Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የካቲት ወር የኢትዮጵያውያን የነፃነት ምልክት ነው

0 1,320

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የካቲት ወር የኢትዮጵያውያን የድልና የነፃነት ተምሳሌት መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ጽህፈት ቤቱ በሳምንታዊ የመንግስት አቋም መግለጫው እንዳመለከተው ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካውያን ብሎም ለጥቁር ህዝቦች የነፃነት ብስራት የሆኑበት የአድዋ ድል የተገኘው በወርሃ የካቲት 1888 ዓ.ም ነበር።

ድሉ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያን እንዲሁም መላው የጥቁር ህዝቦች የትግልና የአንድነት ቀን አድርገው የሚኮሩበት፤  እንዲሁም ጥቁር አሜሪካውያን ለአፍሪካ የትግል አጋርነታቸውን የገለጹበትና የነጻነት ንቅናቄ በአሜሪካን አገርም እንዲቀሰቀስ ያስቻለ ነው።

ይኽውም በጥቁር ህዝቦች ዘንድ የይቻላልና የአሸናፊነት መንፈስን ያላበሰና  የአፍሪካውያን ኩራት ሆኖ ዛሬም በደማቅ ቀለም የሚጻፍ ነው ብሏል መግለጫው።

የካቲት ወር ለኢትዮጵያውያን የአድዋ ድል በዓል ብቻ አይደለም፤ ጭቆና በቃን ያሉ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የትጥቅ ትግል የጀመሩበትና የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) የተመሰረተበት የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም ነበር።

በተሰማራበት ግዳጅ ሁሉ በላቀ ስነ ምግባሩና ብቃቱ የዓለም አድናቆትን ያተረፈው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በአዋጅ የተቋቋመውም የካቲት 7 ቀን 1988 ዓ.ም እንደነበር መግለጫው ያትታል።

ከዘመናት ጭቆና በኋላ የሴቶችን የእኩልነት መብት ተጠቃሚነት ለማረጋጋጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረገው ትግል ለስኬት የበቃውም በወርሃ የካቲት መጨረሻ እ.ኤ.አ ከ 1917 ጀምሮ ነበር።

በመሆኑም የካቲት ወር ኢትዮጵያውያን ያለፉትን ድሎች የሚዘክሩበት ብቻ ሳይሆን፤ ለአገራቸው ህዳሴ ዳግም ቃል የሚገቡበት ወር መሆኑን ይገልጻል መግለጫው።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል።

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ

ሳምንታዊ አቋም መግለጫ

የየካቲት ትሩፋቶች የኢትዮጵያ ህዳሴ መሠረቶች ናቸው

ወርሃ የካቲት፣ ለኢትዮጵያውያን ወርቃማ የመራራ ትግልና የጣፋጭ ድል ወር ናት። የካቲት፣ ለአፍሪካውያንና ለጥቁር አሜሪካውያንም እንደዚያው ወርቃማ ሆና ታሪኳ በደማቅ ቀለም ተጽፎ በየዓመቱ ይዘከራል። የፋሺስቱ የኢጣሊያ ጦር የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በአድዋ ድል መመታቱ፣ በመላው ጥቁር ህዝቦች ዘንድ የይቻላል ስሜትን ቀስቅሶ በቅኝ ግዛት ሥር ይማቅቁ የነበሩ ህዝቦች ሁሉ ቀስ በቀስ ነጻ እንዲወጡ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል። የመላው አፍሪካውያን የትግል አንድነት እና ጥቁር አሜሪካውያን ለአፍሪካ የትግል አጋርነታቸውን የገለጹበት ንቅናቄ በአሜሪካ ሃርለም ግዛት እንዲነሳሳ ያደረገውም – ይኼው የአድዋ ድል ነበር።

በአድዋ ድል ክፉኛ ቂም አድሮበት የነበረው የፋሽስቱ ኢጣሊያ ጦር ዳግመኛ አገራችንን በወረረበት ወቅት በአራቱም አቅጣጫዎች አሻፈረኝ ያሉትንና ይፋለሙት የነበሩትን ኢትዮጵያውያን፣ በዋነኛነትም በአዲስ አበባ ከተማ ሰማዕታትን የጨፈጨፈበት ቀን የካቲት 12 ቀን 1929 ነበር።

በህዝቦች ጫንቃ ላይ ተቀምጦ፣ ህዝቦችን በገዛ አገራቸው በባርነት ሲገዛ የነበረው ፊውዳላዊ አገዛዝ፣ መንበረ ዙፋኑ የተነቃነቀው በየካቲት ወር 1966 ዓ.ም. በተማሪዎች እንቅስቃሴ ይመራ በነበረው ህዝባዊ አመጽ ነበር። ለህዝቦች ነጻነትና እኩልነት ሲባል የተካሄደውን አመጽ፣ በአቋራጭ ጠልፎ ራሱን በንጉሳዊው አገዛዝ ቦታ የተካውን ፋሽስታዊ፣ ወታደራዊ አገዛዝ ለመፋለም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የትጥቅ ትግል የጀመሩትና የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራት(ህወሃት) የተመሰረተውም የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም. ነበር።

ከራሳችን አልፎ ለሌሎች አገራት የሰላም ዘብ በመሆን ብቻ ሳይሆን፣ በተሰማራበት ግዳጅ ሁሉ በላቀ ስነምግባሩና ብቃቱ የዓለም አድናቆትን ያተረፈው ጀግናው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊታችን በአዋጅ የተቋቋመውም የካቲት 7 ቀን 1988 ዓ.ም. ነው።

ሴቶች ከዘመናት ጭቆና በኋላ የእኩል መብት ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋጋጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያደረጉት ትግል ለስኬት የበቃውም በወርሃ የካቲት መጨረሻ እ.አ.አ ከ1917 ጀምሮ ነው። በአጭሩ የካቲት ወር ታላላቅ ገድሎች የተፈጸሙባትና አንጸባራቂ ድሎች የተመዘገቡባት ወርቃማ ወር ናት ብሎ ማጠቃለል ይቻላል።

የወርሃ የካቲትን ትሩፋቶች ስንዘክር፣ የአሁኑን ትውልድ አስተዋጽኦም ማዬቱ ተገቢነት አለው። ከዚህ አንጻርም፣ የአገራችን ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት ባካሄዱት ትግል አዲሲቷን ኢትዮጵያ መፍጠር ችለዋል። ቀድሞ ከነበርንበት የስልጣኔ ማማ ወርደን፣ በእርስ በርስ ጦርነትና በከፋ ድህነት የምንታወቅበትን አሳፋሪ ታሪክ መቀየር አለብን በሚል ቁጭት ተነሳስተውም ባለፉት 26 ዓመታት ባከናወኑት ዘርፈ ብዙ ገድል የአገራችን ትንሳኤ አይቀሬ መሆኑን ያመላከቱ ታላላቅ ድሎችን አስመዝግበዋል።  በተለይም ባለፉት 15 ዓመታት በአገሪቱ በተከታታይ የተመዘገበው ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት የአሁኑን ትውልድ የሚያኮራ የቅርብ ጊዜ ታሪኩ አካል ነው።

ይህም ሆኖ ግን፣  አሁንም ትውልዱን እንቅልፍ የሚነሱ በርካታ ችግሮች ከፊቱ ተደቅነውበታል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ፣ ሃብት መፍጠር የቻሉ ሞዴል አርሶ አደሮችን እና የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪ አንቀሳቀሳቃሾችን ማፍራት የቻልን ብንሆንም፣ አሁንም ሩብ ያህሉ ህዝባችን ከድህነት ወለል በታች እየኖረ መሆኑ አሳሳቢ ችግር ሆኖ ቀጥሏል። በዴሞክራሲ ግንባታ ረገድ ሥር ነቀል ለውጥ ያመጣን ብንሆንም፣ በታሰበው ፍጥነት ልክ ግን አልተጓዝንም። መልካም አስተዳደርን በማስፈን በኩል መሻሻሎችን ያሳየን ብንሆንም፣ የህዝባችንን እርካታ ገና አላገኘንም። ህዝባችንን ያማረሩ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባራትና የመሳሰሉ ሌሎች በርካታ ጉልህ ችግሮችም አሉብን።

መሪው ድርጅት፣ ባለፉት 26 ዓመታት የተመዘገቡ ድሎችን እና ያጋጠሙ ችግሮችን በጥልቀት ገምግሞ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠልና ድክመቶችን በማረም የአገራችንን ህዳሴ ለማፋጠን መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች ለይቶ አስቀምጧል። ችግሮቹን በተደራጀ የህዝብ ንቁ ተሳትፎ ለመፍታት ይቻል ዘንድም ወደ ተግባር በመግባትና አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማካሄድ ላይ ይገኛል።

ይሁንና በመንግሥት ጥረት ብቻ ችግሮቻችን ሁሉ ይፈታሉ ብሎ መጠበቅ አይቻልም። የመንግሥት ጥረት ውጤታማ የሚሆነው መላው ህዝባችን፣ በተለይም ወጣቱ ትውልድ በአገራችን የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ የእድገት ጉዞ በባለቤትነት መንፈስ አጠናከሮ መቀጠል ሲችል ነው።

እንደሚታወቀው፣ የአሁኑ ትውልድ ፍልሚያ ከውጪ ወራሪ ሃይል ጋር ሳይሆን አሁንም ድረስ እየተፈታተነን ካለው ድህነት እና ኋላቀርነት ጋር ነው። የአገራችን የወደፊት እጣ ፋንታ የሚወሠነውም፣ የጋራ ፕሮጀክታችን የሆነውንና የጀመርነውን የኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞ በማስቀጠል ከዳር ማድረስ ስንችል ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የራሱን ወርቃማ ታሪክ እየጻፈ ያለው ወጣቱ ትውልድ፣ የወርሃ የካቲት ትሩፋቶቹን እየተንከባከበ፣ ከአያት ቅድመ አያቶቹ በወረሰው የአይበገሬነት ወኔ  የኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞን ከዳር ለማድረስ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy