Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ማንም መጣ ማን…

0 726

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ማንም መጣ ማን…

አባ መላኩ

ኢህአዴግን  ስኬታማ ካደረጉት አሰራሮች መካከል ውሳኔዎች  በጋራና በመመካከር ማሳለፍ መቻላቸው እንዲሁም ለድርጅቱ ውሳኔዎች ተፈጻሚነት  ሁሉም አመራርና አባላቱ የሚችሉትን ያህል ርብርብ ማድረግ መቻላቸው ነው። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ  የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በኢህአዴግ እጅ ላይ መሆኗን የድርጅቱ አመራሮችና አባላቱ በመገንዘብ እያንዳንዷን ውሳኔ  ሲያሳልፉም ሆነ ለድርጅቱ ውሳኔ ተግባራዊነት የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ኢህአዴግ ከነችግሩና ከነዕጥረቱም  ቢሆን ኢትዮጵያን በሁሉም ዘርፍ ሊባል በሚችል መልኩ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በስኬት ጎዳና እንድትጓዝ አድርጓል። ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ ህዝቦች የዴሞክራሲ ስርዓትን አስተዋውቋል፣ ፈጣንና ቀጠይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብና የበርካታ ዜጎች  ህይወት እንዲሻሻል ምክንያት ሆኗል።

 

ኢህአዴግ  ጥቂቶችን ለማስደሰት ወይም ለማስከፋት  ብሎ የብዙሃኑን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ፓርቲ አይደለም። ኢህአዴግ የመርህ ፓርቲ እንደሆነ  ይታወቃል። እስከማውቀው ድረስ ኢህአዴግ ቤት የድርጅት አመራርነትም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ የመስዋዕትነት  ቦታ ናት። በዚህ ቦታ የሚቀመጥ አመራር ረመጥ ላይ እንደሚቀመጥ፣ የድርጅቱ ብቻ ሳይሆን የመንግስትንም ጥፋቶች የሚሸከም፤ የፓርቲውም ሆነ የመንግስት ሃጢያት  ተጠቅልለው ለመሪው የሚሰጡበት ቦታ ነች። ይሁንና ዛሬ ላይ በኢህአዴግ አመራሮች መካከል የሚሰማው አለመደማመጥ እንግዳ እየሆነብኝ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢህአዴግ ቤት የስልጣን ሽሚያ  ተጀምሯል። ከላይ እንዳልኩት በኢህአዴግ ቤት ትላልቅ ውሳኔዎች በጋራ የሚተላለፉበት ሆኖ ሳለ የአመራር ቦታዋን ለመያዝ የሚደረግ ሩጫ ለጤና አይመስልም።

 

ለነገሩ  ማንም ይመረጥ ማንም አዲስ ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ማንም ተመረጠ ማን የሚፈጽመውም ሆነ  የሚያስፈጽመውም ከዚህ ቀደም እንደነበሩት አመራሮች የኢህአዴግን አቋምና የኢህአዴግን መርህ ብቻ ነው። ደመቀም መጣ፣ አብይ፣ ሽፈራውም ሆነ ደብረጺዮን እነዚህ ሰዎች ከኢህአዴግ አቋም፣ ከኢህአዴግ ፖሊሲና ስትራቴጂ  አንድ ጋት መንቀሳቀስ አይችሉም። ኢህአዴግ ለአገራችን ስኬቶች ሁሉ የአንበሳውን ድርሻ አበርክቷል፤ በማበርከትም ላይ ይገኛል። ነገም የአገራችን የስኬት ምንጭ እንደሚሆን ጥርጥር ሊገባን አይገባም። የዚህ ፓርቲ ህልውና ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር እጅጉን የተቆራኘ እስከሚሆን ድረስ ኢሀአዴግና የኢትዮጵያ ህዝቦች ተቀራርበዋል። በመሆኑም የዚህ ድርጅት  ድክመት የአገራችን ድክመት እስከመሆን ደርሷል። ስለዚህ ኢህአዴግ በአግባቡ ራሱን ሊያጠራ ራሱን ወደቀድሞው አንድነቱና ጥንካሬው ሊመለስ ይገባል ባይ ነኝ።

 

በአገራችን ታሪክ ኢህአዴግ በመልካም ስነ-ምግሩ በጥሩ ዓረዓያነቱ በቀዳሚነት የሚፈረጅ ፓርት ነው ብል አብዛኛዎቻችንን የሚያስማማ እውነታ ነው፡፡ የድርጅቱ የውስጥ አሰራር የግለሰቦች ሃሳብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚንሸራሸርበት ሃሳብ በነፃነት የሚፋጭበት፤ ሁሌም የብዙሃኑ ድምጽ የበላይነት ተቀባይነት የሚያገኝበት  ፓርቲ ነው፡፡ ይህ አሰራሩም ብዙሃኑን ያማከለ፣ ከአንባገነናዊነት የፀዳና በግልፅነት ላይ የተመሰረተ አሰራርን የሚተገብር በመሆኑ በርካታዎችን ወደፓርቲው አባልነት እንዲሳቡ ያደረገ ነገር ይመስለኛል፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ግምገማ ትልቅና የቆየ ባህል ነው፡፡ ይህ የግምገማ ባህሉ ድርጅቱን ጥሩ የስነ ምግባር ምንጭ እንዲሆን፣ አባላት ተጠያቂነትን እንዲያውቁና የተጣለባቸው ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ካደረጋቸው ምክንያቶች ቀዳሚውና ዋንኛው ጉዳይ ነው፡፡ ግምገማ ከኢህአዴግ ጋር አብሮ የኖረ ባህል በመሆኑ ዕድሜው ከድርጅቱ ዕድሜ ጋር እኩል ነው፡፡ ኢህአዴግ ይህን ጠንካራ ባህሉን ሊያበላሸው አይገባም።   

አንድ ድርጅት ወይም ፓርቲ ታማኝና ጠንካራ ከሚያደርገው ባህሪያት ቀዳሚው አባላቱ ለግል ስብዕናና ጥቅም ከመሯሯጥ ይልቅ ለድርጅቱ ወይም ለፓርቲው ዓላማና መርሆ ተገዥ መሆን መቻላቸው ነው። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  ኢህአዴግ ይህን ዓይነት ጠንካራ ስብዕናው ጥያቄ ውስጥ የገባ ይመስላል። በኢህአዴግ ቤት መደጋገፍና መረዳዳቱ ቀርቶ ሁሉም በራሱ ይተም ጀምሯል። ግለሰቦች አለፍም ሲልም ቡድኖች ለስልጣን የሚያደርጉት ስልታዊ እንቅስቃሴ እየተስተዋሉ ነው።  

“ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን” ሁሉ ኢህአዴግም ህዝባዊ ወገንተኝነቱን በረጅምና መራራ የትጥቅ ትግል ተፈትኖ እዚህ የደረሰ፣ በቁርጠኛ የህዝብ ልጆች የተገነባና ለብዙሃኑ ጥቅም የሚታገል ድርጅት መሆኑን በተግባር አስመስክሯል፡፡ አሁንም የቀድሞው የኢህአዴግ ስብዕና ለአገራችን አንድነት ለህዝቦች አብሮነት ያስፈልጋታል።  ኢህአዴግ በቡድን አሰራር ላይ መሰረት ያደረገ ፓርቲ መሆኑ ከከፋ ስህተት ላይ እንዳይወድቅ ያገዘው ይመስለኛል። ከአንድ ብርቱ ሁለት መዳኒቱ እንደሚባለው።

ኢህአዴግ አገራችን ባለፉት 15 ዓመታት  ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብ ያደረገው ህዝቡን ከጎና ማሰለፍ በመቻሉ ነው። ኢህአዴግ ከትጥቅ ትግሉ ጊዜ ጀምሮ  ህዝብን አሳምኖ መስራትና ማሰራት የሚችል ፓርቲ ነው። በዚህም ኢህአዴግ ስኬታማ ሆኗል። አገራችን እያስመዘገበች ካለችው የኢኮኖሚ ዕድገት ሁሉም በየደረጃው ፍትሃዊ  ተጠቃሚ እንዲሆን ኢህአዴግ ጥረት በማድረግ ላይ ነው። እንዲሁም ኢህአዴግ አገራችንን ከዴሞክራሲያዊ አሰራር ጋር እንድትተዋወቅ አድርጓል። ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በማንነታቸው እንዲኮሩ  ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ አድርጓል፤ በአገራችን ድህነት ከግማሽ በላይ እንዲቀንስ አድርጓል፤ አገራዊ ታመግባባት እንዲፈጠር እና የአገራችን ግጽታ እንዲሻሻል ኢህአዴግ ትልቅ ሚና ነበረው።

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በርግጥ በኢህአዴግ ታሪክ እና ባህርይ በማይጣጣም መልኩ በድርጅቱ ውስጥ  አንዳንድ መደነቃቀፎች እየተስተዋሉ ናቸው። ኢህአዴግም እነዚህን ችግሮች በመፍታት ረገድ ያሳየው ዳተኝነት እና መፋዘዝ በህዝቡ ዘንድ  ስጋት ፈጥሯል። ሥጋቱም ተገቢ ሥጋት ይመስለኛል፡፡ እንኳን ህዝቡ አንዳንድ አመራሮችም ወደ ተስፋ መቁረጥ የተገፉ እስኪመስል ድረስ ራሳቸውን  ከትግሉ ለማራቅ ሞክረው እንደነበር የምናስታውሰው ጉዳይ ነው። ነገር ግን ኢህአዴግ ባለው ራሱን ወደውስጥ የማየት ልምድ ሁኔታዎችን በማስተካከል  ላይ ነው። ይህ የኢህአዴግ መልካም ጅምር አገር ወዳድ ዜጋ ሁሉ ይበል ሊለው የሚገባ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም እያንዳንዷ የኢህአዴግ እንቅስቃሴ ከእያንዳንዳችን ህይወት ጋር የተቆራኘ መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል።

 

ድርጅቱ በተለይም ባለፉት ሁለት ወራት በተለየ ኃይል እና ትኩረት ችግሮቹን መፈተሽ መጀመሩን ስንመለከት፤ ኢህአዴግ ያጋጠሙትን በርካታ ችግሮች በማስወገድ ወደ ትክክለኛው ጎዳና ለመመለስ ቁርጠኛ አቋም እንደያዘ እርግጠኛ መሆን ችለናል፡፡ ኢህአዴግ አሁን የያዘውን የእርማትና የተሃድሶ ንቅናቄ በተለመደው ቁርጠኝነት እና ትጋት መያዝ ይኖርበታል ባይ ነኝ። ኢህአዴግ  በአጭር ጊዜ ራሱን አስተካክሎ አገራችንን በስኬት ጎዳና ዳግም እንደሚያረማምዳት እርግጠኛ ነኝ። ኢህአዴግ ተጽዕኖ ፈጣሪ ድርጅት መሆኑን ከሚያረጋግጡልን ነገሮች መካከል አንዱ ነገር በኢህአዴግ አመራሮች መካከል መደማመጥ እንኳን በመቀነሱ ብቻ አገራችን መደነቃቀፍ ውስጥ ገብታለች።

 

ለአገራችን  ወቅታዊ ችግሮች  ውጫዊ ምክንያቶች የሉም ባይባልም  በርካታ ችግሮቿ ውስጣዊ በመሆናቸው  ኢህአዴግ ቤቱን በማጽዳት ራሱን ማስተካከል  መቻል ይኖርበታል። ኢህአዴግ ውስጣዊ ድክመቱን  ያርም፤ ህዝቡ የሚሳተፍባቸው ቀጥተኛ መድረኮች ያመቻቸ፣ በህዝቡና በመንግስት መካከል ከመቸውም ጊዜ በላይ መቀራረብና ጠንካራ ትስስር መፍጠር የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን፣ አደረጃጀቶችንና አሰራሮችን መዘርጋት ይኖርበታል።  በሌላ በኩል ደግሞ አገሪቱን ለማተራመስ የሚደረግን ማናቸውንም አፍራሽ ድርጊቶች ኢህአዴግ እንደቀላል ነገር ሊመለከታቸው አይገባም። ኢህአዴግ ህግና ስርዓትን የማስከበር፣ የህግ የበላይነትንና ሰላምን የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በየትኛውም መስፈርት ለድርድር ባይቀርባቸው መልካም ነው። ወደ  ኢህአዴግም ሆነ ወደ አገሪቱ አመራርነት ማንም መጣ ማን የተለየ አሰራርና የተለየ ፖሊሲ ይዞ ሊመጣ አይችልም። አዲሱ አመራር እንደቀድሞዎቹ አመራሮች ሁሉ የድርጅቱን ፖሊሲና ስትራቴጂ መፈጸምና ማስፈጸም፤ በአገራችን የተጀመሩ ስኬቶችን ማስቀጠል እንዲሁም በወቅታዊ ግጭት ሳቢያ በህዝቦች መካከል  የተፈጠሩ ክፍተቶችን መድፈን ይሆናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy