Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እስከመቼ ይሆን . . . ?

0 259

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እስከመቼ ይሆን . . . ?

ዮናስ

ብላቴን ጌታ ፀጋዬ ገብረመድህን በ”እሳት ወይ አበባ” የስነግጥም መድበሉ ውስጥ በተካተተው ዘመን ተሻጋሪ “አዋሽ” ግጥሙ “እስከመቼ ይሆን አባይ?” ይላል የኢትዮጵያዊው አዋሽ ወንዝ ስራ ላይ ያለመዋሉ ጉዳይ መጨረሻው የት እንደሆን ሲጠይቅ፤ ፀፅቶን እንጠቀምበት ዘንድም ሲያነቃን። እኛም ዛሬ፣ የሎሬት ፀጋዬን ያህል ድምፅ ባይኖረውም “እስከመቼ ይሆን . . . ?” ልንል ወደድን። ይህን “እስከመቼ . . .?” እዚህ እናንጎራጉር ዘንድ ግድ ያለን የወቅቱ ጉዳይ ትንሽ ግራ ገብ ቢጤ ቢሆንብን ነውና እንደሚቀጥለው እናየዋለን።

 

“እስከመቼ . . .?” ሲባል ጉዳዩ ቀልድ ይመስላል፤ ግን ቀልድ መስሎ ያለንበትን ደረጃ፤ እየሄድን ያለንበትን መንገድ የሚያሳይ አደገኛ ተረብ ነው። በተረቡ ውስጥ ያለውን ቁም ነገር ላለመጠራጠር የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ያደረገው የግምገማ ውጤት አስረጅ ነው። ተረቡን እናቆየውና የተረቡን አደገኛነት ወደሚያጠይቀው የግምገማ ውጤት እንሻገር።

 

ለመላው የአገራችን ህዝቦች ግልፅ እንደሚሆነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርከት ባሉ የአገራችን አካባቢዎች ሰላምና መረጋግት እየደፈረሰ ሁከት የለት ተለት ክሰተት እየሆነ መጥቷል፡፡ በክልሎችም ሆነ በክልሎች መካከል በልዩ ልዩ ሰበቦች የሚከሰተው የሰላም መደፍረስ ለዜጎቻችን አሳዛኝ ሞት መበራከትና መቁሰል እንዲሁም ከባድ መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡ በተጨማሪም ከፍተኛ የንብረት ውድመትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መጓታት አስከትሏል፡፡ ይህ ለረጅም አመታት በሰላም በኖረችው አገር ውስጥ የስጋት መንፈስና ጭንቀት ፈጥሯል፡፡ በየቦታው እየተነሱ ያሉ ግጭቶች ከሰው ሞትና ከንብረት ውድመት በዘለለ የሃገራዊ ሕልውናችንን ብቻ ሳይሆን ራሳችንንም ለጥፋት የዳረጉበት ሁኔታ ከመኖሩም በላይ ለውጭ ጥቃት ተጋላጭነታችንን የመጨመር ውጤት አስከትለዋል፡፡ ይህም በአጭር ቃል የመበልፀግ ተስፋና የሐገራዊ ሰላም መናጋት የተፋጠጡበት ሁኔታ ላይ እንድንገኝ አድርጎናል፡፡

 

የመንግስትም ሆነ የድርጅት አመራሩ ዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ በመገንባትና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር እየተገባው ስለ ኪራይ ሰብሳቢነት ፍላጎቱ የህዝብ የተደራጀ ሲቪል እንቅስቃሴ እንዳይጠናከር አድርጓል፡፡ በአገራችን ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲ ዋስትና የሚኖረው ከአዋጅ አልፎ ህዝብ በተደራጀና ንቁ አኳኋን ሲሳተፍና ሲጠቀምበት ቢሆንም በዚህ ረገድ የተደረገው እንቅስቃሴ የሲቪል ማህበረሰቡን ተሳትፎ መሆን በሚገባው ደረጀ ከፍ ለማድረግ ያስቻለ እንዳልሆነም በመሪ ድርጅቱ ግምገማ ተመልክቷል፡፡  

 

ልክ እንደዴሞክራሲው ሁሉ በአገራችን የህልውና ጥያቄ የሆነውን መልካም አስተዳደርን የማስፈን እንቅስቃሴው በአመራር ድክመት ምክንያት ለበረካታ ችግሮች እንደተጋለጠ ስራ አስፈፃሚ ኮማቴው አረጋግጧል፡፡ በዚህ ረገድ የህዝቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማስፋት፣ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የግልፅነትና የተጠያቂነት አሰራርን ለማንገስና ውጤታማና ቀልጣፋ አስተዳዳርን ለመገንባት እና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት የተደረጉ ጥረቶች ባብዛኛው መክነዋል፡፡ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አስፈፃሚ እና ፈጻሚ አካላት በቅን ልቦናና መንግስታዊ መመሪያዎችን በተከተለ አኳኋን ህዝቡን የሚያገለግሉና ተሳትፎና ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡበት እድል ተመናምኗል፡፡ በዚህ የተነሳ ከፍተኛ የህዝብ ምሬት ተፈጥሯል፡፡ ስራ አስፈፃሚው ይህ ችግር ከምንም ነገር በላይ በከፍተኛው አመራር ደረጃ በሚታይ ጉድለት ምክንያት የተፈጠረና የተባበሰ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡

 

የህግ የበላይነት የማስፈን ድክመት በመታየቱ በሙስናም ሆነ በሌሎች ጥፋቶች ውስጥ የተዘፈቁ ግለሰቦችን በወቅቱ ህጋዊና አስተማሪ በሆነ መንገድ መጠየቅ ሳይቻል ቆይቷል፡፡ ዜጎች በህገመንግስቱ ዋስትና ያገኙ መብቶቻቸውን የሚጥሱ ሰዎችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ መሆን በሚገባው ደረጃ ሳይፈፀም ቆይቷል፡፡ በተጨማሪም መንግስት የህዝብና የአገር ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በነደፋቸው ፕሮጀክቶት ዙሪያ የሚታዩ የአፈፅፀምና የስነምግባር ችግሮችን አስተማማኝና ውጤታማ በሆነ መንገድ የማረምና የማስተካከል ጉድለት ታይቷል፡፡ በዚህ የተነሳ አገራችንን በሁሉም መስክ ተወዳዳሪ ሊያደርጉ የህዝቡን ተጠቃሚነት ሊያሰፉ የሚችሉ ፕሮጀክቶች፣ የጊዜ፣ የዋጋ ንረትና የሃብት ብክነት የሚታይባቸው ሆነዋል፡፡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው እነዚህ የመልካም አስተዳዳር ችግሮች ህዝብና አገርን ያልተገባ ዋጋ የሚያስከፍሉ እንደሆኑ በመገንዘብ በአፋጣኝ እንዲስተካከሉ ማድረግ እንደሚገባ አምኖበታል፡፡ በዚህ ረገድ ይህንን የመልካም አስተዳደር ችግር በተግባር ማቃለል ሲገባ ባጉል ተስፋና በባዶ ቃልኪዳን የመሸንገል ህዝበኛ አዝማሚያዎች በጥብቅ መመከት እንዳለባቸው ወስኗል፡፡ ያም ሆኖ ይህ ውሳኔ በቀላሉ ሊስተካከሉ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ እንኳን በተግባር ሊረጋገጥ አለመቻሉ ነው ተረብ መሰል የሆነው አደገኛ ቁም ነገር ከህዝቡ ዘንድ የተሰማው።

 

የተረቡ መነሻ መንግስት የዋጋ መናርን ለማረጋጋት እና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ለዝቅተኛው ማህበረሰብ በድጎማ የሚያከፋፍለው ስኳርና ዘይት ነው። ስኳርና ዘይት እንዲያከፋፍሉ ሃላፊነት የወሰዱ የሸማቾች ሰራተኞችን የተመለከተው የመልካም አስተዳደር እጦት የወለደው ዱላ በተረብ መልክ የተወረወረው ወደ ገዢው ፓርቲ ነው። ስኳር አከፋፋዮቹ በእርግጥ ለፍትሃዊነት ቢመስልም ዘመናዊ አሰራር ያጡ ይመስል አንድ ጊዜ ሄዶ የወሰደን ተጠቃሚ የወሰደበትን ኩፖን በፋስትነር መብሻ ይበሱታል አሉ። ታዲያ ስለፍትሃዊነት በሚል እንዲህ የሚያደርጉቱ ሰራተኞች ከተጠቃሚዎቹ ከ2 ኪሎ ስኳር እና 3 ሌትር ዘይት በላይ ከደላሎች ጋር መስጥረው የሚመዘብሩትን የሚያውቁት ዜጎች እንዲህ አሉ አሉ፤ “ኢህአዴግ ለ2 ኪሎ ስኳር መታወቂያችንን ከበሳ ቂቤ ቢሰጠን ኖሮማ ጆሯችንን ይበሳው በነበር”። ይህ ቀላል ነገር አይደለም የእንዲህ አይነት ጭቆና ተደማምሮ ነው የህዝብን ልብ የሚያሸፍተው።

 

ከሰላም ጋር ተያይዞ በአንድ ሬዲዮ ላይ በተነሳ የቀጥታ ስልክ ውይይት ላይ ደግሞ አንዲቷ እንዲህ አለች፤ “ስኳርና ዘይት ከሸማቾች ሊገዙ የሄዱ አቅመ ደካሞችና ሽማግሌዎች ጸሃይ ላይ መንቃቃት ሳያንሳቸው፤ ዝርዝር አምጣ/አምጪ ተብለው በነዚሁ ሰራተኞች ሲመናጨቁ መመልከት ተስፋ ያስቆርጣል”። እውነት ነው እንዲህ ትናንሽ የሆኑ በደንብ አስከባሪ አካላት ለአንዱ ተፈቅደው ለአንዱ ተመሳሳይ ጉዳይ የሚከለከሉ፤ የስኳር እጥረት ሳይኖር ሰውን ማሰቃየት በእርግጥም ተስፋ ያስቆርጣል።

 

ሸቀጦች በስውር እጅ በኮንትሮባንድ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ በውድ ዋጋ እየተቸበቸቡ እና ህዝቡን ክፉኛ እያማረሩት ነው። ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በሦስት ካሚዮኖች ተጭኖ ሊያልፍ ሲል የተያዘውን ስኳርና ዘይት አስመልክቶ የክልሉ ቴሌቪዥን ያሰራጨው ዘገባ  የዚሁ ማሳያ ነው። አንድ አድማጭም እንዲህ ብለዋል፣ በዚያው ሰላምን አጀንዳው ባደረገው የሬዲዮ ውይይት። “ከአዲስ አበባ በየቀኑ የሚገባው ስኳርና ዘይት እውነት ኬላ ስለሌለ ፍተሻ ስለሌለ ይሆን?”ም ሲል ይጠይቃል፤ በእርግጥ ህዝቡም ይህን መሰሉን ተግባር አይቶ እንዳላየ ከማለፍ ይልቅ ማጋለጥ ቢጠበቅበትም፤ ይህን መሰሉን የአገር ውስጥ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የገቢዎች ሚኒስቴር ምን እየሰራ ነው? የሚለው ግን ከላይ ከተመለከተው የመሪ ድርጅቱ የግምገማ ውጤትና የውሳኔ አቅጣጫ አኳያ የሚያሳስብ ነው።

ጥራታቸውን ያልጠበቁና ከስታንዳርድ በታች የሆኑ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡና ለዚህም ለኬላ ጠባቂዎች ገንዘብ እየተከፈለ እንዲታለፍ ሲደረግ በየደረጃው ያለው የአመራር እጅ እንደሚኖርበት አያጠራጥርም። ለዚህ ደግሞ የንግዱ ዘርፍ ለኪራይ ሰብሳቢነት ካለው ተጋላጭነት አንፃር የህግ ተጠያቂነት ስርዓቱ ክፍተት ያለበት መሆኑ የመጀመሪያው ምክንያት እንደሚሆን በተመሳሳይ አያጠራጥርም፡፡ የዚህ መገለጫ የሚሆኑ ነጥቦችን ስናነሳ አመራሩ አጥፍቶ ሲገኝ ተጠያቂ የሚሆንበት አሰራር ጠንካራና ግልጽ አለመሆኑ የመጀመሪያው ነው፡፡ አመራሩ አጥፍቶ ሲገኝ በአብዛኛው አዛውሮ የማሰራት፣ መደብ የመቀየር፣ የተቋም ለውጥ የማድረግ፣ በኔትወርክ ሹመት የመስጠት፣ አንዳንድ ጊዜም ወደ ዞን እና ክልል ድረስ በሃላፊነትም ጭምር የመመደብ እንጂ ባጠፋው ልክ እንዲጠየቅ የሚደረግበት አቅጣጫ ቢቀመጥም፤ ጊዜ ሳያስፈልግ ተግባራዊ ማድረግ ከሚገባቸው አቅጣጫዎች አንዱ ቢሆንም አለመደረጉ የችግሩ ዋነኛ ምክንያት ነውና እስከመቼ ቢያሰኘን ሊገርም አይገባም፡፡

ከአሰራር ግልፀኝነት ጋር በተያያዘ የህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በሁሉም ላይ እኩል ተፈጻሚ ያለመሆን ሁኔታም አንዱ ለመልካም አስተዳደር መስፈን እንቅፋት እንደሆነ በመንግስት ጥናቶች መለየቱ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ ለምሳሌ  ተመሳሳይ የንግድ ዘርፍና ቦታ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች የተወሰኑት ፍቃድ እንዲያወጡ ሲገደዱ ሌሎች ግን ይታለፋሉ፤ እንዲሁም ቋሚ አድራሻ ለሌለው የንግድ ፈቃድ የማይሰጥ ቢሆንም በቀበሌ ደረጃ መደብ ተሰጥቷቸው ያለንግድ ፈቃድ የሚነግዱ መኖራቸው የአደባባይ ሃቅ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የንግድ ፈቃድ ማደሻ ጊዜው ያለፈበትን ንግድ ፈቃድ ያለቅጣት የማደስ አሰራሮችም እንዳሉም ይታወቃል፡፡ ከላይ በተገለፁት የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶችና ድርጊቶች ምክንያት ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ ማበርከት የሚችለውን ከፍተኛ ድርሻ በአግባቡ እንዳይወጣና የፍትሀዊነትና የተጠያቂነት አሰራር እንዳይሰፍን፣ በዚህም ምክንያት ዜጎች በመንግስት ተቋማት ላይ እንዲያማርሩ በር የሚከፍት መሆኑና ከልማቱ እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ በማድረግ ብልሹ አሰራሮች ይበልጥ እየተስፋፉ እንዲሄዱ እያደረገ ነው። በንግዱ ዘርፍ  የሚፈፀሙ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት ውስጥ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አስፈጻሚ መዋቅሮችና የበላይ ሃላፊዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ እንደሚሳተፉ መንግስት በየደረጃው አድርጌዋለሁ ባላቸው ጥናቶች ተረጋግጧል፡፡ ለምሳሌ ከጥቅም ትስስር ጋር በተያያዘ አመራሩ የተቀመጠውን መሥፈርት የሚያሟሉ ነጋዴዎች እያሉ ለማያሟሉ ነጋዴዎች ጅምላ ስኳርና ዘይት የማከፋፈል ፈቃድ ያለውድድር መስጠት፣ በትውውቅ ንግድ ፍቃድ መስጠት፣ በህገወጥነት የታሸጉ የንግድ ድርጅቶችን አመራሩ ጣልቃ በመግባት የማስከፈትና ያሸገው ባለሙያ ላይ እርምጃ የመውሰድና መስፈርቶችን ለማያሟሉ ነጋዴዎች የብቃት ማረጋገጫ መስጠት ዋና ዋና የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫዎች ስለመሆናቸው መንግስት አድርጌያቸዋለሁ ባላቸው ጥናቶቹ አመላክቷል፡፡

እያንዳንዱ ዜጋ ከአገሩ ሀብት ፍትሐዊ የሆነ ድርሻ፣ ተመጣጣኝ የሆኑ የሥራ ዕድሎችና ተጠቃሚነት ሲኖሩት በሃገሪቱ ማኅበራዊ ፍትሕ መረጋገጡ ይታወቃል፡፡ ሃገራችን የምትከተለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ዜጎች በሀብት ክፍፍል፣ እኩል የሥራ እድል ተጠቃሚነት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በመኖሪያ ቤት እና በመሳሰሉት በጥረታቸው መጠን ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባቸው ያምናል፡፡ ይህ የመስመሩ እምነት የሚለካው ደግሞ የመንግሥት አሠራር ግልጽና አሳታፊ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በዜጎች መካከል ልዩነት የሚፈጠረውና ተመጣጣኝ ያልሆነ የኑሮ ዘይቤ የሚስተዋለው፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለበት ሥርዓት ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን የተዛባ አሠራር ማስወገድ የሚቻለው ደግሞ ማኅበራዊ ፍትሕን በማንገሥ ብቻ ነው፡፡ ካልሆነ ግን ስኳርና ዘይት እስከመቼ ባስባሉት ህዝብ ላይ ሌላም እየተጨመረ ሰላማችን መታወኩ አይቀሬ ይሆናልና መንግስት ህዝቡን ዛሬውኑ ከ”እስከመቼ ቁዘማ?” ሊያወጣው ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy