Artcles

ከህግ የበላይነት ወዲያ . . . ምን?  

By Admin

February 08, 2018

ከህግ የበላይነት ወዲያ . . . ምን?  

ስሜነህ

 

ሰሞኑን ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሃገር ቀስፎ የያዛትን ውጥረት የሚያረግብ ተስፋ ተሰምቷል፤ አንዳንዱም በተግባር ታይቷል፡፡ የኢሕአዴግ አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በውስጣቸው የነበረውን ፀረ ዴሞክራሲ አስተሳሰብና አሠራር በማስወገድ አገርንና ሕዝብን የሚያስቀድም ዴሞክራሲያዊ አሠራር ለማስፈን በቁርጠኝነት መነሳታቸውን አስታውቀዋል፡፡ በእርግጥ ይህ ዓይነቱ የተስፋ ቃል ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲነገር የነበረ መሆኑ ይታወቃል። አሁንም መጠራጠር ያለ መሆኑ በተመሳሳይ። ግን ደግሞ ካሁን በኋላ ወደ ቀድሞ አላስፈላጊ ድርጊቶች መመለስ አደገኛ መሆኑን ሊቃነ መናብርቱ አፅንኦት መስጠታቸው በበጎ ጎኑ ሊታይ ይገባል፡፡ የአገሪቱን የጠበበ የፖለቲካ ምኅዳር ለማስፋትና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ለማስጀመር፣ በተለያየ ምክንያት የታሰሩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ሌሎችንም  ለመፍታትና በብዙዎች ዘንድ በጭካኔ ድርጊቱ የሚታወቀው ማዕከላዊ የምርመራ ቢሮ ተዘግቶ ሙዚየም እንዲሆን ውሳኔ ላይ መደረሱ በራሱ አንድ ጅማሬ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በዚህ ምክንያት እንኳን አገርም ሕዝብም ተንፈስ እያሉ ነው፡፡ ስለዚሁ የተገቡት ቃሎች ወደመሬት መውረዳቸውም በተመሳሳይ ሊዘነጋ አይገባም። በዚሁ አግባብ የፌደራሉ መንግስት በምህረትና በይቅርታ የፈታቸውን ጨምሮ በክልሎችም ተመሳሳይ እርምጃ በመወሰድ ላይ ይገኛል።

 

በኦሮሚያ ከ2ሺህ በላይ እንዲሁም በደቡብ ክልል በተመሳሳይ የተወሰዱትን እርምጃዎች ትተን የሰሞኑን እንኳ ብንመለከት በአማራ ክልል 598 ተጠርጣሪዎች ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል። ክሳቸው የተቋረጠላቸው ተጠርጣሪዎች 224 ከሰሜን ጎንደር ዞን፣ 176 ከአዊ ዞን፣ 107 ከምዕራብ ጎጃም ዞን፣ 41 ከምስራቅ ጎጃም ዞን፣ 17 ከደቡብ ወሎ ዞን፣ 14 ከኦሮሞ ልዩ ዞን፣ 13 ከደቡብ ጎንደር ዞን፣ 2 ከዋግ ኽምራ ዞን እና 1 ከሰሜን ሸዋ ዞን ነው። የአማራ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ቢሮ ሀላፊ የክልሉ መንግስት ለ2ሺህ 905 ታራሚዎች ይቅርታ እንዳደረገ አስታውቀዋል።

 

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያካሄደውን ግምገማ ተከትሎ አራቱ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በሰጡት መግለጫ ላይ “በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው ወይም ደግሞ ወንጀል በመፈፀም ድርጊት ተጠርጥረው በአቃቤ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በምህረት ህግና ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ እንዲፈቱ ይደረጋል።” መባሉ ይታወሳል።

 

ይህን ተከትሎም የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የፍርድ ሂደታቸው በመታየት ላይ የሚገኙ 528 ተጠርጣሪዎች ክስ በመጀመሪያ ዙር መቋረጡን መግለፁ ይታወቃል። ከተጠርጣሪዎቹ መካከልም 115ቱ በፌደራል ደረጃ ሲሆኑ፤ ሌሎቹ 413 ደግሞ ከደቡብ ክልል የቀረቡ ናቸው። በተመሳሳይ ኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባለፈው ሳምንት ለ2ሺህ 345 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ አድርጓል።

 

ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግር መንስዔ የፖለቲካ ኃይሎች ትግል ከሰላማዊና ከሕጋዊ መድረክ ውጪ መሆኑ ነው፡፡ ለዚህም የመጀመሪያው ተጠያቂ እኔ ነኝ ሲል ሌሎቹ ፓርቲዎች ነጻ ናቸው ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ኢሕአዴግ ስለ ‹‹የሕግ የበላይነት›› ሲያወራና ስለሕግ ማስከበር ሲናገር ከዚህ በተቃራኒ ነገሩን ለማኮላሸት የሚሹ ሃይሎች ዛሬም ከዚሁ በሽታቸው የተላቀቁ አይመስልም። የጨዋታውን ሕግ ያፈረሰው ኢሕአዴግ ራሱ እንደ ፓርቲ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት ለመለወጥ፣ ይህም የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር ይዞ ለመገኘት አለመቻሉ መሆኑን አምኖ ለለውጥ እራሱን አመቻችቷል፡፡

 

ኢሕአዴግ የቱንም ያህል ተሃድሶ ቢያደርግ ተቃዋሚዎቹ  ከሰላማዊና ከሕጋዊ መድረክ ውጪ እስከሆኑ ድረስ ለአገሪቱ የፖለቲካ ሰላም ፈተና መሆኑ አይቀርም፡፡ በድርድርና በዕርቅ ተቀራርበው በፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ለሕዝቦች አዲስ ሕይወት ሊበጁ የሚችሉ ነገሮችን ማምጣት የሁለቱም ግዴታ ነው። መቀራረብ የሚቻልበትን መንገድ የመፈለግ ተግባር የኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚዎችም ነው። የሽብርተኝነትና የትርምስ ማጥ ባልደረቀበት አካባቢ ለምትገኝና ከማዶዋ የእነ የመንና የእነ ሶሪያን አወዳደቅ እየተመለከተች ላለች ሃገር የኢህአዴግን ውሳኔ ሌላ ገጽታ እየሰጡ ማብጠልጠል ለማንም አይበጅም፤ እየሆነ ያለው ግን እንደዚያ ነው። ጉዳዩን በደንብ ለመፈተሽ ከላይ የተመለከተውን የመንግስትና የድርጅት የውሳኔ አቋም እንደገና እንመልከት። አቋሙም፤

 

በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው ወይም ደግሞ ወንጀል በመፈፀም ድርጊት ተጠርጥረው በአቃቤ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በምህረት ህግና ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ እንዲፈቱ ይደረጋል።

 

የሚል ነው።

 

ለዚሁ ውሳኔ ቆመናል እንዳላሉ ይህንን ነው እንግዲህ ወዲህና ወዲያ እያጠማዘዙ በማብጠልጠል ሃገሪቱን ለሌላ ፈተና በማመቻመች ላይ የሚገኙት። የተወሰኑት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ከሰጡት ቃለ ምልልስ የተወሰኑትን እንመልከት።             

 

ለአንድ ትልቅ ችግር ግማሽ መፍትሄ የለውም የሚሉት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የተሟላ መፍትሄ መሻት እንጂ ዝም ብሎ እየቀነጫጨቡ ማቅረቡ  ውጤት አያመጣም ሲሉም እርምጃውን ያብጠለጥላሉ፡፡ እርምጃው የተወሰኑ እስረኞችን በመፍታት፣ ነገሮችን ለማረሳሳት የሚደረግ ሙከራ ነው የሚሉት እኚህ ሰው ለኔ የሰሞኑ የእስረኞች ፍቺ ሁኔታ፣ ምኑ ተይዞ ጉዞ ነው የሚሆንብኝ ሲሉ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በመለስም የችግርች ሁሉ እናት የሆነው የዲሞክራሲ ምህዳር መጥፋት፣ የሚቀረፍበትን ሁኔታ የሚያመቻች እርምጃ ሲወሰድ እያየን አይደለም፡፡ ሰፊ ህዝባዊ መሰረት ካላቸው ፓርቲዎች ጋር መነጋገር አይፈልጉም፡፡ ይሄ ሁሉ ተደማምሮ፣ ለኔ ብዙም የሚታየኝ ተስፋ የለም ሲሉም ለጋዜጣው ጨምረው ገልጸዋል፡፡  

አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው ∙∙∙∙ ከዚህ በላይ ጠቃሚ የሚሆነው መንግሥት በሀገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ እስረኞች መኖራቸውን ሲያምን ነው፡፡ አሁን ግን ወንጀል የሰሩ ፖለቲከኞችን ነው የምፈታው እያለ ነው፡፡ ይሄ ማለት የፖለቲካ እስረኞች አሉ ብሎ ለማመን ተቸግሯል ማለት ነው፡፡ ይሄ የተሃድሶ እንቅስቃሴ እውነት ነው ብለን እንድንቀበል ከተፈለገ፣ በሀገሪቱ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች እንዳሉ ማመን ያስፈልጋል፡፡ ∙ ∙ ∙ በየአካባቢው ደግሞ ሁከትና ብጥብጥ አስነስታችኋል ተብለው የታሰሩ አሉ፡፡ እነዚህንና ሁሉንም፣ ከፖለቲካ ጋር የተገናኙ እስረኞችን መፍታት ያስፈልጋል፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲህ ያሉ ቀልዶችን ግማሽ እውነት እየተነገረ የሚቀመጥ መፍትሄ የትም አያደርስም፡፡ ህገ መንግስቱ፣ የፌደራል አደረጃጀቱ መፈተሸ አለበት፡፡ ∙ ∙ ∙ የኢህአዴግ አመራሮች የፖለቲካ ጨዋታ ነው የሚጫወቱት፤ ግን አላወቁም ይሆናል እንጂ ከዚህ በኋላ ሁለተኛ እድል የላቸውም፡፡ ሙሉ ችግሩን አምኖ፣ ሙሉ መፍትሄ መስጠት እንጂ በጥቂቱ አምኖ፣ ጥቂት መፍትሄ ማስቀመጥ፣ ሀገሪቷን አይጠቅምም፤ ለነሱም አይበጅም ወዘተ ሲሉ መናገራቸውን አንብበናል።

ኢህአዴግ ወሳኝ እርምጃ ሲወስድ አናየውም፤ የሚወሰደው እርምጃ መሰረታዊ መፍትሄ የሚያስገኝ ሆኖ አይታይም፡፡ እንዲሁ ለፈረንጆችና ለተወሰኑ ሚዲዎች ፍጆታ የሚውል ነው። በባህሪውም ድርጅቱ መሰረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥቶ መራመድ የሚችል እንዳልሆነ እያየን ነው። አንዳንዴ ያለውን ነገርም መፈፀም እያቃተው መሆኑን እንመለከታለን፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ የለውጥ እንቅስቃሴ የማድረግ አቅም የላቸውም፡፡ ሲሉ ለአዲስ አድማስ የተናገሩት ደግሚ በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ለተነሳው መሻኮት ምክንያት ናቸው ተብለው ከስልጣናቸው በብዙ ውጣ ውረድ የወረዱት ኢንጂነር ይልቃል ናቸው።

በጥቅሉ ለማታለል የተደረገ ሴራ በማስመሰል ለማትረፍ የሚሹት ሃይሎች ከላይ የሰጧቸው አስተያየቶች ከእውነታ የራቁ ከመሆናቸውም በላይ ሃገሪቷ ያለችበትን እና ገዥው ፓርቲ ያለበትን ትክክለኛ ስፍራ ያላገናዘበ ነው። እነሱ ባሉት መልክ ልሁን እንኳ ቢል ኢህአዴግ መሆን እንደማይችል ጭምር ነው በመግለጫው አረጋግጦ ወደስራ የገባው። ከዚያ ባሻገር የእስረኞችም ጉዳይ በተመሳሳይ ነው። በሁከት ውስጥ የተሳተፉትን ግን ደግሞ እንደ ግለሰብ በሁከት ውስጥ ስለተገኙ እንጂ ጋዜጠኛ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ስለሆኑ ያልታሰሩ መሆናቸው በመንግስት በኩል ከላይ በተመለከተው አግባብ ተረጋግጧል። በዚህች ሃገር ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ከህግ በላይ እንዲሆኑ በህግ የተፈቀደ ይመስል በተለያዩ ወንጀሎች ተሳታፊ ሆነው በመገኘታቸው ሲታሰሩ እሪ ማለት በተቃራኒው ቆመንለታል የሚሉትን የህግ የበላይነት መጻረር መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል።

 

እንኳንስ ዛሬ መቼም ቢሆን ከአገር ህልውና በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ ግለሰብም ሆነ ቡድን ከአገር በላይ መሆን አይችሉም፡፡ ሰሞኑን በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋሪያ ሆኖ የሰነበተው የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት መግለጫ፣ አገሪቱ ለገጠማት ፈተና መልሱ ኢሕአዴግ ዘንድ ብቻ እንዳልሆነ የጠቆመው ነገር አለ፡፡ አገሪቱን የገጠማት ችግር በጣም አሳሳቢና ህልውናዋን የሚፈታተን መሆኑ ግልጽ ከመደረጉም በላይ፣ ለዚህ አሳሳቢ ችግር ዋነኛ ተጠያቂው ከፍተኛ አመራሩ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ጉዳዩ በጥልቅ ሲታይ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሕዝብን በአግባቡ ባለማዳመጡ ምክንያት አገሪቱን ችግር ውስጥ መክተቱ ግልጽ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የአገሪቱን ችግር መፍታት የሚቻለው በኢሕአዴግ ብቻ አይሆንም ማለት ነው፡፡

 

ከ90 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንዳላት በሚገመትባት ኢትዮጵያ የተለያዩ ፍላጎቶች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ የእነዚህን ፍላጎቶች ልዩነት አጥብቦ አንድ የጋራ አማካይ መፈለግ ካልተቻለ አገር ችግር እንደሚገጥማት ግልጽ ነው፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶችን ማስተናገድና ችግርን ለመቅረፍ ሲቻል ደግሞ አገር በሰላምና በሥርዓት ትመራለች፡፡ ከዚህ ውጪና ከላይ በተመለከተው መልኩ ሳይመች የህግ የበላይነትን እያነሱ፤ ሲመቻቸው ደግሞ አደጋ ላይ እየጣሉ ካለ እኔ አይሆንም የሚሉ አካላት የሃገር አደጋ ናቸውና ተቀባይነት የላቸውም፡፡ የአገሪቱ ችግር በአንድ ፓርቲ ወይም 36 አባላት ባሉት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይፈታል ብሎ መጠበቅ በዚህ ዘመን አይሠራም፡፡ ይልቁንም በቃል የተነገረው ተግባራዊ መሆን የሚችለው የራሱ የተቃዋሚው ጉልህ ተሳትፎ ሲታከልበት እና በምክንያት እና በህግ አግባብ ብቻ ለድርድር ዝግጁ ሲሆን ነው፡፡ ከላይ በተመለከተው መልኩ እራሱን ሰፊ ህዝባዊ መሰረት እንዳለው ፓርቲ ቆጥሮ ሌላውን በማሳነስ ከእኛ ጋር ብቻ ብሎ ነገር ለዚህ ችግር ከዳረጉን የጽንፈኛ ብሄርተኞች አስተሳሰብ ያልተለየ ምናልባትም የእነርሱ ቅጂ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።

 

በዚህ ሃቲት መግቢያ በተመለከተው መልኩ ኢሕአዴግ ሕዝብን እጅግ ያስቆጡ አሳዛኝ ድርጊቶችን መፈጸሙን አምኗል። ከዚህ ይወጣ ዘንድ ሊደግፉ የሞራልም ሆነ የህግ ግዴታ ያለባቸው ተቃዋሚ ሃይሎች ስለ ህዝብ ሰላም እና ምክንያታዊነት ድጋፋቸው ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ኢህአዴግ እና በእርሱ የሚመራው መንግስት ካለፉት 26 ዓመታት በላይ አገሪቱን ሲያስተዳድሩ ላከናወኑት በርካታ ጠቃሚ ተግባራት እውቅና መስጠት ሲችሉና የትችታቸውም መነሻ እነዚሁ በጎ ተግባራት ሲሆኑ ነው። ይህን እና ከላይ የተመለከተውን ሃሳብ መስጠት ቢያንስ የተቻለው ይኸው ስርአት በፈጠረው እድል መሆኑን መዘንጋት የሃገር ጠላት ከመሆን ተለይቶ አይታይም።

 

ከዚህ ባሻገር ግን እነርሱ ቢሉትም ባይሉትም ይልቁንም እነርሱ ከሚሉትም በላይ በአገሪቱ ግልጽነትና ተጠያቂነት ጠፍተው ግለሰቦችና ቡድኖች እንዳሻቸው እየሆኑ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ኢህአዴግ አምኖ ተቀብሏል፡፡ በዚህም ከአገር ሀብት ዘረፋ እስከ ንፁኃን ሕይወት መቀጠፍ ድረስ የወንጀል ድርጊቶች መፈጸማቸውን አምኖ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚወጣበትን መንገድ እያመቻመቸ መሆኑንም ግልጽ አድርጓል፡፡ የመጨረሻ እድሌ ነው ያለን አካል ከላይ በተመለከተው መልኩ ውሸት ሲሉ ማግለብለብ የሚሆነው በስልጣን የመጠማት መገለጫ ብቻ ነው።

 

እነዚህ አካላት በእርግጥ በጤናማ የፖለቲካ መድረክ ላይ የሚገኙ ቢሆን በቅርቡ በተሰጠው መግለጫ በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ግለሰቦች በይቅርታና ክሳቸው ተቋርጦ በምሕረት እንደሚፈቱ መወሰኑን አድንቀው፤ ከዚህ ውሳኔ ጎን ለጎንም በአገርና በሕዝብ ላይ በደል ያደረሱ ሹማምንትም በሕግ ሊጠየቁ ይገባል ሲሉ ሊሞግቱ በተገባ ነበር፡፡ በአገሪቱ ላይ ችግርና መከራ እንዲደርስ ያደረጉ በሕግ መጠየቅ ያለባቸው፣ ካሁን በኋላ ተጠያቂነት መስፈን እንደሚኖርበት ማረጋገጫ ለመስጠት ጭምር ነው፡፡ ከእስር መለቀቅ ያለባቸውን ያህል ታስረው በሕግ የሚጠየቁ መኖራቸው ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ጠቃሚ ነው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲኖር የሕግ የበላይነት ይኖራል፡፡ ሕገወጥነት አደብ ይገዛል፡፡ የአገር ሀብት መዝረፍና ከሕግ በላይ መሆኑ ይቆማል፡፡ ሕዝብም የሚፈልገው ይህንን ዓይነቱን ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በሥልጣን መባለግ ቦታ እንደሌለው ለማሳያነትም ይጠቅማል፡፡ የአገርን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የሕዝብን ተሳትፎ ያጎለብታል፡፡ከዚያ ባሻገር ግን ከላይ የተመለከተው እይታ የተንሸዋረረ ብቻ ሳይሆን ለራስም ለሃገርም ፋይዳ የሌለው ይልቁንም ከህግ የበላይነት ጋር መጻረር ነው።

 

ከጤናማ ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች የሚጠበቀው በውሳኔ ሰነዱ ላይ በመመሥረት ለሰላምና ለዴሞክራሲ የሚሆን አዳዲስ ሃሳቦችን ማፍለቅ፤ ስለህግ የበላይነት የሚበጀውን የድርድር መንገድ መከተል ነው። የአገር ችግር የሚፈታው በዚህ መንገድ ብቻ መሆኑን መተማመን ይገባል፡፡

 

እንደሚታቀው ከዚህ በፊት የነበሩ አይነት እሰጥ አገባዎችና ንትርኮች አገሪቱንም ሆነ ሕዝቧን አልጠቀሙም፡፡ አሁን ወቅቱ እየተናበቡ በጋራ ከችግር መውጫ ብልሀት መፈለግ እንጂ በነበረው ሁኔታ መቀጠል የማይቻልበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የኢሕአዴግ አመራሮች እንዳሉት የአገሪቱ ችግር በጣም አሳሳቢና ለህልውናዋም አሥጊ መሆኑ መተማመን ከተፈጠረ፣ ካሁን በኋላ የሚጠበቀው ለተግባራዊነቱ በአጭር ታጥቆ በጋራ መነሳት ብቻ ነው፡፡ እኔ ብቻ ነኝ የማውቅልህ በማለት የደረሰው አደጋ መደገም የለበትም፡፡  

 

ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ዕውን የሚሆኑት ሕዝብ የአገሩ ባለቤት መሆኑ በተግባር ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ገዥውን ፓርቲን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ለሕዝብ ፍላጎት ተገዥ መሆን አለባቸው፡፡ በዚህች ታሪካዊት አገር ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ልማት እንዲከናወን ለሕግ የበላይነት መገዛት ያለበት ገዢው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚዎቹም ናቸው። ሥልጣን የሚያዘውም ሆነ የሚለቀቀው በነፃ፣ ፍትሐዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በሚከናወን ምርጫ እና ለሕግ የበላይነት በመገዛት እንጂ በትርምስ አጋጣሚ እንዳልሆነም ተቃዋሚዎቹ በሚገባ ሊያጤኑት ይገባል፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩት የሕግ የበላይነት ሲኖር እና በመነጋገር ላይ በተመሰረተ ግንኙነት እንጂ አጋጣሚዎችን በማጎን አይደለም ፡፡ ዜጎች የፈለጉትን በነፃነት የሚደግፉትና የማይፈልጉትን የሚቃወሙት በሕግ የበላይነት ሥር ነው፡፡ ሥልጡን ዴሞክራሲያዊ ውይይቶችና ክርክሮች የሚኖሩት ለሕግ የበላይነት ክብር ሲሰጥ ነው፡፡ በሥልጣን መባለግ የማይቻለው በሕግ የበላይነት ነው፡፡ ሕዝብም የሚከበረውና የሚደመጠው በዚህ መሠረት ነው፡፡ ኢሕአዴግ አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር  ከራሱ ጋር በታረቀው አግባብ ተቃዋሚዎችም ከራሳቸው መታረቅ፤ ከዚያም ለድርድር እና ውይይት መዘጋጀት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ህዝብ የአገር ችግር የሚፈታው በኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚዎችም ነው እያለ የመሆኑን ከላይ የተመለከቱ አመክንዮዎችን በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል።

 

መመራረዝን ከፓርቲዎችና ከሕዝብ ውስጥ የማስወገድ ሒደት በሥልጡንነት እየተወያዩና እየተከራከሩ ለችግሮች ቅን መፍትሔ የመፈለግ ብቃት የሁሉንም ወገን መተባበር የሚጠይቁ ናቸውና ከሁሉ በፊት ይህን ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎቹ አጢነውና የጋራ ስምምነት ፈጥረው ለተልዕኮው አንድ ላይ መሠለፍ ግድ ይላቸዋል፡፡ ፓርቲዎች እዚህ ወሳኝ ተግባር ላይ ከተገናኙና  አቅማቸውን  ማስተባበር ከቻሉ ለአገሪቱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት የሚቻልበት እድል ይሰፋል፤ ከዚህ ባሻገር ያለው ከላይ የተመለከተው አይነት አካሄድ ለማንም የማይበጅ ኋላ ቀር ዘመቻ ነው።  

 

ባጠቃላይ፣ ስለሃገራችን ሰላምና የህግ የበላይነት ፓርቲዎች እርስ በርስ በመከባበርና በቅንነት እየተወያዩና እየተራረሙ ለችግሮች መፍትሔ ለመፈለግና ለመቀባበል ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለአገሪቱ የፖለቲካ ሰላምና ግስጋሴ የፓርቲዎች ተከባብሮ መኖር አስፈላጊነቱ ተጢኖ መጠማመድ ከተወገደ፣ ኢትዮጵያን ማተራመስ የሚሹ የውጭ ኃይሎችም የተቃዋሚ ታኮ ማግኘት ይቸግራቸዋል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያን ለመበታተንና ከእሳት ጋር ለማገናኘት በጎረቤት ጠላቶች ጉርሻ መገዛትም ሆነ በአሮጌዎቹ ኦነግና ሻዕቢያ ደቀ መዝሙር መሆንም የሚያከትምላቸው እንደሚሆን አያጠያይቅም፡፡ ከሁሉ በላይና በፊት ግን ሁላችንም በህግ የበላይነት እንመን፤ ከህግ የበላይነት ወዲያ ምንም እንደሌለ እንገንዘብ። ያኔ ሁሉም ይሆናል።