ምርጫ ወይስ ሁከት
ኢብሳ ነመራ
ሁከትና ግርግር መፍጠር አብላጫ ቁጥር ያለውን ህዝብ ተሳትፎ አይፈልግም። አንድ ሚሊየን ህዝብ የሚኖርበትን ከተማ አንድ ሺህ ሰዎች ሊያውኩ ይችላሉ። ሁከትና ግርግር ፈጣሪዎች መቼም አብላጫ ሆነው አያውቁም። አብላጫ ቁጥር ያላቸው ደግሞ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሁከትና ግርግር መፍጠር አያስፈልጋቸውም። ሁከትና ግርግር ፈጣሪዎች ጯሂና አውዳሚ ስለሆኑ እጅግ አብላጫ ቁጥር ካላቸው ሰላማዊ ሰዎች የበለጠ በዝተው ይታያሉ። እጅግ አብላጫ ቁጥር ያላቸው ሰላማዊ ሰዎች ሁከትና ግርግርን ስለሚሸሹና በዝምታ ስለሚኖሩ ፊት ለፊት አይታዩም፤ አይሰሙም። ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተጠርቶ የነበረውን አድማና ሁከት መመልከት ለዚህ በቂ አስረጂ ነው።
የአድማውና ሁከቱ መነሻ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ሶስተኛ ድምጽ የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ እንዲሰረዝ ከውጭ ሃገር በማህበራዊ ሚዲያ የተላለፈ ጥሪ ነበር። አድማውና ሁከቱን እዚሁ ሃገር ውስጥ ወይም ኦሮሚያ ውስጥ ከህዝብ የመነጨ ነበር ብሎ መውሰድ አይቻልም። አድማውና ሁከቱ እንዲካሄድ የተደረገው ጥሪ ህዝብ በራሱ ፍቃድ አድማውን እንዲቀላቀል የሚጠይቅም አልነበረም። ህዝቡ፣ የት እንዳሉ የማይታወቁ አድማውን የጠነሰሱ ቡድኖችን ፍላጎት እንዲያስፈጽም የሚያስገድድ መልዕክት ነበር የተላለፈለት። በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨውና ታትሞ በየከተሞቹ የተበተነው የአድማና ሁከት ጥሪ፣ አድማው ላይ ለመሳተፍ ፍቃደኛ ባልሆኑ ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የሚያስጠነቅቅ ነበር።
በዚህ ሁኔታ የአድማና ሁከቱ ቀን ሲደርስ፣ ነጋዴዎች ማን እንደሆኑ በማያውቋቸውና ተጠያቂነት የሌለባቸው በዘፈቀደ እርምጃ ሊወስዱ የሚችሉ ወጣቶች በህይወታቸው፣ በአካላቸውና በቤተሰቦቻቸው ህይወትና አካል ላይ እንዲሁም በንብረታቸው ላይ ሊያደርሱባቸው የሚችሉትን ጉዳት በመፍራት፣ ሁኔታዎች እስኪረጋጉ ሱቃቸውን ከመክፈት ተቆጥበዋል። የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የተሽከርካሪ ባለቤቶችና አሽከርካሪዎች በንብረታቸውና በህይወታቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት አስበው ተሽከርካሪያቸውን ማቆም መርጠዋል። የቀን ስራ ሰርተው በሚያገኟት የእለት ገቢ ጉሮሯቸውን ደፍነው የሚያድሩ ዜጎች ለስራ ከተማ ወጥተው ህይወታቸውን ለአደጋ ከሚያጋልጡ ሁለት ሶስት ቀን መራብን መርጠው ቤታቸው ተከትተዋል። ከተማ መሃል በላስቲክ ዳስ የጀበና ቡና እያፈሉ በመሸጥ የሚተዳደሩ ሴቶች ዳሳቸውን ቢዘረጉ የሚደርስባቸውን አደጋ በመፍራት ቤታቸው መዋልን መርጠዋል። ትራንስፖርት በመቋረጡ ስራ መሄድ ያልቻሉ በተለያየ ስራ ላይ የተሰማሩ ዜጎችና ተማሪዎች ቤታቸው ለመዋል ተገድደዋል። እነዚህ ሁሉ የአድማው ተባባሪዎች አልነበሩም።
ይህን አድማ በየከተማው ሲያስፈጽሙ የነበሩት ራሳቸውን ቄሮ ብለው የሚጠሩ ያልተደራጁና ግልጽ ዓላማና ግብ የሌላቸው፣ ከእውቀትና ከዓላማ ይልቅ በስሜት የሚመሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ናቸው። እነዚህ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ድንጋይ ኮልኩለው መንገድ ዘገተው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን እንቅስቃሴ ገድበዋል፤ ሱቅ ሲከፈት የድንጋይ ኡሩምታ በማዘነብ በርካታ ሺሆች እንዳይገበያዩ ከልክለዋል። አውራ ጎዳና ላይ ጎማ በማቃጠል መቶ ሺሆች የሚኖሩባቸውን ከተሞች በጥቁር ጢስ አፍነው ብዙ የመሰሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ናቸው። እጅግ አብላጫው ሰላማዊ ህዝብ ከጥቂት ጀብደኛ አዋኪዎች ጋር ግብ ግብ ገጥሞ ራሱንና ቤተሰቡን ለአደጋ ማጋለጥ አይፈልግም። ደህንነቱን ግብ ግብ ገጥሞ ሳይሆን ህግ እንዲያስከብርለት ነው የሚጠብቀው።
እንግዲህ የኤርትራ መንግስት የሚመራቸው መረጃ ዶት ኮም፣ ዘ ሃበሻ፣ ዲጄ ኢትዮጵያ ምንትስ ቅብጥርስ የተባሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች እንደ ህዝባዊ አድማ ሲያቀርቡልን የነበረው ከላይ በተገለጸው አስገዳጅ ሁኔታ የተካሄደውን የገበያና የእንቅስቃሴ መገታት ነው። መንግስት፣ ዜጎች በማንኛውም ቡድን የማይፈልጉትን ነገር እንዲፈጽሙ እንዳይገደዱ የመከላከል ግዴታ አለበት። መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር ጥቂት ሁከት ጠንሳሾችና አስፈጻሚዎች አብላጫውን ሰላማዊ ዜጋ አስገድደው ለራሳቸው ቡድናዊ ፍላጎትና ዓላማ ማሳኪያነት መጠቀም የማይችሉ መሆኑን እንዲረዱ ማድረግ ይጠበቅበታል። አለበለዚያ ማንም እየተነሳ ሱቃችሁን ዝጉ፣ ከቤት አትውጡ፣ ይህን ፍጠሩ፣ ያን እድርጉ እያለ የዜጎችን መብቶችና ነጻነቶች የሚጥስበት ስርአተ አልበኝነት የበላይነት ያገኛል።
ይህ ማለት ግን አብዛኛው ህዝብ መንግስት ላይ ቀሬታ የለውም፣ ቅሬታውን በተቃውሞም ይሁን በሌላ ማንኛውም መንገድ የማሰማት መብት የለውም ማለት አይደለም። የኢፌዴሪና የክልል መንግስታት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የህዝቡን በተጨባጭ መሻሻል ያስቻለ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገትና ልማት ማምጣት ቢችሉም የዛኑ ያህል ህዝብን ያማረሩ ችግሮች እንዳሉባቸው እንዲሁም በአግባቡ ያላከናወኗቸው ተግባራት መኖራቸው ይታወቃል።
በከፋ የመልካም አስተዳደር ጉድለት ሳቢያ ህዝብ በመንግስት ተቋማት የመብቱ ተጠቃሚ የሚያደርገውን አገልግሎት ማግኘት የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቆይቷል። አገልግሎት ፍለጋ ወደመንግስት ተቋማት የሚሄዱ ዜጎች መብታቸው የመከበሩና ፍላጎታቸው የመጠበቁ ጉዳይ በህግ ሳይሆን በአሰፈጻሚው ቸርነት የሚወሰን ለመሆን የበቃበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህን የአስፈጻሚ ችሮታ ገንዘብ ሊገዛው ይችላል። ፍርድ ቤቶች በህግ መሰረት ፍትህ የሚሰጡ ሳይሆኑ በጉዳይ አስፈጻሚ ደላሎች አማካኝነት ፍርድ የሚሸጥባቸው ተቋማት ለመሆን የበቁበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በከተሞች መስፋፈትና በኢንቨስትመንት ስም የአርሶ አደሩ መሬት እንደጣቃ እየተለካ ተቸብችቧል። በአማካይ አንድ ሄክታር መሬት ያለው የኢትዮጵያ አርሶ አደር በካሬ ሜትር 2 ብርና 2 ብር ከ50 ሳንቲም ካሳ ተብዬ ገንዘብ ተወርውሮለት የኑሮው መሰረት የሆነውን መሬቱን አጥቶ ለአስከፊ ድህነት እንዲጋለጥ ሲደረግ ቆይቷል። ከዚህ በተጨማሪ ገጠር ባለው የመሬት ጥበት ምክንያት ወደከተማ የሚፈልሱና በከተሞችም በከፍተኛ ደረጃ ጭምር የሰለጠኑ ወጣቶች የስራ እድል በማጣት የዘላቂ ህይወታቸው ተስፋ እንዲጨልም ያደረገ ሁኔታ ተፈጥሯል።
ከዚህ በተጨማሪ፣ በወቅቱ ምላሽ ማግኘት የነበረባቸው ከማንነት ጋር የተያየዙ ጥያቄዎች እንዲሁም የክልሎችን ወሰን ከማካለል ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ከተገቢ ጊዜ በላይ በመወዘፋቸው የግጭት መንስኤ ሆነዋል። እነዚህ ግጭቶች ለበርካታ ዜጎች ህይወት መጥፋትና ከኑሮ መፈናቀል ምክንያት ሆነዋል። በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ግጭትና እስካሁንም መዘዙ ያላበቃውን መፈናቀል ለዚህ ማሳያነት መጥቀስ ይቻላል። በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞንም አስር ሺህ የሚሆኑ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ከኑሯቸው እንዲፈናቀሉ መደረጉም ይታወሳል። እነዚህ ሁኔታዎች ህዝብ በመንግስት እንዲማረር፣ እምነት እንዲያጣ ከማድረግ ባሻገር ለተቃውሞ ምክንያት ሆነዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ተቀስቅሰው የነበሩት የአደባባይ ተቃውሞዎች ከላይ ከተገለጹት ሁኔታዎች አኳያ ሲመዘኑ መቀስቀሳቸው ሳይሆን ሳይቀሰቀሱ ቀርተው ቢሆን ነበር የሚገርመው። ይህ የአደባባይ ተቃውሞ መንግስትን ካንቀላፋበት ቀስቅሶታል። ከዚህ በኋላ መንግስት የህዝቡን ብሶት ለማቃለልና እርካታ ለመፍጠር በልዩ ትኩረት መንቀሳቀስ ጀምሯል። በፌደራልና በክልል መንግስታት እንዲሁም በገዢው ፓርቲ ውስጥ ራስን ፈትሾ የማስተካካል የተሃድሶ እንቅስቃሴ የተጀመረው በዚህ ቀስቃሽ ምክንያት ነው።
ከዚህ በኋላ የመጣው የተሃድሶ አመራር የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት፣ የልማት ጥማት፣ የመሬት ወረራ ያስከተለውን ድህነት፣ የከተሞችን ስራ አጥነት ለማቃለል ተጨባጭ ለውጥ ያመጡ እንቅስቃሴዎችን አድርጓል። እርግጥ አንዳንዶቹ ችግሮች ከቀደሙት ስርአቶች ጀምረው እየተንከባለሉ የመጡ፣ በንጽጽር ሲታዩ መሻሻል ያሳዩ ቢሆንም ስር የሰደዱ በመሆናቸው ከሃገሪቱ እድገትና የብልጽግና ጉዞ ጋር እየተቃለሉ የሚሄዱ በመሆናቸው ጉልህ በሆነ ሁኔታ ተቃለው አልታዩ ሊሆን ይችላል። ሌሎቹ ደግሞ በአዋጅና በመመሪያ ብቻ በቀላሉ የማይቃኑ ከአመለካካት ችግር የመነጩ በመሆናቸው የአመለካከት ለውጥ የሚጠይቀውን ጊዜ ያህል የሚሹ ናቸው። እናም ሙልጭ ብለው አልጠፉም።
በዚህ ላይ በጽሁፉ መግቢያ ላይ የተጠቀሱት ከውጭ ሃገር መንጭተው በማህበራዊ ሚዲያ ተላልፈው የሚፈጸሙ ሁከቶችና አድማዎች መንግስት ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የሚያደረገውን እንቅስቃሴ እያደነቀፉ ይገኛሉ። አድማዎቹና ሁከቶቹ ያለውንም ልማት በማወደም፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን በማስተጓጎል፣ ስጋት በመፍጠር የኢንቨስትመንት ፍሰትን በማደናቀፍ የህዝቡ የልማትና የስራ እድል ጥያቄ ምላሽ እንዳያገኝ እያደረጉ ይገኛሉ። እነዚህ ሁኔታዎች አድማዎቹና ሁከቶቹ የህዝብ ፍላጎት አለመሆናቸውን ያረጋግጣሉ። አድማዎቹ የሚቀሰቀሱት የራሳቸው የፖለቲካ ዓላማ ባላቸው በውጭ ሃገር የሚኖሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ነው። ሃገር ውስጥ የሚፈጸሙት ሁከቶቹና አድማዎቹ በራሳቸውና በወገናቸው ላይ የሚያስከትለውን ቅርብና ዘላቂ ችግር ማገናዘብ ባልቻሉ ጥቂት ስሜታዊ ወጣቶች ነው። መሬት ላይ ያለው እውነታ ይህን ነው የሚነገረን።
መንግስት የህዝቡን ቅሬታ ለማቃለልና ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠት እየተፍጨረጨረ ባለበትና ተስፋ በሚታይበት አሁን ያለ የሃገሪቱ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ህዝብ በመንግስት ላይ ከአፈጻጸም የመነጨ ቅሬታ ሊኖረው፣ ተጨማሪ ምላሽ የሚፈልግ ጥያቄ ሊኖረው ይችላል። እነዚህን ቅሬታዎቹንና ጥያቄዎቹን ለመንግስት የማሳወቅ፣ ማስተካካያና ምላሽ እንዲያገኝም መንግስቱን ወጥሮ የመያዝ ህገመንግስታዊ ምብትና ነጻነት አለው። ይህን የሚያደረገው ግን ራሱን በሚጎዳና ሃገሩን ለጠላት አጋልጦ ለዘለቄታው ስጋት በሚፈጥር ሁከትና አድማ ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ መሆን አለበት። ህዝብ ከቀበሌ እስከ ፌደራል መንግስት በወከላቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በኩል ቅሬታዎቹንና ጥያቄዎቹን ማንሳት ይችላል። የሞያ ስነምግባር አክብረው የሚሰሩና የአንድ ወገን የፖለቲካ ዓላማ አራማጅ ባልሆኑ የህዝብና የግል ሚዲያዎችን በመጠቀም መደመጥ፣ መንግስትን መተቸትና ማስተቸት ይችላል።
መንግስት በእነዚህ ሰላማዊ መነገዶች ሁሉ የሚቀርብለትን ቅሬታና ጥያቄ፣ የሚሰነዘርበትን ትችት አዳምጦ ምላሽ መስጠትና መቃናት አልችል ቢል እንኳን ድንጋይ በመኮልኮል፣ ጎማ በማቃጠል መንገድ ዘገቶ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴን መገደብ አያስፈልግም። ገበያን የማቆም፣ ስራ የማቆም አስገዳጅ አድማ መጥራትና አልተባበር ያሉትን በድንጋይ ናዳ መውገር አያስፈልግም። ይህን የሁሉንም ዜጎች ፍላጎት የማያንጸባርቅ ሰላማዊ ያልሆነ ሁኔታ ለመከላከል የሚወሰደውን ሰላም የማስከበር እርምጃ ለማስተጓጎል ከጸጥታ አስከባሪ ኃይል ጋር መጋጨትና ህይወትን ለአደጋ ማጋለጥ አያስፈልግም።
ህዝብ ወጣቶች ጭምር ለጉዳት አጋላጭ ባልሆነ ሰላማዊና ህገመንግስታዊ በሆነው ምርጫ ምላሽ አልሰጥ፣ አልቃና ካለው መንግስት ላይ ውክልናቸውን አውርደው፣ ሌላ የተሻለ ነው ብለው ያመኑበትን መወከል ይቻላሉ። አልሰማና አልቃና ላለ መንግስት የመጨረሻው መገላገያ ድንጋይ ሳይሆን የምርጫ ካርድ፤ ሁከት ሳይሆን ሰላማዊ ምርጫ ነው። በዚህ የሚገኝ የመንግስት ለውጥ የአብላጫውን የህዝብ ፍላጎት ይወክላል። ሁከትና አድማ ግን የብዙሃንን ፍላጎት አያንጸባርቅም፤ ክፉና ደጉንም መለየት አያስችልም፤ ላደፈጠ የሃገር ጠላት አመቺ አጋጣሚ ይፈጥራል። እናም ሁከትን ሳይሆን ምርጫን እንምረጥ።