ወደ ምዕራብ ተመልከቱ !
ወደ ምዕራብ ተመልከቱ !
ሲሳይ ደርቤ
ወደ ምዕራብ ተመልከቱ… ኢትዮጵያ ከፍ እያለች ነው፡፡ ሠላም ወዳድ የሆኑት ትጉህ ዜጎቿ እየታተሩ ነው፡፡ ምትሃታዊ ህብር ቀለማት ያላቸው ህዝቦቿ በአንድንት ቆመው እያቆሟት ነው፡፡ አበው እና እማው በአጥንታቸው ያነፅዋት፤ በደም በስጋቸው የለሰኗት፤ በመስዋዕትነት ያፀኗት ኢትዮጵያ ዛሬ ዳግም እያንፀባረቀች ነው፡፡
ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ጦማርያን፣ ከያኒያን፣ የመገናኛ ብዙሃን እና መቶ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ትኩረታቸውን አንድ ቦታ ላይ አድርገዋል፡፡ በምዕራብ ኢትዮጵያ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ መቻከል ዞን፤ ጉባ ወረዳ በመገንባት ላይ ባለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ላይ፡፡
በዚህ ሥፍራ በቋንቋ ሊገለፅ፤ በማናቸውም ዋጋ ሊተመን እና በሳይንሳዊ ቀመር ሊሰላ በማይችል መልኩ የዘመናት ቁጭትና ህልም የፈጠረው መግነጢሳዊ ሃይልና ረቂቅ ስሜት ይንተከተካል፡፡ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ይህ መግነጢሳዊ ኃይልና ረቂቅ ስሜት የተገለጠበት ታሪካዊ ቀን ነው፡፡ ቀኑ እንደ ንጋት ኮኮብ ደምቆ እየታየ ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ ይኖራል፡፡
ፕሮጀክቱን ዳር ለማድረስ የቆረጠው ህዘብ ያለውን ጥሪት አሟጦ፤ ሳይሰስተ እየለገሰ ግድቡን እየገነባ ነው፡፡ ጎን ለጎንም በምሳሌያዊ አነጋገሮችና መፈክሮች ደጀን ሆኖ ጉባ የከተሙትን የዚህ ዘመን አርበኞች ሞራል ይገነባል፡፡ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ፤… አንድነት ኃይል ነው፤…..ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለአምሳ ሰው ጌጡ ነው፤…. እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን፤…. ስኬታችን በእጃችን ነው፤…. ፅናት ካለህ ተራራውን ሜዳ ማድረግ የሚያስችል ግዙፍ ኃይል አለህ፤…. እና ሌሎችም በሕዳሴው ግድብ ምዕራባዊው የአባይ ሸለቆ የሚስተጋቡ “እንችላለን!“ን ሰባኪ የህዝብ ድምጾች ናቸው፡፡
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት መገኛ ስፍራ ፀሐይ አትጠልቅም፡፡ከማለዳ እስከ አመሻሽ ፀሐይ የምትረጨው ብርሃን ግድቡን ወርቅ የተርከፈከፈበት ሰንሰለታማ ተራራ ያስመስለዋል፡፡ምሽቱን ደግሞ በዙሪያ ገባው የተተከሉ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች የሚፈነጥቁት ብርሃን ለግድቡ ምትሃታዊ መስህብ ያላብሰዋል፡፡ ምን አለፋችሁ… ኢትዮጵያዊ ወዝ፣ ዕውቀትና ንዋይ የፈሰሰበት ግዙፉ ግድብ በወርቅ የተለበጠና በዕንቁ የተንቆጠቆጠ ያህል የውበት አክሊልን ተጎናፅፎ ይታያል፡፡ ቀልብ ሳቢ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ኅብረ-ቀለማቱ በነብስያ ላይ ሀሴትን ይዘራሉ፡፡ እንዲ ባለ አስደማሚ ትዕይንት መሀል ሕዝባዊና ሀገራዊ ተልዕኮን ያነገቡ ትልቅ አደራ የተጣለባቸው ሰራተኞች ያለ ዕረፍት የግድቡን ግንባታ ያከናውናሉ፡፡ ሁሉም በተሰማሩበት መስክ በትጋት የሚያደርጉት ርብርብ አካባቢውን 24 ሰዓት በማያቋርጥ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በዚህ ቦታ ውበት፣ሰላም፣ፍቅር፣ተስፋ እና እንደ አለት የጠነከረ ሕብረ-ብሔራዊነት አለ፡፡
ወደ ምዕራብ ተመልከቱ… ድህነትን ጠንክሮ በመሥራት ለማስወገድ የተነሳ ታላቅ ሕዝብ ወደ ስኬት ማማ ሲተም ታያላችሁ፡፡ ኢትዮጵያ አባይን ለልማት እንዳታውል ሲደረጉባት የቆዩ ጫናዎችን ተቋቁማ አቅሟን ያሳየችበትን አርማ ታያላችሁ፡፡ የህዝቦቿን ጀግንነት የተሞላ የልብ ትርታ ታደምጣላችሁ፡፡ የስጋት አይነጥላን ገፎ በራስ መተማመንን ያነገሰው ግዙፍ ፕሮጀክት በኢትዮጵያዊነት ኩራት ደረቱን ለሰማይ ሰጥቶ ይህን አኩሪ ገድል ይተርክላችኋል፡፡
ግድቡ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለተፋሰሱ አገራት ሕዝቦች ጭምር ፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ይህም በጥናቶች የተረጋገጠ እውነታ ነው፡፡
የአፍሪካ መዲና ፈክታለች፡፡ በልማት ጎዳና እየገሰገሰች ነው፡፡ በብዝሃነት ደምቃ ጉዞዋን ቀጥላለች…ኢትዮጵያ !