን እንደ ተቋም ሰራዊቱንም እንደ አባል የሚገልፁ ናቸው። በእነዚህና በሌሎች ለህዝብ የወገነ ባህሪያቱም የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ህዝብ ይወደዋል። እናም በፅንፈኞቹ ልፈፋ የሚታለሉ ጥቂት የዋህ ግለሰቦች ካልሆኑ በስተቀር፤ እንደ “የኣግዓዚ ጦር” ዓይነት በሰራዊቱ ላይ የሚነዙ የፈጠራ ትረካዎችን ህዝቡ አምኖ የሚቀበላቸው አይደሉም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ተበታትና እና ተዳክማ ማየት የሚሹ የውጭ ኃይሎች በፅንፈኞች አማካኝነት በቀዳሚነት እያራመዱ ያሉት አጀንዳ፤ ተግባራቸውን ሊቀለብስ የሚችለውን መከላከያ ሰራዊት ከህዝቡ ጋር በማጋጨት አመኔታ ለማሳጣት እየሰሩ መሆኑን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በሚገባ ስለሚገነዘበው ነው።  

    

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy