Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስለሠላም እንዘምር

0 298

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስለሠላም እንዘምር

                   አባ መላኩ                  

በየመንደሩ ላለው የሠላም ሁኔታ ዋነኛው መሠረት ሕዝቡ ነው። በዚያ አካባቢ ለሚከሰት ማናቸውም የፀረ ሠላም ድርጊት መልሶ የሚጎዳው እርሱን በመሆኑ ለሠላሙ ይበልጥ መትጋት አለበት። እንዲህ ዓይነቱ ሠላምን የሚያጎሉ፣ ልማትን የሚያፋጥኑና ንትርክን የሚያስቀሩ መንገዶችን መከተል ባይቻል ኖሮ፤ የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እውን ማድረግና ሕዝቡም የተጀመረውን የፀረ ድህነት ዘመቻ አጠናክሮ ባልቀጠለ ነበር። ከልማት ዕቅዱም በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ተፈላጊውን የዕድገት ራዕይ ሰንቆ ባልተጓዘም ነበር። አሁን እያለመ ላለውና ለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድንም ባላለመ ነበር።

ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ካሉ፣ ሕዝቡን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ ልማታዊ መንግሥት ካለና በዚሁ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በሕዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚጠበቅ ሠላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና ማደግ ይቻላል። ይህንንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅቆ ያውቃል። ለዚህም ነው በየአካባቢው የሠላሙ በለቤት ሕዝቡ እረሱ ዋስና ጠበቃ ሆኖ እየሰራ የሚገኘው። ይህ አኩሪ ተግባሩም ወደፊት ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል። የሠላም ባለቤትነትን ለመራገገጥ ከእርሱ በላይ ማንም ሊመራው አይችልምና።

ከተግባር የበለጠ ትምህርት ቤት የለም። ይህ ሕዝብ የሠላሙ ዘብ ሆኖ በተጠንቀቅ ቆሟል። ሁከቱን ለመቀልበስ በአገራችን የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ የሕዝቡን ሠላምና ፀጥታ ለማረጋገጥና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ሲባል  ጥረቶች ተደርገዋል ይህ ቢሆንም ግን በአገራችን ላይ ተደቅኖ የነበረው አደጋ እንዲቀለበስ ለማድረግ በተደረገው ርብርብ የሕዝቡ ሚና ተዘርዝሮ አያልቅም።

ይህ ሠላም ወዳድ ሕዝብ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በሁከት ተግባር ላይ የተገኙ ወጣቶችን በመገሰፅ፣ ለሠላም እንዲሰሩና የሠላምን እሴት እንዲያውቁ እንዲሁም በቅርቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ባደረገው ግምገማ ሂደቱን ደረጃ በደረጃ ወደ መደበኛው የህግ ማስከበር ሥርዓት እንዲሸጋገር የሚያስችል መመሪያ እንዲወጣ በማድረግ ረገድ ህዝቡ ያከናወናቸው ግዙፍ ተግባራት መገለጫዎቹ ናቸው።

የየትኛውም አገር ሠላም የሚረጋገጠው በሕዝቦች ቅን አስተሳሰብና መልካምነት ዕንደሆና ፀሀይ የሞቃው ሀቅ ነው።  የአገራችንንና የሕዝቦቿን ሠላምና መረጋጋት የማይሹ የውጭ ኃይሎችና የውስጥ ተላላኪዎቻቸው የፈፀሙት ፀረ ሠላም ድርጊት የት ድረስ እንደዘለቀ ከሕዝቡ የተሰወረ አይደለም። ሕዝብ ሁሌም ከማንኛውም ተግባር በፊት ግራና ቀኝ የሚያይ፣ ህጋዊ አካሄዶችን በማጤንና አሉታዊና አዎንታዊ ጎኑን በመገንዘብ ሚዛናዊ ውሣኔ የመስጠት ባህል ያለው ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የሠላምን ጥቅም ጠንቅቆ የተረዳ ነው በማሆኑም ለሠላሙ ሲል እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏልም እየከፈለም ይገኛል፡፡ ስለ ሠላም በተቀነቀነ ቁጥር ህዝቡ ቀድሞ ከሥፍራው የሚገኘው ያለምክንያት አይደለም። ሰላሙ ተስፋው፣ ኑሮውና ሕይወቱ ስለሆነ ነው በተለያዩ ወቅቶች ሕዝቡ የየአካባቢውን ሠላም በመጠበቅ ረገድ ያሳየው ኃላፊነትን በተገቢው ሁኔታ የመወጣት እንቅስቃሴ ሁሌም ሊጠቀስ የሚገባው ነው። ይህም ተግባር የሠላሙ ባለቤት ሕዝቡ ራሱ ስለመሆኑ መልካም አስረጂ ነው።   

የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች በውጭ ኃይሎችና በአገሪቱ የውስጥ ተላላኪዎቻቸው ቅንጅታዊ ዕኩይ ሴራ ግጭት እንተፈጠረ ይታወቀል በዚያን ወቅት ሁከቱን በቁጥጥር ሥር ማዋል እንዲቻልም በሕገ መንግሥቱ መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ ተግባር ላይ ውሏል። ይህ አዋጅም በወቅቱ የተፈጠረውን ትርምስ በማርገብ ዜጎቻችን የሰላምን አየር እንዲተነፍሱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱ ይታወሳል።  ወቅትን እየጠበቀ ብቅ ብቅ የሚለው ሠላምን የማደፍረስ ተግባር አሁንም በአንዳንድ ቦታዎች ቢታይም በሰላም ወዳዱ ሕዝባችን እየተጨናገፈ ይገኛል፡፡

ለሠላምና መረጋጋት ዋነኛ ተዋናይ ሕዝብ እንደሆነ ሁሉ የአገሩም ባለቤት ሕዝብ ነው፡፡ ሠላምና መረጋጋት ለአገር ዕድገትና ልማት ያለው ድርሻም ከሁሉም የጎላ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደታየው መረጋጋት የማይታይባቸው  የዓለም አገሮች ምን ያህል ለከፋ ቀውስ፣ ትርምስና እልቂት እንደበቁ በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ሁኔታ ያስረዳናል።

የውጭ ኃይሎች  በአንድ አገር ውስጥ ትርምስና ሁከት እንዲፈጠር ሆን ብለው የዚያችን አገር ዜጎችና ተቃዋሚዎችን ከጎናቸው በማሰለፍና በገንዘብ በመግዛት ብጥብጥና ሁከት እንዲፈጠር፣ ሥርዓተ አልበኝነት እንዲሰፍን፣ ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ውጭ እንዲወጣ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ማስተዳደር እንዲሳነው ለማድረግ በብዙ ሚሊዮን ዶላሮችን በመመደብ የማተራመስ ተግባራቸውን ለማከናወን ሞክረዋል፡፡

ፀረ ሰላም ኃይሎቹ አመቺና አዋጪ ነው ብለው የሚያምኑበትን  አመጽና ሁከት እንዲቀሰቀስ የተለያዩ ሥልትና ዘዴዎችን ለመጠቀም ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህንን ዘዴያቸውን በተለያዩ ቦታዎች ተግባር ላይ ለማዋል ሲፍጨረጨሩ ታይተዋል፡፡ ይህ መሰሪ ዓላማቸው የተሳካ ቢመስላቸውም ስውር ሴራቸው በህዝቦች መከታናት  ሊከሽው ችሎወል፡፡

የውጭ ኃይሎቹ የአገር ውስጥ የዲያስፖራ ኃይሎችን በመጠቀም የሚያካሂዱት መፍጨርጨር ለአገሬው ሕዝብ ጥቅምና መብት በመቆርቆር አይደለም፡፡ ይልቁንም የራሳቸውን ሰፊ ጥቅም ለማስከበርና ከዚያች አገር በዘረፋ ማግኘት ይገባናል ብለው ለሚያስቡት የተፈጥሮ ሀብት ምዝበራ መንገድ የሚያመቻቹ  የአገሬውን ሰዎች በመመልመልና በገንዘብ ኃይል በመግዛት ሥምሪት በመስጠት፣ መሣሪያም በማስታጠቅና በማደራጀት  ለጥቅማቸው ታማኝ አገልጋይ ይሆኑናል ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡

ሕዝብ ደግሞ በማንኛውም መስፈርት ሠላሙን አጥቶ ሊኖር አይገባውም። በመሆኑም ለሠላሙ እውን መሆን አጥፊዎችን በማጋለጥ ለህግ እያቀረበ ይገኛል።  ይህም ለሠላሙ ምን ያህል ዘበኛ መሆኑን የሚያሳይ ተግባር ነው። ሕዝቡ የወደፊት ዕጣ ፈንታው የሚወሰነው አገሪቱ በምትከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መሆኑን ስለሚያውቅ ሁሌም ከሠላም ወዳድ ኃይሎች ጋር የሚቆምና የሠላምን ጠቀሜታ ስለሚገነዘብም ከምንጊዜውም በላይ ሁሌም በየአካባቢው ለሠላሙ ዘብ እንደቆመ ነው።

የተጀመረውን ዕድገት ለማስቀጠልና በዚያውም ልክ ዴሞክራሲው እንዲያብብና እንዲጎለብት የተደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ ይህ ሕዝብ በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር እንዲሁም ፅንፈኛ ኃይሎችና የአገራችንን መለወጥ በማይሹ አንዳንድ ወገኖች አማካይነት የተከሰተውን ሁከት ለመቋቋም በባለቤትነት የከፈለው መስዋዕትነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የሕዝቡ ስለ ሠላም ያለው ስሜት የመነጨው ከምንም ተነስቶ አይደለም፤ ይልቁንም የሠላምን እሴት በምንም ሊለካው እንደማይችል ያለፉት ተጨባጭ ሂደቶች ስላስተማሩት እንጂ። ሁሌም ስለሠላም ይዘምራል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy