Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የየካቲት ድሎች ሲጨለፉ

0 502

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የየካቲት ድሎች ሲጨለፉ

ዳዊት ምትኩ

ወርሃ የካቲት ገድለ ብዙ ናት። ጥቂቶቹን ለማንሳት ያህል ሰባትን፣ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ የተመሰረተበትን የካቲት 11ን፣ ፋሽሽት ጣሊያን በግፍ የጨፈጨፋቸው ዜጎች መታሰቢያ የሆነውን የካቲት 12ን እና የአድዋ ድል መታሰቢያ የሆነውን የካቲት 23ን እንዲሁም የሠራዊቱ ቀን የሆነውን የካቲት ሰባትን መውሳት ይቻላል። እነዚህ በአገራችን የተፈፀሙ ገድሎች ለአገር አንድነት ያላቸውን ፋይዳ ከፍተኛ ነው። አዲሱ ትውልድ ከዚያ ትውልድ ታላለቅ ቁም ነገሮችን ሊማርባቸው የሚገቡ ናቸው።

ህወሓት የተመሰረተበትን 43ኛ ዓመት ስናስታውስ የትግሉን ጅማሮና መራር ሂደት ልንዘነጋው አንችልም። በጥቂት ግለሰቦችና ብረት የተጀመረው የህወሓት ትግል በደደቢት በረሃ ነው ችቦው የተለኮሰው። ከዚያም በኋላ ከአምባገነኑ የደርግ ሥርዓት ጋር ፍልሚያ ተጀመረ። ደርግ የትግራይ ህዝብን “አሳውን ለማጥፋት ኩሬውን ማድረቅ” የሚል ጨካኝ መርህን በመከተል የትግራይ ህዝብን በጅምላ ጨፍጭፏል። ምናልባትም ከ100 ሺህ በላይ ወጣቶች ሙትና አካለ ስንኩል ሆነዋል። አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ሃብት ንብረቱን አጥቷል።

ትግሉ ግን አልተቋረጠም። ኢህድንና ስምጥ ሸለቆ ተመሰረቱ። ኢህአዴም ፈር ያዘ። ትግሉም ወደ መሃል አገር እየገፋ መጣ። ደርግ ተስፋ ቆረጠ። ኢህዴግ እያየለና በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ተቀባይነቱ ናኘ። ህዝቦች ሁለሉ ተረባረቡ። ደርግም አከርካሪው ተሰባብሮ ወደቀ። 1983 ዓ.ም በአገራችን አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ። ሳጥን ውስጥ ገብተው የተቆለፉባቸው እንደ ዴሞክራሲ፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት፣ ነፃ ፕሬስን የመሳሰሉ ጉዳዩች ብቅ አሉ። በአገራችን ላይ አዲስ የዴሞክራሲ ሥርዓት ፈነጠቀ። የህዝቦች የሰላም የልማትና የዴሞክራሲ የዘመናት ጥያቄዎችም ተመለሱ።

የደደቢቱ የትግል ጅማሮ ዛሬ ለምንገኝበት አስተማማኝ ሰላም፣ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት እንዲሁም ስር በመስደድ ላይ የሚገኝ ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን ምክንያት ሆነ። ድህነታችን ታሪክ እንደሚሆን ዓለም ማመን ጀመረ። ተደማጭነታችንም እየጎላ ነው። የአፍሪካዊያን ወንድሞቻችንም ምሳሌ እየሆንን ነው።ምስጋና ለደደቢት ትገል ጀማሪዎች ይሁን። እናም እነዚያን የትግሉን መሪዎችና መስዋዕቶችን መቼም ቢሆን ልንዘነጋቸው አንችልም። ክብርና ሞገስ ለእነርሱ ይገባል።

በወርሃ የካቲት የምናስታውሰው ሌላኛው ገድል ፋሽሽት ኢጣሊያ ኡትዮጵያዊያንን በግፍ የጨፈጨፈበትን የካቲት 12ን ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ በኢጣሊያ መንግሥት የኢትዮጵያ ወኪል አገረ ገዥ የነበረው ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ፣ የኔፕልስ ልዕልት ልጅ መውለዷን ምክንያት በማድረግ በቤተ መንግሥቱ ለድሆች ምጽዋት ለመስጠት ስለፈለገ የከተማው ድሆች እንዲሰበሰቡ በማዘዝ ሶስት ሺህ የሚሆኑ ምንዱባኖች በቅጥሩ ውሥጥ ተኮልኩለው ነበር፡፡ ለእያንዳንዱ ደሀም ሁለት የማርትሬዛ ብር እንዲሰጥ ተወስኖ ነበር፡፡ በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ራሱ ጀነራል ግራዚያኒ፣ የሜትሮፖሊታን ጳጳስ አቡነ ኪርል እንዲሁም ታላላቅ የኢጣሊያ ሹማምንት ተገኝተው ነበር፡፡

እኩለ ቀን ሲሆን ግራዚያኒ በቤተ መንግሥቱ መግቢያ ደረጃ ላይ ሆኖ ለተሰበሰበው ሕዝብ ዲስኩር ማሰማት እንደጀመረ በግቢው በር በኩል ሁለት ቦምቦች ተከታትለው ፈነዱ፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ የፈነዳው ቦምብ ግን ከፍተኛ የፋሺስት ኢጣሊያ ባለሥልጣናት ከተቀመጡበት መካከል አረፈ፡፡ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች አራት ተጨማሪ ቦምቦች ተወርውረው ፈነዱ፡፡ በግራዚያኒ ላይ ቦምብ የወረወሩት አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ወጣቶች ናቸው፡፡

የዚህ አደጋ ቀያሽ ሆኖ የሚቆጠረው አብርሃ ደቦጭ እና ጓደኛው ሞገስ አስገዶም የኢጣሊያ ወረራ ሲጀመር አዲስ አበባ በሚገኘው የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ማርሻል ግራዚያኒ ጀርባውን ቆስሎ ወደቀ፣ የኢጣሊያ አየር ኃይል አዛዥ የነበረው ጀነራል አውሬሊዮ ሊዮታ ቀኝ እግሩንና ቀኝ ዐይኑን አጣ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጉይዶ ኮርቲሲ እና ሌሎች ኢጣሊያውያን እንግዶች በፈንጂው ተጎዱ፡፡

ፍንዳታው ጋብ ሲል ከንቲባ ኮርቴሲ ከወደቀበት ተነስቶ የተሰበሰቡት ኢትዮጵያውያን ላይ በማነጣጠር የመጀመሪያውን ጥይት ተኮሰ፤ የፋሺስት ፖሊሶችም ምሣሌውን በመከተል ሶስት ቀን የሚቆየውንና መላውን ከተማውን ያዳረሰውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ ከዚያው ከቤተ መንግሥት ውሥጥ ጀመሩ፡፡ በደረሰበት የፈንጂ አደጋ ማርሻል ግራዚያኒ በ350 ፍንጣሪዎች ቆስሏል፡፡ ታዲያ ይህንን ድርጊት ለመበቀል ከሶስት መቶ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ወዲያውኑ ተጨፈጨፉ። ቀጥሎም የተማሩ ወጣቶች፤ የጦር መኮንኖችና ካህናት፤ የደብረሊባኖስ መነኮሳት፤ በሙሉ እየተለቀሙ ተጨፈጨፉ። የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በቤት ውስጥ እያስገቡ ከውጭ ቆልፈው ቤንዚን እያርከፈከፉ አቃጠሏቸው።

ኢትዮጵያውያንን በተገኙበት በአካፋ በዶማ በመጥረቢያ እየቆራረጡ የደም ጎርፍ አወረዱ ፋሺስቶች በሶስት ቀናት ውስጥ ብቻ 30 ሺህ የሚሆን የአዲስ አበባንና የአካባቢውን ሕዝብ በጅምላ ጨፈጨፉ። ይህ የመስዋዕትነት ታሪክ አያቶቻችን በደማቸው ይህችን ሀገር እንዳስረከቡን የሚያሳይ ነው። እናም እነዚህን መስዋዕቶችንም እናከብራቸዋለን።

የአድዋ ድል ገድልም በየካቲት ወር የተከናወነ ነው፤ የካቲት 23 ቀን። የአድዋ ድል በትልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት የተፋለመው የያኔው ትውልድ በቅንነትና በስሌት ተዋድቆ ለመላው ጥቁር ህዝብ ተስፋን ያጫረ ወይም ያማለለ ታላቅ ድል አስመዘገበ። የፋሽሽት ጣልያን ጦር ባልሰለጠነና ኋላ ቀር ጠመንጃ በያዘ ህዝብ ተረታ። ድሉ የጥቁር አፍሪካዊያን ሆነ።

የድሎች ሁሉ የበላይ ድል የሆነውን አድዋን አበውና እመው ለባንዲራቸው ተዋድቀው ባንዲራችንን ከፍ አደረጓት። ኮርተው አኮሩን። ጥቁር አፍሪካን ሁሉ አኮሩ። ክብር ከቃል የገዘፈ ምግባር ላሳዩን የአድዋ ጀግኖች። ክብር በየዘመኑ ለኢትዮጵያ ልዕልና ለተዋደቁና እየተዋደቁ ላሉ ሁሉ! ክብር የእነርሱን ፋና ወጊነት ተከትለው አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ዳግም የማይገኝ ህይወታቸውን ቤዛ ላደረጉ ውድ የህዝብ ልጆች ይሁን!

በቅርቡ የካቲት ሰባት የተከበረው የሰራዊት ቀን የወርሃ የካቲት ሌላኛው ገድል ነው። የካቲት ሰባት መከላከያ ሰራዊታችን በአዋጅ ቁጥር 27/88 የተቋቋመበት ዕለት ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ ሁሉም የሠራዊት ቀን የሚያከብሩ ሀገራት ሠራዊታቸው ለሀገር እና ለባንዲራው ሲል የከፈለው መስዋዕትነትና ያሳየው ጀግንነት ያላቸው አክብሮት የሚገልፁበት፣ ሰራዊታቸው የሃገሩን ደህንነት ለማረጋገጥ ለሰጠው አገልግሎት ምስጋና የሚሰጡበት፣ ዘላቂ ብሄራዊ ጥቅማቸውን መጠበቅ የሚያስችል ወታደራዊ አቅም እንዳላቸው የሚያሳዩበት፣ በሠራዊታቸው ውስጥ የሚፈልቁ አዳዲስ ፈጠራዎችን ይፋ የሚያደርጉበትና ዕውቅና የሚሰጡበት እንዲሁም በሰራዊታቸውና በህብረተሰቡ ያለው ትስስር የሚያጠናክሩበት ቀን አድርገው ያከብሩታል፡፡

በኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት የተለያዩ የሠራዊት ክፍሎች የምስረታ ቀናቸውን ምክንያት በማድረግ በተቋም ደረጃ ዓመታዊ የስፖርት ፌስቲቫል በማዘጋጀትና እንደ ግንቦት 20 የመሳሰሉ የድል ቀናትን ምክንያት በማድረግ የሚያከብሩ ቢሆንም ራሱን ችሎ በታቀደና ወጥነት ባለው መልክ በሰራዊት ደረጃ የሚከበር አገራዊ የሰራዊት ቀን አልነበረም፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮውን ለመፈፀም በሚያሳየው የላቀ ጀግንነት፣ በህዝባዊነቱና በመልካም ሥነ-ምግባሩ በሀገሩም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች ከፍተኛ ተሰሚነትና ታማኝነት እያገኘ የመጣ ሠራዊት ነው፡፡

በመሆኑም ሠራዊታችን ያለው አኩሪ ታሪክ ተጠብቆ እንዲቀጥልና ታሪኩን ለአዲሱ ትውልድ እንዲተላለፍ ከማድረግ አንፃር “የሰራዊት ቀን” በሚል ዕለቱን ማክበር ታላቅ  ጠቀሜታ እንዳለው ስለታመነበት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ የካቲት 7 እንዲከበር በኢፌዴሪ መንግስት ተወስኗል፡፡ በዚህ መሰረትም ሰሞኑን ለስድስተኛ ጊዜ ተከብሯል። ሰራዊቱ ዕለቱን ሲያከብር ህዝባዊነቱን አሳይቷል። ለህዝብ የቆመ መሆኑንም አረጋግጧል። ይህ ተግባሩም ቀጣይ መሆኑን አሳይቷል።

የወርሃ የካቲት ድሎች ለዚህ ትውልድ የአገር ፍቅርን፣ መተባበርን፣ የዓላማ ፅናትንና ጠላትን በተባበረ ክንድ ድል መንሳትን የሚያስተምሩ በመሆናቸው ትውልዱ ሁሌም ሊዘክራቸው ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy