Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የስሜታዊነት ጣጣ

0 236

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የስሜታዊነት ጣጣ

                                                        ደስታ ኃይሉ

ሰላምና መረጋጋት ባልሰፈነበት የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ኢትዮጵያ አንፃራዊ ሰላምን እውን ያደረገች አገር ናት። ይህ የሆነውም አገራችን የህዝቦችን የዘመናት ጥያቄ በመመለስ ላይ የሚገኘውን ፌዴራላዊ ሥርዓትን በመከተሏ ነው። ሆኖም እንደ ጀማሪነታችን በሥርዓቱ አፈፃፀም ውስጥ ጉድለቶች መከሰታቸው አይቀርም። መንግስትም ጉድለቶቹን ለማረም ቃል ገብቶ እየሰራ፣ የችግሮቹን መንስኤዎች በጥልቀት ገምግሞ ችግሮቹን የመፍታት ጉዳይ “የሞት ሽረት ትግል ነው” ብሎ የሚፈቱበትን አቅጣጫ አስቀምጦ ተግባራዊ እርምጃ እየወሰደ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በፍጥነት ለመፍታት አዳጋች የሆኑትን ጉዳዮችንም ትክክለኛውን አካሄድ ተከትሎ ለመፍታት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ የአገራችን ህዝቦች በደምና በአጥንታቸው በመገንባት ላይ የሚገኙትን ስርዓት ለማፍረስ የሚደረጉ ማናቸውም ተግባሮች ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው። በእነዚህ ተግባሮች ላይ የሚሳተፉ ወገኖች ከስሜታዊነት ወጥተው ሰከን ብለው ማሰብ ይኖርባቸዋል። ከስሜታዊነት ጣጣ መውጣትም አለባቸው። ስክነት ትርፍ እንጂ ኪሳራ እንደሌለውም መገንዘብ ይኖርባቸዋል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ሰላምን ዕውን ያደረገ፣ ልማትን ያረጋገጠና በዚህም የህዝቦችን ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ዕውን ያደረገ እንዲሁም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታን መገንባት ችሏል። ይህ ሲሆን ግን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩት ሁከትና ግጭቶች ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ይመስሉኛል።

ያም ሆኖ ህዝቡ በሰላሙ ላይ ስለማይደራደር ለግጭት ኃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳር እንዳይኖር አድርጓል። ምንም እንኳን በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ አንዳንድ ግለሰቦች የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው የሚነቀሳቀሱ ሆነዋል።

በዚህም በመልካም አስተዳደርና በሙስና ህዝቡን ሲያማርሩት እንደነበር የሚታወቅ ነው። እነዚህ ሃይሎች የፈጠሩት ምሬት ከትምክህትና ከጥበት አራማጆች አጀንዳ ጋር ተዳምሮ የሀገራችንን ሰላም ማወኩ የቅርብ ጊዜ ትውሰታችን ነው።

ይህ ሁከት ዛሬም ድረስ በአንዳንድ አካባቢዎች ብቅ ጥልም እያለ በመታየት ላይ ይገኛል። ግና ከሁከት የሚገኝ ምንም ዓይነት ጥቅም እንደሌለ ማንም የሚያውቀው ነው። የሁከቱ አራማጆችም የአገራችንን ሰላም ለማወክ ሌት ተቀን የሚሰሩ የኢትዮጵያ ጠላቶች እንጂ ከሀገራችን ሰላም ወዳድ ህዝብ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። ህዝቡ ከመልካም አስተዳደርና ከብልሹ አሰራር ጋር ተያይዞ ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎች መንግስት አቅም በፈቀደ መጠን ምላሽ እየሰጠ ነው። ከዚህ በመለስ የሁከቱ ባለቤቶች ሌሎች ናቸው።

ሰላማችን ሁከትና አሉባልታ አቀናባሪ በሆኑ ማህበራዊ ድረ ገጾች መታወክ አይኖርበትም። ላይ አንዳንድ ወገኖችም ሳያውቁ የዚሁ አሉባልታ ሰለባ መሆናቸው አልቀረም። በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለያዩ ፎቶዎችን በማቀናጀት በሌሎች ሀገራት ውስጥ የተከናወኑ ድርጊቶችን እዚህ ሀገር የተፈጠሩ በማስመሰል አንዳንድ ወገኖችን ሲያደናግሩ ይታያሉ። በምሳሌነትም እነዚህ ሚዲያዎች በተለያዩ ሀገራት የተገደሉ ተመሳሳይ ቀለም ያለቸውን ግለሰቦች በመለጠፍ ‘ኢትዮጵያ ውስጥ እገሌ የተባለ ቦታ የተገደሉ’ በማለት በፌስ ቡክ ላይ ያሳያሉ፤ የሌሎች አገሮች ኤሌኮፍተሮችን ፎቶ እያነሱም ‘ገሌ በሚባለው ቦታ መከላከያ በአውሮፕላን እየደበደበ ነው’ የሚል አስገራሚ የፈጠራ ድርሰትን ማንሳት ይቻላል። እንዲህ ዓይነት የውሸት ድርሰቶች ስሜታዊ የሚያደርጉና የህዝቡን ሰላም የሚነጥቁ ናቸው። እናም ብርቱ ጥንቃቄን ይሻሉ።

እንደሚታወቀው ሁሉ ህዝቡ የወደፊት ዕጣ ፈንታው የሚወሰነው ሀገራችን በምትከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መሆኑን ስለሚያውቅ ሁሌም ሰላም ወዳድ ኃይሎች ጋር የሚቆም ነው። የሰላምን ጠቀሜታ ስለሚገነዘብም ከምንግዜውም በላይ ሁሌም በየአካባቢው ለሰላሙ  ዘብ እንደቆመ ነው።

ህዝቡ በየቀየው ላለው የሰላም ሁኔታ ዋነኛ መሰረት ነው። በዚያ አካባቢ ለሚከሰት ማናቸው የፀረ-ሰላም ድርጊት መልሶ የሚጎዳው እርሱን በመሆኑ ለሰላሙ ይበልጥ መትጋት አለበት።

እንዲህ ዓይነቱ ሰላምን የሚያጎሉ፣ ልማትን የሚያፋጥኑና ንትርክን የሚያስቀሩ መንገዶችን መከተል ባይቻል ኖሮ፤ የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን እውን ማድረግና ህዝቡም የተጀመረውን የፀረ ድህነት ዘመቻ አጠናክሮ ባልቀጠለ ነበር።

ከልማት ዕቅዱም በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ተፈላጊውን የዕድገት ራዕይ ሰንቆ ባልተጓዘም ነበር። አሁን እያለመ ላለውና ከመጀመሪያው ዕቅድ ጋር ተመጋጋቢ የሆነውን ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድንም ተልሞ ዛሬ ሶስተኛ ዓመቱ ላይ ባልደረሰ ነበር።

በዚህ ደረጃ ላይ ሆኖ የተጀመረውን ዕድገት ለማስቀጠልና በዚያውም ልክ ዴሞክራሲው ሀገር በቀል ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲጎለብት የተደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ፤ ይህ ህዝብ በአንዳንድ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ውስጥ ከመልካም አስተዳደር ጋር እንዲሁም ፅንፈኛ ኃይሎችና የሀገራችንን መለወጥ የማይሹ አንዳንድ ወገኖች አማካኝነት የተከሰተውን ሁከት ለመቋቋም ህዝቡ በባለቤትነት መንፈስ የከፈለው መስዕዋትነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይህ የህዝቡ ስሜት የመነጨው ከምንም ተነስቶ አይደለም። የሰላምን ዋጋ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው። ካለፉት ተግባሮቹ ስለተማረ ነው።

ከተግባር የበለጠ ትምህርት ቤት ባለመኖሩም፤ ይህ ህዝብ የሰላሙ ዘብ ሆኖ ቆሟል። ሁከቱን ለመቀልበስ በሀገራችን የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ሲባል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአስፈጻሚው አካል ታውጆ ተግባራዊ ሲሆንም ይህ ህዝብ የአንበሳውን ድርሻ ተጫውቷል። በዚህ የህዝቡ የነቃ ተሳትፎ በሀገራችን ላይ ተደቅኖ የነበረው አደጋ እንዲቀለበስ ለማድረግ በተደረገው ርብርብ የህዝቡ ሚና ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ይህ ሰላም ወዳድነቱ ዛሬም ይሁን ነገ ይበልጥ መጎልበት አለበት።

ይህ ሰላም ወዳድ ህዝብ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሰላምን በማወክ ተግባር ላይ የተገኙ ወጣቶችን በመገሰፅ፣ ለሰላም እንዲሰሩና የሰላምን እሴት እንዲያውቁ ማድረግ የቻለ ነው። ይህ ህዝብ ላለፉት 26 ዓመታት ገደማ የተራመዳቸው የልማት አባጣና ጎርባጣ ውጣ ውረዶች ያስታውሳል። ለውጦቹ በአሁኑ ወቅት የሚቀራቸው ተጨባጭ ለውጦች ቢኖሩም፤ ከትናንቱ በተሻለ ቁመና እንደሚገኙ ይገነዘባል። እርሱንም በተሻለ ማማ ላይ እንደሚያወጡት በልማቱ ውስጥ ተዋናይ የሆነው ማንኛውም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ራሱን በመግለፅ ጭምር ሊያስረዳ ይችላል።

ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ካሉ፣ ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ ልማታዊ መንግስት ካለና በዚሁ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሰላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና ማደግ እንደሚቻል ጠንቅቆ የሚያውቅ ህዝብ ነው። የስሜታዊነትን መዘዝም በሚገባ ያውቃል።

የስሜታዊነት ጣጣ መዘዙ ብዙ ነው። ስሜታዊነት አገርን ከማፍረስና የስደት ሰለባ ከማድረግ በስተቀር አንዳችም ትርፍ አያስገኝም። እናም ይህ ህዝብ በስሜታዊነት ጣጣ ውስጥ የሚገኙ ወኖችን ሰከን እንዲሉ ማስተካከልና መምራት ያለበት ይመስለኛል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy