Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፕሮጀክቱ የጋራችን ነው

0 348

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፕሮጀክቱ የጋራችን ነው

                                                    ደስታ ኃይሉ

የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ መሪዎች በአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ወቅት የህዳሴው ግድብን አስመልክቶ ባደረጉት የጎንዮሽ ውይይት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሶስቱ አገራት እንደ “አንድ አገር” ሆነው የሚሰሩት የጋራ ፕሮጀክታቸው መሆኑን ገልፀዋል። ፕሮጀክቶቹ የሚያስተሳስራቸው እንጂ የሚለያያቸው አለመሆኑን አስረድተዋል። ሶስቱ አገራት ከህዳሴው ግድብ ባሻገር የሚያስተሳስሯቸው በርካታ ጉዳዩች መኖራቸውን በመግለፅ ተባብረው ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በእርግጥ ይህ አቋም የሚበረታታ ነው።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በወቅቱ ውይይቱን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በሶስትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ውጤታማ ውይይት አድርገዋል። መሪዎቹ በሶስቱ ሀገሮች መካከል የተፈጠረውን ወንድማማችነት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ እንደሚያስፈልግ መስማማታቸውንም እንዲሁ። ሶስቱ አገሮች እንደ አንድ በመቆም የሚያጋጥሟቸው ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መወሰናቸውንም አስረድተዋል።

በውይይቱ ወቅት እንደተነገረው ሶስቱም ሀገራት የጋራ ጉዳያቸውን እንደ ሌላ የተናጠል ሀገራት ሳይሆን እንደ አንድ ሀገር ይመለከቱታል። በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ድግብን በተመለከተ፤ በግድቡ ዙሪያ ሁሉንም ሀገራት ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ በጋራ መንፈስ ለመስራት ከስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል።

የሀገራቱ የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮችም በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና በግብፅ በኩል የሚነሱ ጉዳዮችን በማጣራት እና ጉዳዮቹን ለመፍታት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጥናት አካሂደው ለመሪዎቹ እንዲያቀርቡም ተስማምተዋል።

የሶስቱ ሀገራት መሪዎች በሰጡት አቅጣጫ መሰረት ጥናቱን የሚያካሂዱት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የአገራቱን ህዝቦች ጥቅም ማእከል ያደረጉ ስራዎችን እንዲያከናውኑም አሳስበዋል። በዓመት እንድ ጊዜም በመሪዎች ደረጃ እየተገናኙ በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ለመነጋገርና አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ሶስቱ መሪዎች መስማማታቸው ተገልጿል።

የጋራ የመሰረተ ልማት ፈንድ ለማቋቋም የተስማሙት ሶስቱ አገራት፤ ፈንዱ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅን የሚያስተሳስር በመሆኑ የህዝብ ለህዝብ እና የመተማመን ስሜትን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል። የፈንዱ በጀትም አገራቱ እኩል የሚጋሩት እንደሚሆንም እንዲሁ።

እርግጥ የሶስቱ አገራት የትብብር መንፈስ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአገራቱ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን የሚያስገነዝብ ይመስለኛል። ግድቡ ለአገራቱ የትብብር እንጂ ያላስፈላጊ እሰጥ አገባ ምክንያት ሊሆን እንደማይችልም የሚያስረዳ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ እንጂ ሌሎች አገራትን የሚጎዳ ፕሮጀክት የመገንባት ፍላጎት የለውም። ሌሎችን የመጉዳት ታሪክም የለውም። የሚከተለው ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲም ይህን እንዲያደርግ አይፈቅድለትም።

ይልቁንም መንግስት እየሰራ ያለው ግድቡ ሀገራችን ኤሌክትሪክ በመሸጥ የቀጣናውን ሀገራት በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረት አንዱ ማሳያ እንዲሆን ነው የሚፈልገው። ከግድቡ ኬንያ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ። ግብፅን ጨምሮ ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራትም ተጠቃሚ መሆናቸው አይቀርም።

ከዚህ ቀጣናዊና የተፋሰሱ ሀገራት ተጠቃሚነትና በኢኮኖሚ የማስተሳሰር ፍላጎቷ በመነሳትም ሀገራችን ለዘመናት ተገድቦ የቆየውን ሀገሪቱ በተፈጥሯዊ ውኃ ሃብቷ የመጠቀም መብቷን አሳልፋ ልትሰጥ አትችልም። እናም የራሷን ፕሮጀክት በራሷ አቅም በመገንባት ላይ ያለች እንዲሁም ከድህነት ለመውጣት ስትል የምትገነባቸውን ማናቸውንም የልማት ግድቦችን ለአፍታም ቢሆን የማታቆም መሆኗን መገንዘብ ይገባል። ብሔራዊ ጥቅሟን ለማንም አሳልፋ የማትሰጥ መሆኑንም ጭምር መረዳት ያስፈልጋል።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን ለድርድር አቅርባ የማታውቅ የጥቁር ህዝቦች መኩሪያ ሀገር ናት። ከባርነት፣ ከጭቆና እና ከቅኝ ተገዢነት ለመላቀቅ ብርቱ ትግል ላደረጉ በርካታ የዓለማችን ህዝቦች አርአያና ምሳሌያቸው እስከ መሆንም ደርሳለች።

ዛሬ የሀገራችን ህዝቦች የራሳቸውና የቀጣናው ሀገራት ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ ረሃብና ጦርነት ማብቃት አለበት ብለው ቆርጠዋል። ‘ዋነኛው ጠላታችን ማነው?’ ብለው ጠይቀው “ድህነት” የሚለውን ትክክለኛ ምላሽም አግኝተዋል።

ጎረቤቶቻቸውን፣ በተለይም የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚ ለማድረግ በእኩልና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ የግንኙነት ፖሊሲን ቀርፀውም እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ‘ድህነትንም እንዴት እናስወግዳለን?’ ብለው መክረው መፍትሔ ካበጁም ቆይተዋል።

በሁሉም መስክ ፈጣን ልማትን ሊያመጡላቸው የሚችሉ አቅጣጫዎችን መከተል ብቸኛ አማራጫቸውን ከማውጣትም ባሻገር፤ በትግበራ ሂደቱ ላይ የጋራ መግባባትን እየፈጠሩ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይህን መግባባታቸውን በጠነከረ መሰረት ላይ ያኖረ ነው ማለት ይቻላል። ፕሮጀክቱ የማንም ሳይሆን የህዝብ ነው።

ግድቡ ለታችኛው የተፋሰሱ አገራት የትብብር ማሳያም ጭምር ነው። ከግድቡ የሚገኘውን ጥቅም በጋራ መቋደስ ያስፈልጋል። በተለይ ግብፆች በፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ የስልጣን ዘመን ወደ ድርድር መምጣታቸው ተገቢ ነው። ከግድቡ በጋራ ለመጠቀም ማሰባቸውም ትክክል ነው።

ያም ሆኖ አሁንም የቅኝ ግዛት ውሎችን መከተል የለባቸውም። ለዘመናት የአፍሪካንና የልጆችዋን ማንነት ሲያዋርድ፣ ልጆችዋን በባርነት ሲሸጥና ሲለውጥ እንዲሁም አንጡራ ሃብቶቿን ሲቦጠቡጥና ለራሱ ጥቅም ሲል መርዛማ ውሎችን ሲከትብ የኖረው የቅኝ አገዛዝ ኢ-ሰብዓዊ አስተሳሰብ በፀያፍነቱ ሳቢያ ዛሬ ላይ ከታሪክነት በዘለለ ሰሚ ጆሮ የለውም።

ይህን ፀረ-ሰውዓዊ እሳቤን ከላያቸው ላይ አሽቀንጥረው ለመጣልም አፍሪካውያን በተናጠልም ይሁን በቅንጅት ታግለዋል፤ ህይወታቸውንም ቤዛ አድርገዋል፤ ታስረዋል፤ ተሰቃይተዋል፤ ቤት ንብረታቸውንም አጥተዋል— “ሰውነታቸውን” ከሰው በታች አውርዶ በመፈጥፈጥ እንዳሻው ሲያደርጋቸው የነበረውን አስከፊ ተግባር ከነ ግሳንግስ አስተሳሰቦቹ ለማስወገድ።

እናም ይህ ዘረኛ ተግባር ዛሬ በአፍሪካ ልሳነ-ምድር እንኳንስ አስተሳሰቡ ገቢራዊ ሊሆን ቀርቶ የሚታሰብ አይደለም። ምንያቱም አርጅቶ የተቀበረው የቅኝ አገዛዝ እሳቤ በያኔው የአህጉሪቱ ድርጅትም ይሁን በአሁኑ ህብረት ውስጥ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ነው።

ግብፆች በአል ሲሲ የስልጣን ዘመን ይህን ተገንዝበው ወደ ሰላማዊ የጠረጴዛ ውይይቶች መምጣታቸው እሰየው ነው። ሆኖም አሁንም የሚታየው ነገር “የቅኝ ግዛት ውሎች ሊከበሩልኝ ይገባል” የሚለው አስተሳሰብ ቀደም ሲል ባነሳኋቸው እውነታዎች ሳቢያ ፈፅሞ ተቀባይነት የላቸውም።

በመሆኑም ዘላቂው መፍትሔ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ላይ ተመልሶ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገኘውን ጥቅም በጋራ መቋደስ ብቻ ይመስለኛል። ይህ ካልሆነ ግብፅ ከትናንት ዛሬ የተሻለ የመነጋገርና የመመካከር አቋም ላይ በመሆኗ ጥሩ ነው ሊባል የሚችል ነው። የህዳሴውን ግድብ የጋራ ሃብታችን ስለሆነ በጋራ እናለማዋለን የሚል አቋም መያዛቸው ትክከል ነው። የግድቡ ጠቀሜታ ለታችኛው የተፋሰስ አገራት ጭምር ስለሆነ እንዲህ ዓይነቱ አቋም ዘላቂ፣ ከልብ በመነጨና በትብብር መንፈስ የሚሰራበት መሆን አለበት።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy