የሀገር ሰላም የሕዝብ ሰላም
ይልቃል ፍርዱ
ከሰላም እንጂ ከጦርነትና ከግጭቶች ያተረፈ ሕዝብ የለም፡፡ የግጭቶች ሁሉ መጨረሻው አስከፊ የሆነ ጥፋት ነው፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ የማይበጅ ጥፋት፡፡ ግጭትና ሁከት ሰላምና አብሮነትን የሚያደፈርስ በዚህም በሕብረተሰቡ ውስጥ መረጋጋት እንዳይኖር የሚያደርግ በስተመጨረሻም ሀገርን ምስቅልቅል ውስጥ የሚከት ነው፡፡
ከሰሞኑ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት ግጭቶች፤ መንገዶችን መዝጋት፤ የሕብረተሰቡን መገልገያዎች የማውደም ተግባራትን ለተመለከተ በዚህ መልኩ ሀገራዊ ውድመትን ለማምጣት ሆን ብለው የተሰለፉ ኃይሎች መኖራቸውን በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ከሚካሄድ የጥፋትና የውድመት ድርጊት ተጠቃሚ የሚሆን ማንም የለም፡፡ ንብረቶቹ የግለሰብም ሆኑ የመንግስት አገልግሎት የሚሰጡት ለሕዝብ ነው፡፡ የሚጠቀምባቸው ሕዝብና ልጆቹ ናቸው፡፡ ንብረትነታቸውም የሀገር ነው፡፡ ሊጠፉ ሊወድሙ አይገባም፡፡
በዚህ ብቻ አይገለጽም፡፡ ዜጎች ለፍተው ደክመው ያፈሩት ሀብትና ንብረት ሊቃጠል ሊወድም አይገባውም፡፡ ሀብትና ንብረቱ የተገኘው የሕዝብ ሀብትን በመዝረፍ ነው የሚሉም ካሉ ያንን ሊወስን የሚችለው ማስረጃና ፍርድቤት ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ በትክክል በሙስና የተገኘም ከሆነ በማስረጃ ከተረጋገጠ ፍርድቤት ከወሰነ መንግስት ይወርሰዋል፡፡ ተመልሶ ለሕዝብ አገልግሎት ይውላል፡፡ ሁሉም ዘርፎ ነው የሰራው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ መያዝ አይገባም፡፡ ለፍተው ደክመው ሀብትና ንብረት ያፈሩ ብዙ ዜጎች እንዳሉም መረዳት ይገባል፡፡ ሀብትና ንብረታቸውን ማቃጠል ግለሰቦቹን ከመጉዳት ባሻገር የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡
በስሜታዊነትና በጀብደኝነት መንፈስ በመነሳት ንብረትና መኪና ማቃጠል በዘረኝትና በጥላቻ ተውጦ የዜጎችን ሕይወት ማጥፋት ከወንጀልም የከፋ ወንጀል ነው፡፡ ዛሬ ነገ ሳይባል ሊቆም ይገባዋል፡፡ በዚህ የሚጠቀም ማንም የለም፡፡ ይህ አካሄድ ጤነኛ ተቃውሞ ሊሆን አይችልም፡፡ ሀገርን የመንግስትና የሕዝብን ሀብት የማውደም ተልእኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች የሚፈጽሙት በስርአተ አልበኝነት የተሞላ አስከፊና አስነዋሪ ድርጊት ነው፡፡ ሁሉም ዜጋ በጋራ ሊከላከለው ሊታገለው ሊያስቆመው ይገባል፡፡
መንግስት ይመጣል፡፡ መንግስት ይሄዳል፡፡ የሀገርና የሕዝብ ሀብት መቸም ሆነ መቸም የሀገርና የሕዝቦችዋ ነው፡፡ የሁሉም ዜጋ የጋራ ሀብት ሆኖ ይቀጥላል፡፡ በታዳጊና በድሀ ሀገር የኢኮኖሚ አቅም የተገነቡ ድርጅቶችን ተቋማትን በእሳት ማቃጠል ማጋየት ማውደም እጅግ የከፋ ጸረ ሀገርና ጸረ ሕዝብ ድርጊት ስለሆነ ሊኮነን ሊወገዝ በፍጥነት መቆም ያለበት ነውረኛ ድርጊት ነው፡፡
ለሀገር ልማትና እድገት የተሰሩትን የልማት ስራዎች መንገዶች ድልድዮች ተቋማት ማበላሸት ከስራ ውጪ እንዲሆኑ ማድረግ ሀገራዊ ልማትና እድገትን በሚደግፍ ዜጋ ይፈጸማል ብሎ ለማመን በእጅጉ ይከብዳል፡፡ እነዚህ ንብረቶችና ሀብቶች ብዙ ሚሊዮን የሀገር ሀብት የፈሰሰባቸው ለዛሬውም ለሚቀጥለውም ትውልድ የሚጠቅሙ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ ይህን ድርጊት መፈጸም በሕዝብም በሀገርም ተጠያቂ ያደርጋል፡፡
መንግስት ከሕዝቡ የተነሱትን ጥያቄዎች ለመመለስ በትጋት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በተጨባጭ የሚታዩ ለውጦችን በአጭር ግዜ ውስጥ እያስመዘገበ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ደረጃ በደረጃ ብዙ ጥያቄዎች ሊመለሱ ይችላሉ፡፡ ይሄንን ለመስራት ግዜና ትእግስት ይጠይቃል፡፡ በስሜታዊነትና በእብደት እየጋለቡ የሀገር ሀብት ማውደምና ማቃጥል መልሶ ሀገርን የድሕነት ቁልቁለት ውስጥ ከመክተት የሕዝብን የድሕነት ኑሮና መከራ ከማራዘም ውጭ የሚጠቅም አንድም ምንም ነገር የለውም፡፡
አውራ መንገዶች ሕዘብን ከሕዝብ የሚያገናኙ እንደገናም ንግድንና ማሕበራዊ ግንኙነትን የሚያሳልጡ ናቸው፡፡ ብዙ ቢሊዮን የወጣባቸው በብድርም የተሰሩ የሀገር ሀብት ናቸው፡፡ መንገዶችን መዝጋት፤ ትራንስፖርት እንዳይኖር ማስቆም፤ ሱቆችና ንግዶች ስራቸውን እንዳይሰሩ ማስፈራራት ማገድ የከፈቱትን ማቃጠል፤የመንግስት ተቋማትን ቢሮዎችን በእሳት ማጋየት ይህ ሁሉ የእብደት ስራ በአንድ ድሀ ሀገር ኢኮኖሚ ላይ ሀገርን የማውደምና የማጥፋት ተልእኮ እንጂ መቸውንም ለውጥ የመፈለግ ጥያቄ እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡
ለውጥ ቢመጣም ነገም ከነገወዲያም ወደፊትም የሀገር የሕዝብ የትውልድ ሀብት ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ሲወድሙ የከረሙት ንብረቶችና ሀብቶች ሁሉ የሀገርና የሕዝብ ሀብት ናቸው፡፡ለውጥ ፈላጊ ኃይል ሀገሬ ናት መልካሙንና ደጉን ሁሉ እመኝላታለሁ፤ የሀገሬ ሀብት የእኔ ነው የሚል እምነት ያለው የሀገር ሀብት አያወድምም፡፡ አያጋይም፡፡ በስሜታዊነትና በጀብደኝነት እየተነሳ ጥፋት አያደርስም፡፡ ዛሬም ነገም ወደፊትም ሀገሩ ነች፡፡ የለማውን ማፍረስ በብዙ ድካምና ልፋት ብዙ ሚሊዮን የሀገር ሀብት ፈሶበት የተሰራው ሁሉ የራሴ ነው የሚጠቅመው ለወገኔ ነው ሊጠፋ ሊቃጠል ሊወድም አይገባም የሚል የጸና ሀገራዊ ፍቅር ያለው አቋም መያዝ የሚበጀው ለሁሉም ነው፡፡
ሠራዊቱንም በተመለከተ ሠራዊቱ የተገነባው የተውጣጣው ከመላው ኢትዮጵያ ነው፡፡ ሠራዊቱ የሕዘብ ልጅ ነው፡፡ በጸጥታና ሰላም ማስከበር ግዳጅ ላይ ሲሰማራ የተቻለውን ሁሉ ጥንቃቄ ያደርጋል፡፡ አላስፈላጊ ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ መገፋፋት በሠራዊቱ ላይ መተኮስ መግደል በራስ ወገን ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ሠራዊቱን ሊያስቆጡት ይችላሉ፡፡ መሳሪያ ለመንጠቅ መሞከር ቀጣይ ሁኔታውን ይለውጠዋል፡፡ ለምን ይህን ማሰብ ማድረግስ አስፈለገ ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የትንኮሳ መንገድ ተገቢ አይደለም፡፡
ሠራዊት መደበኛ ከሆነው የሀገርን ብሔራዊ ድንበርና ሉአላዊነት የአየር ክልልዋን ከማስጠበቅ ግዳጅ አልፎ በሀገር ውሰጥ የሰላም መደፍረስና አለመረጋጋት ሲያጋጥም ሰላም በማስከበር ግዳጅ ይሰማራል፡፡ ሰላምን የሕዝብን ሕይወትና ደሕንነት ይጠብቃል፡፡ ይሄ አዲስ ጉዳይ አይደለም፡፡ በመላው አለም የሚሰራበት ሲሰራበትም የኖረ ነው፡፡
እንደ ሕዝቡ ሁሉ ለሠራዊቱም ሀገሩ ነች፡፡ በደሙ በአጥንቱ ክብርና ነጻነትዋን ለማስከበር የቆመ የሀገርና የወገን መኩሪያ አስተማማኝ ክንድ ነው፡፡ ጥንትም ሠራዊት ተልእኮው ይሄ ነበር፡፡ ዛሬም እንደዚሁ፡፡ ሠራዊቱንና ሕዝቡን ለማጋጨት የሚነዛው ፕሮፓጋንዳ ውጤት አያስገኝም፡፡ለመከፋፈል የሚደረገውም ጥረት ሀገርን ከመበተን ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡
ሀገራዊ ሰላም ለማስከበር ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ዜጎች ከሠራዊቱ ጎን በመቆም ሰላማቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡ በአጠቃላይ ከሚታዩት የሰላም መደፍረስ ሁኔታዎች ስንነሳ የሕዝቡ ጥያቄ በአግባቡ መመለስ በጀመረበት በዚህ ወቅት ወደሁከትና ትርምስ የሚያስገባ ንብረትና ሀብትን የማውደም ድርጊቶች ሊወገዙ ሊኮነኑም ይገባል፡፡ ከጉዳት በስተቀር ሀገራዊ ትርፍና ጥቅም የላቸውም፡፡
በተመሳሳይ የስራ ማቆም አድማ በሚል ሲጠራ የነበረው አድማም ሮጠው በሚያድሩ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ግለሰብ ዜጎች በመንግስትና በሕዝብ ላይ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ከማድረስ ውጭ ያስገኘው ጥቅም የለም፡፡ በዚህ መንገድ ለውጥ እናመጣለን ብለው የሚያስቡ ካሉ የሀገርንና የሕዝብን ኢኮኖሚ በመግደል ሀገሪቱን በማሽመድመድ ውድቀት እንጂ ልማትና እድገት መቸም እንደማይኖር አያውቁም አይባልም፡፡
የፈለገው ይምጣ ብቻ ኢሕአዴግ ከስልጣን ይልቀቅ የሚለው አስተያየት በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ አያዋጣም፡፡ አለን ቢሉም የሌሉ ስመ ብዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው ያሉት፡፡ይሄ ደግሞ አፍጥጦ ላለው ሀገራዊ ችግር መፍትሄ ለማስገኘት ሰፊ ስራ መስራት እንዳለባቸው ያሣያል፡፡ ሰፊ የሕዝብ መሰረት ለማግኘት ብዙ ርቀት መሄድ አለባቸው፡፡
ኢህአዴግ ብቻ ከስልጣን ይልቀቅ ሰይጣንም ይሁን የፈለገው ይምጣ የሚለው አካሄድ ታላቅ ሀገራዊ ዋጋ እንዳያስከፍለን በጥንቃቄ ማሰብን ጠይቃል፡፡ አስተያየቱ ከፍተኛ መመረርን የሚያሳይ ቢሆንም ግዙፍና አቅም ያለው ከስህተቱም ተምሮ ዛሬም የተሻለ ሀገራዊ ውጤት ሊያስመዘግብ የሚችል ድርጅት መሆኑን አምኖ መቀበል የችግሩ ብቻ ሳይሆን የመፍትሄውም አካል ሁኖ የተሻለ እንዲሰራ አብሮ መቆምና መስራት ግድ ይላል፡፡
የትኛው ብቁና ሀገራዊ ኃላፊነትን መሸከም የሚችል የተቃዋሚ ፓርቲ አለ ብሎ መጠየቅ ከሕዝብ ይጠበቃል፡፡ ስምንት ሚሊዮን አባላት ያሉትን ድርጅት ማግለልም ሆነ አይመለከትህም ማለት በምንም መስፈርት አይቻልም፡፡ ለሀገር አይበጅም፡፡