Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በጫና የማይጠመዘዘው እጅ

0 421

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በጫና የማይጠመዘዘው እጅ

                                                       ደስታ ኃይሉ

የአንድ ዴሞክራሲያዊ መንግስት መገለጫ ከሆኑት ጉዳዩች ውስጥ የህዝብን ጥያቄ በተገቢው መንገድ መመለስ መቻል ነው። ከዚህ አኳያ የኢፌዴሪ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ አገራዊ መግባባት እንዲጎለብት እንዲሁም የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ያስችላሉ ያላቸውን በርካታ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል።

ከእነዚ ውስጥ የእስረኞች መለቀቅ ጉዳይ ቀደም ሲል በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለዴሞክራሲ መጎልበት እንደሚበጅ ታምኖበት የህዝብ ፍላጎት በመሆኑ ውሳኔ የተላለፈበት ጉዳይ ነው። ይህ ውሳኔ የህዝቡ ፍላጎት ስለሆነ እንጂ በማንም ጫና የተፈጠረ አይደለም። የኢፌዴሪ መንግስት ለጋራ ተጠቃሚነትና በእኩልነት ለመደጋገፍ የሚሰራ እንጂ፣ ማንም በጫና እጁን የሚጠመዝዘው አለመሆኑን ያለፉት ዓመታት ተግባሮቹ ይመሰክራሉ።

ሥርዓቱ በጋራ ጉዳዩች ዙሪያ ለአገራዊ መግባባት መሰረት ከመጣል ባለፈ በዋና ዋና ጉዳዩች ላይ አገራዊ መግባባት እንዲፈጠርና ሁለንተናዊ እድገታችን እንዲለወጥ ያስቻለ ነው። በተለይም በአንድ ተራማጅ ሥርዓት ውስጥ እውን መሆን ላለባቸው የዴሞክራሲና የአገራዊ መግባባት መሰረት ሆኖ ዛሬ ድረስ ዘልቋል።

የኢፌዴሪ መንግስት የአገራችንን የዴሞክራሲ ስርዓት ለማጎልበት በርካታ ጥረቶች አድርጓል፡፡ እነዚህ ጥረቶች የአገራችን ህዝቦች የሞት ሽረት ጉዳይ ነው፡፡ ህዝቦች በራሳቸው ይሁንታ ያጸደቁት ህገ መንግስት በግልፅ እንደተደነገገውም ስልጣን በሕዝብ ድምፅ እንጂ በሌላ መንገድ የሚገኝ እንዳልሆነ ተደንግጓል፡፡

በዚህም የፖለቲካ ፖርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ይህን ዕውነታ ተረድተው የዴሞክራሲን ምንነት በውል ተረድተው በምርጫ በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ የነበራቸው ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

የአገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ 26 ዓመታትን ብቻ የዘለለ ጮርቃ በመሆኑ፣ የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ሂደቱ ስር እንዲሰድና እንከን አልባ ርብርብ ተደርጓል ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም መሰረታዊ የዴሞክራሲ ተግባራትን በማከናወንና ዴሞክራሲው እንዲጎለብት ረጅም ርቀት መጓዝ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት አለቃው ህዝብ እንጂ ሌላ የውጭ አካል አይደለም። ከየትኛውም አካል ጋር የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ነው። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቡ እንዲያስተዳድሩት የሚፈልጋቸውን ይመርጣል እንጂ፣ እንዳለፉት ስርዓቶች የሚያስተዳድሩት ራሳቸውን መርጠው አሊያም በገዥ ፓርቲ ተመርጠው የሚሄዱበት አሰራር ዶሴው ተዘግቷል፡፡ ዳግም አይመለስም፡፡ እናም በአሁኑ ወቅት ዴሞክራሲን መገንባት የውዴታ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሥርዓቱ የሚጠይቀው ግዴታም ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡

ይህ ጠንካራ ዴሞክራሲ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን መውለድ ችሏል፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ በ1987 ዓ.ም የፀደቀው ህገ መንግስት ላይ “ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ” ማለት፣ ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች፣ የሚግባቡበት የጋራ ቋንቋ፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልከአ ምድር የሚኖሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ባለፉት 26 ዓመታት የተከናወነኑት ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን የማጎልበት ጥረት ምንም ችግር አልነበረበትም ማለት አይቻልም። ችግር የሌለበት ነገር ተፈልጎ አይገኝም። ሆኖም ባለፉት ስርዓቶች የነበሩት ውስብስብ የብሔር ጭቆናዎች አኳያ አስተሳሰቡን በቀላሉ ማስረፅ አስቸጋሪ እንደሚሆን አያጠያይቅም። ይሁንና ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የአገራችንን አንድነት በማጠንከር ኢትዮጵያዊነት እንዲያብብ እያደረገ መሆኑን መገንዘብ የሚያስፈልግ ነው።

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም የተተገበረው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፍሬ ማፍራት ችሏል፡፡ ምክንያቱም ፅንሰ ሃሳቡ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በሰላም የመኖርና ችግርንም በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ማህበረሰባዊ ግንኙነትን በብቸኝነት መከተል ነውና፡፡

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ነው። በመሆኑም ጽንሰ ሃሳቡ የበላይነት ባገኘባቸው አካባቢዎች እና ክልሎች ምንም ዓይነት ግጭት አይከሰትም። ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የጋራ የልማት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ነው። ይህንን ይበልጥ ለማስቀጠል አልፎ አልፎ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚስተዋሉትን የጠባብነት እና የትምክህት አስተሳሰቦች በጋራ መዋጋት ያስፈልጋል።

እርግጥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በብሔሮች መካከል የአመለካከት ዝምድና መፍጠር ችሏል፡፡ በመሆኑም ሀገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ያደረሰ እሴት ነው፡፡ የትምክትና ጠባብነት ፈተናዎች በአገሪቱ ቢኖሩም በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መሸነፋቸው አይቀሬ ነው። እየተሸነፉም ነው። ይህም ለአገራዊ መግባባት በር ከፍቷል።

የእረኞች መፈታት ጉዳይም ከአገራዊ መግባባት አኳያ የሚታይ እንጂ በየትኛውም ሃይል ተፅዕኖ የሚከናወን አይደለም። የኢትዮጵያን መንግስት ህዝቡ እንጂ ማንም ሊያዘው አይችልም።

አገራችን ከማንኛውም አገር ጋር በግልጽ ፖሊሲ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ነው የምትፈጥረው፡፡ ይህም ከአገራችን ብሔራዊ ጥቅም አንጻር የተቃኘና ሰጥቶ የመቀበል መርህን የሚከተል አሰራር ያለው ነው፡፡ ግንኙነቱ ኢትዮጵያን እንደ አንዲት ሉዓላዊት ሀገር የሚያከብርና በውስጥ ጉዳይዋም ጣልቃ የመግባት አካሄድን የሚፈቅድ ቀዳዳ የለውም፡፡ መንግስት የሚከተለው አካሄድም ሀገራችንን ተጠቃሚ የሚያደርግና በማናቸውም የውስጥ ጉዳዮች የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት የሚጋብዝ አይደለም፡፡

ይህ እውነት በውጭ ሃይሎች ዘንድ ይታወቃል። የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ሲመሰርቱም በኢትዮጵያ ላይ ፍላጎታቸውን በኃይል መጫን እንደማይችሉ ተገንዝበው ነው፡፡ ለዚህም የራሳቸው ምክንያቶች አሏቸው፡፡ እነርሱም አገራችን በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደትና በልማት ላይ ማተኮርዋን ስለሚገነዘቡ፤ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ጂኦ- ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ስለሚያውቁ፣ በአካባቢው በሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እየተጫወተች ያላችውን የላቀ ሚና ስለሚረዱ እንዲሁም በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ ያላትን ተቀባይነት ስለሚያጤኑ መሆኑን በምክንያትነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ የመንግስታችንና የህዝባችን የማንነት መገለጫዎችና ቁልፍ ተግባራት የሁለትዮሽ የጋራ ተጠቃሚነት ግንኙነቱ የማዕዘን ድንጋይ ሞናቸውን የትኛውም ወገን ያውቃል።

እነዚህ የግንኙነት መሰረቶች በእኩልነት ላይ በተመረኮዘ ሚዛናዊ ተጠቃሚነት ላይ የሚያጠነጥኑ እንጂ፤ በጌታና በሎሌ ግንኙነቶች የሚፈፀሙ አይደሉም፡፡ አገራችን በውጭ ሃይሎች የውስጥ ጉዳይ እጇን ለማስገባት እንደማትፈልግ ሁሉ፤ እነርሱም ከፖሊሲ አንጻር በውስጥ ጉዳያችን እጃቸውን የሚያስገቡበት ምንም ዓይነት ምክንታዊ አመክንዩ ሊኖራቸው አይችልም። በመሆኑም እስረኞችን በመፍታትም ይሁን በሌሎች የሀገራችን ስራዎች የትኛውም አካል ጣልቃ ሊገባና የመንግስትን እጅ ሊጠመዝዝ እንደማይችል መገንዘብ ያስፈልጋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy