Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፍቺ ካልተቻለ…

0 339

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፍቺ ካልተቻለ…

አባ መላኩ

በመዲናችን የተካሄደው 30ኛው አፍሪካ ህብረት ስብሰባ  ጎን ለጎን  የግብፅ፣ የሱዳንና የኢትዮጵያ መሪዎች ተገናኝተው  በዓባይ  የውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ስኬታማ ውይይት አካሂደዋል።  መሪዎቹ  ከህዳሴ ግድብ አጀንዳ ባሻገር  የአገራቱን ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ  የሚችሉ  በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ዙሪያም ተወያይተዋል።  የአባይ ጉዳይ በውጥረት መፍትሄ እንደማይገኝ የተረዱት ግብጻዊያን የንግግርና የትብብር መንገዱን  የመረጡት ይመስለኛል። የአባይ ቁልቁል እስከፈሰሰ ድረስ ኢትዮጵያና  ግብጽ በየትኛውም መስፈርት ሊራራቁ ወይም ንክኪ ላይኖራቸው አይችሉም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የአባይ ምንጭ ግብጽ ደግሞ የአባይ መዳረሻ ናቸውና።   

ታላቁ መሪያችን አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ   ወቅት  የግብጽንና  የኢትዮጵያን  ግንኙነት ሲገልጹት “ፍቺ የማይፈጸምበት ጋብቻ” በማለት ነበር። በዚያን ወቅት ግብጻዊያን ለዚህ ንግግር ብዙም ቁብ አልሰጡትም ነበር። ለሁሉም ጊዜ አለው እንደሚባለው አሁን ላይ በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደር የሆኑት አቡበክር ሂፍኒ  የታላቁን መሪያችንን  አባባል እንዳለ በመድገም የግብጽንና የኢትዮጵያን ግንኙነት ፍች የሌለው፣ ዘለአለማዊና ታሪካዊ  በማለት ጥንካሬውን ገልጸውታል።

የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ አባይ የአስር  አገራት የጋራ ሃብት ነው። በመሆኑም በአገራቱ መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ካልተቻለ ዘላቂ ሰላም ሊሰፍን አይችልም።   የአባይ ጉዳይ በየትኛውም መስፈርት በፍጥጫና ማስፈራራት ወይም በሃይልና በድለላ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት አይችልም። በተፋሰሱ አገራት መካከል ዘላቄታዊ ሠላም ሊሰፍን የሚችለው የኢትዮጵያ መንግሥት የተከተለው “ፍትሃዊ የውኃ ክፍፍል”  የሚለው  መርህ ሲተገበር  ብቻ ነው።  የዓለም ዓቀፍ ህግ የጋራ ሃብትን ዕኩል የመጠቀም መብትን ይፈቅዳል። ይሁን የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት  አባይን በተመለከተ ዓለም ዓቀፉ  መርህ ይተግበር የሚል አቋም አልተከተሉም።  ይልቁንም ግብጻዊያን ጫናሳይፈጠርባቸው እኛም ተጠቃሚ እንሁን ባይ ናቸው። ከዚህ በላይ ህዝባዊነት፤  ከዚህ በላይ የመልካም ጉርብትና መገለጫ ያለ አይመስለኝም። ኢትዮጵያ በየትኛውም ስርዓት የመልካም ጉርብትና ተምሳሌት ሆና ኖራለች።

 

ግብፅ የአካባቢውን አገራት በኢኮኖሚያዊም ሆነ በማህበራዊ ጉዳዮች ረገድ በተሻለ ደረጃ ላይ ብትሆንም የተፋሰሱን አገራት በጥቅም ሊያስተሳስርና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጥ  የሚችል  አንዲት ፕሮጀክት እንኳን ማበርከት ሳትችል ለዘመናት ኖራለች።  በአንጻሩ ኢትዮጵያ ለሁለት አሥርት ዓመታት መረጋጋት በማግኘቷ ሳቢያ  ተከታታይና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ በመቻሏ የቀጠናውን አገራት በጋራ ሊያስተሳስራቸው፤ የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ  ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ማድረግ ችላለች። ይህ ለእኛ ኢትዮጵያዊያን በተለይ ለእኛ ትውልድ ታላቅ  ኩራት ነው።

አገራችን ለአፍሪካ ቀንድ የሠላምና መረጋጋት ካበረከተችው አስተዋጽኦ ባሻገር የአካባቢው አገሮች በኢኮኖሚ ጥቅም እንዲተሳሰሩ ለማድረግ በርካታ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ትገኛለች። ከእነዚህ  መካከል የታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው።  ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለጅቡቲ፣ ሱዳንና በማቅረብ ላይ ስትሆን ለኬንያም ዝግጅቱ ተጠናቋል።  ከዚህ  በተጨማሪ እጅግ ዘመናዊ የባቡር ትራንስፖርቲቴሽን ከጅቡቲ ጋር ተዘርግቷል። እንዲሁም  ከሁሉም የጎረቤት አገራት ጋር የሚያገናኙ ሰፋፊ አውራ ጎዳናዎች ተገንብተዋል፤ በመገንባት ላይ ናቸው።

 

የኢፌዴሪ መንግስት  ታላቁን  የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሲያስጠና ግብፃዊያን በአባይ ወንዝ ላይ ሙሉ ለሙሉ ጥገኛ መሆናቸውን  ከግምት በማስገባት በተፋሰሱ ላይ ዕኩል የውሃ ተጠቃሚነት የሚል መርህ አላራመዱም።  ይልቁንም  የግብጻዊያንን ጥቅም ጥቅም የማይነካ ፍትኃዊ የውኃ  አጠቃቀም የሚል መርህ አራምደዋል፤ ይህ መርህ  የሁሉንም ህዝቦች  የጋራ ተጠቃሚነት  የሚያረጋግጥ በመሆኑ ነው።  የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ለግብፃዊያን ወንድሞችና እህቶች  እንዳሰቡላቸው ሁሉ የግብጽ መንግስትና ህዝብም ለእኛ ልታስቡልን ይገባል።  ግብጻዊያን ወንድሞቻችን እናንተ ሳትጎዱ በድህነት የኖርነው ኢትዮጵያዊያን  መብራት እናግኝ የሚለውን መርሃችንን  ልታደንቁልን ልታግዙን በተገባ ነበር። ይሁን አሁንም አልረፈደም፤ ቢዘገይም  ዕውነታውን መረዳት መጀመራችሁ መልካም ነው።

 

ግብጻዊያን ፖለቲከኞችና ምሁራን  ለህዝባቸው ለዘመናት  ስለአባይና ኢትዮጵያ ዕውነታውን ሲነግሯቸው አልነበሩም። በመሆኑም አባይን በተመለከተ በግብጻዊያን መካከል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል። ከወንዙ 85 በመቶ በላይ መገኛ የሆነችው አገራችን የግብጻዊያን የህይወት መሰላል ሆና ሳለ  በራሷ  ሃብት ጠላት የገዛችበት ሁኔታ እንደተፈጠረ መረዳት ይቻላል። አገራችን  ለዘመናት ከወንዙ ምንም ድርሻ  እንደሌላት ተደረጋ ተገፍታ  ስትኖር  መብቷን መጠየቅ የምትችልበት  አቅምም ዕድልም አልነበራትም።   ይሁንና  ለሁሉም ጊዜ  አለው እንደሚባለው  ብርሃን በአገራችን  መፈንጠቅ  ጀምሯል። ኢትዮጵያችን ከዘመናት እንቅልፍ ነቅታለች።   

 

የኢትዮጵያ መንግሥት የታላቁን የህዳሴ ግድብ ሲያቅድ በዋነኛነት ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚሰጠውን ጥቅም ታሳቢ ቢደረግም የጎረቤት አገሮችም በተለይ የሃብቱ ቀጥታ ተጋሪ የሆኑት ሱዳንና ግብፅ የሚያገኙትን ጠቀሜታም ከግምት እንዲገባ በማድረግ ነበር።   አባይ  ኢትዮጵያን፣ ሱዳንና ግብንፅ የሚያስተሳስር ይሁን እንጂ  የእነዚህ  አገራት ሥነ ምህዳራዊ አቀማመጥ የተለያየ ነው። ኢትዮጵያ ሸለቆማና ተራራማ የሆነ አቀማመጥ በመታደሏ አገሪቱ ለከፍተኛ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ባለቤት እንደትሆን አድርጓታል እንጂ እንደግብጽና ሱዳን ለመስኖ የሚያገለግል መሬት እምብዛም የላትም። በአንጻሩ ሱዳንና ግብፅ ደግሞ የተሻለ የመስኖ ልማት ሊሰሩበት የሚችሉበት ሰፋፊ የእርሻ ሥፍራዎች የታደሉ ይሁኑ እንጂ እንደኢትዮጵያ በቀላል ወጪ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ባለቤት መሆን አይቻላቸውም። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ታሳቢ በማድረግ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በመተግበር የተፋሰሱ አገራትን በኃይል አቅርቦት ለማስተሳሰር እየሰራ ይገኛል።

 

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ለኃይል ማመንጫነት እንጂ ግብፃዊያን ፖለቲከኞች እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውኃውን ለመቆጣጠር ሆነ ለመስኖ ልማት አይደለም። የኢትዮጵያ መልካዓ ምድር በተለይ አባይ በሚያልፍባቸው በዋነኛነት የሰሜንና የሰሜን ምዕራብ አካባቢዎች ተራራማና ሸለቆማ በመሆናቸው ወንዙ  በኢትዮጵያ ምድር ለመስኖ ልማት የሚሰጠው አገልግሎት እጅግም እንደሆነ ግብፃዊያን ፖለቲከኞች የሚያጡት አይመስለኝም። እንግዲህ የተፋሰሱ አገራት በተለይ የኢትዮጵያና ግብጽ ጋብቻ ሊፈርስ የሚችል አይደለም። የሁለቱ አገራት ግንኙነት ጊዜ የማይሽረው  ማንም ሊበጥሰው የማይቻለው ነው። ይህ በሆነበት ሁኔታ ሁለቱ አገራት ያላቸው አማራጭ መደጋገፍ መተሳሰብ እንጂ ሌላ አማራጭ አይኖርም።  ግብጻዊያን ሊረዱት  የሚገባም አንድ ዕውነታ አለ “ማቆም የማይቻለውን ለማስቆም አለመሞከር፤ መነጠል የማይቻለውን  ለመነጣጠል አለመሞከር  መልካም  ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy