Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለአዋጁ ስኬታማነት…

0 309

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለአዋጁ ስኬታማነት…

                                                        ደስታ ኃይሉ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለማስፈጸም የተቋቋመው ኮማንድ ፓስት ስኬታማ የሚሆነው በህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ሲታጀብ ብቻ መሆኑ ግልፅ ነው። ያለ ህብረተሰበቡ ተሳትፎ በመንግስት ብቻ የሚከናወን ምንም ዓይነት ተግባር የለም። በመሆኑም ህብረተሰቡ በአዋጁ መሰረት ለአካባቢው ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል።    ህብረተሰቡ ሰላሙን ማረጋጋትና ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ የሚችለው በራሱ ጥረት ነው። ስለሆነም ሁከት ፈጣሪዎችን ለህግ አሳልፎ በመስጠት ለአዋጁ ስኬታማነት የተለመደውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርበታል።

ይህ ህዝብ ፅንፈኛ ኃይሎችና የሀገራችንን መለወጥ የማይሹ አንዳንድ ወገኖች አማካኝነት የተከሰተውን ሁከት ለመቋቋም በባለቤትነት ስሜት የከፈለው መስዕዋትነት ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። ወጣቶችን ከጥፋታቸው የመመለስ፣ የተሃድሶ ትምህርት ከወሰዱም በኋላ ወደየቀያቸው ሲመለሱ ምክርና ተግሳፅ በመስጠት እንዲሁም ወጣቶቹ የየአካባቢያቸውን ሰላም በኃላፊነት ስሜት እንዲጠብቁ ማድረጉን መጥቀስ የህዝቡን ሰላም ወዳድነት የሚያጎላ ነው።

የአገራችን ህዝብ ላለፉት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዓመታት የተራመዳቸው ተስፋ ሰጪ መንገዶች እንዲሁም አባጣና ጎርባጣ ውጣ ውረዶች በአሁኑ ወቅት የሚቀራቸው ለውጦች ቢኖሩም፤ ከትናንቱ ዛሬ በተሻለ ቁመና እንደሚገኙ ያውቃል። እርሱንም በተሻለ ማማ ላይ እንደሚያወጡት በልማቱ ውስጥ ተዋናይ የሆነው ማንኛውም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ራሱን ዋቢ በማድረግ መግለፅ የሚችል ነው።

ህብረተሰቡ በመንግስት ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራ በተከናወኑት ልማት ተግባራት ራሱ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ ነው። አገሩም በልማቱ መስክ የአፍሪካ ተምሳሌት ሆናለች። የቀጣናውን ሀገራት በልማት ለማስተሳሰር በምታደርገው ጥረት ተጠቃሽ መሆኗንም ያውቃል። በአረንጓዴ የልማት ፖሊሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመሪነት ሚናዋን እየተጫወተችም እንደሆነ ይገነዘባል።

 

ህዝቡ የወደፊት ዕጣ ፈንታው የሚወሰነው ሀገራችን በምትከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መሆኑን ስለሚያውቅ ሁሌም ሰላም ወዳድ ኃይሎች ጋር የሚቆም ነው። የሰላምን ጠቀሜታ ስለሚገነዘብም ከምንግዜውም በላይ ሁሌም በየአካባቢው ለሰላሙ  ዘብ እንደቆመ ነው።

ህዝቡ በየቀየው ላለው የሰላም ሁኔታ ዋነኛ መሰረት ነው። በዚያ አካባቢ ለሚከሰት ማናቸው የፀረ-ሰላም ድርጊት መልሶ የሚጎዳው እርሱን በመሆኑ ለሰላሙ ይበልጥ መትጋት አለበት። እንዲህ ዓይነቱ ሰላምን የሚያጎሉ፣ ልማትን የሚያፋጥኑና ንትርክን የሚያስቀሩ መንገዶችን መከተል ባይቻል ኖሮ፤ የልማት ዕቅዶችን እውን ማድረግ ባልተቻለና ህዝቡም የተጀመረውን የፀረ ድህነት ዘመቻ አጠናክሮ ባልቀጠለ ነበር።

ከልማት ዕቅዱም በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ተፈላጊውን የዕድገት ራዕይ ሰንቆ ባልተጓዘም ነበር። አሁን እያለመ ላለውና ከመጀመሪያው ዕቅድ ጋር ተመጋጋቢ የሆነውን ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድንም ባላለመ ነበር።

ይህ ሰላም ወዳድ ህዝብ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሰላምን በማወክ ተግባር ላይ የተገኙ ወጣቶችን በመገሰፅ፣ ለሰላም እንዲሰሩና የሰላምን እሴት እንዲያውቁ ማድረግ የቻለ ነው። ይህ ህዝብ ላለፉት 26 ዓመታት ገደማ የተራመዳቸው የልማት አባጣና ጎርባጣ ውጣ ውረዶች ያስታውሳል።

ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ካሉ፣ ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ ልማታዊ መንግስት ካለና በዚሁ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሰላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና ማደግ እንደሚቻል ጠንቅቆ የሚያውቅ ህዝብ ነው። በመሆኑም በአንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ስለሚከሰቱ የሰላም እጦቶች ይህ ህዝብ በቀዳሚነት ሊሰለፍ ይገባል። የባለቤትነት መንፈሱንም ይበልጥ የሚያጠናክርበት ወቅት ላይ መሆኑንም መገንዘብ አለበት።  

የትኛውም ሀገር ሰላም በህዝብ ፍላጎት እንጂ በአዋጅ አይጠበቅም። ስለ ሰላም በሚደረጉ ማናቸውም ክንዋኔዎች ውስጥ የህዝቡ ተሳትፎ ፋና ወጊ ነው። የሀገራችንንና የህዝቦቿን ሰላምና መረጋጋት የማይሹ የውጭ ሃይሎችና የውስጥ ተላላኪዎቻቸው የፈፀሙት ፀረ-ሰላም ድርጊት የት ድረስ እንደ ዘለቀ ከህዝቡ የተሰወረ እውነታ አይደለም። ህዝብ ሁሌም ከማንኛውም ተግባር በፊት ግራና ቀኝ የሚያይ፣ ህጋዊ አካሄዶችን በማጤንና አሉታዊና አዎንታዊ ጎኑን በመገንዘብ ሚዛናዊ ውሳኔ የመስጠት ባህል ያለው ነው።

ባለፈው ጊዜ የተፈጠሩ ሁከቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተፈጠረውን ሁከት በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል። አጥፊ ዜጎች በመጠቆምና ለእርምት ወደ ተሃድሶ ማዕከሎች እንዲገቡ በማድረግ ረገድ የህዝቡ የማይተካ ሚና እዚህ ላይ ሊደነቅ የሚገባው ይመስለኛል። ይህም ማንኛውም አዋጅ ያለ ህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ ተፈፃሚ ሊሆን እንደማይችል የሚያረጋግጥ ነው። ዛሬም በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ህዝቡ ሚናውን መወጣት ይኖርበታል።

በየትኛውም ሀገር ውስጥ እውን እንዲሆን የሚፈለግ ሰላም ያለ ህዝቡ ተሳትፎ ምንም ዓይነት ውጤት ሊያመጣ አይችልም። የሰላም ዋጋን ዋነኛ መዛኙ ኃይል ህዝብ ነው። ህዝብ ጥቅሙን የማያውቀው ሰላም ዕውን ሊሆን አይችልም። እርግጥም ለአንድ ሀገር ልማትና ዕድገት ሰላም ከምንም በላይ የገዘፈ ዋጋ ያለው መሆኑ አያጠያይቅም። የሰላም ዋጋ በምንም አይነት ምድራዊ ዋጋ ሊለካ የሚችል አይመስለኝም።

ሰላም የሚተመንበት አሊያም የሚሰፈርበት ልኬት አለው ሊባል የሚችልም አይመስለኝም። ከግለሰብ የነገ ማንነት ህልም ጀምሮ እስከ የሀገር ህዳሴ ዕውን መሆን ድረስ ሰላም ዋጋው እጅግ የገዘፈ ነው። የአንድ ሀገር ሰላም የህዝቧቿ ሰላም ነው። እናም ዜጎች መብትና ግዴታዎቻቸውን ሲያውቁና ሌላውን ለማስተማር ሲነሳሱ የሀገር ሰላም ይረጋገጣል። ልማትና ዕድገትም ይደረጃሉ፤ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችም በዚያው መጠን እያበቡ ይሄዳሉ። ይህ እንዲሆን ታዲያ ህዝቡ ተገቢውን ሚና መወጣት አለበት። አሁን ለወጣው አዋጅ አጋር በመሆን ሰላሙን መልሶ በእጁ ማስገባት ይኖርበታል።

የአገራችን ህዝብ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ የቀጣናውን ሀገራት ሰላም እያስከበረችና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭነት እንዳላትም ይረዳል። ይህ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ቁመናችን እንዳይሸራረፍም ሰላምን በፅኑ እንደሚሻ እሙን ነው። ይህ አገራችን ሰላም መረጋገጥ መሰረቱ ህዝቡ ነው። በዚህም ሳቢያ ባለፈው ጊዜ የአገራችን ሰላም የተጠናከረ እንዲሆን አድርጓል።

ሰላምን በፅኑ የሚሸው የሀገራችን ህዝብ ደሙን ዋጅቶና አጥንቱን ከስክሶ ያመጣው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መንገድ እንዳይደናቀፍ እንዲሁም የኋሊት እንዳይቀለበስ መፍቀድ የለበትም። በአሁኑ ሰዓት በአገራችን በተከሰተው የፀጥታ ችግር የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቷል። በአዋጁ ተጠቃሚ የሚሆነው የአገራችን ህዝብ ከኮማንድ ፖስቱ ጋር በመተባበር ሰላሙን ወደነበረበት ማስመለስ ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy