የህዝባዊው ኃይል ዕለት
ዘአማን በላይ
እነሆ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ቀን ከየካቲት 1 ቀን 2010 ዓ.ም እስከ የካቲት 7 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ለስድስተኛ ጊዜ በመከበር ላይ ይገኛል። ዕለቱ የሰራዊቱ አባላት ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው። በደም መስጠት፣ በእግር ጉዞ፣ ከህዝቡ ጋር በመወያየት፣ በስፖርታዊና በሌሎች ተግባሮች በመከበር ላይ የሚገኘው የሰራዊቱ ዕለት፤ “ህዝባዊ ባህሪያችንን እያጎለበትን ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በመጠበቅ የሀገራችን ህዳሴ ዋስትና ሆነን እንቀጥላለን” በሚል መሪ ቃል ነው።
ርግጥ መሪ ቃሉ፤ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከማናቸውም የውስጥና የውጭ ፀረ-ሰላም ሃይሎችና አሸባሪዎች ከመከላከል በህገ መንግስቱ ተለይተው የተሰጡትን ተልዕኮዎች ተግባራዊ በማድረግ ላይ የሚገኘው መከላከያ ሰራዊታችን፤ ህዝባዊ ባህሪን የተላበሰና የሀገራችን ትንሳኤ ዋስትና ሆኖ ነገም እንደሚቀጥል የሚያሳይ ነው።
መከላከያ ሰራዊቱ ላለፉት ዓመታት ከህዝቡና ከሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን አስተማማኝ ሰላም ፈጥሮ የሀገራችን ልማት ፈጣንና ቀጣይ እንዲሆን የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። ይህን ተግባሩን ሲፈፅምም በአንድ እጁ ጠብ-መንጃ በለሌላኛው ደግሞ አካፋና ዶማ የያዘ የልማት ኃይል መሆኑን እያስመሰከረ ነው። ለዚህም በምሳሌነት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሰራዊቱ አባላት ባለፉት አምስት ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ወደ አንድ ቢሊዮን የሚጠጋ ብር ከደመወዛቸው አዋጥተው ቦንድ ገዝተዋል።
ምን ይህ ብቻ። የመከላከያ ሰራዊቱ አባላትና አመራሮች በተለያዩ ወቅቶች ለአቅመ ደካማዎች 65 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ድጋፍ አድርገዋል። 192 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጭም ለወላጅ አልባ ህጻናት ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን፤ የሀገራችንን የአረንጓዴ ልማት በመደገፍም በ“አንድ ኮዳ ለአንድ ችግኝ” መርህ ችግኞችን በመትከልና ከፀደቁም በኋላ በመንከባከብ በአካባቢ ጥበቃና በሌሎች መስኮች ድጋፍ አድርገዋል፤ በማድረግ ላይም ይገኛሉ። ይህም ሰራዊቱ ሀገራዊ ልማትን በመደገፍ ረገድ ምን ያህል በኃላፊነት መንፈስ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው።
ሰራዊቱ በተሰማራባቸው የግዳጅ ቀጣናዎች ሁሉ ተግባሩን በፍፁም ህዝባዊ ስሜት የሚያከናውን ነው። ግዳጁ በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ቅድሚያ የሚሰጠው ለህዝብና ህዝብ ብቻ ነው። ከየትኛውም ተፋላሚ ወገኖች ጋር የማይወግን፣ ተግባሩን ህዝባዊ ባህሪ ተላብሶ የሚፈፅም የህዝብ ተቆርቋሪ ነው።
በልማቱ መስክም ቀደም ሲል ለህዳሴው ግድብ ከደመወዙ እየቆረጠ የገዛው ቦንድ ባሻገር በሀገር ውስጥና በውጭ ተልዕኮዎች በርካታ ተግባራትን መፈፀም የቻለ የልማት አርበኛም ነው። ለምሳሌ ያህል በሀገር ውስጥ ህዝባችን በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲጠቃ ቀድሞ በመድረስ ንብረትና ሃብቱን ከጥፋት የመታደግ፣ የአቅመ ደካማ አባ ወራዎችንና እማ ወራዎችን እርሻ የሚያርም፣ የሚጎለጉል፣ የሚወቃ፣ የሚያበራይና በአላስፈላጊ ዝናብ ምርቱ እንዳይበላሽ የሚሰበስብ ህዝባዊ ወገንተኛ ኃይል ነው። አሳዳጊ አልባ ህፃናትን እርሱ ከሚበላው ቀለብ የተለየ እየገዛ ሰብስቦ የሚያሳድግ ለተተኪ ዜጎች አሳቢ ሃይል ነው።
በውጭ ሀገር የሰላም ማስከበር ተልዕኮውም ቢሆን፤ በጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎች እንዳይጎዱ የሚያግዝ፣ ካለው ዕለታዊ ቀለብ እየቀነሰ የሚሰጥ፣ ራሱን መስዋዕት አድርጎ የዚያችን ሀገር ህዝብ ከተቀናቃኞች የሚጠብቅ፣ አቅመ ደካማዎችን የሚንከባከብ፣ በኤችአይቪ/ኤድስ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ ህፃናት እስከ ተልዕኮው ፍፃሜ ድረስ ቀለባቸውን በመላክ ኋላ ላይም በዚያች ሀገር የተረጋጋ መንግስት ሲኖር በህዝብ ለተመረጠ መንግስት የሚያስረክብ ህዝባዊ ወገንተኛ ሃይል ነው።
እነዚህ ተግባሮች በሀገር ውስጥና በውጭ “ከሁሉም በላይ ለሀዝብና ለሀገር”፣ “ምንግዜም የተሟላ ስብዕና”፣ ያልተሸራረፈ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ” እና “በማንኛውም ጊዜ/ሁኔታ የላቀ ውጤት” የሚሉ እሴቶቹን አንግቦ ተልዕኮውን በህዝባዊ መንፈስ የሚፈፅመው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት መገለጫዎች ናቸው።
ርግጥ ይህ የሰራዊቱ ሁለንተናዊ ቁመና መታወቅ አለበት። ለዚህም ነው— ከ2005 ዓ.ም ተጀምሮ በየዓመቱ ሰራዊቱ የካቲት ሰባት ቀን በህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 27/88 የተቋቋመበትን ዕለት ለማስታወስ የሰራዊት ቀን የሚከበረው። የዕለቱ ፋይዳ የገዘፈ ነው።
ዕለቱ ሰራዊቱ የተቋቋመበትን መሰረታዊ ዓላማ መነሻ አድርጎ የመከላከያ ኃይሉን የረጅምና ጊዜያዊ ግቦች በሚያንፀባርቁ መሪ ቃሎች በየዓመቱ የሚከበረውም ለዚሁ ነው። እንደ አንድ ሀገር ሰራዊት የተሰጠውን ሀገራዊና ህዝባዊ ኃላፊነት በብቃት ለመፈፀም በየዓመቱ ቃሉን እያደሰ መቀጠል የሚያስችለው አንድ መድረክም ማለት ይቻላል።
እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በህገ መንግስት የተቋቋመ፣ ለህገመንግስቱና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ በፍፁም ታማኝነት ዘብ ለመቆም በሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ቃለ መሃላ የፈፀመ እንዲሁም የኢትዮጵያን ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ ዓላማና ግብ ለማሳካት የተሰለፈ፣ ታላቅ ኃላፊነትን የተሸከመ ህዝባዊና ህገ መንግስታዊ ኃይል ነው። ስለሆነም የሰራዊት ቀን መከበር የመከላከያ ሰራዊቱ የተጣለበትን ከባድ ህዝባዊና መንግስታዊ አደራውን እንዲወጣ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ፋይዳውም የገዘፈ ነው።
ከሁሉም በፊት ግን የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ህገ መንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ እሴቶች ለማጎልበትና የሀገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት የራሱ ድርሻ ምን እንደሆነ ዳግም የሚገነዘብበትንና ህገ መንግስታዊ እምነቱ ይበልጥ እየጠነከረ የሚሄድበትን ሁኔታ ይፈጥርለታል።
ከዚህ በተጨማሪ የሰራዊት ቀን መከበሩ ለሀገራችን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲሁም ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር ሲሉ ውድ ህይወታቸውን ለከፈሉና በከፍተኛ ጀግንነት የተሰው የሰራዊት አባላትን የሚያስብበትና ለወደቁለት ዓላማ ስኬት በፅናት መታገል እንዳለበት ቃሉን እያደሰ እንዲቀጥል የሚያደርገው ነው። ሰራዊቱ ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት የፈፀማቸው ወታደራዊ ግዳጆችን ጨምሮ ሰላም በማስፈንና ልማትን በማረጋገጥ ረገድ ያለውን ሚና ህብረተሰቡ እንዲያውቀው ለማድረግ ያለው አስተዋፅኦም ከፍተኛ ነው።
ዕለቱ መከላከያ ሰራዊቱ ያለውን አጠቃላይ ብቃትና ችሎታ የሚያሳይበት መድረክ በመሆኑም፤ ከውስጥም ይሁን ከውጭ የሀገራችንን የህዳሴ ጉዞ ለማደናቀፍ የተነሱ ጠላቶች ቢኖሩም እንኳን፤ ሰራዊቱ በቅድሚያ ለሰላም እንደሚሰጥ ያለውን የማያወላውል አቋም የሚያንፀባርቅበት ነው። ይህን እውነታም ሰራዊቱ በአከባበሩ ቀናት ውስጥ አንዱ በሆነው እሁድ ዕለት “የህዳሴው ግድብ የሰላም ምንጭ ነው” በሚል መፈክር የኢትዮጵያን፣ የሱዳንንና የግብፅን ባንዴራ በመያዝ ከቴዎድሮስ አደባባይ እስከ መስቀል አደባበይ ድረስ ካደረገው የእግር ጉዞ ለመረዳት የሚከብድ አይደለም። ርግጥም ሰራዊቱ የሰላም ኃይል መሆኑን በግልፅ አሳይቷል።
በሌላ በኩልም የሀገራችን ጠላቶች ህዳሴያችንን ለማደናቀፍ ከተንቀሳቀሱ የህይወት መስዕዋትነት በመክፈል ጭምር የህዳሴያችን ዋስትና ሆኖ እንደሚቀጥል የሚያረጋግጥበት ዕለት ነው—የሰራዊት ቀን። የትኛውም ጠላት አቅሙን ከሰራዊታችን አቅም ጋር እያነፃፀረ ከትንኮሳና አፍራሽ ድርጊቱ እንዲቆጠብ በማድረግ ሁሉን አቀፍ ወታደራዊ ብቃቱንና ቁመናውን የሚያሳይበት መድረክም ነው ማለት ይቻላል—ይኸው የህዝባዊው ኃይል ዕለት። አዎ! ሰራዊቱ በእግር ጉዞውና በሌሎችም ህዝባዊ ውይይቶች ወቅት ህይወቱን እከፈለ ለህዳሴያችን እውን መሆን እንደሚሰራ ቃል ገብቷል። ርግጥም እርሱ እየሞተ እኛን ለሚያኖረን ለዚህ የልማት ኃይል ክብርና ሞገስ ይገባዋል።
ታዲያ የሰራዊቱ ዕለት ፋይዳ እነዚህ ጉዳዩች ሁሉ ከግምት ውስጥ ገብተው የሚከበር መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ይገባል። ርግጥም ለሰባት ቀናት የሚከናወነው የሰራዊቱ ክብረ በዓል ህዝባዊ ወገንተኛ እንዲሁም የሰላምና የልማት ኃይል መሆኑን የሚያንፀባርቅበት ብሎም የተሰጡትን ህዝባዊነና ህገ መንግስታዊ ተልዕኮዎችን አጠናክሮ እንደሚፈፅም ዳግም ቃል የሚገባበት ዕለት ሆኖ የሚታወስ ነው።
እናም እኔም እንደ ዜጋ ለመላው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አባላትና አመራሮች፤ ዕለቱ ህዝባዊ ወገንተኝነታቸውን ይበልጥ የሚያጠናክሩበት፣ የሰላምና የልማት ኃይል በመሆን የሀገራቸው ህዳሴ ዋስና ጠበቃ በመሆን የብስራቱ ተቋዳሽ እንዲሆኑ በመመኘት ይህችን አጭር ፅሑፌን እቋጫለሁ። መልካም የሰራዊት ቀን!