Artcles

ከዝናብ ጥገኝነት ለመላቀቅ፤ የመስኖ ልማት ቀጣይነትን ማፅደቅ

By Admin

February 02, 2018

ከዝናብ ጥገኝነት ለመላቀቅ፤ የመስኖ ልማት ቀጣይነትን ማፅደቅ

 

ስሜነህ

ባለፉት ዓመታት በአፍሪካ በግብርናው ዘርፍ በተወሰኑ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የተሻለ አፈጻጸም ቢመዘገብም በቀጣይ ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ ሀገራት ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ስራዎች እንዳሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ መናገራቸውን የተመለከቱ ዘገባዎች ተደምጠዋል። ይህን የተናገሩት በአህጉሪቱ በግብርናው ዘርፍ የተሻለ አፈጻጻም ያላቸው 10 ሀገራት ውይይት ባደረጉበት ወቅት መሆኑንም እነዚሁ ዘገባዎች ጨምረው ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ አፍሪካውያን በፈረንጆቹ 2025 በግብርናው ዘርፍ የተሻለ እምርታና ለውጥ ለማምጣት፤ በኢኳቶሪያል ጊኒ ከገቡት ስምምነት ወዲህ ዘርፉን ለማሳደግ ሃገራት የተለያዩ ስራዎች መስራታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በዚህም በተለይም ዘርፉን በማዘመን ምርታማነትን ከፍ ከማድረግና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንጻር የተሻለ አፈጻጸም ታይቷል። ይሁን እንጅ ግብርና የአህጉሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ ሞተር ከመሆኑ አንጻር አሁንም ቀሪ ስራዎች ስለመኖራቸው ከስምምነት ላይ ተደርሷል። በ2014 በተደረሰው የማላቦ ስምምነት መሰረት የአፍሪካ ሃገራት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ በዘርፉ የሚፈሰውን መዋዕለ ንዋይ ከፍ ማድረግ፣ ረሃብን በ2025 ማጥፋት፣ ድህነትን በግማሽ መቀነስ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባትን ጨምሮ ዘጠኝ ስምምነቶች መፈራረማቸው ይታወሳል። ይህ እንደው የነገሩን ግጥምጥሞሽ ለማውሳት እንጂ መሰረታዊ ጉዳያችን ሆኖ አይደለም። ጉዳዩ የእኛ ብቻ ሳይሆን የአህጉሪቱም ስለሆነ በዚህ አጋጣሚ የሃገራችንን ተሞክሮ ለማጋራትና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ከላይ የተመለከተ የንግግር ጭብጥ ለማጠየቅ ነው።  

በሃገራችን የሁለተኛው ዙር  የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የትኩረት አቅጣጫ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል በግብርናው ዘርፍ የሴቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚነትንና ተሳታፊነትን ማረጋገጥ ዋነኛው ነው። በዚሁ አግባብ በተከናወኑ ተግባራት የገጠር ሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየጎለበተ መጥቷል። አሁንም ሥራው በተነፃፃሪ ያነሰና ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የገጠር ወጣቶችና ሴቶች ሥራ ዕድል ፈጠራን ከምግብ ዋስትና ጋር በማቀናጀት አዲስ ዘርፍ እንዲቋቋም ተደርጎ ወደሥራ ተገብቷል፡፡ የታዳጊ ክልሎችን አቅም የመገንባትና በሂደትም በክልሎቹ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራትን ማከናውን የተቻለ ሲሆን በነዚህ ክልሎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተ ሁኔታ በመንደር በማሰባሰብ እንደ የኢኮኖሚ መሠረተ ልማትና የማህበራዊ ልማት አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፤ እየተደረገም ይገኛል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም ተፋሰስን መሠረት ያደረገ የግብርና ልማት ሥራ በመሰራቱ፣ ሰፋፊና አነስተኛ የመስኖ አውታሮች ተገንብተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው፣ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ የግብዓትና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት እየተሻሻለ እና ለእንስሳትና ለሰው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንና ተደራሽነት እየጨመረ በመምጣቱ የህብረተሰቡ ገቢና ኑሮ እየተሻሻለ የመጣበት ሁኔታ ከመኖሩ ጋር ተያይዞ የአኗኗር፣ የአመራረትና የአረባብ ዘይቤያቸውም ጭምር መቀየር ጀምሯል፡፡

ግብርናችን በቀጣይነት ያለማቋረጥ እያደገ በመምጣቱ ለአደጋ ተጋላጭነታችንና ድርቅን የመቋቋም አቅማችን እንደ ሀገር እየተገነባ የመጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ከአካባቢ አካባቢ የተለያየ አፈፃፀም ያለና አሁንም ለአየር ንብረት መዛባት ተጋላጭነት ያላቸው አካባቢዎች ያሉን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ጠንከር ያለ ድርቅ ቢከሰት አንኳን ችግሩን ተቋቁሞ የማለፍ አቅማችን እያደገ መጥቷል፡፡ የተሟላ አቅም መገንባት ገና የሚቀረን መሆኑም ግንዛቤ ተይዞ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የግብርና ዕድገት እየተመዘገበ ባለበት ልክ የድርቅ መቋቋምና የአደጋ መከላከል አቅማችንን ማሳደግ እንደሚገባን ግን ሊሰመርበት የሚገባ መሆኑን የተመለከተው አጀንዳ የመንግስት አቋምና አጽንኦት የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

የዚህ መነሻ ደግሞ በበልግ አብቃይ የአገሪቱ ክፍሎች የዝናብ እጥረት ሊያጋጥም ስለሚችል ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ መረጃ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ኤጀንሲው ቀጣዩን የበልግ ወቅት አስመልክቶ ቅዳሜ ጥር 19 ቀን 2010 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ይፋ እንዳደረገው፤ ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ተያይዞ የውኃ እጥረትና በእንስሳት ላይ አደጋ ሊያስከትል የሚችል የአየር ንብረት ለውጥ ስለሚኖር፣ ከወዲሁ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት እንዲደረግ የሚያስጠነቅቅ ነው፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በመጪው የበልግ ወቅት አካባቢዎቹ የአየር ፀባይን ግምት ውስጥ በማስገባት እንዲንቀሳቀሱ፣ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ያለባቸው አካላትም ይህንኑ የአየር ፀባይ አሉታዊ ተፅዕኖን ለመቋቋም መዘጋጀት ይኖርባቸዋል ማለታቸው በዘገባዎቹ ተመልክቷል፡፡

ኤጀንሲው በሁሉም ክልሎች ካሉ የሚቲዎሮሎጂ ጽሕፈት ቤቶች ጋር ያደረገው የምክክር መድረክ፣ ወቅታዊና የመጪውን ጊዜ የአየር ትንበያዎችን በዝርዝር ያቀረበበትና መፍትሔ ይሆናሉ የተባሉ አማራጮችን የጠቆመበት ነው፡፡ ይህንኑ ትንበያ ለሚመለከታቸው አካላት እንዲደርሳቸው በማድረግ፣ ትንበያውን መሠረት ያደረገ ዕርምጃ እንዲወሰድ ይደረጋል ተብሏል፡፡

ከውቅያኖሶች ሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ የተከሰተው የኤሊኞ አየር መዛባት አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል ግምት የሚሰጠው ባለመሆኑ እንደዚህ አይነት ክስተትም ሆነ ተያያዥ ችግሮችን መቋቋም የምንችለው ለአየር ለውጥ የሚይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት ስንችል ብቻ ነው ሲል የባለስልጣኑ ምክረ ሃሳብ ያስጠነቅቃል፡፡ ስለሆነም የጀመርነውን የተፈጥሮ ሀብትና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራችንን ከመስኖ ልማቱ ጋር አስተሳስረን በላቀ ቁርጠኝነት በመፈጸም የግብርናን ምርትና ምርታማነት ዕድገት ማስቀጠል ወደ ኢንዱትራላይዜሽን የምናደርገውን ሽግግር በሚያቀላጥፍና አገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የያዘችውን የህዳሴ ጉዞ በሚያሳካ መንገድ ሊፈጸም ይገባዋል።

እንደገና ስለሆነም ተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች እና የተፋሰስ ልማት ስራዎች ባሻገር ወቅታዊ ስራዎችም ስለመኖራቸው መገንዘብ በጊዚያዊነትም ቢሆን ድርቅን ለመቋቋም ያስችላል። ሊዘነጋ የማይገባውም ጉዳይ የበልግ የእርጥበት መጠን ዝቅተኛ ሊሆን ስለሚችል አርሶና አርብቶ አደሩ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል። የበልግ የእርጥበት ሁኔታ በመጠንም ሆነ በስርጭት የበልግ አብቃይ በሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ መደበኛ እና ከመደበኛ በታች እንደሚሆን ይጠበቃል ብሏል ኤጀንሲው በትንበያው። ስለሆነም አርሶ አደሩ የሚደርሰውን ተጽዕኖ ለመቀነስ የሚያገኘውን እርጥበት በአግባቡ በመጠቀም በጊዚያዊነት ከሚገጥመው አደጋ እራሱን ማዳን ይጠበቅበታል ።  

ዘላቂነት ለሚኖረው የምግብ ዋስትና ከሚደረገው ርብርብ ጎን ለጎን ተለዋዋጭ የአየር ጠባይን ግምት ውስጥ በማስገባት በግብርና ሥራ፣ በውኃ አቅርቦትና በአካባቢ እንክብካቤ ላይ ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ መረዳት በድንገቴ ከሚጠልፈን ድርቅ ለመዳን ያስችላል። እንቅስቃሴያችን ሁሉ ከዝናብ ጥገኝነት መላቀቅን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባዋል። የበልግ ዝናብ መጠንና ስርጭት አብዛኛው የበልግ እርሻ ሥራ እንቅስቃሴ፣ ለቋሚ ሰብሎች የውኃ ፍላጎት መዳረስ ምቹ ሁኔታዎች ይፈጥራል።  ለአርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደር ለመጠጥ ውኃና ለግጦሽ ሳር አቅርቦት እንዲሁም ለረጅም ጊዜ የመኸር ሰብሎች እንደ ማሽላና በቆሎ ለመሳሰሉትም ተስማሚ ነው።

ይህም በበልግ ወቅት ለሚካሄዱ የማሳ ዝግጅት፣ የዘርና የእርሻ ሥራ እንቅስቃሴዎች ጭምር አመቺ ነው። ስለሆነም የእርጥበት መቀነስ በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የተገኘውን እርጥበት በማሳ ላይ በማቆየት ለዕጽዋቶቻቸው ጠቀሜታ እንዲውል ማድረግ የሁሉም አርሶአደሮች ወቅታዊ ስራ ሊሆን ይገባዋል።

ከዚያ ባሻገር ግን የተፋሰስ ልማት ስራዎች ድርቅን ከመቋቋም አልፈው ለገጠር ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥሩ ስለሆነ፤ የስነ ህይወታዊ ዘዴን ስለሚያጠናክሩ፤ ለእንስሳት ሀብት ልማት፣ ለአትክልትና ፍራፍሬና ለደን ልማት ግልጋሎት የሚሰጡ መሆኑን ተገንዝቦ በተጠናከረ መንገድ መስራት ያስፈልጋል። ይህ ማለት ግን ምንም አልተሰራም ማለት ሳይሆን ምናልባትም ከእኛ አልፎ ለሌሎቹም የሚተርፍ ተሞክሮ ያለን እንደሆነ ተዘንግቶ አይደለም።

በሃገራችን የግብርና ፖሊሲና ስትራቴጂውን መሰረት ያደረገ የተፋሰስ የግብርና ልማት ሥራ በመሰራቱ፣ ሰፋፊና አነስተኛ የመስኖ አውታሮች ተገንብተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው፣ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ የግብዓትና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት እየተሻሻለ እና ለእንስሳትና ለሰው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንና ተደራሽነት እየጨመረ በመምጣቱ የህብረተሰቡ ገቢና ኑሮ እየተሻሻለ የመጣበት ሁኔታ ከመኖሩ ጋር ተያይዞ በምግብ ሰብሎች ላይ የዋጋ ጭማሬ ሊኖር የሚችልባቸው ቀዳዳዎች  ሁሉ ተደፍነዋል። የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ድርቅን የመቋቋም ጠንካራ አቅም ፈጥረናል። በግብርና ምርታችን ላይ በየዓመቱ የሚመዘገበው ዕድገት የአርሶ አደሩን ህይወት በተጨባጭ እየለወጠ ይገኛል። በበጋ ወራት የምናካሂደው የግብርና ዝግጅት በምግብ ራስን ለመቻል እየገነባነው ላለው አገራዊ አቅም ጠንካራ መደላድል ፈጥሯል። ግብርናችንን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ድርቅን የመቋቋም አቅም የመፍጠር ሂደት ውስጥ ስለመግባታችን የሚያረጋግጥ ተሞክሮም ባለቤትም ሆነናል። በመሆኑም፣ ያለምንም መዘናጋት ከዝናብ ጥገኝነት ለመላቀቅ የመስኖ ልማትን አጠናክረን ልንቀጥልበት ይገባል።