Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“የአድዋ ድል በእድል ሳይሆን በአባቶች መስዋዕትነትና በአገር በቀል ወታደራዊ ሳይንስ የተገኘ ነው” አቶ ረመዳን አሸናፊ

0 949

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“የአድዋ ድል በእድል ሳይሆን በአባቶች መስዋዕትነትና በአገር በቀል ወታደራዊ ሳይንስ የተገኘ ነው” ሲሉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ረመዳን አሸናፊ ተናገሩ።

122ኛው የአድዋ ድል በዓል  ዛሬ በብሔራዊ ቴአትር በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

አድዋ ከዘመኑ የቀደመ፤  ለአገር ዳር ድንበር መከበር  እምነት፤ ቋንቋ፤ ዘር፤ አስተሳሰብና ጾታ ሳይለያቸው የአገር ፍቅር ከሩቅም ከቅርብም የጠራቸው ኢትጵያውያን ወራሪ የጣሊያን ጦርን ድባቅ የመቱበት የደምና የአጥንት ክፍያ ዋጋ ነው።

ጥቁር የነጭ የበታችና አሽከር ተደርጎ በሚታሰብበት ዘመን፤ ኢትዮጵያውያን ‘አንደፈርም፤ እምቢ ለአገሬ!’ በማለት ታላቅነትን የጻፉበት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ሲታወስ ልክ አድዋ ላይ ሰንደቃችን ከፍ ብሎ በክብር ይውለበለባል።

አድዋ የጥቁር ሕዝቦች አንድነት፤ የአመራር ብቃት፤ ሕብረት፤ ፍቅርና  ጀግንነት የታየበትና ሌላው ዓለም ‘እውነትም ጥቁር ማለት!’  ብሎ የተገረመበት የድል ቀን ነው።

አድዋን ስናስብ ኢትዮጵያውያን ከጭቆና ቀንበር በአጥንታቸውና በደማቸው መስዋእትነት ነጻ መውጣታቸው ብቻ አይደለም የሚጎላው፤ ከወራሪ ነጮች መዳፍ ውስጥ መውጫ አጥተው የነበሩ ሕዝቦች የትግል ምልክትና የነጻ መውጣት መለከት መሆኑም ጭምር እንጂ።

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ጋር በመሆን ዛሬ  ባዘጋጁት መድረክ 122ኛው የአድዋ ድል በዓል ተከብሯል።

በዓሉ ‘አድዋ የአብሮነትና የአንድነት ተምሳሌት’ በሚል መሪ ቃል ነው የተከበረው። በበዓሉም አመራሮች፤ የአባት አርበኞችና ሌሎች ተጋባዦች ተገኝተዋል።

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ረመዳን አሸናፊ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአድዋ ድል ለመላው ዓለምና በተለይም አፍሪካዊያን ከባርነት እንዲላቀቁ ምሳሌ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የአድዋ ድል በዓል መታወስና መዘከር ያለበት የድል ቀን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር  ዋና ዳይሬክተር አቶ መሳይ ደምሴ፤ የአድዋ ድል በዓል ኢትዮጵያውያን አባቶች ለሀገራቸው ያላቸውን ክብር ያሳዩበትና “ለቀሪው ዓለም ወደ ነጻነት መውጫ የዘረጉት ድልድይ ነው” ይላሉ።

በመሆኑውም የአድዋ ድል ከመቼውም በላይ ክብርና ልዕልና የሚገባው የማንነታችን መኩሪያና መታወቂያ ነው ብለዋል።

በዚህ ለ122ኛ ጊዜ ዛሬ በተከበረው የአድዋ ድል በዓል ላይ ግጥሞች ቀርበዋል፤ መነባንቦች ተነብንበዋል፤ ሙዚቃዎችም ተሞዝቀዋል።

በቀጣይ ቀናትም ሌሎች የአድዋን ድል የሚዘክሩና የሚያስታውሱ ዝግጅቶች  በመላ ሀገሪቱ ይከበራሉ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy