እውነት አሁን ይህ ምክንያት ነው?
ዳዊት ምትኩ
አገራችን የምትከተለው የፌዴራል ሥርዓት የኢትዮጵያን የቆዩ ችግሮች እልባት የሚሰጥ እንጂ በአሁኑ ወቅት እየታዩ ላሉት ግጭቶች ምክንያት ሊሆን የሚችል አይደለም። ፅንፈኞች ግን ይህን ምክንያት ያልሆነ ምክንያት በማጋጋል የስርዓቱ ችግር አድርገው ለማቅረብ ይሞክራሉ።
ነባራዊ እውነታውም ይሁን የመጣንባቸው መንገዶች ይህን የጽንፈኞቹን ምክንያት የሚያሳዩ አይደሉም። ምክንያቱም ባለፉት ዓመታት ለአገራችን ፌዴራላዊ ሥርዓትን መከተል የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ለመረዳት የሚከብድ ስላለሆነ ነው።
እንደሚታወቀው ሁሉ በአገራችን እውን በመሆን ላይ የሚገኘው ፌዴራላዊ የመንግስት ሥርዓት አወቃቀር ለአገራችንና ለህዝባችን አንድነት፣ ሠላምና ዕድገት መጠናከር ወሳኝ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። የዚህ አዲስ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በተጨባጭ ተፈትኖ ፍቱንነቱ የተረጋገጠ ነው። በመገንባት ላይ የሚገኘው ፌዴራላዊ ሥርዓት በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ ያስወገደና በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ ለተመሰረተ የህዝቦች አንድነት ዘላቂ ዋስትናን ማስገኘት የቻለም ነው።
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ረጅሙንና አስቸጋሪውን የፀረ-ደርግ የትግል ምዕራፍን በድል አድራጊነት በቋጩ ማግስት በጋራ ተወያይተውና አምነው ዕውን እንዲሆን ያደረጉት ህገ- መንግስት የዘመናት ጥያቄዎቻቸውን ሙሉ ለሙሉ የመለሰ ከመሆኑም ባሻገር፤ በቀጣይ ለሚያካሄዷቸው የጋራ አጀንዳዎች ዘላቂነትና ውጤታማነት ዋስትና የሰጠ ነው።
የሀገራችን ህዝብና ህገ መንግስቱ በብዙ መልኮች እጅግ የጠበቀ ቁርኝት ያላቸው በመሆናቸው፤ የሚያጋጥማቸውን ጊዜያዊ ችግሮች የሚፈቱትም በእርሱው አግባብ ነው። ለዚህ በዋነኝነት የሚጠቀሰው ጉዳይ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የህገ- መንግስቱ ባለቤቶች መሆናቸው ነው። ህዝቡ ህገ- መንግስቱን ያቋቋመ፣ የመንግስትን አወቃቀር የነደፈ ነው። ይህ ባለበት ሁኔታ ውስጥ የጽንፈኛው ፌዴራሊዝሙን የመተቸት አባዜ ግልፅ አይደለም። እናስ እውነት አሁን ይህ ምክንያት ነው? የሚል ጥያቄ ብናነሳ ምላሹ ምክንያት አለመሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም።
እንደሚታወቀው ሁሉ ህገ መንግስቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ስለሆነ፤ ሰነዱን ከማንኛውም አደጋ የመጠበቁ ኃላፊነትም የሁሉም ህዝቦች መሆኑ ነው። ይህ እውነታም የህገ- መንግስቱ ባለቤት የሆኑት ዜጎች በተደራጀ መልኩ ህገ መንግስቱንና የሥርዓቱን ደህንነት መጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው የሚያረጋግጥ ነው።
እንዲሁም ህገ መንግስቱን ከመጠበቅ ባሻገር ተጠቃሚም በመሆኑ የሰነዱ ዋስትና በእያንዳንዱ ዜጋ እጅ ያለ ይመስለኛል። እናም ህገ መንግስቱንም ይሁን ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን መጠበቅ ማለት ዛሬም እንደ ትናንቱ የሚፈጠሩ ጊዜያዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል። ይህም ስርዓቱ የችግሮች መውጫ ቀዳዳ እንጂ ችግር ፈጣሪ አለመሆኑን የሚያሳየን ነው።
እርግጥ የስርዓቱ ምሶሶ በሆነው ህገ መንግስቱ አፈፃፀሞች ላይ ምንም ዓይነት እንከን የለም ማለት አይቻልም። አገራችን ጀማሪ የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አራማጅ መሆኗ፣ ዜጎችም ለእንዲህ ዓይነቱ ስርዓት አዲስ መሆናቸውና ያለው ግንዛቤም ያልዳበረ መሆኑ፣ በአፈፃፀም ረገድም ከአመለካከትና ከአቅም ማነስ ጋር ተያይዞ በህገ መንግስቱ አግባብ ችግሮች በወቅቱ አለመፈታታቸው እንዲሁም በአስፈፃሚዎች ዘንድ ስልጣንን ለህዝቡ ጠቀሜታ ሳይሆን የግል መጠቀሚያ የማድረግ ዝንባሌና ተግባር መኖሩ ለችግሮቹ መንስኤዎች ናቸው ሊባል ይችላል። ይሁን እንጂ ህገ መንግስቱ በራሱ የችግሮች መንስኤ ነው እያልኩ አይደለም። ምክንያቱም ህገ መንግስቱ ምርጥ የሚባሉ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን የያዘና ማናቸውንም ችግር ስልጡን በሆነ መንገድ መፍታት የሚችል ተራማጅ ሰነድ ስለሆነ ነው። ላለፉት 23 ህገ መንግስታዊ ዓመታት አገራችን ውስጥ የታዩት እመርታዎችም የህገ መንግስቱን ችግር ፈቺነት እንጂ የችግር ፈጣሪነትን የሚያሳዩ አይደሉም።
በህገ መንግስቱ መርሆዎች አገራችንና ህዝቦቿ ከራሳቸው አልፈው የአፍሪካ ፖለቲካዊ ድምፅ እስከ መሆን ድረስ ደርሰዋል። በመርሆዎቹ የሀገራችን የድህነትና ኋላቀርነት ገፅታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊለወጥ ችሏል። የህዝብን ተጠቃሚነት በየደረጃው ማረጋገጥ የቻለ የልማት ተምሳሌት ሆነንም ለአፍሪካውያን ልምዳችንን እስከማካፈል ድረስ ያደረሰን ነው። በመርሆዎቹ የህዝቡ ተቻችሎና ተከባብሮ በጋራ የመኖር እሴቶች እየተገነቡ ዛሬ ላይ ደርሰዋል።
እነዚህ ሁሉ ተግባራት የተከናወኑት በህገ-መንግስቱ ቁልፍ መፍትሔ ሰጪነት ነው። ባለፉት 23 ዓመታት ህገ መንግሰታዊ ስርዓቱ የህልውናችን መሰረት ሆኖ ዛሬ ላይ አድርሶናል። ነገም ይህን መሰረት በማስፋት ውጤት እንደሚያስገኝልን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርዓቱ እውን ከሆነ ወዲህ አገራችን ትክክለኛ የዕድገት አቅጣጫ ይዛ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ በድል ለመረማመድ በቅታለች። የብሔሮችና ብሔረሰቦች እስር ቤት እስከመባል ደርሳ የነበረችው ሀገራችን፤ የህዝቦቿ መብት የተረጋገጠባት፣ የዕድገትና ልማት ብሩህ ተስፋን የሰነቀች፣ የእኩልነትና የፍትህ አምባ ለመሆን ችላለች። ይህ ፌዴራሊዝም የህልውና መሰረታችን መሆኑ አንዱ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል። ታዲያ ፅንፈኛው ኃይል ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በችግነት ለማንሳት መሞከሩ ምን ዓይነት ተቃውሞ ይሆን?—በእኔ እምነት ከጭፍን ሙግት ለይቼ አላየውም።
ምንም ተባለ ምን ፌዴራላዊ ሥርዓቱ የህዝቦችን ጠንካራ አንድነት ይበልጥ ያጠናከረ፣ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ መፍጠር የቻለ፣ የዜጎችን ተጠቃሚነት በየደረጃው እውን ማድረግ የቻለ ነው። ይህም የህዝቡ ህልውና በፌዴራሊዝም መሰረት ላይ እየፈካ የሚሄድ መሆኑን ያየሚያረጋግጥ ነው።
ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱ በሀገራችን ታሪክ በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ እንዲፈጠርም ያደረገ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ ከደርግ ውድቀት ማግስት በኋላ የተረጋጋችና ህዝቦቿም አንድ የጋራ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ስርዓት መስርተው እርስ በእርሳቸው እየተከባበሩ በፈጠሩት ፈጣን ልማት ተቋዳሽ የሚሆኑበትን ሀገር ለመገንባት ከባድ ትግልን ጠይቋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች ይህን ትግል ተሻግረው በሁሉም መስኮች ተጠቃሚ ሆነዋል። ታዲያ ይህን ሃቅ የማይቀበሉ ፅንፈኞች ትናንትም ነበሩ፣ ዛሬም አሉ። ነገም ይሁን ከነገ በስቲያ መኖራቸውም አይቀርም።
ይህን በህዝቦች መስዕዋትነት የተገኘን ፌዴራላዊ ስርዓት ለመንጠቅ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ዜጎች ማጋለጥና እኩይ ዓላማቸውንም እንዳያስፈፅሙ በንቃት መከታተል አለባቸው። እነዚህ ሃይሎች የሚፈልጉት ምክንያት ያልሆነ ምክንያትን እየደረደሩ ህዝቡ በመስዕዋትነቱ ያገኘውን ድል ለመንጠቅ መሯሯጥ ስለሆነ ሁሉም የሀብረተሰብ ክፍል ሊያወግዛቸው ይገባል።