Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዕውነት ይቃረናሉ?

0 371

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዕውነት ይቃረናሉ?

ወንድይራድ ኃብተየስ

በኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ውስጥ ሁለት ጉልህ ማንነቶች ይስተዋላሉ። እነዚህም የብሄር/የብሄረሰብ ወይም የቡድን ማንነቶችና ኢትዮጵያዊ ማንነት ናቸው። እነዚህ ሁለት ማንነቶችን   ሳይዛነፉ እኩል ሊዳብሩና ሊተገበሩ የሚገባቸው የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው።  እንደእኔ እይታ እነዚህን ሁለት ማንነቶችን የኢፌዴሪ የፌዴራል ስርዓት ማስታረቅ የሚቻልበትን ሁኔታ ፈጥሯል። ኦሮሞ ሆኖ ኢትዮጵያዊ፤ አማራ ሆኖ ኢትዮጵያዊ፤ ትግራይ  ሆኖ ኢትዮጵያዊ፤ ሶማሌ ሆኖ ኢትዮጵያዊ ወዘተ እየተቻለ የትምክህት ሃይሎች በደፈናው የቡድን ማንነትህን ካልተውክ ኢትዮጵያዊ አትባልም ሲሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ  ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል መስማት የሚያማቸው የጥበት ሃይሎች ለምን ኢትዮጵያ የሚል ቃል ሰማን ብለው  አገርን  ለማወክ ሲሯሯጡ  እናያለን።  እነዚህ የትምክህትና የጥበት ሃይሎች በኢትዮጵያ ከሽግግሩ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ትናንሽ ነገሮችን በማነፍነፍና በማጎን  በኢትዮጵያዊ ማንነትና በብሔር/ ብሄረሰብ ማንነቶች መካከል መጣረስ እንዲፈጠር አበክረው ሲሰሩ ቆይተዋል። በመስራትም ላይ ናቸው።  

እንደእኔ የእነዚህ ሁለት ማንነቶች መጣረስ አይታየኝም። ሁሉም በየፈርጁ መያዝ ብንችል ለአገራችን ድምቀት ናቸው። የብሔር ማንነታችንን በአካባቢያዊ አስተዳደሮች ልንጠቀምባቸው፣ ቡድናዊ ትስስሮቻችንን ልናጎለብትባቸው እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሌሎች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር የምንተሳሰርበት ሊሆን ይገባል። ኢትዮጵያዊ ማንነት ሌሎች ማንነቶችን ደፍጥጦ እንዲገኝ አለማድረግ በተመሳሳይ የቡድን ወይም የብሔር ማንነትን ከኢትዮጵያዊ ማንነት  በላይ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ የተሳሳተ የፌዴራሊዝም ስርዓት  እንዲፈጠር ምክንያት ስለሚሆን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። ሁሉንም በልክ በልክ የማናስኬደው ከሆነ ዋጋ ያስከፍለናል። ለጥበትና ለትምክህት ሃይሉ በር እንከፍታለን። በመሆኑም ህብረተሰቡ ይህን በአግባብ ተገንዝቦ ፍላጎቶቹን  ማስታረቅ ይኖርብናል።

የፌዴራል ስርዓታችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ወይም ቡድኖች አካባቢያቸውን  ራሳቸው በራሳቸው እንዲያስተዳደሩ ዕድል ከመስጠቱም  ባሻገር በመዕከላዊ መንግስትም እያንዳንዱ ቡድን ተገቢው ውክልና እንዲያገኝ  አስችሏል። ከዚህ በፊት በነበሩ የኢትዮጵያ መንግስታት እንኳን በፌዴራል ይቅርና በአካባቢ አስተዳደር ውክልና ያልነበራቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዛሬ በብሔራዊ ደረጃ የፖሊሲ አወጣጥ በአገሪቱ ቁልፍ ጉዳዮች ውሳኔ ማሳለፍ የሚችሉበት  ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል።  ይህ እውነታ ነው። ዛሬ ላይ የትኛውም ህዝብ ቢሆን  በተወካያችን አልተዳደርንም  እንዲሁም  በፌዴራል ደረጃ ተገቢው ውክልና አላገኘንም የሚል ቅሬታ ሲነሳ አይደመጥም። እከሌ እንዲህ አደረገኝ ማለት የማይቻልበት ሁኔታ በአገራችን ተፈጥሯል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን የፌዴራል ስርዓት ላይ ራስን በራስ በማስተዳደር ፅንሰ ሐሳብ ላይ የተሳሳተ ዕይታዎች ይስተዋላሉ። ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት የራስን ቋንቋና ባህልን መጠቀምና ማዳበር እንጂ  አናሳዎችን ማጥቃት መሆን የለበትም። በቅርቡ በአገራችን በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ያስተዋልናቸው አንዳንድ እጥረቶች አሉ። ቡድናዊ ማንነቶች ከኢትዮጵያ ማንነት እኩል ሊጎለብት ሲገባቸው  በአንዳንድ  አካባቢዎች  የቡድነትኘነት ስሜት በተሳሳተ መንገድ ተተርጉሞ አገርን በሚያጠፋ መልኩ ተመልክተናል።  ይህ ስሜት አንድነትን የሚሸረሽሩ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ የአገራችንን ሰላም የሚያውክ ነው። ለዚህ መጥፎ ስሜት ምክንያት የሆኑት ደግሞ የትምክህትና የጥበት አስተሳሰቦች ናቸው።  

የትምክህትና የጥበት ሃይሎች በሁለት ተቃራኒ ጽንፍ ቆመው የህዝቦችን አብሮነት የሚሸረሽር የአገራችንን አንድነት የሚያናጋ ድርጊት ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ ታይተዋል። እነዚህ ሁለት ሃይሎች ራሳቸውን በየጊዜው እየቀያየሩ፣ ለአገርና ለህዝብ መብት የቆሙ በመምሰል ወጣቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለማምራት ጥረት አድርገዋል። እነዚህ የጥፋት ሃይሎች ነገም ከዚህ ድርጊታቸው ይቆጠባሉ ማለት አይቻልም። በመሆኑም እነዚህን ሃይሎች የመታገል የእያንዳንዱ አገር ወዳድ ዜጋ ግዴታ ነው።

እነዚህ አካሎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አገራችንን ወደ ሁከትና ብጥብጥ ለመክተት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። በቅርቡ እንኳን  በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች በህዝቦች መካከል ቅራኔ እንዲፈጠርና የፌዴራል ስርዓቱ ችግር አድርገው ለማረብ ሲሯሯጡ ተስተውለዋል። እነዚህ ሃይሎች በፈጠሩት ሁከት ዜጎች ተገድለዋል፣ ለዘመናት ከኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለዋል፤ ንብረታቸው ተዘርፏል፣ የስነልቦና ጫና ደርሶባቸዋል ወዘተ በአጠቃላይ መልካም ያልሆኑ ነገሮች ለዘመናት በኑሩባቸው አካባቢዎች እንዲደርስባቸው ተደርጓል። እነዚህ መጥፎ ነገሮች ዳግም በአገራችን እንዳይከሰቱ ጥገኞችን መዋጋት የሁላችንም ግዴታ ነው። የትምክህትና የጥበት ሃይሉ ይህን አካሄድ  ከጀግንነትና  ከትግል ስልት እየቆጠሩት  ነው።  “አልሰሜን ግባ በለው አሉ”  ጽንፈኛው የዳያስፖራ  ፖለቲከኞች ይህ ቅጥ ያጣ አካሄድ  በወጉ ያጤኑት አይመስለኝም፤ ከዚህ  አይነት  አካሄድ  የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ  ሁላችንንም  ወደ እሳተ ገሞራው  የሚዶላን  ነው።

እነዚህ ሁለት ማንነቶች አንዱ በአንዱ መስዋዕትነት የሚገኝ ሳይሆን ሁለቱንም ማታረቅ የሚቻልበት ሁኔታ በፌዴራል ስርዓታችን ተመቻችቷል።  ከላይ እንዳነሳሁት መንግስት በዘርፉ  በቂ ልምድና እውቀት ካላቸው ምሁራን ጋር በቅርበት በመስራት ህዝቦች ስለፌዴራል ስርዓታችን በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ማደረግ ይኖርበታል። ከዚህ ባሻገር መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት በመስራረት የጥበትና የትምክህት መፈልፈያ የሆነውን ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋት ይኖርባቸዋል። በቀጣይ የብሄር ማንነቶችንና ኢትዮጵያዊ ማንነትን ለማጋጨት ጥረት የሚያደርጉ አካላትን ከድርጊታችሁ ታቀቡ ካላልናቸው ችግሮቻችን ሊያወሳሰቡብን ይችላሉ። መንግስትም  የህግ የበላይነትን  ከድርድር ማቅረብ የለበትም።   

ኪራይ ሰብሳቢዎች መቼም ቢሆን ለህዝብና አገር የሚጨነቁበት ነገር አይኖርም። ሁሌም ቢሆን  የእነዚህ  ሃይሎች  ህልም  የስልጣን ማማ ላይ መሰቀል ነው።  በመሆኑም ለእነዚህ ሃይሎች  መግቢያ የሚሆኑ  መንገዶችን ሁሉ  መዝጋት ተገቢ ነው።  መንግስት የህዝቦች እውነተኛ ጥያቄዎችን በመለየት በወቅቱ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አንዱ የጥገኞችን አካሄድ ማክሸፍ ይኖርበታል።  እኛ ኢትዮጵያዊያን ሁላችንም ከተለያዩ  ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ብንሆንም ሁላችንንም በአንድነት የሚያስተሳስር  የጋራ ማንነታችን ኢትዮጵያዊነት መኖሩን ማሰብ ተገቢ ነው።  ትናንሽ ግጭቶች ነገም ተነገወዲያም መቼም መከሰታቸው አይቀርም። እንኳን በአገር ደረጃ ይቅርና  ግጭት በቤተሰብ ደረጃም ይከሰታል። ይሁንና ዋናው ነገር ለችግሮች በሰለጠነ መንገድ መፍትሄ መፈለግ ትልቅ ነገር ነው። የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ደግሞ በዚህ ረገድ ራሱን በራሱ ማስተካከል የሚችልበት አሰራር ያለው  ስርዓት ነው። በየአካባቢው የተከሰቱ ግጭቶችን ስንመለከታቸው በህዝቦች መካከል ስር የሰደደ ለግጭት የሚዳርግ ቅሬታ የለም።  

የቡድንና ኢትዮጵያዊ  ማንነቶች ማመጋገብ የማይቻል ከሆነ   አደገኛ ነገር ሊፈጠር ይችላል። ለሰላማችን መደፍረስ ለአንድነታችን መላላት መክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  በአንድነት ሊዋጋቸው ይገባል።  እንዲህ ያሉ አካሄዶች በክልል መንግስታትም ይሁን በፌዴራል መንግስቱ በወቅቱ ተገቢው እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። ጥፋተኞች ለህግ ቀርበው እንደየጥፋታቸው ተጠያቂ መሆን መቻል አለባቸው። በቅርቡ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው ጥፋተኞች ላይ ተገቢው እርምጃ እንደሚወሰድ ማመላከቱ በጎ ጅምር ነው።  

የፌዴራል ስርዓታችን የአገሪቱን ሁለት መሰረታዊ ችግሮች ቀርፏል። የመጀመሪያው ለዘመናት የአገራችን ችግር ሆኖ የኖረውን የፖለቲካ ችግር ማለትም የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የማንነትና የዕኩልነት ጥያቄዎች በመመለስ  ዴሞክራሲያዊ  ስርዓት መገንባት አስችሏል። ሌላው ደግሞ  የአገሪቱን የልማት ፍላጎትን መመለስ የሚያስችል አሰራርን ዘርግቷል።  የፌዴራል ስርዓቱ ፍተሃዊ ልማትን በማስፈንና ድኅነትን በመቀነስ ረገድ ጉልህ  ሚና ተጫውቷል። ባለፉት ሥርዓቶች ፍትሃዊ የሆነ የሃብትና የስልጣን ክፍፍል አለመኖር፣ የህዝቦች የማንነት ጥያቄ በሰላማዊ መንግድ ለማስተናገድ አለመፈለግ እንዲሁም የዜጐች መብትና ነፃነት ያለመከበሩ ተደማምሮ በአገራችን ለረጅም ዘመናት ለቆየ አለመረጋጋት፣ አለመተማመንና ከዚህም ባለፈ ለአስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት ዳርጎን ቆይቷል። ይህን ችግር ከመሰረቱ የቀረፈው የፌዴራል ስርዓታችን ነው። በመሆኑም የአዲሲቷ ኢትዮጵያ እስትንፋስ የሆነውን  ስርዓት የመንከባከብና የመጠበቅ ሃላፊነት  የሁሉም ሰላም ወዳድ ዜጋ ግዴታ ሊሆን ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy