Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስልጣን እንደ እህል ውሃ ይርባልን?፣ ይጠማልን?

0 258

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስልጣን እንደ እህል ውሃ ይርባልን?፣ ይጠማልን?

                                                       ዘአማን በላይ

አንዳንድ የሀገራችን ተቃዋሚዎች ለስልጣን ያላቸውን ኢ-ዴሞክራሲያዊ እይታ ሳስበው በአያሌው ግርም ይለኛል። ነገረ ስራቸውን በአንክሮ ስታዘበው ተቃዋሚዎቻችን ለአቅመ-ተቃዋሚነት ያልደረሱ አሊያም “ነፍስ ያላወቁ” አማተር ፖለቲከኞች የሆኑ ያህል ይሰማኛል። እነዚህ ተቃዋሚዎች የሀገራችንን የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከማጎልበትና ተደማጭ ያልሆኑ ድምፆችን ከማሰማት አንፃር ያላቸውን አዎንታዊ ሚና ሚዛን ላይ ሳስቀምጠው፣ ለስልጣን ያላቸው የተዛባ አተያይ ፊቴ ላይ እየተመላለሰ የምልከታዬን ሚዛን እነርሱ ወደሚያስቡት ኢ- ዴሞክራሲያዊ ጎዳና እንዲደፋብኝ ያደርገኛል። ነገረ ስራቸው ሁሉ ‘ስልጣን እንደ እህል ውሃ ይርባልን፣ ይጠማልን?’ እንድል አድርጎኛል። ‘ነገሩ እንዲያው ችግር ብሎ የቸረገኝ ጉዳይ ሆኖብኛል’ ብል የሃሳቤን ደርዝ ጥልቀትና የውስጤን ይገልፅልኝ እንደሁ አላውቅም። ብቻ በእኔ ሚዛን አንዳንድ የሀገሬ ተቃዋሚዎች እንዲህ ናቸው።…

የተቃዋሚዎቻችን ችግር በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን የህዝብ እንደሆነ አለመገንዘባቸው ብቻ አይደለም— ከዚያም በዘለለ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በሚከናወን የምርጫ ሂደት ላይ ተመርኩዞ የሚገኝ መሆኑን ለማወቅ አይፈልጉም። አሊያም ላለማወቅ ስስ ጋቢያቸውን ተከናንበው አውቀው ተኝተዋል። ከዚህ ይልቅ በአቋራጭ የስልጣን እርካብ ላይ ለመውጣት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን የሚመኙና የሚያልሙ፣ በለስ ቀንቷቸው ካገኙትም ስልጣንን እንደ ፋሲካ ቅርጫ መከፋፈፈልን እንደ መርህ ለመከተል ያቆበቆቡ ሆነው ይታዩኛል።

ለእነርሱ የሀገራችን ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት ህዝቡ መሆኑ ትርጉም አልባ ዲስኩር ነው። ይልቁንም በአቋራጭ ስልጣንን ለመያዝ የሚደረግ ማናቸውም ሙከራዎች ሰናይና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ናቸው ብለው ያምናሉ። ምናልባትም ይህን በማድረጋቸው የህዝቡን ህገ መንግስታዊ መብት አክብረው የቆሙም ሊመስላቸው ይችላል። እኔ አላውቅም። ብቻ ሁኔታቸው እንዲያ ነው። ታዲያ ይህን የምለው ከመሬት ተነስቼ የአንዳንድ የሀገሬን ተቃዋሚዎች ማነነት ለማጠልሸት አንባቢዎቹ እንዲገነዘቡልኝ እሻለሁ። ምክንያቱም ሁሌም የምፅፈው የማምንበትንና ተገቢ አይደለም ብዬ አቋም የያዝኩበትን ጉዳይ ስለሆነ ነው። እናም የጥቂት የሀገሬን ተቃዋሚዎች ጉዳይ ሳነሳ “ምግባርህን ንገረኝና ማንነትህን ልነገርህ” ከሚለው እምነቴ በመነሳት መሆኑ ፈር ሊያዝልኝ ይገባል።

አንዳንድ በተለይ የዓለማችን ልዕለ ሃያላን ሀገራት ለጉብኝት ወደ ሀገራችን ሲመጡ ጭድ እንዳየ በሬ ጓሮ ጓሮውን በመዞር የስልጣን ጥማታቸውን ሲገልፁ አስተውያለሁ። ከመሰንበቻው ከሃላፊነታቸው የተነሱት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክ ቴሊርሰን ሀገራችንን ለመጎብኘት መጥተው በነበረበት ወቅት ያነሷቸው ጉዳዩች የተቃዋሚዎቻችን ምግባርና ማነነት መገለጫ ነው ብዬ አምናለሁ። አንዳንዶቹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ዓላማ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ለማስገደድ እንደሆነ ሲገልጹ፤ እንደ ሰማያዊ ፓርቲ ዓይነቶቹ ደግሞ ‘እንዴት እኛን ሳያናግሩን ይሄሉ?’ በማለት ‘አቤት!’ ባይ ዶሴኞች ሆነው ሰንብተዋል።

በእኔ እምነት ይህ የተቃዋሚዎቻችን ክራሞት የሚያሳየን ነገር ቢኖር፤ እምነታቸው የስልጣን ሉዓላዊ ባለቤቶች በሆኑት በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሳይሆን በውጭ ሃይሎች መሆኑን ነው። በዚህም በባዕዳን የሚዘወር ዴሞክራሲ ናፋቂዎች መሆናቸውን በገሃድ ነግረውናል። ይህም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ አመራሮች ለአገራቸውና ከህዝባቸው ታማኝ ከመሆን ይልቅ ስልጣን ላይ እስካወጣቸው ድረስ የትኛውንም መንገድ ትክክል ነው ብለው የሚያምኑ መሆናቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል።

ያም ሆነ ይህ ግን እዚህ ሀገር ውስጥ የስልጣን ባለቤት በሆነው በሀገራችን ህዝብ አማካኝነት እንጂ በውጭ ሃይሎች ግፊትና ተፅዕኖ የሚፈጠር ስልጣን ሽግግር አለመኖሩን እንደ ዜጋ በግልፅ መንገር ያለብኝ ይመስለኛል። አዎ! በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን ሰጪውም ይሁን ነሺው ህዝብ ብቻ ነው። ሌላ የትኛውም አካል አደለም። ሊሆንም አይችልም።

የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከአምባገነኖች ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገው  ህገ መንግስት ያቀደቁትና ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ያቆሙት የራሳቸው መብት በራሳቸው ለመወሰን እንጂ የውጭ ሃይሎች ስርዓታቸውን እንዲዘውሩላቸው አይደለም። ፍላጎታቸውን በሃይል እንዲጭኑባቸውም አይደለም። ትናንትም ይሁን ዛሬ የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ቦታ እንዳልነበራቸውና እንደሌላቸው ለተቃዋሚዎቻችን መንገር የሚጠበቅብኝ አይመስለኝም—ነገሩ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” እንዲሉት ዓይነት ነውና።

ኢትዮጵያ ከየትኛውም ሀገር ጋር የምታደርጋቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረ ነው። በሰጪና ተቀባይነት አሊያም በጌታና ሎሌነት የምትፈፅመው ምንም ዓይነት ግንኙነት የለም። ይህን ዕውነታ ደግሞ ማንኛውም ሀገር በሚገባ የሚገነዘበው የዲፕሎማሲ ‘ሀሁ’ ነው።

ጉዳዩን ወደ ኢትዮ-አሜሪካ ግንኙነት ስንመልሰው፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በደርግ ስርዓት ወቅት ከመቋረጡ በስተቀር 115 ዓመታትን ያስቆጠረ ሆኖ እናገኘዋለን። በእነዚህ ዓመታት በጎ ሂደቶችን ይዞ የቀጠለም ነው። በአሁኑ ወቅትም በሀገራቱ መካከል ያለው ግንኙነት በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባ ነው። ይህ ፅኑ ግንኙነትም፤ የየሀገራቱን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ፣ በፖሊሲና በመርህ የሚመራ እንዲሁም በመከባበርና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው።

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር የምታደርገው ግንኙነት በግልፅ ፖሊሲ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህም ከሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም አንፃር የተቃኘና ሰጥቶ የመቀበል መርህን የሚከተል አሰራር ያለው መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ግንኙነቱ ኢትዮጵያን እንደ አንዲት ሉዓላዊት ሀገር የሚያከብርና በውስጥ ጉዳይዋም ጣልቃ የመግባት አካሄድን የሚፈቅድ አይደለም። አሜሪካኖችም የዳበረ ዴሞክራሲ ባለቤቶች በመሆናቸው እንዲህ ዓይነቱን መንገድ ይከተላሉ ተብሎ አይታሰብም። ለነገሩ የኢፌዴሪ መንግስትም ቢሆን የሚከተለው አካሄድ ሀገራችንን ተጠቃሚ የሚያደርግና በማናቸውም የውስጥ ጉዳዮች የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት የሚጋብዝ አይደለም።

ያም ሆኖ ግን ዋሽንግተኖች ሀገራችን በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደትና በልማት ላይ ማተኮርዋን የሚያውቁ፣ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ጂኦ- ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ስለሚገነዘቡ፣ በአካባቢው ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እየተጫወተች ያላችውን እጅግ የላቀ ሚና ስለሚረዱ እንዲሁም በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ ያላትን ተቀባይነት ስለሚያጤኑ ኢትዮጵያን እንደ ቅርብ ወዳጃቸው በማየት አብረውን እየሰሩ ነው። በአሁኑ ወቅትም በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በፀረ-ሽብርተኝነት ትግልና አክራሪነትን በመታገል የቅርብ አጋራችን ሆነው አብረውን በመስራት ላይ ይገኛሉ። በቃ ሃቁ ይኸው ነው።

አንዳንድ የሀገራችን ተቃውሞ ጎራ አቀንቃኞች ግን ሁልጊዜም ቢሆን የአሜሪካ መንግስት ጫና የሚያሳድርበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሀገራችን ውስጥ ያለ ይመስላቸዋል። የሀገራቱ የእኩል ተጠቃሚነት ቁርኝት ምስጢር ስለማይገባቸውም፤ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ አንዳች ተፅዕኖ አሳርፋ፣ በአቋራጭ ስልጣን የመያዝ ረሃብና ጥማታቸውን ለማሳካት የሚያልሙ ናቸው። በዚህም ‘የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለምን እኛን ሳያናግሩን ሄዱ?’ የሚል አሳፋሪ ኩርፊያ ሲያስተጋቡ ይደመጣሉ።

ታዲያ ይህ ‘ለምን ሳያናግሩን ሄዱ?’ አባዜ በአንድ ወቅት የወቅቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ወይዘሮ ሂላሪ ሮድሃም ክሊንተን ሀገራችንን ለመጎብኘት በመጡበት ወቅትም ሳይሸራረፍ ተግባራዊ ሆኖ እንደነበር አስታውሳለሁ። መቼም አሳፋሪ ቢሆንም ጉዳዩን እንዲህ አወጋዋለሁ።…

በወቅቱ የተቃውሞ ጎራው ‘ወይዘሮ ክሊንተን እንዴት ሳያናግሩኝ ይሄዳሉ?’ በሚል ብስጭት በወለደው ዲስኩር እንደለመደው ያልነፋው የብሶት እምቢልታና ያላሰናዳው “የባለ ጉዳይነት” ዶሴ አልነበረም። በተለይ “መድረክ” እየተባለ የሚጠራው የማይተማመኑ ባልንጀሮች ስብስብ (አሁን ተሸራርፎ ስንት እንደሆነ ባላውቅም ያኔ የስድስት ቡድኖች ውህድ እንደነበር ትዝ ይለኛል) እንዲሁም በወቅቱ አንደኛው ክንፉ የነበረው “አንድነት” ፓርቲ አመራሮች በአሜሪካ መንግስት ትዕዛዝ የሚንቀሳቀስ ዴሞክራሲ ሀገራችን ውስጥ እንዲፈጠር በመሻት ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ያልተናገሩት ነገር አልነበረም—የዛሬን አያድርገውና።

እናም የመድረክ አመራሮች “ወይዘሮ ክሊንተን መንግስትን ብቻ ማናገር አልበረባቸውም” በማለት በተለይ ዋነኛ አጋራቸው ለነበረው/ለሆነው የአሜሪካ ድምፅ አማርኛው ክፍል ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የዴሞክራሲ ሂደት አሜሪካ እንድታስተካክልላቸው ሲጠይቁ እንደነበር ዛሬም ከትዝታዬ ማህደር ውስጥ አልተፋቀም። ምን ይህ ብቻ! አሁን ድረስ የሚገርመኝንና አዲስ አበባ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ‘ወይዘሮ ሂላር የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ እንዲያስተካክሉ ይነገርልን’ የሚል ማመልከቻ የያዘ ዶሴ ማስገባታቸውንም አልዘነጋም። መድረኮች የተወሰነ የስብስባቸው አካል ዛሬም ያለ በመሆኑ ከተሳሳትኩ ሊያርሙኝ ይችላሉ። ታዲያ ነገሩ “ታሪክ ራሱን ይደግማል” እንዲሉት ዓይነት ሆኖ ነው መሰል ዛሬም ሰማያዊ ፓርቲን የመሳሰሉ አንዳንድ ተቃዋሚዎች የደገሙት ይህንኑ ነው— ምንም እንኳን እንደ የያኔዎቹ መድረኮች አዲስ አበባ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ‘ዴሞክራሲያችንን አስተካክሉልን’ የሚል ዳጎስ ያለ ማመልከቻ በዶሴ ሸክፈው ማስገባታቸውን ርግጠኛ ባልሆንም።

በእኔ እምነት እንደ ሰማያዊ፣ መኢአድና መሰል የሀገራችን አንዳንድ ፓርቲዎች በሀገራችን ህገ መንግስታዊ ስርዓት ውስጥ በህዝቡ የስልጣን ሉዓላዊነት አምነውና ህጋዊ ሰውነት ይዘው ቢንቀሳቀሱም በተቃራኒው መንገድ እየተጓዙ መሆናቸውን ማወቅ አለባቸው። ይህ ደግሞ ለሀገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጠብ የሚያደርገው አንዳችም ነገር የለም። ከዚህ ይልቅ ፓርቲዎቹ ኢ-ዴሞክራሲያዊ መንገድን እየተከተሉ ስልጣን እንደ እህል ከሚርባቸውና እንደ ውሃ ከሚጠማቸው፤ በሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ውስጥ በንቃት ቢሳተፉ በጄ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የዛሬ ዓመት ገደማ መንግሥት የምርጫ ህጉን እሰከ መቀየር ድረስ ረጅም መንገድ ተጉዞ ከተቃዋሚዎች ጋር ለመነጋገር የዘረጋውን መንገድ ቅድሚያ ለህዝብ ሰጥተውና የስልጣን ባለቤትነቱን አምነው እንዲሁም ለህሊናቸውና ለሀገራቸው ታማኝ በመሆን ጉልህ ሚና ያበረክቱ ይችላሉ። ህዝቡ በሚያውቃቸውን ሀገራዊ ጉዳዩች በማጣመም የተለያዩ “የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ” ሰበብ አስባቦችን እየደረደሩ ለዴሞክራሲያችን የሚበጁ ድርድሮችን ረግጦ በመውጣት አሊያም የውጭ ሞግዚቶችን ‘በእናንተው መጀን!’ እያሉ መለማመን ስልጣንን ለማገኘት መሞከር አንድም ጋት የማያራምድ መሆኑን መገንዘብ የሚኖርባቸው ይመስለኛል። ሀገራችን ሰላሙ ይብዛላት!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy