Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቅርጫን ትቶ ምርጫን

0 472

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቅርጫን ትቶ ምርጫን

ኢብሳ ነመራ

የኢፌዴሪ ህገመንግስት ስራ ላይ በዋለባቸው ያለፉ 23 ዓመታት አምስት ሃገራዊና ክልላዊ እንዲሁም አዲስ አበባና ደሬደዋን ጨምሮ አራት አካባቢያዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል። በእነዚህ ምርጫዎች ላይ በርካታ ሃገራዊና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል። በምርጫዎቹ ላይ የተሳተፉት ፓርቲዎች በአቋም ደረጃ ሲታዩ የብሄሮችን፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን እውን ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ የተዋቀረውን ፌደራላዊ ስርአት ከሚቃወሙ አንስቶ በህገመንግስት ለክልላዊ መንግስቶች የተሰጠው ስልጣን አንሷል እስከሚሉ ይገኙበታል።

ፌደራላዊ ስርአቱን የሚቃወሙት ገሚሶቹ አሃዳዊ ስርአት የመመስረት አቋም የነበራቸው ናቸው። አነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች እያደረ ግን የፌደራላዊ ስርአት ደጋፊ መሆናቸውን አሳውቀዋል። ይሁን እንጂ ፌደራላዊ አወቃቀሩ ብሄር ተኮር ሳይሆን መልከዓምድራዊ መሆን አለበት የሚል አቋም እንዳላቸው አሳውቀዋል። ይህ የፌደራሊዝም አቋማቸውም ቢሆን የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ተግባራዊ እንዳይሆን የሚያደርግ በመሆኑ፣ የሃገሪቱ መሰረታዊ የፖለቲካ ገፊ ሃይል የነበረውን የብሄር ቅራኔ ያላገናዘበ ነው። በመሆኑም በኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ዘንድ ተቀባይነት የለውም። እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በርዕዮተ ዓለም ደረጃ ሊበራል ዴሞክራት ነን ባዮች ናቸው።

ፌደራላዊ ስርአቱን ከሚደግፉት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል ከህገመንግስቱም ይሁን ከህገመንግስቱ አፈጻጸም በመነጨ ለክልሎች የተሰጠው ስልጣን አንሷል ወይም ተገድቧል የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ ይገኙበታል። እነዚህ አብዛኞቹ በሃገሪቱ የነበረው መሰረታዊ የፖለቲካ ገፊ ሃይል የሆነው የብሄር ቅራኔ የወለዳቸው በመሆናቸው አደረጃጀታቸው ብሄርን መሰረት ያደረገ ነው። ሌላው መሰረታዊ የፖለቲካ ገፊ ሃይል የነበረው የመሬት ይዞታ ፖሊሲም ላይ ህገመንግስቱ ላይ የሰፈረውን መሬት የማይሸጥና የማይለወጥ የህዝብና የመንግስት ሃብት ነው የሚለውን ይቀበላሉ። በርዕዮተ ዓለም ደረጃ አብዛኞቹ ሶሻል ዴሞክራቶች እንደሆኑ ይናገራሉ።

ያም ሆነ ይህ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ባለፉት ምርጫዎች ውስጥ ተሳትፈዋል። በተለይ እስከ ሶስተኛው ዙር ምርጫ ድረስ ከሁሉም የአመለካካት ወገን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ ለመጋራት የበቁ ነበሩ። በአራተኛና በአምስተኛ ዙር ምርጫዎች ግን ይህ ሊሆን አልቻለም። በአራተኛው ዙር ምርጫ ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶቹ የምክር ቤቱን መቀመጫ ተቆጣጠረውታል። በአራተኛው ዙር አንድ የግል ተወዳዳሪና ሌላ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ብቻ ምክር ቤቱን ሲቀላቀሉ፣ በአምስተኛው ዙር አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ ወይም የግል እጩ ሳይቀላቀል ቀርቷል።

በእነዚህ ምርጫዎች ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶቹ በህገመንግስቱ መሰረት በቀላል አብላጫ የድምጽ ስርአት ማሸነፋቸው በዙም የሚያራጥር አይደለም። ችግሮች ነበሩ ቢባል እንኳን የተገኘውን ውጤት ሊቀይሩ የሚችሉ አልነበሩም። ያም ሆኖ ኢህአዴግ ከአጋሮቹ ጋር በዚህ መጠን የምክር ቤቱን መቀመጫ መቆጣጠሩ እንደጤናማ የሚወሰድ አይደለም። በአነስተኛ ድምጽ የተሸነፉ በርካታ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመረጡ ዜጎች ድምጽ በመንግስት ውስጥ የመሰማት እድል እንዳይኖራቸው ያደረገ ሁኔታን አስከትሏል። ይህ ሁኔታ ጉዳዮን ለህገወጥ ተቃውሞ ዓላማ ለማዋል ያለወጉ ከሚያራግቡ ቡድኖች እንቅስቃሴ ጋር ተዳምሮ ለህዝብ ቅሬታና የመረረ ተቃውሞ ምክንያት ሆኗል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክር ቤት መቀመጫ መግኘት ያልቻሉት በመንግስትና በኢህአደግ ጫና ስለተደረገባቸው ነው የሚል አስተያየት በብዛት የሚሰማ ቢሆንም፣ በጥልቀት ሲታይ ግን ይህ አስተያየት መሰረተ ቢስ ነው። ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አብላጫ ድምጽ አግኝተው ምክር ቤት መግባት እንዳይችሉ ያደረገው ዋናው ምክንያት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጋር ያለ ውስጣዊ ችግር ነው።

ልብ በሉ፣ በሃገሪቱ እስከ ሰባና ሰማንያ የሚደርሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው ይታወቃል። እነዚህን የፖለቲካ ፓርቲዎች በያዙት ርዕዮተ ዓለም፣ ፖሊሲና አቋም ተመሳሳይነትና ልዩነት ቢቧደኑ ቢበዛ ከሶስት አይበልጡም። ፓርቲዎቹ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ሆኖ ሳለ አምስትና አስር ሆነው መወዳደራቸው የሚያገኙት ድምጽ ተበታትኖ አንዳቸውም አብላጫ ድምጽ ሳያገኙ እንዲቀሩ አድርጓል።

በሌላ በኩል፣ በተለይ በሃገር አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል አይነ ግብ ነን የሚሉት የኢትዮጵያን መሰረታዊ የፖለቲካ ገፊ ሃይል መሰረት አድርገው የተቀረጹ አይደሉም። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰሰቦችና ህዝቦች በፌደራላዊ ስርአት ያገኙትን ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት ላይ የማይደራደሩ ሆኖ ሳለ፣ አይነ ግብ ነን የሚሉት ፓርቲዎች፣ ይህን ፌደራላዊ ስርአት ሃገርን ለመበተን አደጋ የሚያጋልጥ አድርጎ ከመመለከት ባሻገር፣ የጎሳ ፖለቲካ በማለት የሚያንቋሸሹ ናቸው። ይህ አመለካከትና አካሄድ አሃዳዊው ስርአት በወደቀ ማግስት በሃገሪቱ ትላልቅ ከተሞችና በተወሰነ ደረጃ በአማራ ክልል ተቀባይነት ማግኘት የቻለበት ሁኔታ ቢኖርም፣ በተቀሩት የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያ ክልሎች ውስጥ ግን ፍጹም ተቀባይነት ማግኘት አልቻለም። ለወደፊቱም ተቀባይነት አያገኝም። ይህ ሁኔታ በምርጫ ሲወዳደሩ በሰፊ የሃገሪቱ አካባቢዎች በአብላጫ ድምጽ የምክር ቤት መቀመጫ የማግኘት እድል እንዳያገኙ አድርጓቸዋል።

ይህ ብቻ አይደለም። በተለይ በሃገሪቱ የዴሞክራሲ ታሪክ ውስጥ አንጋፋ የሚባሉትና ስመ ጥር ፖለቲከኞችን የያዙት በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በውስጠ ዴሞክራሲ እጦት እንደፓርቲ መቆም ያልቻሉበትን ሁኔታ ታዝበናል። በውስጣቸው ያለውን የአቋምና የአካሄድ ልዩነት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ፣ አንዱ ለሌኛው ወገን እውቅና በመንፈግ የሚወነጃጀሉበትና የሚካሰሱበት ሁኔታ የተለመደ ነው። በመጨረሻም አንዱ ወገን ከስሞ፣ ፓርቲው በግማሽ አካሉ የመፎካካረር አቋሙ ተዳክሞ የሚወጣበት ሁኔታ በተደጋጋሚ አጋጥሟል። ይህ ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የመንግስት ስልጣን ተረክበው ሃገር የማስተዳደር ብቃታቸው ላይ ህዝብ አመኔታ እንዳይኖረው አድርጓል።

እነዚህ ሁኔታዎች ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በተለይ ከሶስተኛው ዙር ምርጫ በኋላ ቀላል የማይባል የህዝብ ድምጽ እንዲያጣ ያደረጉትን ድክመቶቹን አርሞ በብርቱ ከመንቀሳቀሱ ጋር ተዳምረው ተቃዋሚዎች ወደምክር ቤት የመግባታቸው እድል እንዲዘጋ አድርገዋል። ይሁን እንጂ፣ ቀደም ሲል እንደተገለጸው፣ ኢህአዴግ ብቻውን ሙሉ በሙሉ ስልጣን መቆጣጠሩ ጤናማ ተደረጎ ሊወሰድ የሚችል አይደለም።

ያም ሆነ ይህ፤ ተቃዋሚዎች ሃገሪቱን ማሰተዳደር የሚያስችል ስልጣን የማግኘታቸው እድል የሚወሰነው በሚከተሉት ርእዮተ ዓለምና በሚያቀርቧቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፖሊሲ አማራጮች እንዲሁም በድርጅታዊ ጥንካሬ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የምክር ቤት መቀመጫ የሚያገኙበትን እድል ማሰፋት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ይህን መነሻ በማድረግ በምርጫ ህጎችና ሌሎች የፖለቲካ ምህዳሩን ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ሊያሰፉ የሚችሉ አጀንዳዎች ላይ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር ማካሄድ ጀምሯል። በዚህ ድርድር በተለይ የምርጫ ስርአቱ ላይ ህገመንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ የሚያስፈልግበት ጉዳይ ላይ ጭምር ስምምነት ላይ ተደርሷል። ይህም የምርጫ ስርአቱ የአብላጫና የተመጣጣኝ ውክልና ቅይጥ እንዲሆን የተደረሰበት ስምምነት ነው። ይህ የምርጫ ስርአት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አብላጫ ድምጽ ማገኘት እንኳን ባይችሉ፣ ባገኙት አናሳ ድምጽ ልክ የምክር ቤት መቀመጫ ማግኘት የሚችሉበትን እድል ይፈጥራል።

ከዚህ በተጨማሪ መንግስት ሃገራዊ መግባባት በመፍጠር የፖለቲካ ፓርቲዎች በስርአቱ ላይ በመተማመን እንዲንቀሳቀሱና በምርጫ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል። በፍርድ ቤት ቅጣት የተወሰነባቸውንና በክስ ሂደት ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ቅጣታቸው ተነስቶ፣ ክሳቸው ተቋርጦ ነጻ እንዲወጡ መድረጉን ለዚህ አስረጂነት ማንሳት ይቻላል።

ይሁን እንጂ፣ አሁን በሃገሪቱ የተወሰኑ ክልሎች በተለይ ኦሮሚያና አማራ ክልሎች ያለውን ቦግ እልም እያለ የሚያጋጥም ቀውስ መነሻ በማድረግ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሽግግር መንግስት ይመስረት የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ተሰምቷል።  በቅድሚያ ህዝብ ላይ ቅሬታ ያሳደረ የመንግስት ችግር መኖሩና ይህን ችግር መነሻ በማድረግ ህዝብ የተቃውሞ ድምጽ ማሰማቱ እውነት ቢሆንም፣ በሁለቱ ክልሎች እያጋጠሙ ያሉ አውዳሚ ሁከቶችና ህዝብን በማሰፈራራት የሚፈጸሙ አድማዎች በህዝቡ የታቀዱናና የሚመሩ አይደሉም። የታቀዱትም የሚመሩትም ውጭ ሃገር ባሉ ስርአቱን በሃይል ለመናድ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችና ግለሰቦች ነው። ይህ ቀውስ ከዘጠኙ የፌደራል መንግስቱ አካል ክልሎች መሃከል በሁለቱ ብቻ ያጋጠመ በመሆኑ እንደአጠቃላይ የሃገር ቀውስ እንዲወሰድ የሚደርግ ሁኔታም የለም።

እንግዲህ፣ የፌደራል መንግስቱ ፈርሶ የሽግግር መንግስት ይመስረት የሚሉት ቡድኖችና ግለሰቦች የፌደራል መንግስቱን ማስወገድ ላይ ብቻ ነው ያተኮሩት። የፌደራል መንግስቱ የስልጣን መገኛ የሆኑት ክልላዊ መንግስታትና ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመንግስት ለውጥ አጀንዳቸው ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን አቋም ዋጋ አልሰጡትም። የክልል መንግስታትን እንዲሁም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ችላ ብሎ ፌደራል መንግስቱን ብቻ መቀየር እንደማይቻልም ያወቁ አይመስሉም። እርስ በርስ ስልጣን ተቃርጠው ሻንጎ ቢመሰርቱ፣ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ገብተው የሽግግር መንግስት ነን ቢሉ የኢፌዴሪ መንግስትን የመሰረቱት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችና ክልላዊ መንግስታት ለአፍታም አይቀበሏቸውም። ይህ ሁኔታ አቋማቸው በወጉ ያልታሰበበት፣ ግባቸውም ህገመንግስታዊ ስርአቱን በማፍረስ የስሜት ስካር የታጠረ ከንቱ መሆኑን ያመለክታል።

በዚህ ሁኔታ በህዝብ ድምጽ ከየክልሉ በተወከሉ ፓርቲዎች የተዋቀረውን የፌደራል መንግስት አንስቶ የሽግግር መንግስት ለመመስረት የሚደረግ ሙከራ፣ ቢሳካ እንኳን ሃገሪቱን ከመበተን ያለፈ የሚያመጣው ነገር የለም። ሃገሪቱን እንደ ሃገር የምትኖርበትን እድሜ ያሳጥረው እንደሆነ እንጂ የሚያስገኘው ፋይዳ የለም። ህዝብ ቅሬታ እንዲያድርበት ያደረገውን ችግርም፣ ችግሩን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሁከትና አድማ በመቀስቀስ ለተፈጠረው ቀውስም መፍትሄ አይሆንም።

በአጠቃላይ፣ በህዝብ የተወከለው መንግስት ፈርሶ ተሽግግር መንግስት ይመስረት የሚለው  አቋም የህዝብን ፍላጎት ያላገናዘበ፣ ለችግሮችም መፍትሄ የማያመጣ፣ መፍትሄ ከመሆን ይልቅ የሃገሪቱን ህልውናም አደጋ ላይ የሚጥል ተገቢ ያልሆነና ኢህገመንግስታዊ አማራጭ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ይህን ሃሳብ የሚያነሱት በጽሁፉ መጀመሪያ ላይ እንደተጠቀሰው በህዝብ አመኔታ ሊያስገኝ የሚችል ድርጅታዊ ቁመናና ሊመረጥ የሚችል  ፖሊሲ ስለሌላቸው ከውክልና ውጭ በምደባ የሚሰጥ ስልጣን ለማግኘት ነው። ይህ ደግሞ ኢዴሞክራሲያዊ ነው። የህዝብ ፍላጎትም አይደለም።

በመሆኑም፣ የሽግግር መንግስት ይመስረት የሚል በአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች በውጭ ሃገር ያሉ ቡድኖች የሚነሳ አቋም የሚያዘልቅ አይደለም። ፓርቲዎቹ የህዝብ ውክልና ያለውን መንግስት አፍርሰን፣ በሽግግር መንግስት ከህዝብ ውክልና ውጭ ስልጣን የመቃረጥ እድል እናገኛለን የሚለውን ደካማ ሃሳብ ትተው፣ ሁለት ዓመት የቀረው ሃገር አቀፍ ምርጫ መተማመን ባለበት መንፈስ እንዲካሄድ ማደረግ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ አተኩረው ቢሰሩ፣ በድርጅት ቁመናና በአማራጭ ፖሊሲ ተጨባጨነት ራሳቸውን አጠናክረው ብቁ ሆነው ለመገኘት ቢጥሩ ይበልጥ ያዘልቃቸዋል። ምርጫን እንጂ ቅርጫን መተማመን አያዛልቅም።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy