Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ያልተፈታው ቋጠሮ

0 268

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ያልተፈታው ቋጠሮ

ዳዊት ምትኩ

ህገ ወጥ ስደት የዓለማችን አንዱ የችግር መገለጫ ነው። በአገራችንም ያልተፈታው የችግር ቋጠሮ ሆኖ ቀጥሏል። የችግሩ መንስኤ የአመለካከት ጉዳይ ነው። ይህ የአመለካከት ችግር መነሻው እዚህ ሀገር ውስጥ ሰርቶ ማደግ አይቻልም ከሚል የተሳሳተ ግንዛቤ የመነጨ ነው። ሆኖም በአሁኑ ሰዓት እዚህ አገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥ የሚቻልና ችግርን መፍታት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው። ይህን የተሳሳተ አስተሳሰብ ማስተካከል ይገባል።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ላለፉት 16 ተከታታይ ዓመታት ጠንክረው በመስራት የተጎናፀፉት ተምሳሌታዊ የዕድገት ትሩፋቶችን እያቋደሳቸው ነው። በዚህም በሀገራቸው ውስጥ ሰርተው ማደግና መለወጥ ብቻ ሳይሆን፣ ሃብት ማፍራትና ጥሪት መቋጠርም ችለዋል። መንግስት ባመቻቸላቸው ሰፊ የስራ መስክ ውስጥ በመሰማራትም ራሳቸውንና ሀገራቸውንም እየጠቀሙ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በርካታዎችም የሚሊዩነርነት ጎራን በመሰለፍ ለሌሎች ወገኖቻቸው የስራ ዕድል እየፈጠሩ ይገኛሉ።  

ይሁንና ከዚህ የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በተለየ መልኩና በሀገር ውስጥ ሰርቶ ማደግና መለወጥ የሚቻልበት መንገድ እያለ ስደትንና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን እንደ አማራጭ የሚወስዱ ዜጎች መኖራቸው የሚታበይ አይደለም።

እርግጥ ህገ- ወጥ ስደት የሁሉም ታዳጊ ሀገሮች ችግር ነው። እናም አገራችንም በችግሩ ከሚጠቁት መካከል አንዷ እንዲሁም የድርጊቱ መነሻና መሸጋገሪያ ናት። በተለይም ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚደረገው ህገ- ወጥ ስደት ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው የዜጎቻችን መዳረሻ እየሆነ መጥቷል ማለት ይቻላል።

የህገ-ወጥ ስደቱ ግንባር ቀደም ተዋናዮች ወጣት ሴቶችና ወንዶች በመሆናቸው በቀላሉ ለችግር ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። እነዚህ ዜጎች ውጭውን እንጂ ውስጣቸውን በቅጡ ማማተር ያልቻሉ ይመስለኛል። በዓለማችን ካለው የተፈጥሮ ሃብት እጥረት ሳቢያ የትኛውም አገር ማርና ወተት የሚዘንብበት አይደለም።

እርግጥ በህገ- ወጥ ስደት አደጋ የሚጠቁ ኢትዮጵያውን የስደታቸው መንስዔ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህ ከፊል ዕውነታ ያለው እሳቤ ሊሆን ይችላል። የተሟላ አስተሳሰብ ነው ማለት ግን አይቻልም።

ዜጎች በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ድህነትን ለመቅረፍ የሚያደርጉት ተነሳሽነት ትክክል አይደለም ሊባል የማይችል ቢሆንም፤ በህገ ወጥ ደላሎችና አፈ ቅቤዎች ተታልለው የእነርሱ ሲሳይ መሆናቸው ግን እጅጉን የሚያስቆጭ ነው። ከዚህ ባሻገርም ሁሉም ነገር ህግን የተከተለ አካሄድ ተጠቅሞ ማደግና መለወጥ ሲቻል ህገ- ወጥ ስደትን መርጦ ለአደጋ መጋለጡ አግባብነት ያለው ተግባር አይመስለኝም።

እንደሚታወቀው ሁሉ በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በትክክለኛ የልማት ጎዳና ላይ ትገኛለች። ዕድገቱም ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፈጠሩ ዜጎች የልማቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። በተለይም ወጣቶች በአነስተኛና ጥቃቅን ልማታዊ ሥራዎች ላይ በመሳተፋቸው የቤተሰብ እጅን ከመጠበቅ ለመዳን ችለዋል። እንዲያውም ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ቤተሰቦቻቸውንም እየረዱ ነው። ይህ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሃቅ ነው።

እንደሚታወቀው ባለፉት ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን የተንሰራፋውን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ ስራ አጥነት መቅረፍ አንደኛው ተግባሩ በማድረግ ነበር።

በዚህም በከተሞች የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት እንዲሁም ለወጣቶች የተዘዋዋሪ ፈንድ አገልግሎት በመስጠት ለዜጎች የስራ ዕድል እየፈጠረ ነው። ዜጎችም በየሙያቸው በመሰማራት ለሀገራዊ ልማት ከፍተኛ ጉልበትና አቅም መሆን መቻላቸውን አረጋግጠዋል።

ዛሬ በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው ከመንግስት እንዲሁም ከቁጠባና ብድር ተቋማት ባገኙት ገንዘብ ተጠቅመው ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለቤትነት የተሸጋገሩ ዜጎች በርካታ ናቸው። እነዚህ ዜጎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር የመንግስትን ጥረት በመደገፍና የሀገሪቱን ልማት በማፋጠን ላይ ይገኛሉ።

መንግስት የቀየሰውን አዲስ የስራ ባህል በተግባር በመተርጎምና ያገኙትን የስራ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ሚሊየነር ለመሆን የበቁ ዜጎቻችን ሊፈጠሩ ችለዋል። በአንፃሩ ደግሞ ለጥቂት አፍራሽ ሃይሎች አሉባልታ ተንበርክከውና ወደ ውጭ በማየት የማያውቁትን ሀገር ሲናፍቁ ለአደጋ የተጋለጡ ወገኖች ቁጥርም ቀላል አይደለም።

እርግጥ በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅቶ በሀገር ሰርቶ ማደግና መለወጥ እየተቻለ የአጭበርባሪ ደላላዎች ሲሳይ ሆኖ ለችግር መጋለጥ አሳዛኝ ቢሆንም፤ አሁንም አልረፈደምና ዕውነታውን መገንዘብ ያስፈልጋል።

በህገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩት እነዚህ ወገኖች ምንም እንኳን በመዲናችን ውስጥ የሚገኙና እስከ አንድ ሺህ የሚገመቱ ቢሆንም፤ በከተማና በገጠር ባሰማሯቸውና እስከ ሃያ አምስት ሺህ እንደሚደርሱ ይታመናል። በእነዚህ ተባባሪዎቻቸው አማካኝነትም ችግሩ ዛሬም ላይ ሊፈታ አልቻለም። በዚህም ሳቢያ ሁሉም የሀገራችን ክልል ዜጎች ሰለባ እየሆኑ ነው።

በአንፃሩም ሀገር ውስጥ ሰርቶ ማደግ እንደሚቻል ከወጣቱ ይልቅ የተሻለ ግንዛቤ ያለው ቤተሰብ እንደሆነ ይታመናል። ታዲያ ይህንን እውነታ አሳምኖና አስረድቶ ገና ለገና አገኛለሁ የሚል አስተሳሰብን ከማስረፅ ይልቅ፤ የጉዳዩ ተባባሪ በመሆን የአጋዥነት ሚና ሲጫወት ይታያል። ጥሪታቸውን ሸጠው አሊያም ተበድረው ልጆቻቸውን የሚልኩ ቤተሰቦች በርካታ ናቸው።

ያም ሆኖ የችግሩን መስፋትና አደገኝነት የተገነዘበው መንግስት የዜጎችን ከአደጋ ለመታደግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ቢጀምርም ጥረቱ የተፈለገውን ያህል ውጤት ማስመዝገብ አልቻለም። የችግሩን አደገኛነት እንደ ፊልም ካልቆጠርነው በስተቀር በአንድ ወቅት በዕቃ ታንከር ውስጥ ታሽገው ህይወታቸውን ካጡት ዜጎቻችን በተጨማሪ በባህር ላይ ተጥለው የአሳ ነባሪ ሲሳይ ለመሆን የሚገደዱ ወገኖቻችንን ስቃይና እንግልት ከራሳቸው የስደት ሰለባ ከሆኑት ወገኖች አንደበት አርምጠናል።

እርግጥ ችግሩ የእያንዳንዳችንን በር እስኪያንኳኳ ድረስ መጠበቅ የለብንም። እናም ለችግሩ መንስዔ የሆኑ ጉዳዩችን ማወቅ ይገባል። እነዚህ የችግሩ ተዋናዮች ግብ አንድና አንድ ነው። ገንዘብን በማንኛውም መንገድ አግኝቶ የተደላደለ ኑሮን መምራት። ለእነርሱ የዜጎች ስቃይና ሞት ምናቸውም አይደለም። የመብታቸው፣ የደህንነታቸውና የክብራቸው ጉዳይም አያሳስባቸውም። ከዚህ ዘግናኝ ድርጊት የሚያገኙት ገንዘብ ብቻ ስለሚታያቸው ለሌላው ጉዳይ ደንታቸው አይደለም። ይህን አሳዛኝ ተግባር እዚህ አገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል በትጋት በማስተማር መለወጥ ይቻላል። የአስተሳሰብ ችግሩን መቅረፍ ከተቻለ ወጣቶቻችን እዚሁ አገር ውስጥ መንግስት በፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ ሰርተው መቀየር ይችላሉ። የህገ ወጥ ስደትን ያልተፈታ ቋጠሮ በአስተማማኝ ሁኔታ መፍታት ይቻላል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy