Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኦ ሰላም!!!

0 332

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኦ ሰላም!!!

                                                              ይልቃል ፍርዱ

ኢሕአዴግ የራሱን ጠንካራና ደካማ ጎኖች እየለየና እያወጣ የተፈጠሩትን ስህተቶችም ለማረም ፈጥኖ ወደስራ የመግባት የካባተ ልምድ ያለው የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡ በዚህም መሰረት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በተጨባጭ የተፈጠሩ ሀገራዊ ችግሮችን በጥልቀት መርምሮ፤ ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱን በመውሰድ ችግሩ የከፍተኛው አመራር መሆኑን አምኖ በመቀበል፤ የተፈጠረውን ችግር በመሰረታዊነት ለማስተካከል ወደስራ ገብቶአል፡፡

ኢሕአዴግ እንደ ግንባር ቢወሰድም ሕብረ ብሔራዊ የሆነ የፓርቲ አደረጃጀት መልክ ነው ያለው፡፡ በዚህ ደረጃ ለተፈጠሩት ችግሮች ሁሉ ኃላፊነቱን በመውሰድ ስሕተቱንም አምኖ በመቀበል መጸጸቱን በመግለጽ ወደተግባር ሲገባ አሁንም ሰፊ የሆነ የሕዝብ እገዛና ትብብር ያስፈልገዋል፡፡ ካለሕዝቡ ከፍተኛ ተሳትፎ የተላለፉትን ውሳኔዎች ወደመሬት ለማውረድና ተግባራዊ ለማድረግ ይከብዳል፤ ስለዚህ የሂደቱ ንቁ ተሳታፊ መሆን ያለበትም ሕዝቡ ነው፡፡   

ብዙዎች የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ራሳቸውን ለመፈተሽ፣ ወደውስጣቸው ለመመልከት፣ ስሕተቶቻቸውን ነቅሰው ለማረምና ብቁ ሁነው ለመገኘት ፈቃደኝነቱም ተነሳሽነቱም የላቸውም፡፡ በዚህ ደረጃ ኢሕአዴግ ራሱን በስፋት ወደውስጥ መመልከት መቻሉ፤ ችግሩን ወደሁለተኛ ወይም ሶስተኛ ወገን ሳያስተላልፍ ኃላፊነቱ የራሱ መሆኑን በግልጽ አምኖ መቀበሉ ሊያስመሰግነው የሚገባ ተግባር ነው፡፡ ይህንን የሚያደርጉ መንግስታትና ፓርቲዎች እስካሁን አልታዩም፡፡ አሁንም ኢሕአዴግ የገጠሙትን ፈተናዎች በድል በመወጣት የበለጠ ሀገራዊ ስራዎችን ለመስራት የሚችል ፓርቲ ነው፡፡

ዋናው ጉዳይ ያለችን አንድና ለሁላችንም የጋራ የሆነች ሀገር እንደመሆኗ መጠን የሚፈጠረውም ችግር ሁሉንም ዜጋ የሚነካ በመሆኑ ችግሮችን ከማባባስ ይልቅ ለችግሮቹ ሰላማዊ መፍትሔ በማስገኘቱ ረገድ ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ ይገባል፡፡ የሀገር ሰላምና መረጋጋት ከሌለ ሕዝብና ልጆቹ  በሰላም ለስራም ሆነ ለትምህርት ወጥተው በሰላም ወደቤታቸው መመለስ ካልቻሉ፤ አርሶ አደሩ ያመረተውን፣ ነጋዴውም ምርቱን መሸጥ ካልቻለ፤ ሕግና ስርአት ካልተከበረ፣ ሰላምና መረጋጋት የለም ማለት መዘዙ ብዙ ነው፡፡

ለአንድ ሀገር ከሰላም በላይ ውድ የሆነ ምንም ነገር የለም፡፡ ሀገራዊ ሰላማችንን መጠበቅ የእለት ተእለት ስራችን ነው ሊሆን የሚገባው፡፡

በሀገር ውስጥ የሚፈጠር ማንኛውም ሁከት/ግጭት በሰላማዊ መንገድ (በውይይት፣ በመነጋገር . . .) ነው መፈታት ያለበት፡፡ እሳቱን የማጥፋት ግጭቶችን በመፍታት ሰላማዊ እልባት የመስጠት ስራ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንጂ ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም፡፡  ሰላሙን የሚያስከብረው ሕዝብ ነው፤ የሰላሙም የሀገሩም ባለቤት ሕዝብ ነው፡፡ የሰላም እጦትና የግጭቶች መዛመት ሀገርን በሙሉ ሊያደፈርስ  ይችላልና ጥንቃቄን ይፈልጋል፡፡

የሀገር ጉዳይ በስሜታዊነት እየተነዱ የፈለገው ይምጣ የሚባልበት አይደለም፡፡ የእርስ በእርስ መባላት፣ መናቆር፣ መጠላለፍ፣ በዘርና በጎሳ ጥላቻ እየተነዱ መጠፋፋት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አይመጥነንም፡፡ ጥንትም የነበሩት አባቶቻችን ተከባብረው፣ ተቻችለው፣ ተጋብተው፣ ተዋልደው፣ ጥላቻን በፍቅር አሸንፈው፣ በክፉውም ሆነ በደግ ቀን አብረው ወንድሜ እህቴ ተባብለው ኖረው ያለፉ ናቸው፡፡

እኛ ልጆቻቸው ደግሞ የበለጠ ተፋቅረንና ተዋደን፤ በከፍተኛ በመስዋእትነት ያስረከቡንን ሀገር ዳር እስከዳር በጋራ ሰላሟንና አንድነትዋን የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃለፊነትና ግዴታ አለብን፡፡ የሀገር ሰላም ሲከበር ሀገር ሰላም ውላ ሰላም ስታድር ነው ልማትና እድገትዋን ልናሳካ የምንችለው፡፡ ለዚህም ነው ደጋግመን ቀዳሚው አጀንዳችን ሰላምና ሰላም ብቻ ነው መሆን ያለበት የምንለው፡፡

የሰላም እጦትና መደፍረስ የበለጠ ተጽእኖ የሚያሳድረው ከማንም በላይ በራሱ በሕዝቡና በልጆቹ ላይ ነው፡፡ ሰላማዊ የእለት ተእለት እንቅስቃሴን፣ ትምሕርትን፣ የንግድ ዝውውርና ግብይትን፣ በሰላም ከቤት ወጥቶ በሰላም መመለስን ሁሉ ከባድና አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ የሌቦች፣ የዘራፊዎች፣ የቀማኞች ኢላማ መሆንን ያስከትላል፡፡ ሕግና ስርአት ካልተከበረ የስርአተ-አልበኞች መጫወቻና መፈንጪያ መሆን፡ የቤትና ንብረት መዘረፍ፣ የነጻነት ማጣት . . . ሁኔታዎች ሁሉ በገሀድ ይከሰታሉ፡፡

አዲስ የተተካው ትውልድ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠረበት ዘመን መጀመሪያ ላይ ከታየው የባድሜ ጦርነት ውጪ በሀገሪቱ ፍጹም ሰላምና መረጋጋት የሰፈነበት፣ ትምሕርቱን ለመማር፣ በአቅሙ የራሱን የግል ስራ ሰርቶ ለመኖር ከቀድሞዎቹ ዘመናት ሁሉ እጅግ የተሻለ እድል ያገኘበት የሰላም ዘመን ሆኖ ነው የቆየው፡፡

የአሁኑ ትውልድ ወጣት አባቶቹ ባለፉበት የፈተናና የመከራ ሕይወት ውስጥ አላለፈም፤ እንደቀደመው ትውልድ ለተለያዩ ጦርነቶችና ፈተናዎች አልተዳረገም፤ በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ውስጥ እንዲሳተፍ አልተጠየቀም፤ ትውልዱ ለሀገሩ ሰላም ዘብ ሆኖ መቆም ያለበትም ለዚህ ነው፡፡

ይሄ ዘመን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አምናና ካቻምና ከተፈጠሩት የውስጥ ግጭቶች ውጪ ፍጹም ሰላም የሰፈነበት ዘመን ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ የቀደመው ትውልድ አንድም በውስጥ የፖለቲካ ትግልና እርስ በእርስ መናቆር፤ ሌላም በሶማሊያና በኤርትራ ጦርነት ውስጥ በመሳተፉ መከራ አንገቱን አስደፍተውት የኖረና ያለፈ ትውልድ ነበር፡፡

የቀደመው ትውልድ በየትኛውም ችግር ውስጥ ተፈትኖ ሲያልፍ ሁሌም ለሀገሩ ሰላምና መረጋጋት አንድነትዋና ሉአላዊነትዋ ተጠብቆ እንድትኖር በማድረግ ረገድ ጸንቶ በመገኘት መከፋፈልን የዘርና የጎሳ ፖለቲካን በመጸየፍ የገዘፈ መስዋእትነት ከፍሎአል፡፡ ይሄንን ጠንካራና ብርቱ የአብሮነት ቅርስ ጠብቀን ዛሬም ሳንለያይ ሳንከፋፍል በጎሳና በዘር ፖለቲካ ሳንባላ የሀገራችንን ሰላም የመጠበቅ ግዴታ የእከሌና የእነእከሌ ሳይባል የመላው ዜጎቿ የጋራ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው፡፡

የውስጥ የፖለቲካ ችግሮች ሁሉ ሊፈቱና እልባት ሊያገኙ የሚገባቸው በመወያየት፣ በመነጋገርና በሰከነ መንፈስ ብቻ ነው፡፡ ሰክኖ ነገሮችን ማስተዋል፣ ከስሜታዊነት መላቀቅ፣ የእይታ አድማስን በማስፋት ትልቅ ሀገራዊ ራእዮችን መመልከት ከሁሉም ወገን ይጠበቃል – በተለይም በዚህ ባሁኑ ወቅት፡፡

የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ችግሮቹን ወደራሱ የወሰደው መፍትሔው ከውስጥ ነው ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡ በቅራኔ ሕግጋት መሰረት ሁልግዜም የእድገትና የአዲስ ነገር መሰረት የሚሆነው የውስጥ ትግል ሲኖር ነው፡፡ ለእድገት መሰረት ነውም ይባልለታል፡፡ በዚህም መሰረት በኢህአዴግ በራሱ ውስጥ የተደረገው ትግል አዲስ ለውጥ ይዞ እንደሚመጣ መጠራጠር አይቻልም፡፡

ብዙዎች የፖለቲካ ድርጅቶች በውስጣቸው የተፈጠረውን የፖለቲካ ልዩነትም ሆነ ስር የሰደደ ችግር ለመፍታት የሚሄዱበት መንገድ ጎራ ለይቶ መበላላት፤ አንጃ መፍጠር፤ እርስ በእርስ እስከ መጠፋፋት የዘለቀ እንደነበር በሀገራችንም ታሪክ ብዙ አይተናል፡፡

እስከ ዛሬ ስናያቸው የኖርናቸው ስርአቶች ችግሮችን ከራስ አኳያ ከመመልከት ይልቅ ወደውጭ ሲገፉ የነበሩ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ኢሕአዴግ አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ችሎአል፡፡ ይህ አዲስ ታሪክ አዲስ ተነሳሽነት ለኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደ ትንሳኤ የሚቆጠር ነው፡፡ በውስጥ የተፈጠሩት ችግሮች የቱንም ያህል የመረሩና የሚጎመዝዙ ቢሆኑም በሰከነ መንፈስ ግልጽ አድርጎ በመወያየት፣ በመደማመጥና በመከባበር የሀገርና የሕዝብ ሰላም እንዳይታወክ ለችግሮቹ ሰላማዊ እልባት ለማስገኘት ቆርጦ ለመስራት መወሰንና ወደተግባር መግባት ትልቅ ታሪካዊ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ተግባር ነው፡፡

ሀገራዊ ሰላምና አንድነታችንን አጥብቀን መጠበቅ ያለብን ለማንም ሲባል አይደለም፡፡ አንድነቱና አብሮነቱ የተሸረሸረ ሀገርና ሕዝብ በቀላሉ ለሀገሪቱ የውጭ ጠላቶች ተጋላጭ በመሆን የሀገሩን ነጻነትና ሕልውና አሳልፎ እስከመስጠት ብሎም እስከመበታተን ስለሚደርስ ነው፡፡ ይህም በታሪክ በተጨባጭ ታይቶአል፡፡    

በሰላም ማጣትና መናጋት በሚፈጠረው ትርምስ የየሀገራቱን የተፈጥሮ ሀብት የውጭ ኃይሎች በፈለጉት መጠን እንዲመዘብሩና እንዲያግዙ የተመቸ በር ይከፈትላቸዋል፡፡ እነሱም የሚፈልጉት ይሄንኑ ነው፡፡ ከሀገራት ሰላም ማጣትና ትርምስ ተጠቃሚ የሚሆኑት የውጭ ኃይሎች ብቻ እንጂ ዜጎች አይደሉም፡፡ የትም አገር ሕዝብ በሰላም መደፍረስና ማጣት ተጠቃሚ ሆኖ አያውቅም፡፡ ለዚህም ነው ከምንም ነገር በፊት ቅድሚያ ተሰጥቶ ሊጠበቅ የሚገባው ነገር ቢኖር የሀገር ሰላም ነው የሚባለው፡፡

ኢሕአዴግ ችግሮችን ውጫዊ በማድረግ መፍትሔ እንደማይመጣ ግልጽ አድርጎአል፡፡ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿን በአግባቡ ለመፍታት ከቻለች የሕዝቡ አብሮነትና አንድነት ከጎለበተ የትኛውም የውጭ ኃይል የመግቢያ ቀዳዳ አያገኝም፡፡ በሀገር ውስጥ ሁከት ለማስነሳት የሚያደርጉት የትኛውም ጥረት አይሳካላቸውም፤ ይህንንም በሚገባ ሊገነዘቡት ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy