Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በችግር ላይ ሆኖ የሚፈለግ ማነው?

0 238

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በችግር ላይ ሆኖ የሚፈለግ ማነው?

                                                           ታዬ ከበደ

የሁለቱ ተቀናቃኝ ልዕለ ሃያላን አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች (የአሜሪካና የሩሲያ) ኢትዮጵያን ለመጎብኘት መምጣታቸው በችግር ወቅት ላይ ሆነን እንኳን ሳይቀር ተፈላጊነታችን መጨመሩን የሚያመላክት ይመስለኛል። ይህም ትናንት በሰላሙ ወቅት ያከናወንነው ጠንካራ የዲፕሎማሲ መስመር ያስገኘለን ትሩፋት ነው።

እርግጥም ለመሆኑ በችግር ላይ ሆኖ፣ ችግሩ ከምንም ሳይቆጠር የሚፈለግ ሀገር ማነው? ብለን ብንጠይቅ ኢትዮጵያ መሆኗ ግልፅ ነው። ሌላን አገር በአስተማማኝነት ማንሳት አንችልም። ሁለቱ ልዕለ ሃያላን አገራት በችግራችን ጊዜ የፈለጉን የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ያጋጠማቸውን ጊዜያዊ ችግር እንደሚፈቱት ስለሚያውቁና ነገ የተለመደው ሰላማዊነታችን እንደሚመለስ ስለሚገነዘቡ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ መንግሥት የሚከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ ብሎም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ተገርጎ የተዘጋጀ ነው።

ይህን በመመርኮዝም ሀገራችን ለኢንቨስትመንት ምቹ እንድትሆን ምጣኔ ሃብታዊ ዲፕሎማሲው በጥናት ላይ ተመርኩዞ እየሰራ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ አንድ ሀገር ለኢንቨስትመንት አመቺ ናት ለማለት በርካታ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ይገባሉ። ከእነዚህም ውስጥ ሰላምና የተረጋጋ ፖለቲካ፣ የተረጋጋና እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚ፣ የዳበረ የመሰረተ ልማት አውታር፣ ሰፊ የገበያ ዕድል፣ በቂ የሰለጠነና ውጤታማ የሆነ ሰው ኃይል እንዲሁም ኢንቨስትመንትን የሚያሳካ ፖሊሲና ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት ሊኖር ይገባል። በዚህ ረገድ ሀገራችን ምቹ ናት።

ዳሩ ግን እነዚህ ሁኔታዎች መኖራቸው ብቻ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ዋስትና ሊሆኑ የሚችሉ አይመስለኝም። የቱንም ያህል ጥሩ የኢንቨስትመንት አዋጅ ቢኖርም ሀገሪቷ ለኢንቨስትመንት ያሏትን ምቹ ሁኔታዎች በውጭው ዓለም የሚያስተዋውቃቸው አካል ከሌለ ውጤታማ የሚሆኑ አይመስለኝም።

ርግጥ በአንድ ሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን እውን እንዲሆን ሰላም ወሳኝ ጉዳይ ነው። የሰላም ዲፕሎማሲያችንም መሳ ለመሳ መጓዝ አለበት። ቀደም ሲል እንዳልኩት በሀገር ውስጥ ያለው ሰላም አስተማማኝ መሆን ይኖርበታል።

ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲው ያስገኘው ውጤት ባለፉት ሁለት ዓመት ገደማ ሀገራችን ውስጥ አልፎ አልፎ ብቅ ጥልም የሚሉ ግጭቶች በተስተዋሉበት ወቅት ነው። ይህ ሁኔታ ባይፈጠር ደግሞ ምን ያህል ውጤት ሊመዘገብ እንደሚችል ለማወቅ ነቢይ መሆንን አይጠይቅም። ያም ሆኖ ክንዋኔው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነንም ቢሆን ዓለም የመሰከረለት ውጤት ማምጣት ችለናል።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት መርህ የአገሪቱን ገፅታ ከመለወጡ ባሻገር፤ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረኮችም ተሰሚነቷንና ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን ከፍ እንዲል አድርጓል። ሀገራችን እያካሄደች ያለው ዲፕሎማሲ ስኬት አንዱ ማሳያ እየተመዘገበ ያለው ፈጣንና ተከታታይ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ነው።

ይህ ፈጣንና ተከታታይ ልማትን በመደገፍ ረገድ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ጉልህ ሚና በመጫወቱ በችግር ጊዜ ሳይቀር ለውጥ አምጪነታችን ተረጋግጧል። ይህ ሁኔታ ሁለቱ ልዕለ ሃያላን አገራት በሚገባ ያውቃሉ። ተመልሰን ወደ ነበርንበት የኢኮኖሚ ግስጋሴ እንደምንገባ፣ ተፅዕኖአችን ቀላል አለመሆኑን ስለሚገነዘቡ በችግራችን ጊዜ ውስጥ እንኳን ሳይቀር ይፈልጉናል።

ልዕለ ሃያላኑ አገራት ተፅዕኖ ፈጣሪነታችንንም ተገንዝበዋል። ዛሬ የኢትዮጵያ የአደራዳሪነት ሚና እየጨመረ ሄዷል። ይህ የዲፕሎማሲ ድል በንጉሱ ዘመነ መንግስት ወቅት የነበረ ቢሆንም፤ ተቋማዊና በሰለጠነ መንገድ እየተመራ ይበልጥ ተቀባይነታችን እየጎላና እየደመቀ የመጣው በኢፌዴሪ መንግስት ነው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ድምፅ መሆን የጀመረችው በኢፌዴሪ መንግስት ነው።

ኢትዮጵያ አፍሪካን ብሎም ዓለምን በሚያስጨንቀው የሙቀት መጠን መጨመር የአፍሪካዊያን ልሳን ሆና ብቅ ያለችው በዚሁ መንግስት ነው። የመፍትሔው አካል ሆናም በቅድሚያ በራሷ የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫን በአርአያነት ያሳየችውም በኢፌዴሪ መንግስት ነው። ይህ ሁሉ ተግባሯም በየጊዜው ተቀባይነቷ እንዲጎለብት አድርጓል።

በእኔ እምነት የኢፌዴሪ መንግስት በአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ይሁን በአፍሪካ ህብረት ያበረከታቸው አስተዋፅኦዎች በአሁኑ ወቅት ለተጎናፀፈው የዲፕሎማሲ ድል መሰረት ናቸው።

የኢትዮጵያ መንግስት በየትኛውም ሀገር ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ያደረገው ጥረት የሚመነጨው ሌሎች ሃይሎች በተሳሳተ መንገድ እንደሚተረጉሙት ሳይሆን፤ የጐረቤቶቻችን ሰላም ለሀገራችን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን መፋጠን ካለው ፋይዳ አኳያ እንደሆነ ሊጤን ይገባል። ምክንያቱም እኛ ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለመዋጋት የምናደርገው ትግል ሊሳካ የሚችለው ጐረቤቶቻችን ሰላም ሲሆኑ በመሆኑ ነው።

ርግጥም እንኳንስ የድንበር አዋሳኞቻችን ቀርቶ የሩቅ ሀገራት ሰላም መሆንም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለእኛ ሰላም መጐልበት ያለው ሚና የላቀ መሆኑ እሙን ነው። ይህም በአፍሪካ ደረጃ በጋራ ሰላም እጅ ለእጅ ለማደግና በዚህም አፍሪካዊ ህዳሴን ማጎልበቱ አይቀሬ ነው።

በተለይ አዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ነፃ ከወጣች ጉዜ ጀምሮም በውስጧ የተፈጠረውን የእርስ በርስ ግጭት የኢፌዴሪ መንግስት ከኢጋድ ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው። በዚህም ውጤቶች ተገኝተዋል።

የመንግስታችን ከጐረቤት ሃገሮች ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት የመፍጠር ጥረት በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሀገሪቱ ለጀመረችው የፈጣን ልማት ቀጣይነት መረጋገጥ ብቸኛው አማራጭ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ውስጥ የአንድ አገር ህዝብ መጎዳት ዞሮ…ዞሮ ለሀገራችን የሚኖረው ዳፋ የሚታወቅ በመሆኑ ህዝቦች ሀገራቸው ውስጥ በሰላም እየኖሩ ለቀጣናው ልማት እመርታ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ያግዛል። በሂደትም ክፍለ አህጉራዊው የኢኮኖሚው ትስስር ይበልጥ እንዲዳብር ያደርጋል።

ይህም ሀገራችን የምትከተለውና የቀጣናው ሃገራት በምጣኔ ሃብት ተሳስረው ሁሉም ከሚገኘው እድገት ተቋዳሽ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው። እያንዳንዱ አገር የተፈጥሮ ሃብተቱን በአግባቡ ካለማና በፍትሐዊነት መጠቀም ከቻለ በዚያው ልክ ለግጭትና ለቁርቋሶ ምንጭ የሆኑትን ውስጣዊ ተጋላጭነቱን ይቀንሳል። ቀጣናውም የሰላም መናኸሪያ ይሆናል። እነዚህ ሁሉ በምስራቅ አፍሪካም ይሁን በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ አገራችን ያላት ዕቅድና ተሰሚነት በልዕለ ሃያላኑ አገራት የሚታወቁ ናቸው። ይህ ሁኔታም አገራቱ በችግራችን ወቅትም እንዲፈልጉን ያደረገ ይመስለኛል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy