Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዳሴ ጉዟችን አመላካቾች

0 244

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዳሴ ጉዟችን አመላካቾች

                                                      ዘአማን በላይ

የኢህአዴግ አመራሮች ድርጅቱ ያደረገው በስራ አስፈፃሚ ደረጃ ያደረገውን ግምገማ ተከትሎ፤ ግምገማው ወደ ሁሉም አባል ድርጅቶች ተላልፎ እንደሚቀጥል አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወቃል። በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረትም ይህ ፅሑፍ እስከተሰናዳበት ጊዜ ድረስ ሁለት ድርጅቶች በስራ አስፈፃሚና በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ግምገማ አካሂደው መግለጫ አውጥተዋል—ኦህዴድና ህወሓት። በእኔ እምነት የድርጅቶቹ መግለጫዎች የሀገራችን ህዳሴ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተካሄደ መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው። ይህ ፅሑፍም በሁለቱ ድርጅቶች መግለጫ ላይ የሚወሰን ነው።

የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አስር ቀናት በጥልቀት ከተወያየ በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ የህዝቡ ሰላምና አብሮነት በምንም መልኩ አደጋ ውስጥ እንዳይገባ የክልሉን ህዝቦችና መሪ ድርጅቱ ኦህዴድን በቅንጅት በመምራት የሀገራችንን ህልውና መታደግና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በስኬት እንዲጠናቀቅ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ቅድሚያ ሰጥቶ ተወያይቷል።

ድርጅቱ ከሚታወቅባቸው መለያ ባህሪያቱ እያንደንዱ ጉድለቶቹን ያለማመንታት መቀበልና ለማረም ጥረት ማድረግ መሆኑን የገለፀው መግለጫው፤ ይህ የዴሞክራሲያዊ ድርጅት ባህሪይ በመሆኑ ከህዝብ የሚነሱ ቅሬታዎችን ማድመጥ፣ ህዝቡን ከልብ ይቅርታ የመጠየቅና የእርምት ርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን በማመን የአፈፃፀም አቅጣጫ አስቀምጧል።

የፌዴራል ስርዓቱን አደጋ ውስጥ ሊጥሉ የሚችሉ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለይቶ አፋጣኝ ርምጃዎችን በመውሰድ የሕዝቡን መሻት ማሳካት ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው። በመሆኑም ድርጅቱ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል፣ አሳታፊ የፖለቲካ ስርዓት፣ ሰላምና ፍትህ እንዲሰፍን በጥብቅ ዲስፒሊን በመስራት የህዝብ እርካታን ማረጋገጥ ጊዜ የማይሰጠው መሰረታዊ አጀንዳ እንደሆነ ያምናል።

ይህም የኦሮሞ ሕዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመተባበር የሀገራችንን ቀጣይ ጉዞ የማቅናት ሚናውን ዛሬም እንደ ትላንቱ እንዲጫወት አስምሮበታል። ርግጥ ይህ የድርጅቱ አቋም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያለመን ራዕይ በመተግበር ረገድ ቁልፍ ሚና ሊጫወት የሚችል በመሆኑ ሊመሰገን የሚገባው ነው።

በኦህዴድ የሚመራው ታታሪው የኦሮሞ ህዝብ ለዚህች ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ትላንትም ይሁን ዛሬ ሲተጋ የመጣና ወደፊትም የሚተጋ በመሆኑ መግለጫው የድርጅቱን ቁርጠኛ አቋም የሚያሳይ ነው ብዬ አምናለሁ። በዚህ አጋጣሚ አመራሩ በየጊዜው ለሚወስዳቸው የማስተካከያ ርምጃዎች ያለኝን አድናቆት ሳልጠቁም አላልፍም።

ኦህዴድ ኢህአዴግ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እየተመራ መሆኑን ለመግለፅ አሁንም መግለጫውን መመልከት በቂ ነው። በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ያለውን ግንኙነት በዴሞክራሲ አግባብ በማጠናከር የጋራ ዓላማችንን ለማሳካት ርብርብ ማድረግና የሀገሪቱን ህልውና ከአደጋ መከላከል እንደሚገባ በዝርዝር መክሮ መሆን የሚገባውን አቅጣጫ አስቀምጧል። በዚህም ፌዴራላዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣሉ ሙስና እና ብልሹ አሰራሮችን፣ ህዝቡ በመሪ ድርጅቱ ላይ እንዲያምፅ ያስቻሉ የመልካም አስተዳደር እጦቶችን፣ ስልጣን ህዝብን ማገልገያ መሳሪያ መሆኑን በመዘንጋት በርስትነት ይዞ ለግል ምቾትና ጥቅም ቅድሚያ መስጠትን፣ በነፃነት ተዘዋውሮ የመስራት መብት ነፍጎ ህዝቦችን እስከማፈናቀል የደረሰ ድርጊትን፣ በኢንቨስትመንት ስም የመንግስትና የህዝብ መሬት መመዝበርን፣ የህዝቦች ሰላምና ሠጥታ መደፍረሱንና መሰል አደገኛ ድርጊቶችን ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ አምርሮ በመታገል የሀገራችንን ሕልውና መታደግ ልዩ ትኩረት የሚሹ ዐበይት ጉዳዮች ሆነው ቀርበው ጥልቅ ውይይት ተካሂደውባቸዋል።

በእኔ እምነት ይህ የድርጅቱ አቋም የሀገራችንን ህዳሴ ለማሳለጥ ገዥው ፓርቲ እያከናወነ ባለው ተግባር፤ ኦህዴድም ህዳሴውን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ችግሮችን በመለየት ዛሬም ህን ነገ ለመታገል ወስኗል። ይህ ትክክለኛ አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን፤ የህዳሴያችን መንገድ በአስተማማኝ ጎዳና እየተመራ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። እናም ኦህዴድ በዚህ ረገድ የወሰዳቸው ትክክለኛ አቋሞች ለሀገራችን ህዳሴ ዐብይ ሚና የሚጫወቱ በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ባይ ነኝ።

በተለይ ከህዝቡ ጋር ፊት ለፊት በመነጋገር እርካታን በመፍጠርና በዚያውም ልክ የተጠያቂነትን መንፈስ እንዲሁም የህግ የበላይነትን በማዳበር ማከናወን ያለበት ተግባር ወሳኝ ነው። ማዕከላዊ ኮሚቴው በአስር ቀን ጥልቅ ውይይቱ የወሰዳቸው የእርምት ርምጃዎች ድርጅቱ ምን ያህል የሀገራችንን ህዳሴ በማሳለጥ ረገድ የበኩሉን ሚና መጫወት እንደሚሻ ያመላከቱ በመሆናቸው ወደፊትም ይበልጥ መጎልበት ይኖርባቸዋል እላለሁ።

በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አቅጣጫ መሰረት በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ግምገማውን ያካሄደው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ነው። የትግራይን ህዝብ የሚመራው ይህ ድርጅት እንደ ሌሎቹ ብሔራዊ ድርጅቶች የራሱ ችግር የነበረበት ነው። ታዲያ አዲሱ አመራር ችግሩን ለመፍታት ኢህአዴግ ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ ተንቀሳቅሷል። በዚህ መሰረትም በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ባደረገው ግምገማ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

ለሶስት ቀናት የተካሄደውን የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴን መግለጫን ጨልፈን ስንመለከተው፤ ድርጅቱ ያሉበትን ችግሮች በመቅረፍ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኑን ያስገነዝበናል። በድርጅቱ የተሃድሶ ሂደት ተወያይቶ አስፈላጊ ውሳኔዎችን አስተላልፏል። በዚህም በተካሄደው ስብሰባ በስድስት የኮሚቴው አባላት ላይ የእርምት ርምጃ ወስዷል—የማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ።

ድርጅቱ የጀመረው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ግለቱን ጠብቆ እንዲጓዝ የሚያስችል አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል። ቀደም ሲል የድርጅቱ ስትራቴጂክ አመራር ባካሄደው ጥልቅ ግምገማ መሰረት የህወሓት ከፍተኛ አመራር በየዞኑ ውይይት ተካሂዷል።

የተካሄዱት መድረኮች የክልሉና የሀገሪቱ ወቅታዊ ጥያቄዎች በአስተማማኝ መንገድ መልስ እንዲያገኙ እንዲሁም የድርጅቱን ህዝባዊ ወገንተኝነት ዳግም ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች መንፈስ ተካሂዷል። እንደ ማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ፤ ውይይቶቹ የማዕከላዊ ኮሚቴውን ግምገማ በጥልቀት በሚያስቀጥል መንገድና የህዝቡን ጥያቄ በተገቢ አኳኋን ለመመለስ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል መግባባት ላይ የተደረሰበት ነው።

የህዝቡን የልማት፣ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ ጥያቄዎችን በተሟላ ሁኔታ ለመመለስ በየደረጃው ያለው አመራር ተጠያቂነት በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲገመግም ማዕከላዊ ኮሚቴው ወስኗል። እንዲሁም የድርጅቱን 13ኛ ጉባኤ የህዝቡን ሁለንተናዊ ፍላጎቶች በተገቢውና በሚያረካ መልኩ ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ተከናውኗል። ማእከላዊ ኮሚቴው በየዞኑ የተካሄዱ ውይይቶች የተነሱ ጉዳዮች እና ጥያቄዎች ላይ በመወያየት በስድስት የኮሚቴው አባላት ላይ የእርምት ርምጃ መውሰዱም ተመልክቷል።

በእኔ እምነት ይህ የህወሓት መግለጫ ድርጅቱ ራሱን ከማረም ባለፈ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል። የህዝብን እርካታ በመፍጠርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ እንዲሁም የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብንና ተግባርን ከመዋጋት አኳያ አስተዋፅኦው የላቀ ነው። ይህም የሀገራችንን ህዳሴ ሊያናጉ የሚችሉ እንቅፋቶችን ያስወግዳል ብዬ አምናለሁ።

በመሆኑም ድርጅቱ የያዘው ይህ ቁርጠኛ አቋም ግለቱን ጠብቆ መቀጠል ይኖርበታል። ይህን ፅሑፍ በማሰናዳበት ወቅት የድርጅቱ መካከለኛና ጀማሪ አመራሮች ወደ ግምገማ ገብተዋል። ግምገማቸውን ክልላዊና ሀገራዊ ህዳሴን በሚያረጋግጥ መልኩ እንደሚያጠናቅቁ እምነቴ የፀና ነው።

በአጠቃላይ የሀገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ኦህዴድና ህወሓት በመግለጫቸው የህዳሴውን አይቀሬነት የሚያረጋግጡ አመላካች አቋሞችን ወስደዋል። የደቡብና የአማራ መሪ ድርጅቶችም ተመሳሳይ አቋም እንደሚወስዱ እሙን ነው። ይህም ሀገሪቱን የጀመረችው የትንሳኤ ጎዞ እንደማይስተጓጎል ማረጋገጫ የሚሰጥ ይመስለኛል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy