Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መለኪያው ምን ይሆን?

0 439

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መለኪያው ምን ይሆን?

ዳዊት ምትኩ

የሰላም ዋጋ መለኪያ የለውም። በተለይም እንደ እኛ በማደግ ላይ ለሚገኝ ማህበረሰብ ትርጉሙ ከፍተኛ ነው። የአንድ ቀን ሰላም መስተጓጎል ሊያስከትልብን የሚችለውን ሁለንተናዊ ጫና እንገነዘባለን። ሰላም አርሶ ለማምረት፣ አምርቶ ለመጠቀም፣ ተጠቅሞም ድህነትን ለመቅረፍ የሚኖረውን የላቀ ሚና እናውቃለን።

ታዲያ ይህን መለኪያ አልባ ሰላም አቅቦ በመያዝ የተረጋጋን ምህዳር መፍጠር ያለበት ህብረተሰቡ ነው። በእጃችን ያለው ሰላም ወድቆ እንዳይሰበር ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

ሰላምን ለማስከበር በሁለም አካባቢዎች የፀጥታ ሃይልን ብቻ በማሰማራት ውጤት ማግኘት አይቻልም። ከዚህ ይልቅ ህብረተሰቡ የየአካባቢውን ሰላም በዋነኛነት መጠበቅ ይኖርበታል። ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን የሚችለውም ይኸው ነው።

ታዲያ ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ በሁሉም አካባቢዎች ተጠያቂነት መንገሱ እንደማይቀርና ችግሮችን በመፍጠርና በማወሳሰብ የተሳተፉ አካላት ሁሉ ተጠያቂ መሆናቸው እንደማይቀር ህብረተሰቡ መገንዘብ ያለበት ይመስለኛል።

ህዝቡ የወደፊት ዕጣ ፈንታው የሚወሰነው ሀገራችን በምትከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መሆኑን ስለሚያውቅ ሁሌም ሰላም ወዳድ ኃይሎች ጋር የሚቆም ነው። የሰላምን ጠቀሜታ ስለሚገነዘብም ከምንግዜውም በላይ ሁሌም በየአካባቢው ለሰላሙ  ዘብ እንደቆመ ነው።

ህዝቡ በየቀየው ላለው የሰላም ሁኔታ ዋነኛ መሰረት ነው። በዚያ አካባቢ ለሚከሰት ማናቸው የፀረ-ሰላም ድርጊት መልሶ የሚጎዳው እርሱን በመሆኑ ለሰላሙ ይበልጥ መትጋት አለበት።

እንዲህ ዓይነቱ ሰላምን የሚያጎሉ፣ ልማትን የሚያፋጥኑና ንትርክን የሚያስቀሩ መንገዶችን መከተል ባይቻል ኖሮ፤ የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን እውን ማድረግና ህዝቡም የተጀመረውን የፀረ ድህነት ዘመቻ አጠናክሮ ባልቀጠለ ነበር።

ከልማት ዕቅዱም በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ተፈላጊውን የዕድገት ራዕይ ሰንቆ ባልተጓዘም ነበር። አሁን እያለመ ላለውና ከመጀመሪያው ዕቅድ ጋር ተመጋጋቢ የሆነውን ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድንም አልሞ ሶስት ዓመታትን ባልተጓዘ ነበር።

የተጀመረውን ዕድገት ለማስቀጠልና በዚያውም ልክ ዴሞክራሲው ሀገር በቀል ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲጎለብት የተደረገው ጥረት፤ እንዳለ ሆኖ ይህ ህዝብ በአንዳንድ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ውስጥ ከመልካም አስተዳድር ጋር እንዲሁም ፅንፈኛ ኃይሎችና የሀገራችንን መለወጥ የማይሹ አንዳንድ ወገኖች አማካኝነት የተከሰተውን ሁከት ለመቋቋም ህዝቡ በባለቤትነት መንፈስ የከፈለው መስዕዋትነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይህ የህዝቡ ስሜት የመነጨው ከምንም ተነስቶ አይደለም። የሰላምን ዋጋ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው።

ሁከቱን ለመቀልበስ በሀገራችን የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ሲባል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአስፈጻሚው አካል ታውጆ ተግባራዊ ሲሆንም ይህ ህዝብ የአንበሳውን ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል።

ይህ ሰላም ወዳድ ህዝብ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሰላምን በማወክ ተግባር ላይ የተገኙ ወጣቶችን በመገሰፅ፣ ለሰላም እንዲሰሩና የሰላምን እሴት እንዲያውቁ ማድረግ የቻለ ነው። ይህ ህዝብ ላለፉት 27 ዓመታት ገደማ የተራመዳቸው የልማት አባጣና ጎርባጣ ውጣ ውረዶች ያስታውሳል።

ለውጦቹ በአሁኑ ወቅት የሚቀራቸው ተጨባጭ ለውጦች ቢኖሩም፤ ከትናንቱ በተሻለ ቁመና እንደሚገኙ ይገነዘባል። እርሱንም በተሻለ ማማ ላይ እንደሚያወጡት በልማቱ ውስጥ ተዋናይ የሆነው ማንኛውም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ራሱን በመግለፅ ጭምር ሊያስረዳ ይችላል።

በሰላም የተገኙትን ውጤቶች ህዝቡ ያውቃል። ባለፉት 27 ዓመታት መንግስትና ህዝቡ የሀገሪቱን ሰላም በአስተማማኝ የሰላም መሰረት ላይ ለማቆም ባረደጉት ጥረት እንዲሁም መንግስት ለቱሪዝምም ሆነ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫን በመከተሉ፤ ሁለቱም ዘርፎች ከፍተኛ የሆነ እመርታ አሳይተዋል።

አገራችን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በማስመዝገቧና የነገ ራዕይዋ ከወዲሁ እየታየ በመሆኑም የተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች መዋዕለ ነዋያቸውን ሀገራችን ውስጥ በማፍሰስ ለልማት አብረውን እየተረባረቡ ነው።

የአገራችን ሰላም በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ ነው። ሰላማችን የተገነባው በህዝቦች ፅኑ ፍላጎት በመሆኑ በቀላሉ ሊናጋ የሚችል አይደለም። ይሁን እንጂ ልክ እንደ ቅርብ ጊዜው ሰላማችን የመሸራረፍ ሁኔታ ሲያጋጥመው የሰላሙ ባለቤቶች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመሆናቸው በቀላሉ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተለያዩ ድንጋጌዎችን በማውጣት መጠገን እየተቻለ ነው።

አገራችን ለወደፊቱ ብሩህ ተስፋ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት አንዷ እየሆነች ነው። ለዚህም በተለያዩ ወቅቶች ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋሞች ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ መሪ አገር እንደምትሆን ሲተነብዩ መጥተዋል። ይህ ትንበያቸው በአገራችን የተፈጠረው ችግር በቀላሉ በመንግስትና በህዝቡ ጥረት ሊስተካከል የሚችልና በመስተካካል ላይ ያለ ጉዳይ እንደሚሆን ስለሚያምኑ ነው።

እርግጥ ሰላም ከሌለ የህግ የበላይነት ብሎ ነገር የለም። መብት አይከበርም። መብት ሰጪና ነሺዎች ጥቂት ጉልበተኞች ይሆናሉ። ጉልበት ያለው የህግ አስፈፃሚ ይሆናል። በሰላም ወጥቶ የመግባት ጉዳይም በህግና በስርዓት ሳይሆን በጉልበተኞች የሚወሰን ይሆናል።

ጉልበተኞቹ ከሚፈልጉት ጊዜና ዕውቅና ውጭ ማንም ሰው መነቃነቅ አይችልም። ህግ የበላይነቱን ስለሚነጠቅም በእነዚህ ሃይሎች እጅ ይወድቅና ሁሉም ነገር ምስቅልቅሉ ይወጣል። ለነገሩ የሰላም እጦት ፈተናን የየትኛውም ሀገር ህዝብ ይገነዘበዋል። ያለ ሰላም አንዳችም ነገር መፈፀም እንደማይቻል የሁሉም ሀገር ህዝብ በሚገባ ያውቃል።

ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ካሉ፣ ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ ልማታዊ መንግስት ካለና በዚሁ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሰላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና ማደግ እንደሚቻል ጠንቅቆ የሚያውቅ ህዝብ ነው። ስለሆነም በአንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ስለሚከሰቱ የሰላም እጦቶች ይህ ህዝብ በቀዳሚነት ተሰልፎ እንደ ትናንቱ ሰላሙን ማረጋገጥ አለበት።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy