Artcles

ይህ ስኬት አይደለምን?

By Admin

February 22, 2018

ይህ ስኬት አይደለምን?

ዳዊት ምትኩ

በአሁኑ ሰዓት አገራችን ምርትና ምርታማነትን እያሳደገች ነው። በተለይ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት መንግስት ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በሰጠው ትኩረት ስኬት ከተመዘገበባቸው ዘርፎች አንዱ ለመሆን በቅቷል። ከ20 ዓመታት በፊት የአገራችን  ዓመታዊ የምርት መጠን ከ80 ሚሊዮን ኩንታል ያልበለጠ ነበር፤ አሁን ላይ በመኸር ምርት ብቻ ከ345 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማግኘት ተችሏል። ይህም የሚሊዩኖች ህይወት እንዲለወጥ ምክንያት ሆኗል።

ከዚህ ባሻገር የግብርናው ምርት የዋጋ ግሽበትን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተደረገ ላለው ርብርብ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ነው። እርግጥ መንግስት ግሽበትን ለመቆጣጠር እያደረገ ካላቸው ጥረቶች መካከል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚለው መስፈርት ፍሬ እያፈራ ነው። የአንዳንድ ወገኖችን ስኬት አልተመዘገበም የሚል ሾላ በድፍን ዓይነት ትችትን ስንሰማ፤ ይህ ስኬት አይደለምን? ብለን መጠየቅ ይገባናል።

እውነትም ላለፉት 26 ዓመታት የዚህ አገር ጉዞ በስኬት የታጀበ ነው። በተለይ የዋጋ ግሽበትን በምርትና ምርታማነት ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለው ጥረት ፍሬ ማፍራት ጀምሯል። በአሁኑ ወቅትም ከፍ ብሎ የነበረው የዋጋ ግሽበት እያሽቆለቆለ ነው። ይህ የመንግስት እርምጃ ወደፊት ተጠናክሮ ከቀጠለ ግሽበቱን ትርጉም አልባ ሊያደርገው የሚችል ነው።

በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ኑሮው እንዲሻሻል ተገቢ ትኩረት አግኝቷል። ለዚህም በቂ ማሳያዎችንም ማቅረብ የሚቻል ይመስለኛል። መንግሥት የዘመናት ቁጭቱን ሀገራዊ መሠረት ባላቸው አቅጣጫዎች የመፍታት ትግሉን እያካሄደ ነው። አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ ሀገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን የመጀመሪያው የልማት ዕቅድ አረጋግጧል።

እርግጥ በአርሶ አደሩ እጅ እንዳለ የሚታሰበው መሬት አነስተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካለችው መሬት የሚያገኘው ምርት ዝቅተኛ ነው። ይህን መንግሥት በሚገባ በመገንዘቡ ዘርፈ ብዙ የማሻሻል ጥረቶች አድርጓል። በውጤቱም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ይዞ ለውጥ  ማምጣት አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ መስበር ችሏል። አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለሰፋፊ እርሻዎች ትኩረት መስጠትና ለውጥ ማምጣትን የሚሰብኩ ወገኖች እንዳሉ ግልጽ ነው። እነዚህ ወገኖች የሚሰብኩት በግብርናው ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ትኩረት የመስጠትን አስፈላጊነት የሚሰብክ ነበር። ይህ ደግሞ ሀገራዊና ህዝባዊ ጥቅም የሚመጣበትን ምስጢር ካለመረዳት ወይም ለመረዳት ካለመፈለግ የመጣ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

መንግሥት አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ገልጿል። ይህን የመንግሥትን ፖሊሲ ትክክለኛነት ለማረጋገጥም ተችሏል። የሚታይና አሳማኝ ውጤት ማምጣትም እንደተቻለም ከአርሶ አደሩ በላይ ምስክር የሚያሻው አይመስለኝም። ምንም እንኳን ለውጡን የማይፈልጉ ኃይሎች ስህተት ፈላጊ ሆነው ቢቀጥሉም፤ በግብርናው ዘርፍ ባመጣነው ለውጥ ብዙዎች በመስማማት ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ፣ ለምርቱ ገበያ በማመቻቸትና ከግሉ ዘርፍ ጋር ትስስር በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን አሳድጋ ተጠቃሚ በመሆን ላይ ትገኛለች።

አርሶ አደሩ የለውጥ መስመሩን ተረድቶ በእምነት ወደ ሥራው በመግባቱ በዓመት ሁለቴና ከዚያም በላይ ለማምረት ችሏል። እንዲሁም በከርሰ ምድርና በገጸ -ምድር ያለውን የውኃ ሃብት የመጠቀም ሰፊ ተግባር አከናውኗል። በውኃ ማሰባሰብና ማቆር፣ የጉድጓድ ውኃን በመጠቀም የወንዝ ውኃን ጠልፎ ጥቅም ላይ በማዋል ብዙ ርቀት ተጉዟል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለከተማው ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍላጎት የሆኑትን ምርቶች ማቅረብ ችሏል። ከነዚህ ውስጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ናቸው።

ከዝናብ ጥገኝነት በተላቀቁ አመራረት የተገኙትን ምርቶች መጠቀምም እየተቻለ ነው። የመስኖ ልማት ሥራው በበጋ የበቆሎ እሸት ተመጋቢዎች እንዲሆን አስችሎናል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ሥራው ከሁለት እጥፍ በላይ አድጓል። ለገበሬው በዚያው ልክ ገበያው ተመቻችቷል። አርሶ አደሩ በራሱ ባቋቋማቸው የአርሶ አደሮች የህብረት ሥራ አማካይነት ምርቱን ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል። በዚህም ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ነው። የግብርናው ዘርፍም በአስተማማኝ ሁኔታ ገበያው ሳያሳስበው ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ላይ ብቻ አተኩሮ ለልማት ለውጥ ሽግግሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል።

አርሶ አደሩን በማህበር የማደራጀት ሥራ በተናጠል ሊፈቱ ያልቻሉ ችግሮች በጋራ እንዲፈታ አስችሎታል። መንግሥት ያቋቋመው የምርት ገበያም በተለይ ቡና፣ ሰሊጥ፣ በቆሎና ቦሎቄ በዘመናዊ ግብይት ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት አረጋግጧል።

ከዚህ በተጨማሪ አርሶ አደሩ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የማድረግ ጥረት ለምርታማነቱ የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው። በመኸር ወቅት ብቻ ከ345 ሚሊዩን ኩንታል በላይ ተገኝቷል። ይህ ምርታማነትም የዋጋ ግሽበትን እየተቆጣጠረው ነው።

ላለፉት ዓመታት የግብርናው ዘርፍ ባሳየው እድገት የአገራችን የኑሮ ሁኔታ እንዲረጋጋ ማድረግ ተችሏል። እንደሚታወቀው ሁሉ መንግሥት አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ገልጿል። ይህን የመንግሥትን ፖሊሲ ትክክለኛነት ለማረጋገጥም ተችሏል።

መንግስት እስካሁን እያደረጋቸው ያሉው ጥረት ህዝቡ በዋጋ ግሽበት እንዳይጎዳ ለማድረግ የታሰበ መሆኑ ግልጽ ነው። እርግጥ ለዜጎቹ ሃላፊነት የሚሰማው መንግስት የሚያደርገው ይህንኑ ነው። መንግስት ለህዝቡ የገባውን ቃል መቼም አጥፎ ስለማያውቅ ይህንንም በማድረግ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ በተለያዩ ጊዜያት የፈፀማቸው ተግባራት ህያው ምስክር ናቸው። እነዚህ ተግባሮች የስኬቶቻቸን መገለጫዎች ናቸው።

በተለያዩ ወቅቶች መንግስት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ተከታታይ የሆኑ ልማታዊ እርምጃዎችን በመውሰድ የህዝቡን ጥያቄ መልሷል። የዋጋ ግሽበቱ ከፍ ሲል ህብረተሰቡ እንዳይጎዳ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ እንዲሁም መሰረታዊ የሆኑ የፍጆታ ዕቃዎችን ራሱ በማስገባትና በሸማቾች ማህበራት አማካኝነት አከፋፍሏል።

በአሁኑ ወቅትም ከመሰረታዊ ፍጆታዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን የስኳር ፍጆታ ለመሸፈን አንድ ሚሊዩን ኩንታል ስኳር ከውጭ እያስገባ ነው። እነዚህ ተግባሮቹ ሁሉ የሚያሳየን ነገር ቢኖር መንግስት በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚም ይሁን በመሰረታዊ ሸቀጦች ዙሪያ እያከናወናቸው ያሉት ተግባራት ምን ያህል ስኬታማ መሆናቸውን ነው። እነዚህ ስኬቶች ነገም ተጠናክረው የሚቀጥሉ ናቸው።