Artcles

ኮንትሮባንዲስቱ፤ ከወቅቱ አገራዊ ቀውስ አንፃር

By Admin

February 15, 2018

ኮንትሮባንዲስቱ፤ ከወቅቱ አገራዊ ቀውስ አንፃር

 

ዮናስ

 

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግሥት አንቀፅ 97 ስለ ግብርና የገቢዎች ጉዳይ በግልጽ ተመልክቷል። በተለያዩ ጊዜያት ይፋ በተደረገው እና ይህንኑ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ መሰረት አድርጎ በየወቅቱ ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የግብር ገቢ የመሰብሰብ ስልጣን ተሰጥቶታል። ይሀ ተቋም የሚሰበስበው ገቢ ለልማት በሚውለው የሃገሪቱ አመታዊ የበጀት ምንጭ ላይ ከፍተኛ ድርሻ እያያዘ በመምጣት አሁን ላይ 80 ከመቶ ደርሷል። ያም ሆኖ ግን ግብር ከፋይ የሆነው ዜጋ ሁሉ ከአመት አመት ስለግብር ያለው ግንዛቤ የሚጨምር እንደሆነ ቢጠበቅም የሚሰበሰበው ገቢ ይህን አያመላክትም። ግንዛቤ ብቻ ሳይሆን ወደ ግብር ከፋይነት የሚቀላቀለው ህብረተሰብ የሚጨምር የመሆኑን አመክንዮም አያመላክትም። አምናና ካቻምናን ስለዚሁ አስረጅ አድርገን ስንመለከትም የምናገኘው ይህንኑ እውነታ ነው። ለምሳሌ በ2008  በጀት ዓመት መንግሥት በአጠቃላይ 106 ቢሊዮን ብር ገቢ የሰበሰበ ሲሆን ይህም ከእቅዱ ከ91 በመቶ በላይ ነው። ከ2007  ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው። የ2009ኝን በአንጻሩ ስንመለከተው ደግሞ የተገላቢጦሽ ሆኖ እናገኘዋለን።

ግብር የፌዴራል፣ የክልልና የአካባቢ አስተዳደር አካላት በግለሰቦችና ህጋዊ ተቋማት ላይ ከሚያገኙት ገቢ ይከፍሉ ዘንድ የሚጣል የውዴታ ግዴታ እንጂ እዳ አይደለም።  መንግሥት ከዜጎች በግብር የሰበሰበውን ለመከላከያ፣ ለት/ቤቶች፣ ለጤና ተቋማትና መሰል የመሰረተ ልማት ግንባታ ወጪዎች መሸፈኛ ያውላል። ስለሆነም ማናቸውም ግብር ከፋይ በህግ በተመለከተው ጊዜ ውስጥ ግብሩን አስታውቆ የመክፈል ግዴታ አለበት ፡፡ ያም ሆኖ ግን በዚህ አግባብ እየተመራ እንደማይገኝ በብዙ ጥናቶች የተረጋገጠበት የገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን ህዝቡን ኢፍትሃዊ ለሆነ የሃብት ክፍፍል በመዳረግ ረገድ ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወተ ጥናቶቹ ያረጋግጣሉ። ከጥናትም በላይ እራሱ የገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን ከሰሞኑ የ6 ወር የአፈጻጸም ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት በራሱ ላይ መስክሯል።

ምስክርነቱ የተሰጠው ማክሰኞ ጥር 22 ቀን 2010 ዓ.ም ባለስልጣኑ የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን  ባደረገበት ወቅት ነው፡፡ የፓርላማው አባላት በከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ሳይቀሩ በአገሪቱ ለሚታየው የፖለቲካ ቀውስ ጣታቸውን የሚቀስሩት “ኮንትሮባንዲስት” በተባሉ ማንነታቸው በማይታወቅ ኃይሎች ላይ ስለሆነ፣ የእነዚህን ማንነት ፓርላማው በግልጽ የማወቅ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ማንነታቸው እንዲገለጽላቸው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አመራሮችን ጠይቀዋል፡፡

አንድ የፓርላማ አባል፣ “ስሙ የማይጠራው ኮንትሮባንዲስት ማነው?” ሲሉ በስላቅ መጠየቃቸውን የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡ በአገሪቱ የብሔር ግጭት እየፈጠሩ ያሉት እነዚህ ኮንትሮባንዲስት የሚል ስም የወጣላቸው፤ በኔትወርክ ተሳስረው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች እንደሆኑ የጠቆሙት ሌላ የምክር ቤቱ አባል ደግሞ፣ “በእነዚህ ኃይሎች ጡንቻ ገቢዎችና ጉምሩክ ራሱ ታስሯል፤” ሲሉ መተቸታቸውም በተመሳሳይ በዘገባዎቹ ተመልክቷል፡፡

በተለይ በጉምሩክ ቅርንጫፎች ላይ የሚመደቡ የሥራ ኃላፊዎች ለዚሁ ሕገወጥ ሥራ እንዲመቹ ሆነው የሚመለመሉ መሆኑን፣ በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት አንድ ብሔር ነጥሎ የማጥቃት ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል ሲሉ እኚሁ የምክር ቤት አባላት የወቀሱ ሲሆን፤በአገሪቱ የወጪ ንግድ መስመሮች በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በድንገት የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋረጠ ማለት ኮንትሮባንድ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እያለፉ እንደሆነ በገሃድ የሚታወቅ መሆኑን የጠቀሱ ሌላ የምክር ቤት አባል፣ በዚህ ኔትወርክ ውስጥ የተቋሙ ሠራተኞች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያሳያል ማለታቸውንም ከዘገባዎቹ መረዳት ተችሏል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው በፓርላማ አባላቱ እንደተነሳው ኮንትሮባንዲስቶቹ የራሳቸው መጋዘን ያላቸው፣ በኔትወርክ የተደራጁና ተግባራቸውም በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ የሚባል መሆኑን ጠቁመው፤ ይኼንን መበጣጠስ ካልተቻለ ከኢኮኖሚ ጉዳቱ በላይ የፖለቲካ ቀውስ የሚፈጥር መሆኑን መናገራቸውም ተመልክቷል፡፡ በግማሽ ዓመት ውስጥ 331.6 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ንብረቶች በኮንትሮባንድ ሊገቡ ሲሉ የተያዙ መሆኑን፣ 105.3 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ደግሞ ሊወጣ ሲል መያዙ ተገልጿል፡፡

ይህ ደግሞ በተሟላ መልኩም ባይሆን ከቁሳቁስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ከሰው ሃይል አንጻር ለዘመናዊ የግብር አሰባሰብ ስርአት የተመቹ ሁኔታዎች የተፈጠሩ ቢሆንም በግብር አስተደደር ስርዓቱ ውስጥ ኪራይ ሰበሰቢነትን ከመድፈቅ፣ መሰብሰብ ያለበትን ገቢ ከመሰብሰብ እና ፍትሃዊነትን ከማስፈን አኳያ በየደረጃው ባለው አመራርም ሆነ በባለሙያዎች ዘንድ ያልተቀረፉ በርካታ ጉድለቶች የሚታዩ መሆኑን የመያመለክት ምስክርነት ነው። እነዚህ ችግሮች በፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ላይ አሉታዊ ተጽእኖ በመፍጠር ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ግብርን እንደ እዳ እንዲመለከተው ከማድረጉም በላይ ህዝቡ የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዳይሆን የሚያደርግ እንደሆነም አያጠያይቅም።

በጥናት የተደገፉት እነዚህ  መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በፌዴራሉ የገቢዎችና ጉምሩክ  ባለስልጣን  ከጉምሩክ ስርዓቱ ጋር ተያይዞ በወደብ፣ ደረቅ ወደብና በአውሮፕላን ማረፍያ አካባቢ የሙስና፣ የስራ መጓተትና ኢ-ፍትሃዊ ትመና በስፋት እንደሚታይ እንዲሁም ከገቢ ግብር ትመና ጋር በተያያዘ ዝቅተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ያለው ነጋዴ ላይ ከፍተኛ የግብር ግምት የሚጣልበት፤ በተቃራኒው ደግሞ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ያለው ነጋዴ ላይ አነስተኛ የግብር ግምት የሚጣልበት ሁኔታ በስፋት መኖሩ እንዲሁም ተመሳሳይ ጥፋት ያጠፉትን ተመሳሳይ ቅጣት አለመቅጣት ኪራይ ሰብሳቢነት በግልጽ እንደሚፈጸም ያሳያሉ።

በጥናቶቹ  የተገኙ  መረጃዎች እንደሚያሳዩት በጉምሩክ ስርዓቱ ባለጉዳይን ማስተናገድ ላይ የሚታይ ኢ-ፍትሃዊነት፣ ሠነድ በፍጥነት አለመበተን፣ ታሪፍ እያሳሳቱ ያልሆነ ቀረጥና ታክስ መጠየቅ፣ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት መደራደርና ከጉምሩክ አስተላላፊዎች ጋር ተመሣጥሮ መስራት የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫዎች ናቸው፡፡ ከሰሞኑ በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 የምሽት ዜና ላይ የተደመጠውም ይህንኑ በሚገባ የሚያጠናክር አስረጅ ነው።

ጉዳዩ እንዲህ ነው።መንግስት ለሳውዲ ተመላሾች የሰጠውን ከቀረጥ ነጻ የማስገባት መብት በመጠቀምና ቤት ለቤት በተደረገ ቅስቀሳ የቀረበላቸውን ጥሪ መሰረት አድርገው በዚህ ሃገር ለመስራት የሚያስችላቸውን እቃና የቤት ቁሳቁሶች ባልና ሚስት ሸክፈው ወደሃገር ይመጣሉ። የሸከፉት እቃን ዛሬ ነገ እያለ፤ቆጠራ ላይ … ስብሰባ ላይ ነን እያለ የአዲስ አበባ ቦሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ባልና ሚስቲቱን ካጉላላ በኋላ ወር ስላለፈው ተወርሷል ሲል ምላሽ ሰጥቶ ኩም ያደርጋቸዋል። የሚለብሱት ብርድልብስን እንኳ ከጎረቤት በትውስት እየተጠቀሙ የሚገኙት ባልና ሚስቲቱ ህግን ተደግፈው አንቀጽ ጠቅሰው እሪ ቢሉም ያገኙት መልስ ከቃጠሎ የተረፈ ካለ ይሰጣችኋል የሚል ነው። ግብር ከፋይ የሆነውን ህብረተሰብ የሚያሳስበው ይህ ነው። ቀድሞ ነገር ህጉ ምን ይበል ምን ጉዳያችን አይሁንና ፤1ወር የቆየ ንብረት ይወረሳል የሚለውን ተቀብለን የተቋሙን ምላሽ ስናሄሰው፤ከቃጠሎ ስለምን ሲባል የተረፈ ንብረት ኖረ የሚለው ጥያቄ ስናሄሰው የባልና ሚስቱ ንብረት ቀድሞ ነገር እንዳልተቃጠለ እና ወራሹም መንግስት ሳይሆን መንግስት የሚያካክሉት የተቋሙ ባለስልጣናት እንደሆኑ ይገባናል። የተቃጠለማ ቢሆን ሁሉም እንጂ የተወሰነው ሊሆን ስለማይችል።አልያም ደግሞ የሚቃጠሉ የውርስ ንብረቶች ለማሳያ ተቆንጥሮ የሚቃጠልና ቀሪው ለነዚሁ ኪራይ ሰብሳቢዎች እንደሆነ የሚያመላክት ጭብጥን ነው ከዜናው መገንዘብ የሚቻለው። ይህ ደግሞ ግብር ከፋይ የሆነውን ህብረተሰብ ግብር እዳዬ ነው እንዲል የሚያስችል ውንብድና ነው።

አንዳንድ አመራሮች በገቢ አሰባሰብ ሂደት የሚታዩ ክፍተቶችን ተጠቅመው ጣልቃ በመግባት አለአግባብ ጥቅም ለማግኘት የመሻት፣ አድልዎና ኢፍትሃዊ ተግባራት በፍትሃዊ የንግድ ውድድር ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳረፉ መሆናቸውን በጥናቶቹ የተገኙት መረጃዎች አሳይተዋል፡፡ በተጨማሪ እሴት ታክስ አመዘጋገብ ላይ አንዱን መመዝገብ ሌላኛውን ችላ ማለት ይታያል፡፡  

መሃንዲሶች ቢል ኦፍ ኳንቲቲ አጋንነው በመፃፍ የቀረጥ ነፃ መብት ተጠቃሚዎች የንግድ ሰርአቱን ወደሚያዛባ እንቅስቃሴ እንዲገቡ ይደግፋሉ፡፡ ከቀረጥ ነፃ መብትን ለህገወጥ መንገድ የሚያውሉትን በህግ ተጠያቂ ማድረግ ላይም በገንዘብና በትስስር ከህግ ስለሚያመልጡ በቁርጠኝነት ለመታገል የሚደረገው ጥረት ደካማ ሆኗል። በተመሳሳይ አየር ባየር ነጋዴዎች ለህግ ቢቀርቡም በአፋጣኝ አይቀጡም፡፡    

ዋነኛው መንስኤ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር በመዋቅሩም ሆነ በህብረተሰቡ ውስጥ የተንሰራፋ መሆኑ፤ የተጠያቂነት ማነስና በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የሚደረገው ትግል ያዝ ለቀቅ የበዛበትና በሙሉ ልብ የማይካሄድ መሆኑ ነው። በርከት ያሉ አመራሮችና ባለሙያዎች በጥቅም ትስስር የተነካኩ ወይም አድርባይነት የተጠናወታቸው በመሆናቸው የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉን በቁርጠኝነት ለመቀላቀል የማይደፍሩ አንዳንዴም በፀረ ዲሞክራሲ መንገድ የመታገያ መድረኩ እንዲጠብ የሚያደርጉ መሆናቸው ነው።

ሌላው መንስኤ በዘርፉ ያለው በርካታ አመራር ምደባውና ስምሪቱ ለዘርፉ የሚመጥን ፖለቲካዊና ሙያዊ ብቃት እንዳለው በሚያረጋግጥ መንገድ አለመሆኑ፤ ብቃቱን ለማዳበርም በቂ ጥረት የማያደርግ በመሆኑ ያለበት የብቃት እጥረት በስራው ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳረፉ ነው። ከዘርፉ ውጪ የሚገኘው አብዛኛው አመራርም በግብር ማሰባሰብ ስራው ላይ ትክክለኛ አመለካከትና ዕውቀት ባለመያዙ የግብር መሰብሰብ ስራን ከፖለቲካል ኢኮኖሚ ለውጡ ጋር አስተሳስሮ ከማየት ይልቅ ተራ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ አድርጎ በመመልከት፤ ለልማት የሚውለውን የግብር ማሰባሰብ ሂደት የሚደረገውን ትግል በትክክለኛ ይዘቱ አለመገንዘብና  በዚህም ምክንያት ግብር ከፋዩ ግዴታው የሆነውን ግብር እንደ እዳ እንዲመለከተው እያደረጉት ነው።

ስለሆነም የግብር አስተዳደር ስርአቱን በማዘመን ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ማረጋገጥ የሚቻልባቸው የቅርብና የረዥም ጊዜ የሆኑ ወሳኝ የመፍትሄ ሃሳቦችን ጠቁመዋልና በዛው አግባብ መስራት ያስፈልጋል። በገቢዎች ዘርፍ የሚታየውን የኪራይ ሰበሳቢነትና ኢፍትሃዊነት ችግር  ለመፍታት የአሰራር ጉድለቶችን በጥልቀት በመፈተሸ  በተለይም በዘርፉ ከፍተኛ የግብር ስወራ የሚካሄድባቸውን መስኮች በማጥናት የሚፈፀመውን የታክስ ማጭበርበር ሊገቱ የሚችሉ የአሰራር ማሻሻያዎች ማድረግና ሌሎች  ዘርፉን የማጥራት ርምጃዎች መውሰድ ይገባል፡፡  

በዘርፉ የሚታየውን የመፈፀምና የማስፈፀም ጉድለቶች ለማስተካከል ከአጭር ጊዜ አኳያ አሁን ያለውን አመራርና ባለሙያ ሁኔታ በመገምገም አፋጣኝ የማሻሻያ እርምጃ መውሰድ ይጠይቃል። ከረጅም ጊዜ አኳያ ደግሞ ችግሮቹን  በጥናትና ምርምር እየለየ የምክር እና የስልጠና አገልግሎት የሚሰጥ የታክስ ኢንስቲትዩት ማቋቋም ይገባል፡፡  

በዘርፉ ያለውን የመረጃ ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት የመረጃ ስርዓቱን ማዘመን ይጠይቃል። በጥቅሉ የታክስ አስተዳደር ህጉን በሁሉም አካባቢዎች ወጥነት ባለው መንገድ ተግባራዊ በማድረግ እና ስርአቱን በማዘመን ልማትን ማፋጠን እና ከተገኘው ልማት እኩል ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበትን እድል በማስፋት ግብር እዳ ሳይሆን የውዴታ ግዴታ መሆኑን አምኖ የሚቀበል ማህበረሰብ መገንባት ግድ ይላል።