ውሣኔ ያለተግባር ጥርስ የሌለው አንበሳ ነው
ብ. ነጋሽ
የአፍሪካ ህብረት 30ኛ የመሪዎች መደበኛ ስብሰባ ከቀናት በፊት በአዲስ አበባ ተካሂዷል። የአፍሪካ ህብረት መደበኛ የመሪዎች ስብሰባ ጥር ወር ላይ በየዓመቱ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ይታወቃል። የዘንድሮው የህብረቱ የመሪዎች ስብሰባ “ዘላቂ የጸረ ሙስና ዘመቻ ለአፍሪካ ስር ነቀል ለውጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል። በዘንድሮው ስብሰባ ላይ ከ55 የአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራት የ49ኙ መሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል። ይህም ካለፉት ጊዜያት ጋር ሲፃፀር ከፍተኛ ቁጥር ነው። ከጉባኤው ጋር በተያያዘ አዲስ አበባ በአጠቃላይ 10 ሺህ ተሳታፊዎችን አስተናግዳለች። 678 ጋዜጠኞችም ከመላው ዓለም ስብሰባውን ለመዘገብ በአዲስ አበባ ታድመው ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ ስብሰባው ለኢትዮጵያ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስራ የማከናወን እድል የፈጠረ ነበር። ከስብሰባው ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ከ30 ሃገራት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን የሚያጎለብቱ ስብሰባዎችን አካሂዳለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከ30 ሃገራት መሪዎችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል። በአጠቃላይ 30ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ተሰሚነቷን ያሳደገችበት፣ በጎ ገፅታዋን በስፋት ያስተዋወቀችበትና በርካታ ተሳታፊዎች በመምጣታቸው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያገኘችበት ነበር። ይህ እድል ታድያ በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ ለአህጉሪቱ ነጻነትና ለፓንአፍሪካኒዝም ባበረከተችው ጉልህ አስተዋጽኦ ነው እንጂ።
የህብረቱ የመሪዎች ስብሰባ የአፍሪካ ሙስናና የፀረ ሙስና ትግል፣ ነፃ የአፍሪካ የንግድ ቀጣና ምስረታ፣ የአፍሪካን አየር ክልል ለአፍሪካ አየር መንገዶች ነፃ ማድርግ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ አጀንዳዎች ላይ ነበር የተወያየው። የህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች በእነዚህ አጀንዳዎች ላይ ተወያይተው ውሳኔዎች አሳልፈዋል። መሪዎቹ በአህጉሪቷ የደህንነትና ፀጥታ ስጋቶች ዙርያ፣ በፀረ ሽብር ዘመቻው፣ በተወሰኑ ሃገራት የተፈጠሩ ግጭቶችን ለማስቆም የሚያስችሉ ጉዳዮችም ላይ ተወያየተው ውሳኔዎች አሳልፈዋል። የደቡብ ሱዳን የሰላም ቀውስም ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መሃከል አንዱ ነበር። በደቡብ ሱዳን ያለው የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን መነሻ በማድረግ፣ በተለያየ ጊዜ የሚፈረሙ የሰላም ስምምነቶችን የሚጥሱ ወገኖች ላይ ማዕቀብ የሚጣልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተካሂዷል።
እነዚህ ህብረቱ የተወያየባቸውና ውሳኔ ያሳለፈባቸው ጉዳዮች የኢትዮጵያም አብይ ጉዳዮች ናቸው። ህብረቱ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈባቸውን ጉዳዮች በኢትዮጵያ መንግስት ከተያዘባቸው አቋምና እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት አንጻር ምን እንደሚመስሉ በመጠኑ እንመለከት።
ሙስና የአፍሪካ ሃገራትን እየተፈታተነ የሚገኝ ትልቅ ችግር ነው። የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል መረጃ እንደሚያመለክተው አፍሪካ በሙስና በየዓመቱ 148 ቢሊየን ዶላር ሃብት ታጣለች። ይህ ሀብት ደሃ ለሆኑት የአፍሪካ ሃገራት ከፍተኛ ነው። የስራ አጥነት፣ የማህበራዊ ልማት፣ የመሰረተ ልማት ችግር ወዘተ ያለባቸው የአፍሪካ ሃገራት ይህን ሃብት ከብክነት መታደግ ቢችሉ የዜጎቻቸውን ህይወት በማሻሻል አቅማቸውን ያጠናክሩ ነበር። የአፍሪካ ሃገራት በአስከፊ ድህነት ውስጥ ያሉ ዜጎቻቸውን ህይወት መቀየር የሚችለውን ሃብት በሙስና ምክንያት ማጣታቸው ለፖለቲካ ቀውስም አጋልጧቸዋል። ድህነት ለሰላምና መረጋጋት መጥፋት፣ ለአክራሪነት መስፋፋት፣ ለሽብርተኝነት ያጋልጣል። በመሆኑም ሙስና ለአፍሪካ ሃብት ከማጣት ባሻገር የፖለቲካዊ ቀውስ መንስኤም ነው። እናም የአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራት አጀንዳው ላይ ተወያይተው ውሳኔ ማሳለፋቸው ተገቢ ነው።
ኢትዮጵያም የዚህ የሙስና ችግር ተጠቂ ነች። ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ባወጣው የአውሮፓውያኑ 2016 ዓ/ም የዓለም ሃገራት የሙስና ደረጃ አመልካች ኢትዮጵያን ከ176 ሃገራት 108ኛ ተራ ላይ ያስቀምጣታል። በዚህ የሙስና ደረጃ አመለካች መሰረት የብዙዎቹ የአፍሪካ ሃገራት የሙስና ደረጃ ከ100ኛ በላይ ነው። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ለዚህ የሙስና ችግር ልዩ ትኩረት ከሰጠች ሁለት አስርት ዓመታት ሊሞላት ነው። ሙስና የኢኮኖሚ እድገቱን ከመፈታተን ባሻገር የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ስርአቱ ላይ ችግር በማስከተል የህዝብ እርካታ ላይ ጉልህ ተጽእኖ ስለሚያሳድር የጸረ ሙስና አዋጅ አውጥታ አዋጁን የሚያስፈጽም የስነምግባርና የጸረ ሙስና ተቋም አዋቅራለች።
የሙስና ወንጀሎችን ጥቆማ ከመቀበል ጀምሮ የምርምራና ተጠርጣሪዎችን የመክሰስ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ከዚህ በተጨማሪ ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠር ዜጎችን በስነምግባር የማነጽ ስራ ሲያከናውን ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የሙስና ወንጀል ምርመራና ክስ ምስረታ ወደ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተዘዋውሮ ተቋሙ የስነምግባር ማነጽ ላይ እንዲያተኩር ተደርጓል። ተቋሙ ከተመሰረተ ጀምሮ በርካታ የሙስና ወንጀሎችን መርምሮ ክስ በመመስረት የህግ እርምጃ እንዲወሰድ አድርጓል። በዚህ ውስጥ በሚኒስትር ደረጃ ያሉ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትም ይገኙበታል። ይህ ሃገሪቱ የሙስናን ችግር ለማቃለል የሰጠችውን ትኩረት ያመለክታል።
የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ የተወያየበት ሌላው አጀንዳ የአህጉሪቱን ብልጽግና እውን ለማድረግ ሃገራት ከግሉ ዘርፍ ጋር ተቀራርበው መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ የሚመለከት ነው። ከዙሁ ጋር የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የሚመሰረትበት ሁኔታም ላይ ውይይት አድርጓል።
ከግል ባለሃብቶች ጋር ተቀራርቦ በመስራት ረገድ ኢትዮጵያ ለብዙዎቹ የአፍሪካ ሃገራት ሊተርፍ የሚችል ተሞክሮ አላት። ኢትዮጵያ የግል ባለሃብቶችን የሚያበረታታ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ቀርፃ ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በሃገሪቱ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የውጭና የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች በተለያየ የኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ ሃብታቸውን አውለዋል። በሚሊየን ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል ፈጥረዋል። ለአንድ ተኩል አስርት ዓመታት በተከታታይ ለተመዘገበው እድገት የግል ባለሃብቶች ኢንቨስትመንት የማይናቅ አስተዋዕኦ አበርክቷል። ይህ የግል ባለሃብቶችን የሚያበረታታ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትም በአማካይ በዓመት 12 በመቶ እንዲያድግ አድርጓል። በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ዓመታዊ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ደርሷል። ይህም በአጠቃላይ ወደምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ከሚመጣው ግማሽ ያህሉን ይሸፍናል።
ከዚሁ ከኢኮኖሚ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የህብረቱ ጉባኤ የተወያየበት ሌላው ጉዳይ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ምስረታን የሚመለከት ነው። የ2063 የበለጸገች አፍሪካን የመፍጠር የህብረቱ ራዕይ እንዲሳካ የአፍሪካ ሃገራት ኢኮኖሚያቸውን ከማሳደግ ባሻገር በመሃከላቸው ያለውን የንግድ ልውውጥ ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል። ለዚህም የንግድ ልውውጥ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ከእነዚህ እርምጃዎች መሃከል አንዱ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና መመስረት ነው። ይሁን እንጂ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ተግባራዊነት ደከም ያለ የተወዳዳሪነት አቅም ያላቸውን ሃገራት አርሶ አደሮች ሊጎዳ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ኢትዮጵያ አሳስባለች።
የህብረቱ ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ሃገራት ነፃ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት ይፋ ተደርጓል። ከዚህ ቀደም አንዳንድ ሃገራት የአፍሪካ አየር መንገዶች ወደ ሃገራቸው በሚያደርጉት ሳምንታዊ በረራ ቁጥር ላይ የሚጥሏቸው ገደቦች እንዲሁም ለአየር ትራንስፖርት እንዲጠቀሙ የሚያስቀምጧቸው የአውሮፕላን ዓይነትና መጠን የዘርፉን እድገት ገድቦት እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ። ህብረቱ በጉባኤው ላይ ይፋ ያደረገውን ነጻ የአየር ትራንስፖርት ስምምነት 23 ሃገራት ፈርመዋል። የተቀሩት ሃገራት በሂደት የውስጥ ጉዳዮቻቸውን እያስተካከሉ ስምምነቱን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ስምምነት የአፍሪካ ሃገራት በቀልጣፋ የእርስ በእርስ የአየር ትራንስፖርት እንዲገናኙ የሚያስችል ነው ተብሏል። በተጨማሪም ከ300 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች ቀጥተኛ እንዲሁም ከ2 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑት ደግሞ በተዘዋዋሪ መልኩ የስራ እድል እንደሚፈጥርም ተነግሯል። የአፍሪካ መንገደኞችን ቁጥር በ5 ሚሊየን እንደሚጨምርም ተነግሯል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጠንካራ አየር መንገድ ያላት ሃገር በመሆኗ ከዚህ ነጻ የአየር በረራ ስምመነት ትጠቀማለች። ደከም ያለ የአየር መንገድ ያላቸውም ሃገራት ከስምምነቱ ተጠቃሚ እነደሚሆኑ ባለሞያዎች አብራርተዋል።
በአጠቃላይ የአፍሪካ ህብረት 30ኛ መደበኛ ስብሰባ በርካታ ወሳኝ አጀንዳዎች ላይ ውይይት የተደረገበትና ውሳኔ የተላለፈበት ነው። ይሁን እንጂ የህብረቱ የከዚህ ቀደም ተሞክሮ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ማድረግ ላይ ክፈተት መኖሩን ያመለክታሉ። ለምሳሌ ከዓመታት በፊት ህብረቱ የአፍሪካ ሃገራት የኢኮኖሚያቸው መሰረት የሆነውን ግብርና እንዲያሳድጉ፣ ከአጠቃላይ ዓመታዊ የመንግስት ባጀታቸው ቢያንስ 7 በመቶውን ለዘርፉ ልማት እንዲመድቡ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር። ይሁን እንጂ መረጃዎች የሚያመለክቱት አሁንም አብዛኞቹ ሃገራት ለዘርፉ ከሚመድቡት አጠቃላይ ባጀታቸው ከ3 በመቶ በታች መሆኑን ነው። ኢትዮጵያ ለግብርና ልማት የበጀቷን 16 በመቶ ገደማ የምትመድብ መሆኗ ይታወቃል።
ባለፈው ዓመት ህብረቱ ባካሄደው ስብሰባ የወጣቶች የስራ ፈጠራ ዋና አጀንዳው እንደነበረም ይታወሳል። ይሁን እንጂ ሃገራቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ልዩ የወጣቶች የስራ ፈጠራ ተግባር እንዳላከናወኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ባለፈው አንድ ዓመት ከፍተኛ ተግባር አከናውናለች። የወጣቶች የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ፖሊሲዋን ከማሻሻል በተጨማሪ በ10 ቢሊየን ብር ተንቀሳቃሽ ፈንድ የስራ ፈጠራ ፕሮግራም ነድፋ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምራለች።
እናም የአፍሪካ ሃገራት አጀንዳ ቀርጸው ተወያይተው ውሳኔ ማሳለፍ ብቻ ሳይሆን ውሳኔውን ተግባራዊ ማድረግና አፈጻጸሙን እየተከታተሉ ማረም የሚያስችላቸውን ስርዓት በመዘርጋት ውሳኔን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። ውሳኔ ብቻውን ጥርስ የሌለው አንበሳ ነው።