Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በሕዝባዊነት የታነፀው ኃይል

0 407

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በሕዝባዊነት የታነፀው ኃይል

                                                         ታዬ ከበደ

አገራችን የገነባቸው መከላከያ ሠራዊት ህዝባዊ፣ ለህዝብ ጥቅም የሚሰራ እንዲሁም ለህዝብ ሰላም ሲል ለህይወቱ ሳይሳሳ መስዋዕትነት የሚከፍል እንዲሁም የህገ መንግስቱና የህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ጠባቂ ሆኖ ተግባሩን በታማኝነት እየተወጣ ነው። የሠራዊቱ አባላት ከሕዝብ አብራክ የወጡ ናቸው። ሁሌም ለህዝቡ በተለያየ መልክ አገልግሎት ከመስጠት ቸል ብለው አያውቁም። በተለያዩ ወቅቶች ከህብረተሰቡ ጋር በቁርኝት የልማት ስራዎችን ያከናውናሉ።

የአንድ አገር ሰራዊት ለህገ መንግስቱን የሚጠብቅ ከሆነ የዘመናዊ ሰራዊትን ባህሪ ተላብሷል ማለት ነው። የዘመነ ሰራዊት ለሀገሪቱ ሕገ መንግስት ታማኝና ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን በቁርጠኝነት ከማንኛውም አደጋ ለመጠበቅ ኃላፊነት የተሸከመ፣ በዘመናዊ መንገድ የተደራጀ፣ ለህግና ሥርዓት ተገዥ የሆነና ማንኛውንም ተግባራት በሀገሪቱ ሕጐች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች መሰረት በመፈፀም የዕለት ተዕለት የተግባር መመሪያው አድርጎ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡

የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ከዘመናዊ ሠራዊት ባህሪያት አንዱ ለአገሪቱ ሕገ -መንግስት ታማኝ መሆን ነው፡፡ የሠራዊቱ ዋና ተልዕኮ ሕገ- መንግስታዊ ሥርዓቱን ከማንኛውም አደጋ የመጠበቅና የመከላከል ተግባር ነው፡፡ በማንኛውም ሀገር ሕገ- መንግስቱ የህዝቡ የሉዓላዊነት መገለጫ በመሆኑ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም አዋጅ፣ ደንቦችና፣ መመሪያዎች ሕገ- መንግስቱን መሰረት በማድረግ እና እሱን በማይፃረር መንገድ  መውጣት አለባቸው፡፡

ዘመናዊ ሠራዊት ለሕገ- መንግስቱ ታማኝ የሚሆነው የህዝቡ የሉዓላዊ ሥልጣን መገለጫ  እና የሀገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነውን ህገ- መንግሥት ሲያከብርና ሲያስከብር ነው፡፡ ይህንን ኃላፊነት የሚሸከም ኃይል በዋናነት ለሕገ መንግስቱና ለህዝብ ሉዓላዊነት ታማኝና ተገዥ መሆን አለበት፡፡ በሕገ -መንግስቱ የተደነገጉ መርሆችን፣ መብቶችንና ግዴታዎች መቀበልና ሕገ-መንግስቱን መሰረት በማድረግ የሚወጡና የወጡ የሀገሪቱን ህጐች  በማክበርና በማስከበር ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

የአገሪቱ ሕጐች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መነሻቸው ሕገ- መንግስት ስለሆነ የዘመናዊ ሠራዊት ህልውና እና ተልዕኮም ከዚሁ የመነጨ በመሆኑ እነዚህን ሕጐች ተግባራዊ ማድረግ አለበት፡፡ በሕገ – መንግስቱ እንደተደነገገው ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት ባለሥልጣን፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ እንዲሁም የፖለቲካ ድርጅቶች  ሕገ- መንግስቱን የማክበር ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ ሠራዊቱም የአገሪቱ ዜጋ በመሆኑ ሕገ- መንግሥታዊ ሥርዓቱን የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይሁን እንጂ ከማንኛውም ዜጋ ላቅ ያለ ኃላፊነትና ተግባር አለው፡፡ ስለሆነም ሕገ- መንግስቱን እና ሕገ መንግስቱን መነሻ አድርገው የሚወጡ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን የማክበር ግዴታና ኃላፊነት አለበት፡፡

የዘመናዊ ሠራዊት ሌላው ባህሪ ለህግ የበላይነት ተገዥ መሆን ነው፡፡ የህግ የበላይነት ማለት ማንኛውንም ተግባራት ህግን መሰረት በማድረግ እንዲፈጸሙ ማድረግ ሲሆን፣ መከላከያ እንደ ተቋም ተልዕኮውን ለመወጣት የሚያስችሉትን አዋጅ፣ ደንብና  መመሪያዎች በሁሉም የሠራ ዊት አባላትና ሠራተኞች ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ማንኛውም አመራር የሚሰጠው ውሳኔ እና ማንኛውም የሠራዊት አባል የሚያከናውነው ተግባር የሀገሪቱን ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መሰረት በማድረግ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ የዘመናዊ ሠራዊት አንዱ ባህሪ ለህግ የበላይነት ተገዥ የመሆኑና ማንኛውንም ተግባሩን በህግ የሚወሰንና በቁርጠኝነትና በታማኝነት ተግባራዊ የሚያደርግ እንዲሁም ከግለሰቦች ፍላጐት ነፃ የሆነ፣ ሁሉንም የሠራዊት አባል በህግ መሰረት በእኩልነት የሚያይ፣ ከአድልዎና  ከልዩነት የፀዳ ሥርዓት ያለው መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ መከላከያ ሠራዊታችን በሚገባ እየፈፀመው ነው፡፡ ይህም ሠራዊቱን ዘመናዊ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

ዘመናዊ ሠራዊት የህዝቡ ወገንተኛ ነው። ሠራዊታችን በአገሪቱ የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል የመከላከያ መሠረተ- ልማት ዘርፍ የተቋሙን የልማት ስራዎች ከመስራት በዘለለ፤ እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎች ላይ ለህዝቡ ወሣኝ የሆኑ የመንገድ ፣የድልድይ፣የመስኖ ልማት ..ወዘተ ቁልፍ ስራዎችን እያከናወነ ነው፡፡

ከዚህ በተጓዳኝም በብረታ ብረትና ኢንዱስትሪ ኮርፖርሬሽን ውስጥ የሚገኙ የሠራዊቱ አባላት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ኮርፖሬሽኑ የወሰዳቸውን የሜካኒካል ስራዎች ከውጭ እንዳይገቡና ሀገር ውስጥ እንዲመረቱ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ወጪን የማዳን ተግባራትን ገቢራዊ እያደረጉ ነው፡፡

ይህ ብቻ አይደለም። የኮርፕሬሽኑ ሠራዊት አባላት የትራንስፖርት እጥረትን ለመቅረፍ የከተማ አውቶብሶችንና ሌሎች ተሽከርካሪዎችን ሀገር ውስጥ በመገጣጠም እንዲሁም የሀገሪቱ ልማት ወሣኝ የሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳይቆራረጥ ከፍተኛ ሃይል መሸከም የሚችሉ ትሪንስፎርመሮችን በመስራት.. ወዘተ ተግባራትን በማከናወን የልማት አጋርነታቸውን በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ አብነታዊ ሃቆች የሚያመላክቱት ሠራዊታችን በመንግስት የተመደበለትን በጀት አብቃቅቶ ከመጠቀም ባሻገር በአገራዊ ልማት ውስጥ እጁን በማስገባት የውጭ ምንዛሪን በማዳን በኢኮኖሚያዊ እመርታችን ላይ ጉልህ አሻራውን እያሳረፈ መሆኑን ነው፡፡

የሠራዊታችን ልማታዊ ኃይልነት በዚህ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ቀደም ሲል ከተጠቀሱት አብነቶች ባሻገር በየዕዙ፣ በየክፍለጦሩና በየሬጅመንቱ በጉልበቱ፣ በገንዘቡ፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና በሌሎች ዘረፎች የልማት አጋርነቱን በተግባር በማረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡

ሠራዊቱ ለተለያዩ የልማት ስራዎች ከደመወዙ በማዋጣት ከሚያደርገው እገዛ ባሻገር፣ በተሰማራባቸው አካባቢዎች ጊዜውንና ጉልበቱን መስዋዕት በማድረግ የህብረተሰቡን ችግሮች በሚፈቱ ተግባራት ላይ በንቃት እየተሳተፈ ነው፡፡

በሀገሪቱ ውስጥ ተሰማርቶ በሚገኝባቸው የግዳጅ ቀጠናዎች ሁሉ ለአቅም ደካማ አባወራዎችና አማወራዎች ድጋፍ የመስጠት ስራዎችንም አከናውኗል፤ በማከናወን ላይም ይገኛል፡፡ ማሳቸው ላይ ሰብሎችን በመዝራት በማረም በማጨድና በመሰብሰብ ህዝባዊነቱንና የልማት አጋርነቱን እያረጋገጠ ነው፡፡ የአርሶ አደሩ ምርት በፍጥነት ለገበያ እንዲደርስ ለማስቻልም የትራንስፖርት መንገድ በሌላቸው ቦታዎች ከየአካባቢው ህብረተሰብ ጋር እየተቀናጀ በመንገድ ስራ ላይ በንቃት ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በአንድ እጁ ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮውን የሚወጣበት በሌላኛው እጁ ደግሞ ልማትን የሚያከናውንባቸውን ድርብ መሣሪያዎች ይዞ ምንጊዜም ከራሱ በፊት ለህዝብና ለሀገር የቆመው ሠራዊታችን ህዝባዊ ልማታዊነቱ ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም፡፡

ሠራዊቱ ከህብረተሰቡ ጋር አብሮ ስለሚኖርና ችግሩንም ስለሚገነዘብ የሚመደብለትን በጀት በማብቃቃት ከደመወዙ እያዋጣ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ኬላዎችን፣ መንገዶችን ..ወዘተ በመገንባት እንዲሁም የውስጥ ቁሳቁሶቻቸው እንዲሟላ በማድረግ ለየአካባቢው ህዝብ አስረክቧል፡፡

የአካባቢን ስነ ምህዳር በመጠበቅ ረገድም ከህብረተሰቡ ጋር በመሰለፍ ችግኞችን ይተክላል፣ እንዲፀድቁም በመንከባከብ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል፡፡ በተለይም ችግኞች እንዳይጠወልጉ ተገቢውን ክትትል በማከናወን እንደ ዜጋ ልማታዊ ተግባርን ከህዝቡ ጋር ተሳስሮ እየፈፀመ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ መከላከያ ሠራዊታችን ተልዕኮውን በሚወጣባቸው አካባቢዎች በራሱ የውስጥ አቅም፣ ጥረትና ተነሳሽነት ከሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች በተጓዳኝ ምግባረ ሰናይ ተግባራትንም ያከናውናል፡፡ በመሆኑም በተለያዩ የሠራዊቱ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ የሠራዊት አባላት ከደመወዛቸው ተቆራጭ እያደረጉ በኤች-አይ-ቪ/ኤድስ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን እንደ ወላጅ አባት ሆነው ያስተምራሉ፤ ይደግፋሉ፡፡

አገራችን ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱት ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በህዝብ በእንስሳትና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱም ሠራዊታችን ጉልህ አስዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በደረሰባቸው አካባቢዎች ሠራዊታችን በእግረኛ፣ በኮማንዶና በአየርሃይል ቀድሞ በመድረስ የከፋ ጥፋት እንዳይከሰት በማድረግ የህዝቡን ህይወትና ንብረት በመታደግ ህዝባዊነቱንና የልማት ደጋፊነቱን በማያሻማ መልኩ አረጋግጧል፡፡

ከልማቱ በመለስም በተፈጥሮ የአየር ንብረት መዛባት ምክንያት በተከሰቱት የድርቅ አደጋዎች ሠራዊቱ ከደመወዙ ተቆራጭ በማድረግ ወገኑን ከመደገፉ ባሻገር ለተጐጂው የህብረተሰብ ክፍል ዕርዳታው እንዲደርስለት በተሽከርካሪዎቹ በማጓጓዝ ብሎም ዕርዳታው የሚፈለገው ቦታ እንዲደርስ እጀባ በማድረግ አኩሪ ተግባራትን ፈፅሟል፡፡ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመገንባት በስድስት ወር ውስጥ ብቻ አንድ ሚሊዮን በሚጠጋ ብር ቦንድ ገዝተዋል፡፡

ይህም ሠራዊቱ የልማቱ ጠባቂ ብቻ ሳይሆን አልሚም ጭምር መሆኑን ያረጋገጠበት ነው፡፡ በአጠቃላይ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውና ሌሎች የሠራዊታችን ህዝባዊና ልማታዊ ተግባራት ለሠራዊታችን አንቱታን ተቀባይነትንና ከበሬታን ናቸው፡፡ ይህም ሠራዊቱ በተሰማራባቸው ቦታዎች ሁሉ በህዝብ እንዲወደድ እንዲታመንና እንዲፈቀር አድርጎታል፡፡ የሠራዊቱ የልማት ተግባራት በሠላም ወቅት ህዝባዊ የልማት ኃይል መሆኑን ማስመስከር ችሏል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy