Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰላም አምባ

0 213

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሰላም አምባ

ዳዊት ምትኩ

በቅርቡ በተካሄደው አፍሪካ ህብረት መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከ10 ሺ በላይ እንግዶች ተካፋይ ሆነዋል። በጉባኤው ላይ 49 የአገራት መሪዎችም ተገኝተዋል። በእርግጥ የዚህ እድምተኛ ብዛት ለአገራችን ትርጉሙ ከፍተኛ ነው። በተለይ ከፖለቲካ፤ ከኢኮኖሚያዊ እና ከማህበራዊ ፋይዳ አኳያ ጉባኤው ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው። ይህን ያህል ታዳሚ በሀገራችን ተገኝቶ ጉባኤውን መሳተፉ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ፣ መዲናችን ደግሞ በተለይ የሰላም አምባ መሆናቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል።

እርግጥ አገራችን የሰላም አምባ ናት። ኢትዮጵያ ከደርግ ውድቀት በኋላ ሰላም መርሁ በሆነው የኢፌዴሪ መንግስት አማካኝነት አፍሪካዊ አስተዋፅኦውንና ኃላፊነቱን ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ ተወጥቷል፤ እየተወጣም ይገኛል። በዚህ መሰረትም በሩዋንዳ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ በተከሰተውና የዓለምን ሕዝብ ባስደነገጠው የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ ሰላም እንዲያስከብሩ ከተደረጉት ሀገሮች አንዷ ሀገራችን ተደርጓል። ያኔ ቡሩንዲ ውስጥ ሁቱና ቱትሲ የተባሉ ጎሳዎቿ ግጭት ላይ ነበሩ። ዘር ለይቶ የተፈጠረውን ዘግናኝ ድርጊት ለማስቆም በአፋጣኝ ሰላም አስከባሪ ኃይላቸውን እንዲልኩ ከተደረጉት ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት። በዚህም ታሪካዊ አስተዋጽኦዋን አበርክታለች። በላይቤሪያም እንዲሁ። ላይቤሪያ በከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በነበረችበት ወቅት ሀገሪቱን ወደ ሠላምና መረጋጋት ጎዳና ለመመለስ በተደረገው ሂደት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪነት ሚና የገዘፈ ነበር። በዚያች ሀገር ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን በማድረግም ሀገራችን የተጫወተችው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

በሱዳን ዳርፉር ግዛት ከሌሎች ሀገሮች ጋር በመሆን ባሰማራችው ሰላም አስከባሪ ሃይልም የእርስ በርስ ግጭት እንዳይከሰት በማድረግ ላይ መሆኗም ይታወቃል። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በይገባኛል በሚከራከሩበት የአብዬ ግዛት ከዓለም በብቸኝነት ተልዕኮውን የሚወጣ ሰላም አስከባሪ ኃይል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ሥር በመሆን አሰማርታለች። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነቷን ያሳደገ ተግባርም እየከወነች ነው። ሀገራችን በምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ሠላም፣ ጸጥታና መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች ባለችው ሚና በሶማሊያ የነበረውን መንግሥት አልባነትና አክራሪነት በመታገልም ውጤታማ መሆን ችላለች።

እርግጥ ሰላማቸው የተረጋገጠ፣ በኢኮኖሚያቸው የበለጸገና ዴሞክራሲ ያበበባቸው ጎረቤቶች የጋራ ጥቅም መሠረት መሆናቸው የማይታበይ ቢሆንም፤ ሀገራችን ከዚህ ባለፈ ለጎረቤቶቿ ህዝቦች ሰላም ያለማሰለስ በመሥራት ላይ ትገኛለች። ለዚህም በአሁኑ ወቅት በአዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ውስጥ በተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት የበኩሏን ጥረት በማድረግ የዚያች ሀገር ህዝብ የሰላም አየርን እንዲተነፍስ በማድረግ በገለልተኝነት የበኩሏን ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።

ከዚህ በተጨማሪም ሀገራችን በኢኮኖሚው መስክ ያላት አህጉራዊ ትብብር ኮሜሳ በሚሰኘው በምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ የጋራ ገበያ የተጠናከረ ውህደት ለመፍጠር ያላት ሚናም ከፍተኛ ነው። በመሠረተ-ልማት ግንባታ መስክ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመሳብም ጥረት እያደረገች ነው። የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግም በመሥራት ላይ ነች። ከጅቡቲ፣ ከሱዳንና ከኬንያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከታንዛኒያ ጋር የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር ለጋራ ተጠቃሚነት በመትጋት ላይ ትገኛለች። በዚህም ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኝ የባቡር መስመር ግንባታው ተጠናቅቋል።

ከኬንያ ጋር የሚያገናኘው መስመርም ወደ ስራ እንዲገባ ጥረት እየተደረገ ነው። ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ተጠቃሚ እንድትሆን ከማድረጓም በላይ፤ ኬንያንን እንዲሁም ታንዛኒያን በተመሳሳይ ሁኔታ በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር ጥረት እያደረገች ነው። ይህ ሁኔታም ወደፊት ለአፍሪካ ህብረት አንድ መሆን ለሚደረገው ጥረት የበኩሉን ዕገዛ ሊያደርግ እንደሚችል ህብረቱ የሚገነዘበው ይመስለኛል።

ሀገራችን ህብረቱ የሚቀበለውንና የአድሪካ ህዝቦች በፍትሃዊነት የተፈጥሮ ሃብቶቻቸውን እንዲቀበሉ በምታደርገው ጥረትም ትታወቃለች። በዚህም የአባይ ውኃ አጠቃቀምን ፍትሃዊና አግባብ ባለው መልኩ የመጠቀም አስፈላጊነትን አምና በፅናት እየሰራች ነው። የናይል የላይኛው ተፋሰስ ሀገሮች የጋራ ማዕቀፍ ፈርማን አብዛኛዎቹ ሀገራት እንዲፈርሙ ማድረጓን በምሳሌነት መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል።

አዲስ አበባ ሰላማዊና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ መናኸሪያ እንድትሆን በማድረግም አገራችን የአፍሪካን ገፅታ እየገነባች ነው። በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ውስጥ የሚካሄዱት ጉባዔዎች፣ ስብሰባዎችና ዐውደ ጥናቶች…ወዘተ. ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር አንድ የአፍሪካ ከተማ በዚህ ረገድ ተመራጭ እንድትሆን ያደረገ ስለሆነ ለህብረቱ ሀገራትም በኩራት የሚመዘገብ ነው። አፍሪካዊ እሴትን በመጨመር ረገድም ዋጋው ከፍ ብሎ የሚታይ ይመስለኛል።

እነዚህ ጥቅል ዕውነታዎችም የአፍሪካ ህብረት ሀገራችንና ህዝቦቿ በሰላም ውስጥ ለአህጉሪቱ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ የሚገባና ህብረቱ ሁሌም ሀገራችን በምትሰጠው መረጃ ላይ እንዲመሰረት ያደረገው ነው ማለት ይቻላል። የአፍሪካ ህብረት የኢፌዴሪ መንግስትና ህዝቡ ለሰላም ያላቸውን ፍፁም የማያወላውል አቋም በሚገባ ይገነዘባል።

ላለፉት 26 ዓመታት ሀገራችን የራሷን ሰላም ዕውን ከማድረግ አልፋ የአፍሪካውያንን ሰላም ስትጠብቅ እንደነበረች ከህብረቱ መሪዎች የሚሰወር እውነታ አይመስለኝም። ህብረቱ የኢፌዴሪ መንግስት በሀገር ውስጥ የሚያከናውነው ሰላምን አስተማማኝ የማድረግ ስራዎችን ይረዳል።

ቀደም ባሉት ዓመታትም የህብረቱን ጉባኤዎች ፍፁም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ሀገራችን ማስተናገዷንም ያውቃል። ለዚህም መንግስትና ህዝቡ የሚያካሂዱትን ማህበረሰብ አቀፍ የፀጥታ አጠባበቅ ሁኔታ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድ ይገነዘባል። እናም እንግዶች የህብረቱን ጉባኤ ያለ ስጋት ተካፍለው እንዲሄዱ ምክንያት ሆኗል።

አገራችን የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት የዚህ ሁሉ ጉዳይ መሰረት ነው። በሀገራችን እውን መሆን የቻለው አስተማማኝ ሰላም ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገርና የመጻፍ እንዲሁም ባህላቸውንና እሴቶቻቸውን በነፃነት የመግለፅ መብቶቻቸውን ማረጋገጥ ችሏል። ይህም የዚህ ፅሑፍ ማጠንጠኛ የሆነውን ሰላም በመመለስ ለትግላቸው እውቅና በመስጠት ጥያዌዎቻቸውን መመለስ ችለዋል።

በሀገራችን ዕውን እየሆነ ያለው ስርዓት ሰላምን ማረጋገጥ በመቻሉ፤ በማህበራዊ መስተጋብሮች ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝና የማንነት ልዩነቶችን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሳሪያ ሆኗል። ይህ አብሮነትም ዜጎች የጋራ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ፌዴራሊዝም የጎላ ሚና እንደሚጫወት እምነትን አስይዞ በአዲስ የአስተሳሰብ መንፈስ ወደ ልማት ጎዳና መትመም እንዲችሉ አድርጓቸዋል።  

እናም ስርዓቱ እነዚህን ሁሉ ውጣ ውረዶችን አልፎ ሰላምን ዕውን ያደረገ፣ ልማትን ያረጋገጠና በዚህም የህዝቦችን ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ዕውን ያደረገ እንዲሁም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታን መገንባት ችሏል። እናም አፍሪካዊ ወንድሞቻችን ሁሌም ቢሆን በዚህ ሰላማዊነታችን ይተማመኑብናል። ነገም ወደ አገራችን ሲመጡ ይህን የሰላም አምባነታችንን በማመን ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy