Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ማርች 8” እና ሰላም

0 1,173

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ማርች 8” እና ሰላም

                                                      ደስታ ኃይሉ

“ማርች 8” የሴቶች ቀን በመላው አገራችን ሰሞኑን ተከብሯል። አከባበሩን ስናስብ አንዳንድ እውነታዎችን ማንሳት ያስፈልጋል። የአገራችን ሴቶች ትናንትና ዛሬ መብቶቻቸው እንዴት እንደሚከበሩ እንዲሁም ስለ ሰላም አስፈላጊነት ማውሳት ይገባል። እንደሚታወቀው ሁሉ ትናንት ሴቶች ከማጀት ስራዎች ውጭ ይህ ነው የሚባል ስፍራ አልነበራቸው። “ሴትና ድስት ወደ ማጀት” ሲባል ነበር። ዛሬ ግን ሴቶች ራሳቸው ከወንድ እኩል ታግለው ባመጡት ሀገ መንግሥት ይህን ሁኔታ ሽረውታል። መብቶቻቸውን ባልተሸራረፈ ሁኔታ እውን እያደረጉ ነው።

በኢኮኖሚያዊ መስኮች እንዲሁም በመንግስትና በግል ተቋሞች ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል ተወዳዳሪና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ እንዲቻል ልዩ ትኩረት ለመስጠት ነው” በሚል ሴቶች ቀደም ባሉት ጊዜያት በነበሩባቸው የተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ሳቢያ በበታችነትነና በተጨቋኝነት መንፈስ ያሳልፉ የነበረው ሁኔታ በህገ መንግስቱ ፍፁም መሻሩና የቀረ መሆኑ ተመልክቷል።

የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 35 የተሰጣቸውን መብቶችና ትኩረት ተጠቅመው ለራሳቸውና ለአገራቸው በርካታ ውጤቶችን እያስመዘገቡ ናቸው። የእነርሱን የልማት ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም መንግሥት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን እንዲሁም ፕሮግራሞችንና ፓኬጆችን በመቅረጽ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል። ይህን ጉዳይ ከፖለቲካና ከኢኮኒሚ ተጠቃሚነታቸው አንፃር መመልከት ይቻላል።

ያገኘኋቸው መረጃዎች እንደሚገልፁት፤ ከተሳትፎ አኳያ የሴቶች አጀንዳዎች በሁሉም ዘርፎች እንዲካተቱና ተጠያቂነትን በሚያጎሉ መንገድ ክትትል የማድረግ አቅጣጫ ተቀምጦ ገቢራዊ ሆኗል።

በመሆኑም ሴቶች በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በአደረጃጀታቸው የአባላት ብዛትና በአመራር ሰጪነት ብቃት እንዲሁም በፖለቲካው መስክ የሚያደርጉት ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እንዲጠናከሩ የሚያደርጉ ስራዎች ተከናውነዋል። በፌዴራልና በክልል ደረጃ ውሳኔ ሰጪነታቸው ትልቅ እመርታንም ማስመዝገብ ችሏል።

ከኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት አንፃር በመንግስት ከፖሊሲ ጋር የተያያዙ እርምጃዎች በመወሰዳቸው ሴቶች በተለያዩ ሀገራዊ የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊ መሆን ችለዋል። በዚህም አበረታች ሊባል የሚችል ውጤት ተመዝግቧል። በተለይም ሴቶች መሬት፣ ብድርና ቴክኖሎጂ የመሳሰሉ የኢኮኖሚ ሃብቶችን የመጠቀምና የመቆጣጠር መብት እንዲጐናፀፉ ተደርጓል።

በሕገ መንግስቱ ላይ የሰፈረውን የሴቶችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት አግኝተዋል።

በቤት ውስጥ ያለባቸውን የስራ ጫና ለመቀነስም በርካታ ሴቶችን የአማራጭ ኢነርጂና የተለያዩ ተስማሚ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይህም የሴቶችን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብና ያለ ብዙ ድካምና እንግልት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስችሏቸዋል። በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በስልጠና፣ የብድር አገልግሎት በማመቻቸትና የቁጠባ ባህላቸውን የሚያበረታታ እንቅስቃሴም ተከናውኗል።

በህገ መንግስቱ ጥበቃ ያገኙት እንደ ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደርና የመቆጣጠር መብታቸውም የመሬት ተጠቃሚነት የባለቤትነት መብታቸውን አረጋግጧል። ይህም የባለቤትነት ስሜቱን ይበልጥ በማረጋገጥ በተዘረጋው የኤክስቴንሽን አገልግሎት በሥልጠና፣ በቴክኖሎጂ አቅርቦት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

የሴቶችን እኩል የመሬት ተጠቃሚነትን መብት ለማረጋገጥ የክልል መንግስታት የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት በአባወራዎችና በእማወራዎች ስም በጥምር የመመዝገብ እርምጃ ተወስደዋል። በዚህም በርካታ እማወራና አባወራ በጥምረት የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል።

በጥቃቅንና አነስተኛ የልማት ዘርፍ ውስጥም ቢሆን የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ ነው። በዚህም በስልጠና፣ በመስሪያና በመሸጫ ቦታ እንዲሁም በብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል።

በግንባታ፣ በንግድና በከተማ ግብርና በመደራጀትም ተጠቃሚነታቸውን ከፍ አድርገዋል። በከተማ በዝቅተኛና መካከለኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሴቶች የቤት ባለቤት የመሆን፣ ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደርና የመቆጣጠር ሕገ መንግስታዊ መብታቸው ተፈፃሚ መሆን ችሏል።

በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ፕሮግራም የሚሳተፉ ሴት አንቀሳቃሾች ብድር እንዲያገኙና የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠሩ ሲሆን፤ ከጥቃቅን ወደ አነስተኛ፣ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ፣ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሸጋገሩበት አቅጣጫ ተቀምጦም ተግባራዊ እንዲሆን በመደረጉ በመስኩ ያላቸው ተጠቃሚነት ከፍተኛ ሊሆን ችሏል።

በዚህ ረገድ ያገኘኋቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ መንግስት በጥቃቅንና አነስተኛ ልማት መስክ 50 በመቶ የሚሆነውን የሥራ ዕድል ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረገ እንዲሆን በከተማ ልማት ፓኬጅ ግብ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል። በዚህ ግብ መነሻነትም በርካታ ሴቶች ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ሲሆን፤ በመንግስት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ ካለው የስራ ዕድል ግማሽ የሚሆነው በሴቶች እንዲሸፈን ተደርጓል።

ባለፉት 23 ሕገ መንግስታዊ ዓመታት ሴቶች በሀገሪቱ ውስጥ በተፈጠሩ የመሰረተ-ልማት አውታሮችም ተጠቃሚነታቸው እየጎላ መጥቷል። ይህም የሴቶችን ህይወት ይበልጥ ቀላል እንዲሆን አድርጎታል። ሴቶች ረጅም ርቀት ተጉዘው የሚያባክነኑትን ጊዜና ጉልበት በመቀነስ በምርት ተግባር ላይ እንዲያውሉ ማድረግ ተችሏል።  

እንዲሁም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት በማሳየቱ፤ በርካታ የገጠር ከተሞችንና ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ከመቻለሉም በላይ፤ የሴቶችን ተጠቃሚነት የጎላ እንዲሆን አድርጎታል። የአገልግሎቱ መስፋፋት ሴቶችን ወጪ፣ ጊዜና ማገዶ ቆጣቢ በሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲጠቀሙ አስችሏቸዋል።

በማህበራዊ መስክም ሴቶች ተሳትፏቸውና ተጠቃሚነታቸው እየጎለበተ መጥቷል። በተለይ ጎታች የህብረተሰቡን ባህልና አመለካከት በመቀየር፣ የትምህርት ተሳትፏቸውን የሚገድቡ እንቅፋቶችን የማቃለልና የመደገፍ ተግባራት ገቢራዊ ሆነዋል። ባለፉት ስርዓቶች የነበረው የስርዓተ-ፆታ ልዩነትም እየጠበበ መጥቷል።

ሴቶች በገንዘብ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡም፤ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ፣ ስልጠና በመስጠትና ተጨማሪ የትምህርት ጊዜ በማመቻቸት ትምህርታቸውን በውጤታማነት እንዲፈፅሙ እየተደረገ ነው። በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ባገኙት ከፍተኛ ተጠቃሚነትም በጤና የልማት ሰራዊት ምክንያት በበርካታ አካባቢዎች በተከናወኑ አመርቂ ስራዎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ሽፋኑ እጅግ ከፍ አድርጎታል። የእናቶችና ህፃናት ሞትም በእጅጉ ቀንሷል።

የእናቶች ሞት ምጣኔ መቀነስ ትርጉም ያለው ብቻ ሳይሆን በጤናው ዘርፍ ያለውን እመርታ በጉልህ በማሳየት በህይወት የመኖር ዓመት እንዲጨምር አድርጋለች። እነዚህ ጉዳዩች ሴቶች ማርች ስምንትን ሲያከብሩ ማስታወስ ያለባቸው እውነታዎች ናቸው።

የመብቶቹ መጠበቅና ተጠቃሚነታቸው በሰላም ውስጥ የተገኙ መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም። ሰላም ባይኖር ምንም ዓይነት ተጠቃሚነት እንዲሁም “ማርች 8”ትን ማክበር አይቻልም። እናም ሴቶች እናቶች በመሆናቸውና የህብረተሰቡ ግማሽ አካል ስለሆኑ ለሰላም ተግተው መስራት ይኖርባቸዋል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ሰላም ሲደፈርስ ቀዳሚ ተጎጂዎች ሴቶች ናቸው። ሴቶች ለሰላም መከበር ዓይነተኛ ሚና መጫወት ይገባቸዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ መሆን በተለይም ሴቶችንና ሕፃናትን ከስጋት በማላቀቅ ላይ መሆኑ ግልፅ ነው። ስለሆነም በአገራችን ዘላቂ ሰላም ይኖር ዘንድ እናቶች ልጆቻቸውን በመምከርና ከጥፋት ሃይሎች መነጠል ይኖርባቸዋል።

እናቶች የወለዱትን መርቆ ለማሳደግ፣ ለማስተማርና ለቁም ነገር ለማብቃት የሚችሉት አስተማማኝ ሰላም ሲኖር በመሆኑ ልጆችን በማነጽ ረገድ ሚናቸው የላቀ ስለሆነ ይህን አዎንታዊ አስተዋጿቸውን ይበልጥ በመጠቀም ለአገራቸው ሰላም የድርሻቸውን ማበርከት ይኖርባቸዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy