Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዝባዊነት ማማ

0 406

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዝባዊነት ማማ

ዳዊት ምትኩ

መከላከያ ሰራዊታችን በሚፈፅማቸው ተልዕኮዎቹ ህዝባዊነትን ተመስርቶ ተግባሩን የሚወጣ ሃይል ነው። ሰራዊታችን እንኳንስ ለአገሩ ህዝብ ይቅርና በሰላም ማስከበር የተሰማራባቸው አገራት ሁሉ በህዝባዊነቱና በዲሲፕሊኑ የተመሰገነ ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያትም ይሁን በአሁኑ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎቹ በሚያሳያቸው ህዝባዊ ተግባርና በጠንካራ ዲሲፕሊን ሽልማቶች የተበረከቱለት የህዝብ ወገንተኛ ነው።

መከላከያ ሰራዊታችን በተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ ሰላም ማስከበር የቻለና ህዝባዊ አመኔታ የተጣለበት ነው። የመጀመሪያው የሆነው የሩዋንዳ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ህገ-መንግስቱ ከመጽደቁ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ በሠራዊታችን ተከናውኗል። ይህ ግዳጅ፤ ህገ-መንግስቱ እየተረቀቀ በነበረበት ዓመት ውስጥም በመሆኑ የሠራዊቱን ህዝባዊ ባህሪይ የሚያመላክት ነው ማለት  ይቻላል፡፡

በወቅቱ  በሩዋንዳ ውስጥ  በሁቱና ቱትሲ  መካከል  በተነሳው  የጎሳ  ግጭት  የዘር ማጥፋት ተግባር ተቀጣጥሎ ነበር፡፡ ይህን የዘር ማጥፋት  ወንጀል  ለማስቆም የሚችል ኃይል አልነበረም። ሰራዊታችን በቀረበለት ጥሪ መሰረት ወደ ስፍራው ሄዷል። መንግስትም ሠላም ወዳድ በመሆኑና  በሠራዊቱም ህዝባዊ አመለካከት ላይ ከፍተኛ እምነት  ስለነበረው፤ አስቸጋሪውን ተልዕኮ ለመወጣት ቃል ገባ፡፡

በመሆኑም ሠራዊታችን በሩዋንዳው የሠላም ማስከበር ተልዕኮው ድንቅ ያሰኘውንና ለማንም ያልወገነ ግዳጅን በተሰማራበት ቀጣና ፈጽሟል፡፡ ሠራዊታችን ለየትኛውም ጎሳ ሳይወግን ገለልተኛ እንቅስቃሴ በማድረጉ፤ በዚያች ስፍራ ከሁለቱም ባላንጣ ጎሳዎች (ሁቱና ቱትሲ) እኩል ፍቅርን ማትረፍ ችሏል፡፡ በዚህም ሠላምን በኃይል ሳይሆን በህዝባዊ ፍቅር በእጁ በማስገባቱ፤ የመንግስታቱን ድርጅት  ጨምሮ በርካታ ሠላም ወዳድ ኃይሎችን አድናቆት የተቸረው ሃይል ነው፡፡

ሠራዊታችን ለሁሉም ሩዋንዳዊያን ፍቅርን ሰጥቶ ፍቅርን በመቀበሉ፤ ለስኬታማነቱ ቁልፍ ምስጢር ነበር፡፡ ከመሰረቱ ጀምሮ በባህሪው  የህዝብ አጋር  በመሆኑ፣ ህዝብ ውስጥ ዘልቆ በመግባት የዘር ማጥፋቱ ወንጀል እንዲቀጥል ፍላጎት ያላቸው ፀረ- ሠላም ኃይሎችን አፍራሽ ወሬ እርቃኑን እንዲቀር ያደረገ የህዝብ ወገን ነው፡፡ ታዲያ በወቅቱ ተልዕኮውን ሲጨርስ ሁሉም ሩዋንዳውያን በለቅሶ ነበረ የሸኙት፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ሠራዊታችን ለፈፀመው ክቡር ተግባር  በወረታው ሜዳሊያ እንደሸለመው መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

የሠራዊታችን ሌላኛው ተልዕኮ በብሩንዲው ነው። ሠራዊታችን በብሩንዲ የተሰማራው በአፍሪካ ህብረት የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረት በወቅቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለሠላም ማስከበር ተልዕኮ እንዲሰማራ ሲወሰን ሀገራችን ከምትከተለው የሠላም ፖሊሲ አኳያ አንድ ሻለቃን ወደ ብሩንዲ በመላክ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥታለች፡፡

በዚህም ሠራዊታችን በብሩንዲው ተልዕኮን የተሰጠው ግዳጅ በተቃዋሚዎች መካከል የተደረሰውን የተኩስ  አቁም ስምምነትን ተግባራዊነት መቆጣጠር፣ ትጥቅ ማስፈታት፣ ለመልሶ ግንባታ ፕሮግራም ምቹ ሁኔታን መፍጠር እና የሀገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን ወደ ነበረበት  ሁኔታ መመለስ ነበር፡፡

ሠራዊታችንም በብሩንዲ ቆይታው ከባህሪው በመነጨ ሰፊ ህዝባዊና ሰብዓዊነቱ የሚያስገድዱትን በጎ ተግባሮች በመከወን ከህዝቡና ከብሩንዲ መንግስት አካላት ፍቅርና አክብሮትን አግኝቷል፡፡ በአፍሪካዊ ወንድማማችነት መንፈስ የህዝቡን ችግር  በመጋራት  በዚያች  ሀገር ዜጎች  ውስጥ ትልቅ  ትዝታን ጥሎ አልፏል፡፡ ምክንያቱም በርካታ የህዝባዊ ወገንተኝነት ተግባራትን ስለፈፀመ ነው፡፡ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ወላጆቻቸውን ላጡ ህጻናት ያደረገውን ድጋፍና በጦርነት ለተፈናቀሉ የሀገሪቱ ዜጎች ያደረገው እገዛ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህ ምግባረ- ሰናይ ተግባሩም የሀገሪቱን  የመንግስት አካላትንና ህዝቡን ስሜት  በእጅጉ በመሳፍ ፍቅርን አትርፎለታል፡፡

በላይቤሪያ የነበረው ተልዕኮም እንዲሁ የህዝቡን አመኔታ ማትረፍ ችሏል። ሰራዊቱ ህዝባዊ ባህሪውን ሰንቆ በላይቤሪያ ሠላምና መረጋጋትን በማስፈን፣ የተቃዋሚዎችን ትጥቅ  በማስፈታት፣ የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠበቅና በመልሶ ግንባታ እንቅስቃሴ ላይ ቀጥተኛ የልማት  ተሳትፎ በማድረግ  ግዳጁን ከህዝቡ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በአኩሪ ሁኔታ ሊፈጽም ችሏል፡፡

በተለይም ሠራዊታችን ካለው ቀለብ በመቀነስ ለተቸገሩ ላይቤሪያዊያን በመስጠት እንዲሁም በመንገድ ግንባታ፣ በድልድይ ስራ ወዘተ በመሳሰሉ ልማታዊ ተግባሮች በመሳተፍ ከራሱ በፊት ለህዝብ የቆመ ኃይል መሆኑን አስመስክሯል፡፡ ከዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቡ በመነጨም በዚያች ሀገር ምርጫ እንዲካሄድ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል፡፡ ዛሬ ላይቤራዊያን የኢትዮጵያን ሰራዊት ህዝባዊ ፍቅር በአያሌው ያስታውሱታል፡፡

የመንግስታቱ ድርጅትም ሠራዊታችን ላይቤሪያ እንደ ሀገር በሁለት እግሯ እንድትቆም ለነበረው ከፍተኛ ድርሻ በየዙሮቹ ሜዳሊያና ሪቫኖችን በመሸለም የላቀ ዕውቅና ሰጥተውታል፡፡

ሠራዊታችን በአሁኑ ሰዓት በሱዳን ምዕራባዊ ክፍል በሚገኘው የዳርፉር ግዛት በአማፂያንና በሀገሪቱ መንግስት መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ለመፍታት በሳም አስከባሪነት ተሰልፏል። ሰራዊታችን በየተሰማራባቸው በዳርፉር ወንድም ለሆነው የሱዳን ህዝብ በነጻ ህክምና በመስጠት፣ የውስጥ ተፈናቃዮች በታጣቂዎች ጥቃት እንዳይደርስባቸው ተከላክሏል።

አብዛኛው ክፍሉ በረሃማ በሆነው የዳርፉር ግዛት ውስጥ ውሃ ቆፍሮ በማውጣት ህብረተሰቡንና እንስሳቶቹን ከእንግልት በመታደግ እንዲሁም ከዕለታዊ ቀለቡ ቀንሶ ችግረኞችን በመርዳት ወዘተ… ህዝባዊ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ እያከናወነም ነው፡፡ በዚህም በአካባቢው ማህብረሰብና በመንግስት  ኃላፊዎች  እኩል ተቀባይነትንና  አድናቆትን የህዝብ ወገን ነው፡፡

ሌላኛው የሠራዊቱ ህዝባዊነት መገለጫ በአብዬ ግዛት በብቸኝነት በማከናወን ላይ የሚገኘው ተግባር ነው፡፡ መከላከያ ሠራዊታችንም ህዝብና መንግሥት የሰጡትን ተልዕኮ በቁርጠኝነት ተቀብሎ በተሰማራባቸው የግዳጅ አካባቢዎች ሁሉ በጠንካራ ህዝባዊ ወገንተኝነት ተግባሩን በብቃት፣ በጀግንነትና በሚያኮራ ሁኔታ መፈጸሙ በመንግሥታቱ ድርጅትም ይሁን በሁለቱም ተቀናቃኝ ወገኖች ጽኑ እምነትንና አክብሮትን ያጐናፀፈውና ብቸኛው የአብዬ የተልዕኮው ተመራጭ ሠራዊት ሊያደርገው ችሏል።

መንግስታችንና ህዝባችን በሰጡት አደራ መሠረት ሠራዊታችን ባከናወናቸው ሠላም ተኮር ተግባራት በተለይም ባለፉት የድል ዓመታት በዘርፉ ተወዳዳሪ ለመሆን በሰራቸው ጠንካራ ሥራዎች የበርካታ የአፍሪካ ህዝቦችና መንግስታት በሙሉ እምነት እንዲቀበሉት አድርጓል።

በሶማሊያ ውስጥም በአሚሶም የሰላም ማስከበር ስራ ከህዝቡ ጋር በመሆን የፈፀማቸውና እያደረጋቸው ያሉት ህዝባዊነትን የተላበሱ ተግባሮች የሠራዊቱን ማንነት የማያረጋግጡ ናቸው። በአዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ጁባ ውስጥም የሚያከናውናቸው ስራዎች በህዝቡ አክብሮትን እያተረፈ ነው።

እነዚህ ሁሉ ተግባሮች ሰራዊቱ የሰላም ማማ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው። ይህም ሰራዊቱ እንኳንስ ለሀገሩ ሰላም ቀርቶ በውጭም ህዝባዊ ሆኖ ተግባሩን የሚያከናውን ለህዝብና ለህዝብ ብቻ ታማኝ የሆነ ሃይል መሆኑን ያስረዳል። የሰላም ማማችን መኩሪያችንና መከታችን ነው።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy