Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዓባይ ለግብፅ ፖለቲከኞች የስልጣን እርካብ አይሆንም!

0 258

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዓባይ ለግብፅ ፖለቲከኞች የስልጣን እርካብ አይሆንም!

ሰሎሞን ሺፈራው

ሰሞኑን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ሲያነጋግሩ ከሰነበቱ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ በግብፅ የፕሬዚዳንታዊው ምርጫ ከመቃረቡ ጋር ተያይዞ እየተስተዋለ ስላለው የፖለቲካ ትኩሳት የሚያወሳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እናም በዚህ ረገድ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ አነጋጋሪ ነጥብ ሆኖ ያለው፤ አንድ ከፍተኛ የግብፅ ወታደራዊ መኮንን (ጀኔራል) በመጪው ምርጫ ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ለእስር የመዳረጋቸው ጉዳይ ነው፡፡ እኚህን ሳሚአናን  የሚባሉ ግብፃዊ የጦር ጀኔራል ዘብጥያ ለመውረድ ያበቃቸው ዋነኛ ጉዳይ፤ አሁን በመንበረ ስልጣኑ ላይ ካሉት አብዱል ፈታህ ዓልሲሲ ይልቅ በምርጫው የማሸነፍ ዕድል ይኖራቸዋል ተብሎ ስለሚታመን እንደሆነም ውስጥ አዋቂ ምንጮች ያመለክታሉ፡፡ ስለዚህ እኔም ለወትሮው ግብፃውያኑ ፖለቲከኞች መሰል የእርስ በርስ ሽኩቻና ፍጥጫ የሚስተዋልበት የስልጣን ፉክክር የሚኖርበት አጋጣሚ ላይ፤ በተለይም የዓባይ ተፋሰሱን ጉዳይ እያነሱ ህዝቡ እነርሱን ካልመረጠ በስተቀር ህልውናው ለአሳሳቢ የውሃ እጥረት አደጋ ሊጋለጥ እንደሚችል አድርገው መስበክን የሚያዘወትሩበት አግባብ መስተዋሉ የተለመደ ነገር መሆኑን ግምት ውስጥ አስገብቼ ጭምር ነው ጥቂት ለማለት የፈለግኩት፡፡

እንግዲያውስ አሁን በቀጥታ ወደዋናው የዚህ ፅሁፍ ማጠንጠኛ ነጥብ አልፌ፤ ዓባይ ተፋሰስን ለግብፅ ፖለቲከኞች የስልጣን መወጣጫ እርካብ የማድረግ ልማድ ቢያንስ ዛሬ እንኳን ሊቆም እንደሚገባው የሚያስገነዝብ የአንድ ተራ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ቅን አስተያየቴን ለመሰንዘር እሞክራለሁ፡፡ በዚህ መሠረትም፤ ከመላው የዓባይ ተፋሰስ አባል ሀገራት መካከል፤ይልቁንም ኢትዮጵያ፤ግብፅና ሱዳን ለዝንተ ዓለም እንዳይለያዩ ሆነው የተቆራኙበት ተፈጥሯዊ እውነታ ስለመኖሩ ለመረዳት ያን ያህልም ዕውቀት የሚጠይቅ ጉዳይ አይሆንም፡፡ ስለዚህም የሶስቱን ሀገራት ህዝቦች ህልውና የሚያቆራኘው የጋራ ዕጣ ፈንታ እጅጉን የጠበቀና ሊነጣጠል የማይችል የመሆኑን ያህል፤ ዕርስ በርስ ከመተሳሰብ በሚመነጭ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ቀጣናዊ የስምምነት ማእቀፍ ማስፈለጉ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ በግልፅ አነጋገር፤ የየትኛውም የዓባይ ተፋሰስ አባል ሀገር ፖለቲከኞች ለየራሳቸው ስልጣን መደላደል ሲሉ የቀጣናውን ወንድማማች ህዝቦች እያቃቃሩና አንደኛውን የሌላኛው ህልውና ፀር አስመስለው እያቀረቡ የጋራ ጥፋትን ሊያስከትል የሚችል የጦርነት እሳት እንዲጭሩ ዕድል ሊሰጣቸው አይገባም የሚል ፅኑ እምነት ነው ያለኝ እኔ፡፡

ይሁን እንጂ በተለይም የካይሮ ፖለቲከኞች የፕሬዚዳንታዊ መንበረ ስልጣኑን ለመቆናጠጥም ሆነ ከተቆናጠጡ በኋላ ላለመልቀቅ ሲሉ፤ የግብፅን ህዝብ ድጋፍ ለማግኘት የሚጥሩበት አግባብ ‹‹ኢትዮጵያውያን የዓባይ ወንዝ ውሃን ገድበው ህልውናችንን አደጋ ላይ እንዳይጥሉት አደርጋለሁ›› የሚል እጅጉን አነካኪና አናቋሪ ፕሮፖጋንዳቸውን ከማዛመት ቦዝነው እንደማያውቁ የተፋሰሱን አባል ሀገራት ያለፈ ግንኙነት የሚያወሱ ታሪካዊ ሰነዶች ያትታሉ፡፡

ከዚህ በካይሮ ፖለቲካና ፖለቲከኞች ዘንድ ከትናንት እስከ ዛሬ ሲወርድ ሲዋረድ እንደመጣ ከሚነገርለት፤ ዓባይ ተፋሰስን እንደ ዋነኛ የስልጣን መቆናጠጫ ዕርካብ አድርጎ የመውሰድ ፕሮፖጋንዳዊ ቅኝት የተነሳም ነው የግብፅ ወንድም ህዝብ ኢትዮጵያውያንን፤ አንድ ቀን ወንዙን ሙሉ ለሙሉ አስቁመን ልንበቀላቸው እንደምንችል አድርጎ ሲገምተን የሚስተዋለውም፡፡ እናም ሀገራችን በዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ለመገንባት ቆርጣ ስለመነሳቷ መግለፅዋን ተከትሎ አብዛኛው ግብፃዊ ለብርቱ ስጋት የተዳረገበት ሁኔታ እንደተፈጠረ ይታመናል፡፡ እንዲያውም የኢፌዴሪ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፤ አቶ መለስ ዓለም ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙሃን ስለጉዳዩ በሰጡት ማብራሪያ ‹‹ዛሬ እያንዳንዱ ግብፃዊ ጠዋት ላይ ከእንቅልፉ እንደነቃ የመጀመሪያ ተግባሩ ቧንቧውን ከፍቶ ውሃ መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ ሆኗል›› ሲሉ ነው በዚያች ሀገር ህዝብ ዘንድ የተፈጠረውን ብርቱ ስጋት የገለፁት፡፡

በዚህን ያህል መጠን የተጋነነ የስጋት ስሜት ለመፈጠሩ እንደዋነኛ ምክንያት ሊወሰድ የሚችለውም፤ የራሷው የግብፅ ፖለቲከኞችና እንዲሁም ደግሞ ሚዲያዎች ናቸው፡፡ እንጂማ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ምንም እንኳን ግዙፍነቱ ባይካድም፤ ግን ደግሞ ግብፃውያኑን ወንድሞቻችንን የመጠጥ ውሃ እጥረት እንዲያጋጥማቸው እስከማድረግ የሚደርስ የጎላ ተፅእኖ እንደማያሳድር የኛ መንግስት ለማስረዳት ከመሞከር የቦዘነበት አጋጣሚ አለ እንዴ? ስለዚህ እንደኔ እንደኔ፤ መፍትሄው የግብፅ ወንድም ህዝብ፤ የካይሮ ፖለቲከኞችን የምርጫ ሰሞን ፕሮፖጋንዳ እየሰማ ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ህዝቦች ጋር በስጋት ዓይን የሚተያይበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር ሊሰመርበት የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ይህን ስልም ደግሞ፤ የዓባይ ተፋሰስን የውሃ ሀብት በተለይም ለኢትዮጵያ፤ ለሱዳንና ለግብፅ ወንድማማች ህዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ ዕጣ ፈንታ መቃናት እንዲበጅ አድርጎ ትርጉም ላለው የጋራ ጥቅም የማዋል አስፈላጊነትን አምኖ የማይቀበል መንግስት በየትኛውም አባል ሀገር ውስጥ መኖር የለበትም ማለቴ እንጂ የካይሮዎቹን ፖለቲከኞች ብቻ ለመኮነን እየቃጣኝ አይደለም፡፡

ምንም እንኳን የታችኞቹ የተፋሰሱ አባል ሀገራት ‹‹ናይል›› እያሉ ለሚጠሩት የዓባይ ወንዝ ውሃ፤ ከ85 በመቶ የማያንሰውን ድርሻ የምታዋጣው ሀገራችን ኢትዮጵያ ስለመሆኗ ተደጋግሞ የተነገረ ጉዳይ ቢሆንም፤ ግን ደግሞ በሌላው ክፍለ ዓለም እንደሚደረገው ሁሉ፤ እያንዳንዱን አባል ሀገር ሊያስማማ የሚችል ፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ለተመሰረተ ግልፅ መርህ መገዛት ለሁሉም ወገን ዘላቂ ዕጣፈንታ ዋስትና ያለው ህልውና እንደሚበጅ ለመረዳት የተለየ ዕውቀት ስለማይጠይቅ መንግስታቱ ይህን ሀቅ ላለመቀበል ሲያንገራግሩ የሚታዩበትን አግባብ የቀጣናው ህዝቦች አምርረው ሊቃወሙት ግድ ነው፡፡ እናም ከዚህ አኳያ በተጠቃሾቹ ሦስት የዓባይ ተፋሰስ አባል ሀገራት ውስጥ ስለሚስተዋለው የፖለቲካና ፖለቲከኞች አሉታዊ ተፅዕኖ አንስተን እውነቱን መነጋገር ካለብን፤ የግብፅን መንግስታት ያህል የዓባይ ወንዝ ውሃን እንደዋነኛ የስልጣን መወጣጫ እርካብ ሲጠቀምበት የሚታይ የለም ማለት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ይህን ዓይነቱ የካይሮ ፖለቲካና ፖለቲከኞች ከትናንት እስከ ዛሬ የሚታወቁበት እጅጉን ስር የሰደደ ልማድ አሁንም ድረስ እንደቀጠለ መሆኑን ልብ ስንልም ደግሞ፤ ጉዳዩ ያሳስበን ዘንድ ግድ ሆኖ ያሰማኛልና ነው እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አስተያየቴን ከመሰንዘር አለመቦዘኔ፡፡

ለዚህ የመከራከሪያ መሰረተ ሃሳብ ተአማኒነት የተሻለ ምሳሌ ተደርጎ ሊጠቀስ የሚገባው ጉዳይ ደግሞ፤ ከፕሬዚዳንት ሁስኒ ሙባረክ በኋላ ወደ ስልጣን የመጡት የግብፅ መንግስታት መሪዎችም ጭምር፤ የዓባይ ተፋሰስን ጉዳይ በሚመለከት ከቀድሞዎቹ የካይሮ ፖለቲከኞች እንብዛም የተለየ አቋም እንደሌላቸው የሚያመለክት አዝማሚያ ማሳየታቸው ነው፡፡ ለአብነት ያህልም፤ ሆስኒ ሙባረክን ተክተው በግብፅ ፕሬዚዳንታዊውን መንበረ ስልጣን የመቆናጠጥ ዕድል የገጠማቸው፤ መሐመድ ሙርሲ ከወራት ላልበለጠ ጊዜ ያቺን ሀገር የመሩበት አግባብ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የጀመረችውን የህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ እንድታቆም ለማድረግ ያለመ የሚመስል አላስፈላጊ ዛቻና ማስፈራሪያ ከመሰንዘር የተቆጠቡት አጋጣሚ እንዳልነበር ማስታወስ ይቻላል፡፡ እርሳቸውን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ  አይቶ እንዳላየ ባለፈው መፈንቅለ መንግስት አስወግደው የካይሮውን ፕሬዚዳንታዊ መንበረ ስልጣን ለመቆናጠጥ የበቁት የቀድሞው ጀኔራል መኮንን አብዱል ፈታህ ዓልሲሲሰም እንዲሁ፤ የዘመነ ቅኝ አገዛዙን የዓባይ ተፋሰስ አባል ሀገራት ኢ.ፍትሐዊ ግንኙነት ለማስቀጠል እንደሚፈልጉ እየገለፁ ስለመሆናቸው ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡ ይልቁንም ደግሞ የቀድሞው ጀኔራል አብዱል ፈታህ አልሲሲ ለሁለተኛ ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚቀርቡበት ጊዜ እየተቃረበ በመጣ ቁጥር፤ ንግግራቸው ሁሉ ‹‹የግብፅን ህዝብ አንድ ጠብታ የውሃ ድርሻ አሳልፈን እንደማንሰጥ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ!›› ወዘተ የሚል ቅኝትን የተከተለ መሆን ጀምሯል ነው የሚባለው፡፡

ይሄን መሰሉ በግብፅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማሸነፍ ሲባል ብቻ የዚያችን ሀገር ወንድም ህዝብ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያውያን ጋር የሚያቃቅር መሰረተ ቢስ ስጋት የመፍጠር የካይሮ ፖለቲከኞች ፕሮፖጋንዳዊ ቅስቀሳ፤ ዛሬ የተጀመረ አይደለም ሊባል ቢችልም፤ አሁን ላይ ጉዳዩን ከወትሮው በተለየ መልኩ ጥንቃቄ የሚያሻው እንዲሆን የሚያደርጉ አሳማኝ ምክንያቶች ስለመኖራቸው ግን ደፍሮ መናገር ያቻላል፡፡ እንዴት ብትሉኝም ደግሞ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የህዳሴ ሃይል ማመንጫ ግድብ ሲጠናቀቅና ኤሌክትሪክ የማመንጨት ተግባሩን ሲጀምር የቧንቧቸው ውሃም ምንጭ እንደሚቆም አድርገው እያሰቡ በአጉል የስጋት ስሜት እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ግብፃውያን ጥቂት አይደሉም ሲሉ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ሰሞኑን መናገራቸው ይታወሳልና ነው፡፡ ስለዚህም ከጥቂት ወራት በኋላ እንደሚካሄድ ለሚጠበቀው የግብፅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በተፎካካሪነት የሚቀርቡት የካይሮ ፖለቲከኞች አሁንም እንደተለመደው ሁሉ፤ የዓባይ ተፋሰስን ጉዳይ ለእነርሱ ስልጣን መቆናጠጫ መሰላል አድርገው ሊጠቀሙበት እንዳይሞክሩ መላው የዚያች አገር ሰላም ወዳድ ህዝብ ከወዲሁ መንቃት ይኖርበታል የሚል ነው የኔ መልዕክት ሲጠቃለል፡፡ አለበለዚያ ግን ግብፃያኑ ወንድሞቻችን የግድቡን ግንባታ ሂደት ከመጠናቀቅ ላያግዱት ነገር ራሳቸውን ባልተገባ ስጋትና ጭንቀት ምክንያት ይጎዱ እንደሆነ እንጂ ከእንግዲህ እውነታውን መለወጥ አቅም አይኖራቸውም፡፡ የሚያዋጣው መንገድ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር ሃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን ወደ ካይሮ ተጉዘው ስለጉዳዩ የተናገሩትንና በግብፅ ብሄራዊ ቴሌቪዥን የተላለፈውን እውነት አምኖ መቀበል እንደሆነም ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡ መዓ ሰላማት!  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy