Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የማይደበዝዝ ጉልህ አሻራ

0 437

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የማይደበዝዝ ጉልህ አሻራ

ኢብሳ ነመራ

ኢትዮጵያን በቡራቡሬ ትመሰላለች። አንዳንዶች ኢትዮጵያን ሲገልጹ እንደነብር ቡራቡሬ ይሏታል። ኢትዮጵያ ከሰማንያ በላይ የተለያዩ ቀለማት ያላት ሀገር ሆና ሳለ፣ የሁለት አይነት ቀለማት ቡራቡሬ በሆነው ነብር የምትመሰልበት ምክንያት ግን አይገባኝም። ነብር ላይ ያሉት የሁለቱ ቀለማት ነቁጦች መብዛት  ከቀለማቱ የዓይነት ስብጥር በላይ ትኩረት ስቦ ከሆነ ያስማማን ይሆናል። ለማንኛውም ኢትዮጵያ ከ80 በላይ የየራሳቸው የተለየ መገለጫ ቀለም ያላቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሀገር ነች።

ይሁን እንጂ፣ እነዚህ ከ80 በላይ የተለያየ ማንነት ያላቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ልዩነታቸው በዘውዳዊው ሆነ በወታደራዊው ሥርዓት አልተፈለገም ነበር። እናም ይህን የብሔር ብዝሃነት በመጨፍለቅ አንድ ቀለም ያላት ኢትዮጵያ የመመሥረት ስትራቴጂ ሥራ ላይ ውሏል። የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋቸው፣ ባህላቸውና ታሪካቸው በህግ ዕውቅና ተነፍጎት ቆይቷል። ቋንቋቸው ለፍትህ አገልግሎት እንዳይውል፣ ለትምህርት መስጫነት እና ለሚዲያ ሥርጭት እንዳያገለግል ተደርጓል። ዘውዳዊው ሥርዓት የኢትዮጵያዊነት መለያ ነው ብሎ ካወጀው ቋንቋ ውጭ በተቀሩት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋዎች ማስተማርና መማር፣ ለሚዲያ ስርጭት መጠቀም፣ መጽሃፍ ማሳተም ወዘተ የተከለከለ ነበር።

 የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የየራሳቸው ባህልና ወግ ያላቸው ቢሆንም፣ ባህላቸውና ወጋቸው እንደኋላ ቀርነት እንዲቆጠር ተደርጓል። በባህላቸው መሠረት የመኖር፣ ባህላቸውን የማጎለበት፣ የማስተዋወቅ መብታቸው ዕውቅና ተነፍጎት ቆይቷል። የየራሳቸው ታሪክ ያላቸው ቢሆንም ሥርዓቱ ማንነታቸውን ለመድፈቅ በሚመቸው መልክ ታሪክ አዘጋጅቶላቸው ነበር። ሁሉም ህዝብ የየራሱ ታሪክ ያለው መሆኑ ዕውን ቢሆንም ፣ ታሪክ የላቸውም የሚባሉ ብሔሮችና ብሔረሰቦችም ነበሩ።

በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የየራሳቸው መለያ ማንነትና ባህሎችን ቢይዙም የዜግነት ስሜት እንዳይሰማቸው፣ በማንነታቸው እንዳይኮሩ፣እንዲያፍሩና እንዲሸማቀቁ ሲደረግ ቆይቷል። እንደዜጋ የሚገባቸውን ጥቅም ለማግኘት ማንነታቸውን ለመደበቅ የሚገደዱበት ሁኔታ ነበር። ከተማ ገብተው የመንግሥት ሥራ ለማግኘት ወይም ከተሜውን ማኅበረሰብ ለመቀላቀል በቋንቋቸው የወጣላቸውን የመጠሪያ ስም ለመቀየር ይገደዱ የነበሩ ዜጎችን ማስታውስ ይቻላል። በቋንቋ የወጣን የመጠሪያ ስም እንዲቀይሩ ያስገደደው ማንነታቸው አሸማቃቂ እንዲሆን ስለተደረገና በአንዳንድ ሁኔታ ደግሞ የመቀጠርና አገልግሎት የማግኘት መብቶችም ላይ ተፅዕኖ ያሳድር የነበረ ሁኔታ መኖሩ ነው።

 ዘውዳዊው ሥርዓት ወሰኑን ለማስፋፋት የተቆጣጠራቸው የደቡብ፣ ምስራቅና ምእራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የኑሯቸው መሠረት የሆነው መሬታቸው ላይ የነበራቸውን የባለቤትነት መብት ተቀምተዋል። መሬታቸው በንጉሡ ውሳኔ ለመሳፍንቱና መኳንነቱ ተከፋፍሎ ነበር። ሌሎች የመንግሥት ተሿሚዎችም መሬት በርስትነትና ጉልትነት ይሰጣቸው ነበር። መሳፍንትና መኳንንቱም ለታማኞቻቸውና ወዳጆቻቸው የባለሃገሩን መሬት በጋሻ እየለኩ ያድሉ ነበር። በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለባለርስትና ባለጉልቶች ወይም ለመሬት ከበርቴዎች ገባር ጢሰኛ ሆነው ለማደር ተገደዋል። የራሳቸውን መሬት እያረሱ ምርታቸውን ለባለርስትና ባለጉልት የሚገብሩ፣ ከነቤተሰባቸው በጉልበታቸው ላይ የማዘዝ መብት የሌላቸው ጢሰኞች ሆነው ነበር።

ይህ የፊውዳላዊ ዘውዳዊ ሥርዓት መገለጫ ነበር። የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለብሄራዊና ኢኮኖሚያዊ (የመደብ) ጭቆና ተዳርገው ነበር። ብሄራዊና የመደብ ጭቆናው ምንጭ አንድና የማይነጣጠል ነበር።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ይህን ጭቆና በፀጋ ባይቀበሉትም ከላያቸው ላይ ለማራገፍ ግን ቀላል አልሆነላቸውም። በመጀመሪያ በየአካባቢው ቁጣ የሚቀሰቅሱ አጋጣሚዎችን እየጠበቀ በሚፈነዳ ዐመጽ ነበር ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ቆይቷል። በየአካባቢው በጎበዝ አለቃ እየተመሩ የአካባቢ ገዢዎች ላይ የሚሸፍቱባቸው ሁኔታዎችም ነበሩ። እነዚህ እንቅስቃሴዎች ግን የጨቋኙን ሥርዐት ባህሪ በመተንተን ስትራቴጂ ኖሯቸው በተደራጀ መልክ የሚካሄዱ ስላልነበሩ ለውጥ ማምጣት አልቻሉም። እርግጥ የአምስቱ ዓመት የጣሊያን ወረራ በአርበኞች ትግል በተቀለበሰ ማግስት የተቀሰቀሰው የትግራይ ቀዳማይ ወያኔ አመጽ፣ የባሌ አርሶ አደሮች በመባል የሚታወቀው የኦሮሞ አመጽ ሥርዐቱን ያስደነገጡ ነበሩ።

ያም ሆነ ይህ፤ እያደረ በሀገሪቱ ትምህርት እየተስፋፋ ሲመጣ የጭቆናውን ምንጭ የሥርዐቱን ምነነት በመተንተን መረዳትና ማስረዳት የቻሉ ልሂቃን ተፈጠሩ። እነዚህ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የፈለቁ ልሂቃንና ተማሪዎች በከተሞች በተለይ በሀገሪቱ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ ይፋዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ማካሄድ ጀመሩ። ይህ ትግል የተማሪዎች እንቅስቃሴ በመባል ይታወቃል።

በ1950ዎቹ የተጀመረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ሁሉንም የሁለተኛና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በማሳተፍ በመላ ሃገሪቱ ተስፋፋ። ይህ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ሥርዐቱን እጅግ ተፈታተነ። በመጨረሻም በከተሜ ላብ ደሮችና ሌሎች ጭቁን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደግፎ 1966 ዓ/ም ላይ ሥርዐቱን አንገዳገደው። ይሁን እንጂ ይህ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የተደራጀ ስላልነበረ ስልጣን ወደህዝብ እንዲሸጋገር የማድረግ አቅም አልነበረውም። እናም ሥርዐቱ ተንገዳግዶ መውደቁ አይቀሬ የሆነበት ደረጃ ላይ ሲደርስ በሃገሪቱ ብቸኛው የተደራጀ ሃይል የነበረው ያንኑ ሥርዐት ሲያገለግል የነበረው ወታደራዊ ቡድን ሥልጣኑን ለመረከብ ተዘጋጀ። ወታደራዊ ኃይሉ በ1966 ዓ/ም በየካቲት ወር ከልዩ ልዩ የጦር ክፍሎች ፖሊስ ሠራዊትን ጨምሮ የተወከሉ 120 ገደማ አባላት ያሉት ብሔራዊ አስተባባሪ ምክር ቤት (ደርግ) የሚባል አካል አደራጀ። ይህ ንጉሠ ነገሥቱ ሥልጣን ላይ እያሉ የተደራጀ ደርግ የተሰኘ ወታደራዊ ቡድን የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቶ በመጨረሻም መስከረም 2፣ 1967 ዓ/ም ዐፄውን ከሥልጣን አስወገደ።

 ንጉሡን አስወግዶ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ያወጀው ደርግ በመጀመሪያ ያንኑ ዘውዳዊ ሥርዐት የማስቀጠል ዓላማ ነበረው። በመጀመሪያው አዋጁ አልጋወራሽ የነበሩት ልዑል አስፋ ወሰን ዙፋኑን እንደሚወርሱ ገልጾ ነበር። ጥቂት ቆይቶ ግን አልጋ ወራሹም ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ዕቅድ እንደሌላቸው ሲያውቅ፣ አዋጁን ሸሮ በጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥትነት ሥልጣን ላይ ጸና።

 ይህ ወታደራዊ ቡድን ዘውዳዊውን ሥርዐት ያገለግል ስለነበረ፣ በሀገር ምንነት ላይ የነበረው አመለካካት ከወደቀው ሥርዐት ጋር ተመሳሳይ ነበር። ለወታደራዊው ደርግ ሀገር ልክ እንደ ተስፋፊ ፊውዳል ነገሥታቱ መሬቱ ላይ ያተኮረ  እንጂ በላዩ ላይ ለሚኖረው ህዝብ የሰጠው ቦታ አልነበረም። በመሆኑም ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዕውቅና ለመስጠት አልፍቀደም። ወታደራዊው ደርግ በመሬት ለአራሹ አዋጅ  አርሶ አደሩን ባለመሬት ቢያደርግም፣ ከዚህ የመደብ ጭቆና ለማይነጠለው ብሄራዊ ጭቆና ግን መፍትሄ ማበጀት አልፈለገም።

በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ላይ የነበረው ጭቆና እንደነበረ ቀጠለ። ለመደብ ጭቆናው መፍትሄ ያመጣል የተባለው የመሬት ለአራሹም አዋጅ ቢሆን አርሶ አደሩን የምርቱ ባለቤት ማድረግ ስላልቻለ፣ አርሶ አደሩ ተመልሶ የመንግሥት ገባር ሆኗል። ከድህነት መውጪያ መንገድ አላገኘም። በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ላይ የነበረው ብሄራዊ ጭቆናና ድህነት ቀጠለ። የብሄራዊ ነጻነት ትግሉም ቀጠለ።

በኤርትራ በ1955 ገደማ ተጀምሮ የነበረው የብሄራዊ ነጻነት የትጥቅ ትግል ተፋፍሞ ቀጠለ። 1965 ዓ/ም ተደራጅቶ የነበረው የኦሮሞ ነጻነት ግንባርም ትግሉን ቀጠለ። ወታደራዊው ደርግ አብዮቱን መንትፎ ለነጻነት ጥያቄ ምላሽ የመስጠት ፍቃደኝነት የሌለው መሆኑ ቁርጥ ሲሆን፣ በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፀረ ዘውዳዊ ሥርዐት ትግል ሲያካሂዱና ሲመሩ የነበሩ የትግራይ ወጣቶች ጭቁኑን ህዝብ ለማታገል ጫካ ገቡ፤ የካቲት 1967 ዓ/ም ላይ። የዛሬ 43 ዓመት የካቲት 11 ህወሃት የተመሰረተው በዚህ አኳኃን ነበር። ህወሃት በሰዎች ፍላጎት የተፈጠረ ድርጅት ሳይሆን በሃገሪቱ የነበረው ብሔራዊ ጭቆና በፈጠረው ታሪካዊ ሁኔታ አስገዳጀነት የተወለደ ነው።

 በሀገሪቱ ባለው ታሪካዊ ሁኔታ አስገዳጅነት የተፈጠሩት ህወሃትና ሌሎችም ብሄራዊ የነፃነት ቡድኖች በየአቅጣጫው የትጥቅ ትግሉን አቀጣጠሉት። ከእነዚህ በየአቅጣጫው ከተቀጣጣሉት የብሄራዊ ነፃነት ትግሎች ሁሉ በአካባቢው ከነበረው የተለየ መልክዐ ምድራዊና ታሪካዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የህወሃት ትግል ጎልቶ ለመውጣት በቃ። ህወሃት እያደረ ከሌሎች ብሔራዊ የነፃነት ቡድኖች ጋር በመቀላቀል የትግራይን ህዝብ ጭቆና የሚጋሩትን የተቀሩትንም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከብሄራዊ ጭቆናና ድህነት የማላቀቅ ሀገራዊ ራዕይ ሰነቀ። እናም ከኢህዴን/ ብአዴን ጋር ግንባር ፈጥሮ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባርን (ኢህአዴግ) መሠረቱ።

በትግሉ ሂደት የኢህአዴግን ተዋጊ ኃይል የሚቀላቀሉት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወላጆች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ፣ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ተመሠረተ። የአሁኑ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲ ንቅናቄም በዛው ኢህአዴግ ውስጥ የስምጥ ሸለቆ ታጋዮች በሚል የተፀነሰ ነበር። እናም ህወሃትን፣ ኢህዴንን፣ ኦህዴድንና የስምጥ ሸለቆ ታጋዮች ማህበርን ያቀፈው ህብረ ብሔራዊው ኢህአዴግ የትግል ሜዳውን አስፍቶ ወታደራዊውን ደርግ ለማስወገድ በቃ። ወታደራዊውን ደርግ ለማስወገድ በተደረገው ትግል በርካታ የብሔራዊ ነጻነት ግንባሮች የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የነበረ ቢሆንም፣ ኢህአዴግ ህብረ ብሔራዊ ባህሪም ስለነበረው ደርግን በማስወገድ ትግል ውስጥ ጉልህ ድርሻ ነበረው።

አሁን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሕገ መንግሥት ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸው ተረጋግጦ በዕኩልነት ላይ በተመሠረተ አንድነት የሚኖሩበት የኢፌዴሪ ሥርዐት የዚህ ኢህአዴግ ጉልህ ድርሻ ያበረከተበት ድል ውጤት ነው። የዛሬ 43 ዓመት በኢትዮጵያ ብሄሮች ላይ ተጭኖ የነበረው ጭቆና የወለደው ህወሃት ደግሞ ለኢህአዴግ መመሥረት ጥንስስ ነው። እናም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ነጻነት ሲታወስ ህወሃት/ ኢህአዴግም አብሮ ሲዘከር ይኖራል። እናም የየካቲት 1966 ዓ/ም ህዝባዊ አብዮት በተቀማ በዓመቱ የካቲት 1967 ዓ/ም የተመሰረተው ህወሃት የተቀማውን አብዮት በማስመለስ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብትና ነጻነት የተረጋገጠበት ሥርዐት  ውስጥ ሊጠፋም፤ ሊደበዝዝም የማይችል ጉልህ አሻራ አለው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy