Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጉዳት አልባው የሕዳሴ ግድብ

0 309

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጉዳት አልባው የሕዳሴ ግድብ

                                                                 ዋኘው  አባይ

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታው ከተጀመረ አመታትን አስቆጥሯል፡፡ ይህ በአፍሪካ የመጀመሪያ፤ በአለም ካሉት ግዙፍ ግድቦች በስድስተኛ ደረጃ መሆኑ፤ ከ6000 ሜጋዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ የሚነገርለት ግዙፍ ግድብ የሀገራችንን የድሕነት ታሪክ በብዙ መልኩ ይቀይረዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ረገድ ጎረቤት ሀገሮችንም ተጠቃሚ የሚያደርግ፤ የኢኮኖሚ ትስስሩንም የሚያሳድግ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት ኢትዮጵያ አቅም አግኝታ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ እንዳትሰራ በዚህም ተጠቃሚ እንዳትሆን በተለይ የግብጽ መንግስት ይህ ቀረው የማይባል ትግል አካሂዶአል፡፡

ግብጾች አለም አቀፍ ገንዘብ አበዳሪ ተቋማት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ  እሰራለሁ ካለች ምንም አይነት የገንዘብ ብድርና ድጋፍ እንዳይሰጡ ያገኙትን መድረክ ሁሉ በመጠቀም ሲያስከለክሉ ኖረዋል፡፡ የዛኑም ያህል የአባይ ውሀ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ድርቅና ረሀብ፣ በአየር ንብረት መዛባት ተጠቂ ሁና ስትኖር፣ ሚሊዮን ዜጎችዋን በሞት ስትነጠቅ፣ ስሟ በድርቅ፣ በረሀብና በችግር ሲነሳ የኖረችበት ዘመን ነበር ረጅም ዘመናትን ያለፈችው፡፡

በአባይ ውሀ እንደልብ ተጠቅመው ሀገራቸውን ያለሙት ግዙፍ እርሻዎችን ከፍተው በማምረት፣ በአለም ገበያ አትክልትና ፍራፍሬ በመሸጥ፣ የሚነግዱት፤ ሰው ሰራሽ ኃይቅ ገንብተው ሰፊ የአሳ እርባታ የሚያካሂዱት፣ እንደገናም በአባይ ውሀ ላይ በገነቡት የአስዋን ግድብ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩት ግብጾች በአባይ ውሀ  ላይ ታሪካዊ መብት አለን የሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደርሰውም ነበር፤ እስካሁንም ይሄንን ከማስተጋባት ወደኋላ አላሉም፡፡

በቅኝ ግዛት ዘመን ውል ለግብጽና ለሱዳን በእንግሊዞች የተሰጠው የውሀ ድርሻ ክፍፍል በቅኝ ግዛት ስር ወድቃ የማታውቀውን ኢትዮጵያን እንደማይመለከታት በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡

የአባይን ወንዝ ተፈጥሮ በጋራ ያደለችን በመሆኑ የኢትዮጵያን የመልማትና የማደግ ፍላጎት በማይነካ መልኩ በጋራ ሁላችንም መጠቀም እንችላለን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድም የሆነው የግብጽ ሕዝብ እንዲጎዳ አይፈልግም፤ በፍቅርና በመተሳሰብ ተፈጥሮ የሰጠችንን ጸጋ የግጭት መነሻ ሳይሆን በሰላም ለልማት ማዋል ይበጃል የሚለውን አቋሟን በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡

ሱዳን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለእኔም የሚጠቅመኝ በመሆኑ ማገዝ ይገባኛል ማለትዋ ግብጾችን አበሳጭቶአል፡፡ ግብጾች የአባይ ወንዝ ውሀ ጉዳይ ለእኛ የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው እንደሚሉት ሁሉ የአባይ ወንዝ ውሀና የግድቡ ግንባታ ለኢትዮጵያም የሕልውና የሞት የሽረትም ጉዳይ ነው፡፡ በጋራ በሰላም በመከባበር ልንጠቀምበት እንችላለን  በሚለው  መስማማቱ ነው  የሚበጀው፡፡

በግብጽ ለረዥም ዘመናት በአፈ ታሪክነት በሕዝቡ አእምሮ ላይ እንዲሰርጽ ተደርጎ ሲሰራበት የኖረው የአባይ ውሀ የእኛ ነው የሚለው ታሪክ ነው ከፍተኛ ችግር የፈጠረው፡፡ የአባይን ውሀ የተቆጣጠረ የአካባቢውን የፖለቲካ የበላይነት ይቆጣጠራል የሚለው ስጋታቸው ነው የመጨናነቃቸው ምክንያት የሆነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል በአባይ ውሀ ወይንም በሕዳሴው ግድብ ምክንያት የትኛውም ሕዝብ እንዲጎዳ አትፈልግም፡፡ በሕዝብ መጎዳት የሚገኝ ጥቅምም አይኖርም፡፡

ኢትዮጵያ የራስዋ የሆነውን የአባይን ውሀ በመጠቀም ሀገርዋን የማልማት የማሳደግ ሕዝቦችዋን ከድሕነት የማውጣት ሙሉ መብት አላት፡፡ ይህንን መበት ለድርድር አታቀርብም፡፡ ደሀ የሆነች ሀገር ይህን ግዙፍና ትልቅ ግድብ ለመስራት የገንዘብ አቅም ከየት ታገኛለች ብለው ተሳልቀውም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የጀመረችው በራስዋ አቅም ያለምንም እርዳታና እገዛ መሆኑ ነበር ታላቅ ድንጋጤ ውስጥ የከተታቸው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በራሱ ገንዘብና አቅም መገንባት የጀመረው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ስራው በከፍተኛ ደረጃ እየተካሄደ ከስድሳ ፐርሰንት በላይ ደርሶአል፡፡ ለአፍታም ሳይቋረጥ በከፍተኛ ደረጃ ቀጥሎአል፡፡ እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን የሚለው ሕዝባዊ ቁርጠኝነት ዛሬም በጋለ ወኔ ወደፊት እንደቀጠለ ይገኛል፡፡

የአባይን ወንዝ ውሀ ከኤሌክትሪክ አመንጪነቱም ባሻገር በብዙ መልኩ  ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡በግድቡ ዙሪያ ሰፋፊ የመስኖ ልማቶችን፤ ሰው ሰራሽ ኃይቆችን በመፍጠር ለአሳ እርባታ ጭምር በማዋል ከፍተኛ ገቢ ያስገኛል፡፡ የአነስተኛ መርከቦችና ጀልባዎች እንዱስትሪ ማስፋፋትም ይቻላል፡፡ ለዜጎች በቁጥር ተገልጾ የማያበቃ የስራ መስኮችን ይከፍታል፡ ሰፊ የስራ እድሎችን የመፍጠር አቅም  አለው፡፡

ለዘመናዊ የመስኖ ልማት፤ ለአሳ እርባታ፣ ለከብት ማድለብ ተዘርዝረው ለማያልቁ አዳዲስ ስራዎች መከፈት የአባይ ግድብ መነሻ ይሆናል፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ሕዝብ በራሱ ሀበትና ገንዘብ የሰራው፤ ከእኛም አልፎ ለአፍሪካውያን ሁሉ መከበሪያ የሆነ ታላቅ ፕሮጀክት ነው፡፡

በእኛ ተምሳሌነት ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ዛሬ ወደራሳቸው መመልከት ጀምረዋል፡፡ ግድብ መገንባት የሀገርን ልማትና እድገት ማፋጠን መሆኑን በይበልጥ የተገነዘቡበት ወቅት ነው፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በተቀመጠለት እቅድ መሰረት ሙሉ በሙሉ እውን የሚሆንበት ግዜ ሩቅ አይደለም፡፡

ግድቡ ከድሕነት መውጪያና መላቀቂያ የአዲስ ዘመን አዲስ ብስራት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ጠቀሜታው ለጎረቤቶቻችንም የጎላ ነው፡፡ ይበልጥ በኢኮኖሚው መስክ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሰላም የምታምን ሀገር ነች፡፡ ለሰላም ያላትም ቁርጠኝነት ለክርክር የሚቀርብ አይደለም፡፡ የአባይ ውሀ በጋራ እንድንጠቀምበት ለሁሉም የተሰጠ የተፈጥሮ ስጦታ በመሆኑ በሰላም አንዱ ሌላውን ሳይጎዳ ልንጠቀምበት እንችላለን ብላ ኢትዮጵያ ታምናለች፡፡

ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ ውሀ በመጠቀም የመልማት መሰረታዊ መብትዋ የተከበረ በመሆኑ ራስዋን ከድሕነት ለማውጣት ሕዝቦችዋን ተጠቃሚ ከማድረግ ያለፈ ሌሎችን በውሀው ምክንያት የመጉዳት ሀሳቡም ፍላጎቱም የላትም፡፡ ሌሎች ተጠቃሚዎች ከውሀው ማግኘት ያለባቸውን ድርሻ የከለከላቸው የለም፡፡ አባይ  የተፈጥሮ ፍሰቱን ጠብቆ ዛሬም ይተማል፡፡ መድረስ  ያለበትን ቦታ እያደረሰ  የተፈጥሮ  ጉዞውን  ይቀጥላል፡፡ የኢትዮጵያም ሀገራዊ ልማት  ይቀጥላል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy