Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፎረሸው ፖለቲካ ሃይሎች እና የወጣቱ ዝንጋኤ

0 382

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፎረሸው ፖለቲካ ሃይሎች እና የወጣቱ ዝንጋኤ

ዮናስ

በሀገሪቱ ግጭት ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም የማስፈን ስራው ተጠናክሮ ስለመቀጠሉ በርካታ አስረጂዎች መጥቀስ ይቻላል። ለአብነት ያህልም መንግስት በሀገሪቱ ግጭት ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም የማስፈን ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ አረጋግጠዋል።

ሀላፊ ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ፤ በተለይ በቅርቡ በሰሜን ወሎ ዞን ሶስት ከተሞች ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች የሰው ህይወት መጥፋቱንና በመሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ገልፀዋል። በአካባቢው ግጭት እንዲከሰት የአመራር ክፍተት፣ የህዝቡ የመልማት ጥያቄ በሚፈለገው መጠን ምላሽ አለማግኘት እና ለወጣቶች በበቂ ሁኔታ የስራ እድል አለመፈጠርን በምክንያትነት አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት በሰሜን ወሎ ዞን ግጭት ተከስቶባቸው የነበሩት ወልዲያ፣ ቆቦ እና መርሳ ወደ ቀድሞ ሰላም እና መረጋጋት መመለሳቸውም በመግለጫቸው ተመልክቷል።   ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን በመስራት ለውጦች እየተመዘገቡ ነው ያሉት ዶክተር ነገሪ ወጣቶችን ማእከል ያደረጉ ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማቶች ተስፋፍተው በርካታ የስራ እድሎች መፈጠራቸውን ገልፀዋል። የተመዘገበው እድገት አመርቂ ሆኖ እያለ አሁንም ያልተፈቱ በርካታ ችግሮች አሉ ያሉት ሚኒስትሩ፤ በድህነት ቅነሳ፣ በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ፣ የመልካም አስተዳደር ችግርና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት በኩል የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለአብነት አንስተዋል።

እነዚህንና ሌሎችንም ችግሮች ለመፍታት መንግስት በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ባለበት ወቅት ጎታች የሆኑ እንቅስቃሴዎች በአንዳንድ አካባቢዎች የመከሰታቸውን ሚስጥር መግለጥ የዚህ ትርክት አብይ ጉዳይ ነው።

በእርግጥም የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች አሁንም በፎረሸው ፖለቲካ እየነገዱ ሃገሪቱ በመንታ መንገድ ላይ እንድትወድቅ ስለማድረጋቸው የኢህአዴግ ሊቀመንበር ጓድ  ሃይለማርያም ደሳለኝ አረጋግጠዋል። የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ 4 መደበኛ ጉባዔ ላይ ተገኝተው የነበሩት ሊቀመንበሩ “የምንገኝበት ምእራፍ ሁለት ተቃራኒ ጉዳዮች መሳ ለመሳ እየሄዱ ያለበት ነው፤ አንደኛው ለ25 ዓመታት ሀገሪቱ ፈጣንና ተከታታይ እድገት ማስመዝገብ የቻለችበት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እየጨመረ የመጣውን ፍላጎት ማስተናገድ የሚችል አቅም ለመፍጠር ትግል የሚጠይቅበት ወቅት ላይ ነን” ሲሉ ነው ያረጋገጡት።

የጨመረውን ፍላጎት ያህል ህብረተሰቡን በሚፈለገው ደረጃ ማርካት አለመቻልን እንደ ችግር ጠቅሰው፤ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች በጀማሪ ካፒታሊዝም የእድገት ደረጃ የሚያጋጥም መሆኑን፤ ግን ደግሞ በፎረሸ ፖለቲካ የተቃኙ ሃይሎች ነገሩን በማጦዝ ሃገሪቱ ፈተና ላይ እንድትወድቅ መስራታቸውን እና እየሰሩ መሆናቸውን በማብራራት፤ ወጣቱ ትውልድም በዚህ መድረክ ላይ የነቃ ተሳትፎና ትግል በማድረግ የሀገሪቱ የህዳሴ ጉዞ እንዲሳካ ከፍተኛውን ሚና መጫወት ይኖርበታል ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በእርግጥ ችግር አለ። የወጣቱን ፍላጎት ለማሟላት መንግስት ዳተኛ ነው የሚሉ ሃይሎች ግን እንቅስቃሴውን ለማኮልሸት ካልሆነ ሌላ ግብ የሌላቸው ለመሆኑ የግጭቶች መነሻ የነበረችውን የሶማሌ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ በማየት ማጠየቅ ይቻላል።

በሱማሌ ክልል መንግስት የመደበውን ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ በመጠቀም 5ሺህ 927 ወጣቶች ወደ ስራ መግባታቸው ነው የእንቅስቃሴው ቀዳሚ ማሳያ፤ ይህ ደግሞ የጠቅላላ ሃገሪቱ እንቅስቃሴ ማሳያ ይሆናል። በአጋር ድርጅቱ እና በዳር ሃገር ይህ ከሆነ በአባል ድርጅቶችና በግንባሩ ክልሎች ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አይከብድም።

በክልሉ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ  እንደገለጸው ወጣቶቹ ወደ ስራ የገቡት ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ ደግሞ ሂደቱ በምን ፍጥነት እንደሚጓዝ ለማስላት ይቻላል። ወጣቶቹ ጅግጅጋን ጨምሮ በክልሉ 12 የተለያዩ ከተሞች ወስጥ በ426 አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች በማደራጀት 234 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ ተሰጥቷቸው ወደስራ እንደገቡም የቢሮው መረጃ አያይዞ አመልክቷል፡፡

የስልጠናም ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን ከተደራጁት አባላት መካከል ከሦስት ሺህ በላይ ሴቶች ናቸው፡፡ ወጣቶቹ በብረታ ብረት፣ በጸጉር ስራ፣ በአነስተኛ ንግድ፣ በእንስሳት እርባታና ማድለብ፣ በንብ ማነብ፣ በጓሮ አትክልትና የቤት እና የቢሮ እቃዎች እንዲሁም በእንስሳት መኖና ማዕድን ማምረት ስራ መሰማራታቸውም ታውቋል፡፡ በፌደራል ደረጃም ጉዳዩ በተመሳሳይ የተያዘ ለመሆኑ ስለፎረሸው ፖለቲካ ሲባል አስረጂዎች መጥቀስ ተገቢ ይሆናል።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በከተሞች የመንግሥት ዋና ትኩረት ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ሥራ አጥነትንና ድህነትን መቀነስና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች እኩል ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የሥራ ፈጣሪነት አስተሳሰብና ዕውቀትን በማዳበር ዜጎች የራሳቸውን ሥራ በመፍጠር ለአገሪቱ ቀጣይ የኢንዱስትሪ ልማት መሠረት እንዲሆኑ ማድረግም የትኩረት አቅጣጫው ማጠንጠኛ ነጥብ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ በተለዩት የትኩረት አቅጣጫዎች መሠረት ግቦች ተቀምጠው ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ዕቅዱን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ያስችል ዘንድም ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ጉዳዩን በባለቤትነት የሚመራ ራሱን የቻለ የመንግሥት አካል ተቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ነው የፎረሸው ፖለቲካ አስረጂያችን፡፡

በዚህ ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት እየተከናወኑ ከሚገኙ ሥራዎች መካከል አንደኛው በዕቅድ ዘመኑ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ በተመረጡ አስራ አንድ ከተሞች ውስጥ ለሚኖሩ ከ604ሺ በላይ የሚሆኑ የደሃ ደሃ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተተገበረ የሚገኘው የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር ነው፡፡

በዚህም በመጀመሪያው ዙር የትግበራ ምዕራፍ ከአስራ አንዱም ከተሞች ማለትም ከአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌ፣ ሰመራ፣ ደሴ፣ አዳማ፣ ጅግጅጋ፣ አሶሳ፣ ሃዋሳ፣ ጋምቤላና ሐረሪ የተመረጡ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ አንድ መቶ ዘጠና ሺህ ዜጎችን በአካባቢ ልማት ሥራዎች በማሳተፍና በቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ በተያዘው የበጀት ዓመትም በሁለተኛ ዙር በሰባት ከተሞች (አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌ፣ ደሴ፣ አዳማ፣ ጅግጅጋ፣ ሃዋሳ) የሚኖሩ 210ሺ 743 ዜጎችን የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ለማድረግ ያልተቋረጠ የድጋፍና ክትትል ሥራዎች እየተሰራ መሆኑን ኤጀንሲው በመረጃ መረቡ አመልክቷል፡፡

በጥቅሉ የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ዜጎችን በአካባቢ ልማት ሥራዎች በማሳተፍና የሥራ ዕድል የሚፈጥሩበትን መንገድ እየተመቻቸ ነው። የመርሃ ግብሩ ተቃሚዎች የሚሰማሩባቸው የአካባቢ ልማት ሥራዎችም የተለዩ ሲሆን፤ እነዚህም የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት፣ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ፣ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት፣ መሠረተ ልማት ግንባታና የከተማ ግብርና ናቸው፡፡ የፋይናንስ ፍሰትና ግብዓት አቅርቦትን በተመለከተም በበጀት ዓመቱ በሁሉም የፕሮጀክቱ ማዕቀፎች የበጀት ድልድል ተሰርቶ ለከተሞች እንዲዳረስና ሥራ ላይ እንዲውል መደረጉም በመረጃው ተመልክቷል።

ይህ በቂ ባይሆንም የወጣቶች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የመንግስትን ቁርጠኝነት ግን በበቂ ሁኔታ የሚያረጋግጥ ይሆናል። ይህ ከሆነ ታዲያ ወጣቶች የግጭት ሰለባ የሚሆኑት ለምንድነው ሲባል በፎረሸው ፖለቲካ ትእግስት እንዲያጡ የማድረግ ዘመቻ መሆኑ የማያከራክር እውነታ ይሆናል።

የፎረሸው ፖለቲካ ሃይሎች ዋነኛ ስልት በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ሐሳባቸውን የሚያካፍሉ ዜጎች ጨለምተኛ አስተሳሰብ እንዲይዙ የሌለውን እና ያልሆነውን እንዳለና እንደሆነ አድርጎ ማራገብ ነው። በዚህም ወጣቶች  በተለያዩ ጎራዎች በመሠለፍ የቡድን ጥቅምን ታሳቢ ያደረጉ ጭቅጭቆችና ውዝግቦች ውስጥ እንዲገቡ ያመቻምቻሉ፡፡ በእልህና በግትርነት ላይ በተመሠረቱ ጉንጭ አልፋ ክርክሮች በመጥመድም  ወደፊት ከሚያራምዱ የለውጥ ሐሳቦች እንዲርቁ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ በሃገር ሚዛን ላይ ሲቀመጥ የፎረሸ ፖለቲካ ይሆናል። በተቃውሞ ጎራ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና አመራሮችም ለአዲሱ ጅማሬ የሚጠቅሙ ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ ወጣቶች ከገቡበት አረንቋ ውስጥ እንዲቆዩ በመስራት ነው ሃገሪቱን ጨምሮ እነርሱንም አደጋ ላይ እየጣሉ የሚገኙት።  

ወቅቱ አገርን ከውድቀት የመታደጊያ እንጂ፣ የቆዩ ቁስሎችን እያነካኩ ማመርቀዝ ባይሆንም ፖለቲካ የፎረሸባቸው ግን ይህን ማጤን የሚያስችል ቁመና ላይ አይገኘም። ለማንም አይጠቅምም፡፡ በተለይ ከተበላሸው የፖለቲካ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በማስወገድ፣ ለአዲሱ ጅማሬ የሚጠቅሙ ግንኙነቶችን ለመፍጠር ራሳቸውን በብቃት ማዘጋጀት ሲገባቸው ሰለባ የሚሆኑ ወጣቶችን ወደግጭት መድረክ ማምጣት ዋነኛ ስራቸው ነው፡፡ ራሳቸውን አንድም ቀን ሳይፈትሹ ይልቁንም ሊፈትሿቸው የሚሞክሩትን እየኮረኮሙ ሌሎችን በመውቀስ የፎረሸ ፖለቲካ በማጥመድ ወጣቶችን እያጠመዱ ነው፡፡ ከዘመኑ ፍላጎት ጋር መጣጣም የማይችል አካል በርግጥም አማራጩ የፎረሸን ፖለቲካ መሞከር ነው፡፡  

ስለሆነም ወጣቱ ከጥቅም በላይ አገርና ሕዝብን ሊያከብር ይገባል፡፡ በጎራዎች ተቧድኖ አገርን መገንባት እንጂ ማፍረስ መገለጫው እንዳልሆነ ሊያሳይ ከተገባ ወቅቱ አሁን ነው፡፡   ዴሞክራሲን እያነበነቡ ፀረ-ዴሞክራሲ ሀይሎች አዘቅት ውስጥ ሊዘፍቋቸው የሚሹ ሃይሎችን ከላይ የተመለከቱ መሰረታዊ ስልቶችን በመገንዘብ እራሳቸውን ሊያቅቡ ከተገባ ጊዜው አሁን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ የሚታወቀው በመከባበር፣ በመረዳዳትና በመተሳሰብ ተምሳሌትነቱ ነው፡፡ ችግር ሲፈጠር እንደ ባህሉ የሚፈታበት አርዓያነት ያለው ልምድ አለው፡፡ ከአገሩ በላይ ምንም ስለሌለው አገሩን ለጥቅም አሳልፎ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ ይልቁንም ለአገሩ በፍቅር መስዋዕትነት ሲከፍል የኖረ አንፀባራቂ ታሪክ ያለው ጀግና ሕዝብ ነው፡፡ ይህንን ማስቀጠል ደግሞ የወጣቱ ግዴታ ነው። ይህንን ሕዝብ አክብሮ ማገልገል አለመቻል የትውልድና የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ግዴታውን እንዲወጣ ካስፈለገ ደግሞ በውስጡ የሰረጸውን የፎረሸ ፖለቲካ እና የዚሁ ፖለቲካ መቀመሚያ የሆነውን የፀረ-ዴሞክራሲ አመለካከት ሙልጭ አድርጎ ማራገፍን ይጠይቃል፡፡ ሲደመደም፣ ወጣቱ እንዳይዘናጋና በአፍራሽ ሀይሎች የፖለቲካ ወጥመድ እንዳይጠለፍ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ከወዲሁ ሊያደርግ ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy